ልጆች! እንደምን ሰነበታችሁ? ሳምንቱን እንዴትና በምን አይነት መልኩ አሳለፋችሁ? መቼም መጽሀፍ በማንበብ፣ በቤት ውስጥ ስራ በመስራት፣ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ በማድረግ እንዲሁም ፊልም በመመልከት እንደምትሉ ተስፋ አደርጋለሁ። የእስልምና እምነት ተከታዮችስ የኢድ አል-አድሃ በዓልን እንዴት አሳለፋችሁ? በጣም ጥሩ ነበር እንደምትሉ አስባለሁ።
በአሳለፍነው አርብ በእስልምና ዕምነት ተከታዮች ዘንድ የአረፋ በዓል በታላቅ ድምቀት ተከብሯል። ሙስሊም ልጆችም እንደከዚህ ቀደሙ ከዘመድ አዝማድ ቤት፣ ከጓደኛ ጋር በመገናኘት ሳይሆን በቤታችሁ ሆናችሁ በስልክ ከወዳጅ ዘመዶቻችሁ ጋር የመልካም ምኞት መልዕክት እንደተለዋወጣችሁ ተስፋ አደርጋለሁ። ይሄ ወቅት የሚጠይቀው እንደዚህ አይነት ጥንቃቄን ነው። ከቤት አለመውጣት፣ እጅን ቶሎ ቶሎ መታጠብ፣ ደግሞም መራራቅ ያስፈልጋል።
ሙስሊም ወገኖቻችን የአረፋን በዓል ሲያከብሩም ኢድሙባረክ የተባባሉት ከእምነቱ ተከታዮች ጋር ብቻ አይደለም፤ ከክርስቲያን ዘመዶቻቸውና ጓደኞቻቸው ጋር ጭምር ነው። በበዓሉ እለት ደግሞ ብዙዎቹ ሙስሊሞች የተቸገሩ ወገኖቻችንን በመርዳት፣ ካላቸው በማካፈል ጭምር ነው በዓሉን ያከበሩት። ይሄ በጣም ደስ የሚል የኢትዮጵያዊነት መገለጫ ባህላችን ነው።
ልጆች ! ዛሬ እንግዳ አድርጌ ያቀረብኩላችሁ ተማሪ ሂክማ ኡመር ትባላለች። በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ህዳሴ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ናት። ተማሪ ሂክማ ትምህርቷን በአግባቡ በማጥናት ቀጣዩ የትምህርት ጊዜ የሚከፈትበትን ወቅት በጉጉት በመጠባበቅ ላይ ትገኛለች። 1441ኛውን የአረፋ በዓል ባሳለፍነው አርብ ያከበረችው ከቤተሰቧ ጋር ለየት ባለ መልኩ መሆኑን አጫውታኛለች። በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ከጓደኛዋና ከዘመዶቻቸው ጋር አልተገናኘችም።
ሂክማ እንደምትለው ልጆች በዓል ሲመጣ በቤት ውስጥ ያለው ድባብ ያስደስታቸዋል። እኔም በጣም ደስ ብሎኝ ነው ያሳለፍኩት ብላላች። የአረፋን በዓል በአካባቢያቸው የሚኖሩ ጎዳና ተዳዳሪዎችን፣ አቅመ ደካሞችን፣ እናትና አባታቸውን በሞት ያጡ ወገኖችን በማብላት፣ በማጠጣት፣ በመርዳት እና በመጠየቅ ማሳለፋቸውን ተናግራለች።
ከሚበሉትና ከሚጠጡት ቀንሰው ለተራቡት በማብላትና በማጠጣት በዓሉን በማሳለፏ ደስተኛ እንደሆነች ገልፃለች። ሁሉም ሰው የእለት ተዕለት ኑሮውን በዚህ መልክ ቢያሳልፍ መልካም ነው ብላለች። ተማሪ ሂክማ እንደ አረፋና መሰል በዓላት ሲከበር ሁልጊዜም ደስታን የሚፈጥርባት ገና በህፃንነታቸው ጎዳና ላይ በልመና የዕለት ምግባቸውን የሚፈልጉ ለጋ ህፃናትን ምግብ ስታበላና አልባሳት መስጠት ስትችል መሆኑን ትናገራለች። ይህን ስታደርግ ታዲያ ተርፏት ሳይሆን ከራሷ ቀንሳ መሆኑን ነግራናለች።
አረፋም ሆነ ሌሎች ሀይማኖታዊ በዓላት ሲመጡ ሁልጊዜም ተማሪ ሂክማ የምታስታውሰው ከዘመዶቿና ከጓደኞቿ ጋር በመገናኘት በደስታ የምታሳልፈው ጊዜ ነው። ጓደኞቿ በዓል በሚያከብሩበት ወቅት ለተቸገሩ ወገኖች አቅማቸው የፈቀደውን ነገር እንዲያደርጉ ትመክራለች። በተለይ ሁላችንም በየቤታችን ተዘጋጅቶ የሚቀርበውን ምግብ ለተራቡት በማብላት መተሳሰብ እንደሚገባ አሳስባለች።
ወቅቱ ትምህርታችን እንዳን ማርና በየቤታችን እንድንቀመጥ ያደረገንን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እንዳይስፋፋ ጥንቃቄ ማድረግ የሚገባን ነው ስትል ትናገራለች። በተለይም ልጆች የለመድነው በሰፈር ተሰባስበን መጫወት በመቀነስ ነገ ተምረን ልናሳካው ላለምነው ራዕያችን ማሰብ ይገባል ብላለች።
ተማሪዎች ትምህርት ቢዘጋም በቴሌቪዥን ትምህርታችንን እንድ ንከታተል ስለተደረገ ሳንዘናጋ በመማርና በማጥናት ጊዜያችንን በአግባቡ መጠቀም ይኖርብናል የምትለው ተማሪዋ ቤተሰቦቻችንም ሆነ ታላላቆቻችን የሚሉንን በመስ ማት፣ የተቸገሩትን በመርዳትና በመዋደድ መኖር አስፈላጊ ነው ትላለች።
ልጆች! የሂክማ መልካምነት መቼም እንዳስደሰታችሁ ተስፋ አደርጋለሁ። እናንተም ልክ እንደ ሂክማ በየአካባቢያችሁ ለተቸገሩት ማዘን፣ መርዳትና መደገፍ እንዳለባ ችሁ አትዘንጉ። መተሳሰብ፣ መቻቻል፣ መረዳዳት የሁሉም እምነት አስተምሮ የሚያዘው መሆኑን ተረድታችሁና መልካ ምነት ለራስ ነው ብላችሁ ቀጥሉበት። ሰላም ቆዩን!
አዲስ ዘመን ሐምሌ 26/2012
ሞገስ ተስፋ