በፌዴራል ፍርድ ቤቶችና ማረሚያ ቤቶች የዳኝነት ስራን ለማቀላጠፍ እንዲሁም ተደራሽነትን ለማስፋትና የወጪ ቅነሳ ለማድረግ አራት አዳዲስ መተግበሪያዎች እየተሞከሩ ሲሆን፤ ከእነዚህ መካከል የፕላዝማ ችሎት ችግር ፈቺነቱና ጥቅሙ የጎላ እንደሆነ ምሁራን ይናገራሉ።
ከፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የኢንፎርሜሽንና ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዳይሬክቶሬት የተገኘ መረጃ እንደሚያመላክተው፤ በማህበረሰቡ ላይ የሚደርሰውን እንግልት ከመቀነስ አኳያ የፕላዝማ ችሎት ከፍተኛ ፋይዳ አለው፡፡ በተለይም በየክልሉና ወረዳው የሚደረገውን የዳኞች ዝውውርና የታራሚዎችን ያልተገባ እንግልት በመቀነስ በኩል የማይተካ ሚና አለው። በተጨማሪም የወጪ ቅነሳው ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ ያለ አገልግሎት ነው።
በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የኢንፎርሜሽንና ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን አማረ እንደተናገሩት፤ የፕላዝማ ችሎት በተለይ ለታራሚዎች የሚሰጠው አገልግሎት መተኪያ የሌለው ነው። የፕላዝማ ችሎት የተሻለ ፍትህ ከማስገኘቱም በላይ ከወጪና እንግልት ይታደጋል፡፡ ታራሚዎች ጠበቃቸው በሌላ ቦታ እንኳን ቢሆን ያለበት ቦታ ሳይሄዱ በፕላዝማ ቀርበው ጉዳያቸው በምን መልኩ እየተካሄደ እንደሆነ እንዲከታተሉ ያግዛቸዋል። ለመከራከርም ሆነ ለመናገር እድሉን የሚያገኙበትን አማራጭም ይሰጣቸዋልም። ስለዚህም ይህ የችሎት አገልግሎት ከመንግስትና ውጪ ከሚገኘው ማህበረሰብ በበለጠ ለታራሚዎች የሚሰጠው አገልግሎት ከፍተኛ ይሆናል።
በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በቂርቆስ ምድብ የባንክና ኢንሹራንስ ችሎት ዳኛ አቶ ጌታሁን ገብረመስቀል በበኩላቸው፤ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትና ጠቅላይ ፍርድ ቤት አካባቢ የፕላዝማ ችሎት አገልግሎቶች በስፋት ይሰጣሉ። ዋና አገልግሎታቸውም ከተደራሽነት አኳያ ችሎትን ማፋጠን ነው። በተለይም በሁለት መልኩ የላቀ ጥቅም እንዳላቸው ይገልጻሉ። የመጀመሪያው ተከራካሪዎች ሰበር ችሎቱ በሚደረግበት ስፍራ ሳይሄዱ በቅርባቸው ባለው የፕላዝማ ችሎት እንዲከራከሩ ያስችላል። ሁለተኛው ጠበቃዎች በተገኙበት ቦታ ቀርበው ደንበኛቸውን እንዲያገለግሉ ይረዳቸዋል። ይህ ደግሞ በተለይ ማህበረሰቡን ከወጪ ከመታደጉም በላይ የፍትህ ተደራሽነቱ እንዲረጋገጥ ያደርገዋል ይላሉ።
እንደ አቶ ጌታሁን ገለጻ፤ ጠበቃው በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሆኖ ደንበኞቹ በየትኛውምክልል ቢሆኑ በፕላዝማ ተገናኝተው ጉዳያቸው እንዲታይ ከማድረግ አንጻር የፕላዝማ ችሎት ትልቅ ጥቅም ይሰጣል። በተለይ በወንጀል ችሎቶች ላይ ያላቸው ፋይዳ ቀላል የማይባል ነው። ባለጉዳዮች በማያውቁት ቦታ ሄደው እንዳይጉላሉና አላስፈላጊ ወጪ እንዳያወጡም ፕላዝማ ችሎት ያግዛቸዋል።
ፕላዝማ ችሎቶች በፌዴራል የሚፈጠሩ የቋንቋ ችግሮችን ከመፍታት አኳያ የማይተካ ሚና እንዳላቸው የሚጠቁሙት አቶ ጌታሁን፤ የፌዴራል መንግስት የስራ ቋንቋ አማርኛ በመሆኑ የተነሳ አማርኛ ለማይችለው ማህበረሰብ ጠቀሜታቸው የጎላ ነው። ተርጓሚ ለማምጣት ከመሯሯጥ ይልቅ በአቅራቢያቸው በሚገኝ ሰው ይጠቀማሉ፤ የጊዜ ቀጠሮ ከማራዘምም ይታደጋል። በተለይም በማረሚያ ቤቶች የታራሚዎችን ደህንነት ከመጠበቅ አኳያ ትልቅ ፋይዳ አለው።
በደብረብረሃን ዩኒቨርሲቲ የህግ አገልግሎት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ሰይፈ ደርቤ በበኩላቸው፤ ፍትህን ተደራሽ ከማድረግ አኳያ የፕላዝማ ችሎት ፍቱን መድሃኒት እንደሆነ ይናገራሉ። ለዚህም ምክንያታቸው በየከፍተኛ ፍርድ ቤቶችና ማረሚያ ቤቶች አገልግሎት እየተሰጠ ህዝቡን ከወጪ መታደግ በመቻሉ ነው።
በፌዴራል ደረጃ አዲስ አበባ መጥቶ ጉዳዩን ቢከታተል ከወጪው ባልተናነሰ መልኩ የቦታ አለማወቅና የሚያማክረው ማጣት ለጭንቀት ይዳርገዋል። በዚህም ትክክለኛ መረጃ ለመስጠት ይሳነዋል። ይህ ደግሞ ፍትህ እንዲዛባ ያደርጋል። ተጎጂ ሆኖ እያለ ቅጣት ሊጣልበትም ይችላል። ስለሆነም ፕላዝማ ችሎቶቹ መኖራቸው ይህንን ሁሉ ችግር ለመፍታት እንደሚያስችሉ ይናገራሉ።
የፕላዝማ ችሎቱ ሲጀምር አምስት ብቻ ነበር የሚሉት አቶ ሰለሞን ደግሞ፤ ዛሬ 43 ለመድረሳቸው መንስኤው አገልግሎቱ ምን ያህል ጠቀሜታ እንዳለው በመታመኑና ተደራሽነቱን ለማስፋት ታቅዶ በመሰራቱ ነው። በእነዚህ መተግበሪያዎችም በዓመት ከ2000 በላይ መዝገቦች እየታዩ ተደራሽነታቸው እንዲሰፋ ተደርጎባቸዋል። ይሁን እንጂ የፕላዝማ ችሎት ቁጥር በሚፈለገው ደረጃ ያለመሆኑ፣ የመብራት፣ የኢንተርኔት አገልግሎቶች መቆራረጥ ወደነበረበት የአሰራር ክፍተት ሊመልሰው እንደሚችል ይናገራሉ። ጥቅሙንም የሚያሳጣበት ሁኔታ ቀላል እንደማይሆን ያስረዳሉ። ስለሆነም መንግስት በተለይ የኢንተርኔትና የመብራት አገልግሎት ዋጋን ተመጣጣኝነት ማየት እንዳለበትም ይናገራሉ። መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም ለዚህ የማህበረሰብ ተጠቃሚነት የበኩሉን ሊያደርግ እንደሚገባ ያስገነዝባሉ።
የፕላዝማ ችሎት አገልግሎቱ በተገቢው ሁኔታ መሰጠት ከቻለ ከተደራሽነቱ አልፎ ጥራቱ ላይ፣ ግልጸኝነቱ ላይ፤ የቀጠሮ ርዝማኔን ማሳጠር ላይ ሰፊ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ያሉት አቶ ጌታሁን ደግሞ፤ በዋናነት ድርሻው ሊሆን የሚገባው የመንግስት እንደሆነ ይናገራሉ። አገልግሎቱ በአገር ደረጃ ያለው እንቅስቃሴ ጅምር በመሆኑ በርካታ ችግሮች አሉበት። በዚህም የጊዜ ቀጠሮዎች መጓተት ይፈጠራል። ይህ ደግሞ በፍትህ ሥርዓቱ ላይ ሰፊ እንቅፋት ያመጣል። በተለይም የኔትወርክ መቆራረጥ፣ የመብራትና በቂ ባለሙያ ያለመኖር ችግር በዋናነት ችግሩን እንዲሰፋ ምክንያቶች እንደሚሆኑ ይናገራሉ።
አንድ ፕላዝማ ከተበላሸ እስኪሰራ ችሎቱ ይቋረጣል። በተመሳሳይ በሁሉም ማረሚያ ቤቶችና ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች የለም ያሉት ደግሞ አቶ ሰይፈ ሲሆኑ፤ አሁንም የፕላዝማ ችሎቶች መጓተት ለሌሎችም ጫና የመፍጠሩ ሁኔታ መንስኤ እየሆነ መጥቷል። ከቀደመው በተሻለ ሁኔታ የቀጠሮን ጊዜ መቀነስ አልተቻለም። የራሱ የሆነ የጊዜ ገደብ ስላለው እንደማንኛውም ችሎት በየቀኑ አይታይምና ትኩረት ተነፍጎታል። ስለዚህ በተሻለ ባለሙያና ግብዓት ካልተደገፈ በስተቀር ጥቅሙ ሊጎላ እንደማይችል ያስረዳሉ። አነስተኛ ጄኔሬተርና የዋይፋይ አገልግሎትም መሟላት እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ።
የፕላዝማ ችሎት በ11 ማረሚያ ቤቶች እንዲሁም በሁሉም ክልሎችና አንዳንድ ዞኖች ላይ አገልግሎቱ የሚሰጥ ሲሆን፤ አገልግሎቱ የጀመረው በ2003 ዓ.ም ነው። እስከ 2010 ዓ.ም ድረስ በተገኘው መረጃም 10ሺ 29 መዝገብ የታየ ሲሆን፤ 50 ሚሊዮን 342 ሺ 454 ብር ከወጪ ማዳን ተችሏል። በ2011ዓ.ም የስድስት ወር ጊዜ ውስጥም 4 ሚሊዮን 564 ሺ377 ብር ማዳን ተችሏል። ለዚህ ሁኔታ መምጣት ደግሞ በመጀመሪያ ማረሚያ ቤቶች ላይ የተሰራው ሥራ የተሻለ እንደሆነ ከፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የኢንፎርሜሽንና ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዳይሬክቶሬት የተገኘ መረጃ ያመላክታል።
የፕላዝማ ችሎት ማህበረሰቡ ኢኮኖሚውን ለማሳደግ የሚያስችለውን ጊዜ ይቆጥብለታል። እንግልቱን ቀንሶ በቅርብ ሥራዎቹን ጨርሶ ወደ ቀን ተግባሩ እንዲመለስም ያግዘዋል። በከባድ ወንጀል ተከሰው ለፍርድ የሚቀርቡ ታራሚዎች እንዳይንገላቱ፤ የመንግስት ወጪ እንዲቀንስና ፖሊስ ወንጀለኛ አምልጦት ተጠያቂ እንዳይሆን መፍትሄ ነው።
አዲስ ዘመን ጥር 19/2011
ጽጌረዳ ጫንያለው