ኢትዮጵያ ሰሞኑን ዝርዝር የስደተኞች መብት የያዘውን አዋጅ አጽድቃለች። አዋጁ የስደተኞችን መብት ከማስከበር ባለፈ የኢትዮጵያን ጥቅሞች በማስከበር ረገድ ምን ፋይዳ ይኖረዋል በሚለው አብይ ጉዳይ ላይ የዘርፉ ተዋንያን ሃሳባቸውን ይሰነዝራሉ።
የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ የህግ አገልግሎት እና የስደተኞች እውቅና መስጠት ኃላፊ አቶ ኃይለስላሴ ገብረማሪያም እንደሚገልጹት፤ሰሞኑን የጸደቀው የስደተኞች ረቂቅ አዋድ በአስገዳጅ ሁኔታ ህይወቱን ለማዳን የኢትዮጵያን ድንበር አቋርጦ የገባን ስደተኛን በካምፕ እየተቀለቡ ከማቆየት ይልቅ እየሰራ የሚኖርበትን መንገድ ይፈቅዳል። ቀድሞ በኢትዮጵያ የነበረውን የስደተኞች ሰብአዊ አያያዝ ወደልማታዊ አያያዝ ይቀይረዋል። ከካምፕ ኑሮ ወጥተው በተዘጋጀላቸው ቦታ ተንቀሳቅሰው እንዲኖሩ ይፈቅዳል። ይህ አዋጅ መውጣቱ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ የሚገነቡ ፕሮጀክቶች በውጭ ተቋማት ድጋፍ እንዲያገኝ ይረዳል። አሁን አዋጁ በመጽደቁ ለስደተኞች እና ኢትዮጵያውያን በጋራ የሚሰማሩባቸው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ፣ ለመስኖ ፕሮጀክቶች እና ለተለያዩ የስራ እድሎች የሚለቀቀው ገንዘብ በከፍተኛ መጠን ይጨምረዋል።
ከአዋጁ መረቀቅ ጀምሮ ሲሳተፉ የነበሩት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፍትህ የዴሞክራሲና የህግ ጉዳዮቸ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ፎዚያ አሚን እንደሚገልጹት፤ አዋጁ ስደተኞች በየአምስት ዓመቱ በሚታደስ ፈቃድ አማካኝነት ስራ ላይ እንዲሰማሩ ይፈቅዳል። የአገራቸው ሁኔታ ሲመቻች ደግሞ ፍቃዳቸው ሳይታደስ እንዲመለሱ ይደረጋል። ይህ ጉዳይ ከደህንነት አንጻር ለኢትዮጵያ አዋጭ ነው። ምክንያቱም ማን የት እንዳለ እና ምን እየሰራ ስለመሆኑ የተጠናቀረ መረጃ ለመመዝገብ ያስችላል። ስደተኞቹ ለስራ ሲባል ሙሉ መረጃዎቻቸው ተመዝግቦ እና የት እንዳሉ ተጣርቶ ስለሆነ ፈቃድ የሚሰጣቸው የደህንነት ጉዳይ ላይ አስተማማኝ ስራ ለማከናወን ይጠቅማል።
ወይዘሮ ፎዚያ እንደሚገልጹት፤ አንድ ስደተኛ የመኖሪያ ፈቃድ አግኝቶ ሲሰራ ከህገ ወጥነት ወጥቶ ገንዘብ በመፍጠር ረገድ ኢኮኖሚው ላይ የበኩሉን አስተዋጽኦ ሲያደርግ በሌላ በኩል ደግሞ በህገወጥ ስራዎች ከመሳተፍ ይቆጠባል። በተጨማሪ እንደ ጋምቤላ እና የተለያዩ አካባቢዎች ብቻ በካምፕ ውስጥ ስደተኞቹ ቢቆዩ ለአካባቢው ማህበረሰብም ሆነ ለመንግስት የኢኮኖሚ ጫና እና የተፈጥሮ ውድመት ይፈጥራል። ነገር ግን ተበታትነው እና በተለያዩ አካባቢዎች እንዲሰሩ መፈቀዱ በርካታ ስደተኞች ያሉባቸው አካባቢዎቸ ጫና በመቀነስ ከእርዳታ ተቀባይነት ብቻ ሳይሆን ሰርተው ኢትዮጵያንም እራሳቸውንም እንዲጠቅሙ ያደርጋል።
የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ የህግ አገልግሎት እና የስደተኞች እውቅና መስጠት ኃላፊ አቶ ኃይለስላሴ እንደሚገልጹት፤ አዋጁ ከጸደቀ አንድ ሳምንት በኋላ ከተለያዩ ተቋማት አንድ ቢሊዮን ዶላር ያለው ድጋፍ ለኢትዮጵያ ቀርቧል። ገንዘቡ በሰመራ፣ በሶማሌ እና በአሶሳ ለሚገነቡ እና ስደተኞች እንዲሁም ኢትዮጵያውያንን ለሚቀጥሩ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ማዋል ይቻላል። የኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ሲጠናቀቁ 70 በመቶ ኢትዮጵያውያን እና 30 በመቶ ስደተኞች የስራ እድል ይሰጣል።
‹‹ስደተኞቹ ተንቀሳቅሰው እንዲሰሩ በመፍቀድ እና ከእነርሱ የሚገኘውን ድጋፍ መቀበል ጥቅሙ እንጂ ጉዳቱ አይታየኝም›› የሚሉት አቶ ኃይለስላሴ በሚገኘው ገንዘብ በተመረጡ ቦታዎች የፍራፍሬ መስኖ ልማት ለማከናወን እንደሚቻል ይገልጻሉ። በተለይ በገናሌ ወንዝ አካባቢ ያሉ በረሃማ ቦታዎችን ለፍራፍሬ ልማት ለማዋል የሚያስችል የገንዘብ ድጋፍ ስለተገኘ ኢትዮጵያውያን እና የተለያዩ አገር ስደተኞች በ70/ 30 መስፈርት መሰረት ወደ ስራ ማሰማራት ይቻላል። በመሆኑም ስደተኞችን እና ኢትዮጵ ያውያንን በጋራ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶችን በማዘጋጀት በርካታ የገንዘብ ድጋፍ ከተለያዩ ተቋማት ማግኘት ያስችላል። ስለዚህ አዋጁ በጎ ጎኑን ተቀብሎ ወደ ስራ ማስገባት ያስፈልጋል።
ወይዘሮ ፎዚያ እንደሚያስረዱት፤ በዋናነት ስደተኞቹን በካምፕ ከማኖር ይልቅ ህብረተሰቡ ውስጥ ተቀላቅለው እንዲኖሩ በማድረግ የኢትዮጵያውያንን መሰረተ ልማት ፍላጎት በተያያዥነት ማሟላት ይቻላል። ስደተኞች በሚቆዩባቸው አካባቢዎች ለትምህርት፣ ለጤና እና ለተለያዩ ጉዳዮች የሚያስፈልጉ መሰረተ ልማቶችን ዓለም አቀፍ ተቋማት በሚሰጡት ገንዘብ ይገነባል። በመሆኑም ለስደተኞች ተብለው የሚገነቡ ዘመናዊ ትምህርት ቤቶች፣ ሆስፒታሎች፣ የውሃ አቅርቦት እና ለሌች ግንባታዎችን ኢትዮጵያውያንም በአካባቢያቸው በጋራ እንዲጠቀሙ ያስችላል። ስደተኞቹ ሁኔታው ተመቻችቶላቸው ወደአገራቸው ሲመለሱ ደግሞ ንብረቶቹ ሙሉ በሙሉ የኢትዮጵያውያን መገልገያ ሆነው ይቀጥላሉ። በዚህም መንግስት በእራሱ ወጪ ከሚገነባቸው ተቋማት ባሻገር ዓለምአቀፍ ተቋማትም ለኢትዮጵያውያን የሚሆኑ መሰረተ ልማቶችን በተዘዋዋሪ መንገድ የሚያቀርቡበት እድል ይፈጥራል።
ኢትዮጵያ እ.አ.አ በመስከረም 20 ቀን 2016 ላይ በአሜሪካን ኒውዮርክ በተደረገው የመሪዎች ጉባኤ የስደተኞችን አያያዝ ለማሻሻል በዘጠኝ ጉዳዮች ላይ ቃል ገብታ እንደነበረ የሚታወስ ነው። ጥቅል ህጎችን የያዘው የስደተኞች ጉዳይ አዋጅ 409/1996 ባለፈው ሳምንት በአዲስ ተተክቷል፡፡ የተወካዮች ምክር ቤት ዝርዝር ጉዳዮችን በያዘው እና ሰፊ የመስራት እና የመንቀሳቀስ መብቶችን የያዘ አዲስ አዋጅ አጽድቋል። የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ መረጃ መንግስት ከጠቅላላ ስደተኛው እስከ 10 በመቶ ያህሉን ስደተኛ የስራ እድሉ ተጠቃሚ ለማድረግ ተዘጋጅቷል። በዚህም በውጭ ድጋፍ በሚገነቡ የኢንዱስትሪ ፓርኮችና የመስኖ ልማት ስራዎች ውስጥ ስደተኞችንና ኢትዮጵያውያን በጋራ እንዲሰማሩ ይደረጋል። ፕሮጀከትቹንም የሚደግፉት እንደ ዓለም ባንከ ያሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት ናቸው። ለመስኖ ሥራ የሚሆን 10 ሺ ሄክታር መሬት አዘጋጅቶ ኢትዮጵያውያንና ስደተኞች በጋራ እንዲሰማሩ ለማድረግ የተያዘው ዕቅድ ነው። በዕቅዱ መሠረት እስከ አንድ መቶ ሺ ሰዎች ተጠቃሚ ይሆናሉ።
እንደ አቶ ኃይለስላሴ ከሆነ፤ በአዋጁ መሰረት ስደተኞችንና የአካባቢውን ነዋሪ የሚጠቅሙ የልማት ፕሮጀክቶች በመተግበር የሁለቱንም ማህበረሰቦች የኑሮ ደረጃ ማሳደግ ይገባል። ነገር ግን አዋጁን ተግባራዊ አለማድ ረግ እና የነዋሪውን ጥቅም አያስከብርም ብሎ መቀመጥ ሊገነቡ የታሰቡ ኢንዱስተሪ ፓርኮች እና የመስኖ ፕሮጀክቶች ላይ የገዝብ እጥረት ይፈጥራል።
እንደ ወይዘሮ ፎዚያ ገለጻ ደግሞ፤ አዋጁ የስደተኞችን የመንቀሳቀስ መብት ሲሰጥ አስገዳጅ ችግር የሌለባቸውን ለይቶ ለመቆጣጠር ይረዳል። በመሆኑ ትክክለኛ ስደተኛውን እና ያልሆነውን በመለየት የደህንነት እና የወንጀል ችግሮችን ለመቆጣጠር አይነተኛ ሚና አለው። በተጨማሪ አዋጁ ሲተገበር በስደተኞችና በአካባቢው ነዋሪ መካከል በውሱን የተፈጥሮ ሀብት ሽሚያ ሊነሱ የሚችሉ አለመግባባቶችን እና ግጭቶችን በመቀነስ ሚናው የላቀ ነው።
አዲስ ዘመን ጥር 19/2011
ጌትነት ተስፋማርያም