
የኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥትና የ‹‹ኤም23›› (M23) አማፂ ቡድን የምስራቃዊ ኮንጎ ግጭትን ለማስቆም በኳታር፣ ዶሃ፣ የሰላም ስምምነት መፈራረማቸው ተገልጿል፡፡ ይህ ስምምነት አማፂያኑ ከወራት በፊት ጥቃታቸውን ከከፈቱ በኋላ በሁለቱ ወገኖች መካከል የተደረገ የመጀመሪያው ቀጥተኛ ስምምነት እንደሆነ ተገልጿል።
‹‹የመርሆዎች መግለጫ (Declaration of Principles)›› የሚል ስያሜ የተሰጠው እና ወደ ቋሚ የሰላም ስምምነት ያደርሳል ተብሎ የታሰበ ፍኖተ ካርታ እንደሆነ የተነገረው ስምምነቱ፣ ሁለቱም ወገኖች ከጥቃት፣ የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ እና በመሬት ላይ ያሉ አዳዲስ ቦታዎችን በኃይል ለመያዝ ከሚደረጉ ሙከራዎች መቆጠብ እንዳለባቸው ይደነግጋል። ከሦስት ሳምንታት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ የዘላቂ ሰላም ስምምነት ድርድር ይጀመራል፡፡
‹‹የኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት እና ኤም 23› በሁሉም ብሔራዊ ግዛቶችና ድንበሮች መንግሥታዊ ሥርዓት እንዲሰፍን ተስማምተዋል›› ተብሎ በስምምነቱ ላይ ቢጠቀስም፣ የሩዋንዳ ወታደሮችና የ ‹‹ኤም 23›› ታጣቂዎች ከምስራቃዊ ኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ስለሚወጡበት አካሄድ በዝርዝር አልተገለጸም።
የኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት ቃል አቀባይ ፓትሪክ ሙያያ፣ ‹‹ስምምነቱ ‹ኤም23› ከያዛቸው አካባቢዎች ያለድርድር እንዲወጣ ማድረግን ጨምሮ የመንግሥትን ቀይ መስመር ግምት ውስጥ ያስገባ ነው›› ብለዋል። የ ‹‹ኤም 23›› ተደራዳሪ ቤንጃሚን ምቦኒምፓ ግን፣ ‹‹ስምምነቱ በቁጥጥር ስር ካሉ አካባቢዎች መውጣትን አልጠቀሰም›› ብለዋል።
የአፍሪካ ኅብረት የሁለቱን ወገኖች ስምምነት ‹‹ወሳኝ ለውጥ›› ብሎታል፡፡ የኅብረቱ ኮሚሽን ሊቀ መንበር ማህሙድ አሊ የሱፍ ስምምነቱ በምስራቃዊ ኮንጎ ዴሞክራሲዊ ሪፐብሊክ እና በታላላቅ ሃይቆች ቀጣና ዘላቂ ሰላምና ደህንነትን ለማስፈን የሚደረጉ ጥረቶችን ለማጠናከር የሚረዳ ትልቅ ምዕራፍ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ አደራዳሪዋ ኳታር ድርድሩ እንደሚቀጥል አስታውቃለች።
የአልጀዚራው አላይን ኡይካኒ ከሰሜን ኪቩ ግዛት ዋና ከተማ ጎማ ባሰራጨው ዘገባ፣ ስምምነቱ ለኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕዝብ ጠቃሚ ርምጃ እንደሆነ አመልክቷል፡፡ ከስምምነቱ አስቀድሞ በመሬት ላይ ያለው ሁኔታ መረጋጋት የማይታይበት እንደሆነም ጠቁሟል፡፡ ‹‹የተፈረመው ስምምነት በኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥትና በ ‹ኤም 23› መካከል ሰፊ ውይይት እንዲጀመር መንገድ ይጠርጋል›› ብሏል፡፡
ማጺው ቡድን ስለግጭቱ መሰረታዊ መንስኤ ለመወያየት በሁለቱም ወገኖች ዘንድ መተማመን ሊኖር እንደሚገባ ስለማሳሰቡም ኡይካኒ በዘገባው ጠቅሷል፡፡
ሁለቱ ወገኖች የስምምነቱን ውሎች እስከ ሐምሌ 22 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ ተግባራዊ ለማድረግ ተስማምተዋል። ከአንድ ወር በኋላ የመጨረሻ የሰላም ስምምነት እንደሚፈረም የሚጠበቅ ሲሆን፣ ባለፈው ወር በአሜሪካ አደራዳሪነት በኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ እና ‹‹ኤም 23››ን ትደግፋለች ተብላ በምትወቀሰው በሩዋንዳ መካከል ከተፈረመው ስምምነት ጋር መጣጣም አለበት ተብሏል።
የኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት እና ሩዋንዳ ከሦስት ሳምንታት በፊት በአሜሪካ፣ ዋሺንግተን ዲሲ የሰላም ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል፡፡ የአሜሪካ፣ የኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክና የሩዋንዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፣ የኳታር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ፣ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር እንዲሁም ዲፕሎማቶች በተገኙበት በዋሺግተን ዲሲ፣ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቢሮ የተፈረመው ስምምነት፤ በሁለቱ ሀገራት መካከል ለዓመታት ለዘለቀው አለመግባባትና በኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ እና በ‹‹ኤም23›› (M23) ታጣቂ ቡድን መካከል ለሚካሄደው ውጊያ እልባት እንደሚያስገኝ ተስፋ ተጥሎበታል።
በስምምነቱ መስረት ኪንሻና ኪጋሊ በዘጠና ቀናት ውስጥ ቀጣናዊ የምጣኔ ሀብት ትስስር ማሕቀፍ ይፋ ያደርጋሉ፤ የሩዋንዳ ወታደሮች ከኮንጎ ግዛት ውስጥ ይወጣሉ፡፡ በ30 ቀናት ውስጥ ደግሞ የጋራ የፀጥታ ቅንጅት ሥርዓት ይዘረጋሉ፡፡ የተፈናቀሉ ሰዎች ወደ አካባቢያቸው ይመለሳሉ፡፡
የሰላም ስምምነቱ የአሜሪካ መንግሥትና ኩባንያዎች ለቴክኖሎጂ ምርቶች አስፈላጊ ግብዓቶች የሆኑትን እንደታንታለም፣ ወርቅ፣ ኮባልት፣ መዳብና ሊቲየም ያሉ ብርቅዬ ማዕድናትን እንዲያለሙ ያስችላቸዋል፡፡
በተለይም አሜሪካና ቻይና የንግድ ጦርነት ውስጥ በገቡበት እና በአፍሪካ ውስጥ የበላይነትን ለመያዝ በሚፋለሙበት በዚህ ወቅት ይህ የስምምነቱ ክፍል ለአሜሪካ ትልቅ ብስራት ነውም ተብሏል፡፡ የዋሽንግተኑ ስምምነት ለአሜሪካ ጣልቃ ገብነት ቁልፍ ማበረታቻ የሚሆንና የኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሰፊ የማዕድን ሀብትን ለውጭ ኃይሎች ጥቅም የሚያጋልጥል ነው ተብሎ ሰፊ ትችት አስተናግዷል።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከስምምነቱ መፈረም ቀደም ብሎ ባሰሙት ንግግር ‹‹ብዙ የማዕድን መብቶችን ከኮንጎ ለአሜሪካ አስገኝተናል›› ማለታቸው የሚታወስ ነው፡፡
ኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ 24 ትሪሊዮን ዶላር የሚገመት ያልተነካ እምቅ የማዕድን ሀብት ያላት ሲሆን፣ በጦርነቱ በፈጠረው ሕገ ወጥ ንግድ ምክንያት ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጣ ማዕድን እንዳጣች ገልፃለች፡፡
የኮንጎ ዴሞክራሲዊ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ፌሊክስ ሺሴኬዲ እና የሩዋንዳው አቻቸው ፖል ካጋሜ ባለፈው መጋቢት ወር በኳታር ተገናኝተው አፋጣኝ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጠይቀው ነበር። በቀጣዩ ወር ደግሞ የኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት እና የ‹‹ኤም23›› (M23) ታጣቂ ቡድን በኳታር አሸማጋይነት ተኩስ ለማቆም ቢስማሙም ግጭቱ ግን ቀጥሎ እንደነበር ይታወሳል።
ምንም እንኳን ቀኑ ባይወሰንም ሺሴኪዲ እና ካጋሜ ትራምፕን ለማግኘት ወደ ዋሺንግተን እንደሚሄዱ ተነግሯል። በትራምፕ ግብዣ በነጩ ቤት ይገኛሉ የተባሉት ሁለቱ ባላንጣ ፕሬዚዳንቶች ‹‹የዋሺንግተን ስምምነት››ን (Washington Accord) ይፈራረማሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ስምምነቱን ቀድመው ስያሜ የሰጡት ባለፈው ሰኔ በዚያው በዋሺንግተን የተፈረመውን የሁለቱን ሀገራት የሰላም ስምምነት ያመቻቹት ሊባኖሳዊ-አሜሪካዊው ባለሀብት ማሳድ ቡሎስ ናቸው፡፡ ግለሰቡ የትራምፕ ልጅ የቲፋኒ ትራምፕ ባለቤት አባት ሲሆኑ፣ ትራምፕ የአፍሪካ ጉዳዮች ከፍተኛ አማካሪያቸው አድርገው ሾመዋቸዋል፡፡
የኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት እና የ‹‹ኤም23›› ታጣቂ ቡድን ግጭት ከአስከፊው የሩዋንዳ የዘር ፍጅት ጋር የተሳሰረ ታሪክ አለው። የቡድኑ አብዛኞቹ ታጣቂዎች በዘር ጭፍጨፋው ዋና ተጠቂ የነበረው የቱትሲ ጎሳ አባላት ናቸው። ቀደም ሲል የአማፂ ቡድኖች አባላት የነበሩት ብዙዎቹ የቡድኑ ታጣቂዎች፣ የኮንጎ ብሄራዊ ጦር አባል ለመሆን ተስማምተው የነበረ ቢሆንም ‹‹መገለል ደረሰብን፤ የተገባልንም ቃል አልተፈፀመልንም›› ብለው በድጋሚ ‹ጥራኝ ዱሩ› ብለው ወደ ጫካ የተመለሱ ተዋጊዎች መሆናቸው ተገልጿል፡፡
ስሙን እ.አ.አ ማርች 23 ቀን 2009 (March 23) በተፈረመው የሰላም ስምምነት ምክንያት ‹‹ኤም23›› (የማርች 23 ንቅናቄ) ብሎ የሰየመው አማፂ ቡድን በዋናነት የሚንቀሳቀሰው በምስራቃዊ ኮንጎ በምትገኘውና ኮንጎ ከኡጋንዳና ከሩዋንዳ ጋር በምትጎራበትባት ሰሜን ኪቩ ግዛት ውስጥ ነው፡፡ ቡድኑ በማዕድን ሀብት የበለጸገውን የኮንጎ ምስራቃዊ ክፍል ለመቆጣጠር በአካባቢው ከሚርመሰመሱት ከ100 በላይ ታጣቂ ቡድኖች መካከል የተሻለ ጥንካሬ ያለው ተዋጊ ኃይል እንደሆነም ይታመናል፡፡
አካባቢው ከግጭት የተላቀቀ ባይሆንም የቅርቡ ደም አፋሳሽ ጦርነት የተስፋፋው የ‹‹ኤም23›› አማፂያን ጎማ እና ቡካቩ የተባሉ የምስራቃዊ ኮንጎ ሁለቱን ትልልቅ ከተሞች ከተቆጣጠሩ በኋላ ነው፡፡ ከዚያ ወዲህ ቡድኑ ግስጋሴውን በማፍጠን ሌሎች ከተሞችን ተቆጣጥሯል፡፡ በኮንጎ ምዕራባዊ ጫፍ ወደምትገኘው እስከ ዋና ከተማዋ ኪንሻሳ ድረስ እዘልቃለሁ ብሎም መዛቱም የሚታወስ ነው፡፡
ሩዋንዳ በዚህ የኮንጎ ግጭት ውስጥ ወሳኝ ሚና ያላት ሀገር ናት።ትደግፈዋለች የሚባለው የ‹‹ኤም23›› አማፂ ቡድን የቱትሲ ጎሳ አባላት ስብስብ ነው። የሩዋንዳ ፕሬዚዳንት ካጋሜም የቱትሲ ተወላጅ ናቸው፡፡ የ‹‹ኤም23›› አማፂ ቡድን ከኮንጎ መንግሥት ጋር የሚዋጋው ሁቱዎች የሚመሩት ‹‹የዴሞክራሲ ኃይሎች ለሩዋንዳ ነፃነት›› (FDLR) የሚባለው ታጣቂ ኃይል ከኮንጎ መንግሥት ጋር ተባብሮ በደል የሚያደርስባቸውን በኮንጎ የሚኖሩትን የባንያሙሌንጌ ቱትሲ ወገኖቼን ከጥቃት ለመጠበቅ ነው ይላል፡፡
ሩዋንዳ ደግሞ ‹‹የዴሞክራሲ ኃይሎች ለሩዋንዳ ነፃነት›› የተባለው ታጣቂ ቡድን ‹‹በሩዋንዳን የዘር ጭፍጨፋ እጁ አለበትና ደመኛ ጠላቴ ነው፤ ለሉዓላዊነቴም ትልቅ ስጋት ነው›› ትላለች፡፡ ከእዚህ በተጨማሪም ቡድኑን የሚያስታጥቀው የኮንጎ መንግሥት እንደሆነ ሩዋንዳ ደጋግማ ገልፃለች። ስለሆነም ቡድኑ በኪጋሊም ሆነ በምስራቅ ኮንጎ ቱትሲዎች ላይ የደቀነው ስጋት በዘላቂነት እንዲወገድ የቡድኑ መወገድ አማራጭ የሌለው መፍትሄ ነውና ቡድኑን ከምድረ ገጽ ሳላጠፋ እንቅልፍ አይወስደኝም የሚል አቋም አላት፡፡
ኮንጎ በበኩሏ የጎን ውጋት ለሆነባት የ‹‹ኤም23›› አማፂ ቡድን ወታደራዊ ድጋፍ የምታደርገው ሩዋንዳ እንደሆነች ታምናለች፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሩዋንዳ አራት ሺህ ወታደሮቿን ከቡድኑ ጎን አሰልፋ እየተዋጋች እንደሆነ ይፋ አድርጓል።
ፈረንሳይና እና አሜሪካም ሩዋንዳ ቡድኑን እንደምትደግፍ ቢገልጹም፣ ሩዋንዳ ግን እጄ የለበትም ባይ ናት፡፡ በጉዳዩ ላይ ያላትን ተሳትፎም አማፂ ቡድን የማስታጠቅ ሳይሆን ሉዓላዊነትን የማስከበር ብሔራዊ ተልዕኮ አድርጋ ትቆጥረዋለች፡፡
ግጭቱ የሚካሄድበት አካባቢ የተትረፈረፈ የማዕድን ሀብት ባለቤት መሆኑ ደግሞ ግጭቱ ፖለቲካዊ ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚያዊ ምክንያትም እንዲኖረው አድርጎታል፡፡
እነዚህ ማዕድናት ደግሞ የሞባይል ስልክ፣ ካሜራና የመኪኖችን የውስጥ ክፍሎችን ለመሥራት የሚያገለግሉት እጅግ ውድና ተፈላጊ ሀብቶች ናቸው። ኮንጎ ሩዋንዳ እነዚህን ማዕድናት እየዘረፈችኝ ነው የሚል ተደጋጋሚ ክስም ታሰማለች፡፡ ሩዋንዳ ግን እንደተለመደው ‹‹የለሁበትም›› ትላለች፡፡ ተፃራሪ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎቶች በተፈጥሮ ሀብት የበለፀገውን ምስራቃዊ ኮንጎን ሰላም የራቀው፣ ድህነት፣ ረሀብ፣ በሽታ፣ ሞት፣ ስደትና እንግልት የሚፈራረቁበት የምድር ሲኦል አድርገውታል፡፡
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሐምሌ 15 ቀን 2017 ዓ.ም