እየሮጥኩ ነው። ጫማዬን ጨምሮ እስከጉልበቴ ድረስ የዝናብ ፍንጣሪ አበስብሶኛል። ከላይ ይዘንባል። ከኮሮና ፍራቻና ከሰው ላለመጋፋት እሸሻለሁ። ዝናቡ አባይን ለመሙላት ሳይሆን እኔን ለማበስበስ የሚያሯሩጠኝ ይመስላል። በዚህ መሃል ደግሞ ነብሴ ከስጋዬ ካልተላቀቅኩ እያለች ግብግብ ይዛለች። ‹‹በዚህ ሰዓት ነበር አትሌቶችን ማመስገን›› እያልኩ እራሴን እረግማለሁ። ደሞ ስፖርት ለመጀመር ልክ እንደ ሁልጊዜው እምላለሁ፤ እገዘታለሁ።
አይደረስ የለ ደረስኩ። ካፍቴሪያው ሞልቷል። በሽታው ያራራቀውን ብርዱ በእልህ ያስተቃቀፈው ይመስላል። ስጋት ሆይ ወዴት ነው ያለሽው? ‹‹ድጋሚ ልሮጥ ነው›› እያልኩ በገባሁበት ፍጥነት ተስፈንጥሬ ወጣሁ። የታባቴ! ምን አስጎልቶ አስዋለኝ። ስፖርት ብሰራስ!
በረንዳው ላይ ስደርስ እግዜሩ አዘነልኝ መሰል አንድ ክፍት ወንበር ተመለከትኩ። ከወንበሩ ወዲያ ደግሞ ራቅ ብላ የተቀመጠች አንድ ወጣት ትታየኛለች። ድካሜን ረስቼ በደስታ ‹‹ዘርፈጭ›› ብዬ ተቀመጥኩ። በረጅሙ እየተነፈስኩ እያለ ደግሞ አስተናጋጇ ከተፍ አለች። ወይ ጉድ ምናለ ተንፍሼ ብጨርስ።
ዓይኗን እያስለመለመች ‹‹ምን ልታዘዝ?›› አለችኝ። ትንፋሼን ሳልውጥ ‹‹የሞባይል ካርድ አለ?›› አልኳት። ፈገግ ብላ ቃላት ለማውጣት ስቸኩል ‹‹በቃ እሺ ሻይ በበሶ ብላ አምጪልኝ›› አልኳት። እየሳቀች ወደ ሻይ አላቢው ሄደች። ሻይ በበሶ ብላ ምን ምን ይል ይሆን!?
በዚያኛው ጥግ የተቀመጠችው ወጣት ነገረ ሥራዬን ስትታዘብ ነበር። ካርዱን ከአቅራቢያ ጀብሎ ገዝቼ እስክመጣ ‹‹ስልጣኑን ማለቴ ወንበሩ ሰው አለው በይልኝ›› ብያት ተነስቼ ልሄድ ስል ‹‹እንካ በኔ ስልክ ደውል›› አለችኝ። እንደመደንገጥ ብዬ የምንኖርበት ዓመተ ምህረት ስንት ላይ እንደሆነ ለጥቂት ሰከንድ አሰብኩ። ግን ያው 2012 ነው። ሆሆ! በዚህ ሰዓት ማን ስልኩን አምኖ ለሰው ይሰጣል?
እየገለፈጥኩ ‹‹ኧረ ችግር የለውም እዚህ ጋር እኮ ነው›› ብዬ ስሽኮረመም ‹‹እንካ ጥላ ይዘህ ሂድ ዝናብ እንዳይመታህ›› በማለት ጭራሽ ሌላ ድንጋጤ ፈጠረችብኝ። ወይ ጥጋብ! ቅድም የስፔን ሰንጋ እንደሚያባርረው ሰው ስሮጥ የነበርኩ ሰውዬ በውስጤ ‹‹እኔ የጋሽ ከበደ ልጅ መች ዝናብ እፈራና›› በማለት የምስጋና ፈገግታ ለግሻት አሎሎ አሎሎ በሚያካክል ዝናብ እየተወቀጥኩ ካርዱን ገዝቼ ተመልሼ መጣሁ። ሻዩ ጠረጴዛው ላይ እኔ ወንበሬ ላይ እኩል ደረስን።
ልጅቷ አሁንም እዛው እንደተቀመጠች ነው። ቸርነቷ በዛብኝ። ደግነቷ ማረከኝ። ቀልቤንና ትንፋሼን ሰብሰብ አድርጌ ወደ ደግዬዋ ልጅ አቅጣጫ አማተርኩ። የእስልምና ሃይማኖት ሂጃብ ጠምጥማለች። በዚያ ውስጥ ትህትና የተላበሰ፤ በውብ ፈገግታ የተሞሸረ ቆንጆ ኢትዮጵያዊ ፊት አየሁ። ድፍረቴን ሰብስቤ ጉሮሮዬን ጠራርጌ ‹‹በዚህ ዘመን እንኳን ሳይጠይቁ ተለምኖም ንብረትን ለማያውቁት አይሰጥም ለትብብርሽ በጣም አመሰግናለሁ›› በማለት የምስጋና ፈገግታዬን ብልጭ አደረኩ። ቀጣዩ ምላሿ ደግሞ ይበልጥ ሰው እንዳምን ጥርጣሬዬን በቅጡ እንዳደርገው በር ከፋች ነበር። ዛሬም ተስፋ የሚሰጡ ንፁህ ልቦች እንዳሉ ትክክለኛ ማረጋገጫ ነበር።
ካርድ ፍለጋ ስቅበዘበዝ እንደተመለከተችኝና ልትተባ በረኝ እንደፈለገች ነገረችኝ፡፡ በፈጣሪዋ ሙሉ እምነት እንዳላት እንደዛው። ስጋት እንዳላደረባት ገለፀችልኝ። አስገራሚው ጉዳይ ግን ይሄ አይደለም። ጠዋት ወደ ከተማ ስትወጣ ያጋጠማት ነገር እንኳን እንድትተባበረኝ በቅጡ ፊት እንዳትሰጠኝ የሚያደርግ ነበር።
ነገሩ እንዲህ ነው። ወደ አንድ ስፍራ ለመሄድ እየተጣደፈች ነው። እሷና ሌሎች ሁለት ወንዶች በቆሙበት አንድ ሚኒባስ ይመጣና ይቆማል። በሴትነቷ እንዳከበራት አድርጎ ከወንዶቹ መርጦ ያስገባትና ጉዞውን ይቀጥላል።
ወዲያው ወያላው ‹‹ሂሳብ›› ሲል ጮክ ብሎ ይጠይቃታል። ለመክፈል ቦርሳዋን በከፈተችበት ቅፅበት እርሷ ከተቀመጠችበት ጀርባ የተቀመጠች አንዲት ወጣት የህመም ስሜት በማሳየት ለማስመለስ ትታገላለች። በዚህ ጊዜ ወያላው ‹‹ዝም ብለሽ ታያታለሽ እንዴ መስኮቱን ክፈችላት እንጂ ሲል ይጮህባታል›› በዚህ ሰዓት ውስጧ አንድ ነገር ጠረጠረ። ብዙ ጊዜ ሲወራ ትሰማለች። እሷም ብትሆን ንቁና ቀልጣፋ ነች። ክፉውና ደጉ ቶሎ ይገለፅላታል። የዘረፋ ታክቲክ መሆኑ ወዲያው ስለገባት የወያላውን ቁጣና ግፊት ችላ አለችው። እውነቷን ነበር። ከእርሷ በተሻለ ለመስኮቱ የቀረበ ሌላ ወጣት ልጅ ነበር።
ወያላ ሆኖ ዘረፋውን የሚተውነው ሰው በእንቢታዋ ተበሳጭቶ እርግማንና ስድብ ያዘንብባት ጀመር። አሟት ለማስመለስ የምትጥረው ወጣትም ወደ ቀልቧ ተመለሰች። እሷ ግን የከፈተችውን ቦርሳ ጠበቅ አድርጋ ይዛ በውሳኔዋ ፀናች። ሴራቸው እንደከሸፈ የገባቸው ‹‹የሿሿ ተዋንያን›› በብስጭት ወደምትፈልገው ቦታ እንደማይሄዱ በቁጣ ነግረዋት ከሚኒባሱ አስወረዷት። በጉልበት ያላትን የያዘችውን ሊቀሟት ይችሉ ነበር። ቲያትረኞቹ ግን ይሄ ትወና ስክሪፕታቸው ላይ አልነበረምና ሳይሳካ ቀረ። ከዚያ በላይ ግን ጥንቃቄዋና የምታምነው ‹‹አላህ›› ከዝርፊያ ጠበቃት።
ዝርፊያው የተሞከረባት ከእኔ ጋር በካፌ ከተገናኘን ከሰዓታት በፊት ነው። ሊያውም በጠራራ ክረምት! ሙከራው የዚህችን ቅን ኢትዮጵያዊ ልብ አልሰበረውም። ታዲያ ድርጊቱ ከልቧ ገና ሳይወጣና ማንነቴን ሳታውቅ ነው ስልኳን ለመስጠት እጇን የዘረጋችልኝ። ከዝናቡ በጥላዋ ልትከልለኝ የሞከረችው። በእርሷ እሳቤ ውስጥ በአንዲት ቀን በሰዓታት ልዩነት ያገኘችን ሰዎች የተለያየን ነን። ብትፈልግ በተመሳሳይ ከረጢት ውስጥ ከታን ቦርሳዋን ጠበቅ አድርጋ ይዛ እጆቿን ልትሰበስብ ትችል ነበር። ግን አላደረገችውም። ምክንያቱ ደግሞ ግልፅ ነበር። ለምን ብዬ ስጠይቃት እንዲህ ነበር ያለችኝ…
‹‹አየህ እኔ የተቸገረና ውስጡ በተንኮል የተሞላን ሰው ለይቼ ማወቅ እችላለሁ። ስመለከትህ የእውነትም እንደተቸገርክ ገብቶኝ ስልኬንም ሆነ ጥላዬን ልሰጥህ ፈቀድኩ። ከሁሉ በላይ ግን ሁሌም ጠዋት ከቤቴ ስወጣ በመንገድ ላይ ችግር እንዳያጋጥመኝ ‹ዱአ› አድርጌ ነው የምወጣው!›› አለችኝ ንፁህ ፈገግታዋን ብልጭ እያደረገችልኝ። እኔም በውስጤ እንዲህ አልኩና መረኳት ‹‹ቅን ኢትዮጵያዊ ልቦች ለዘላለም ይኑሩ››…
አዲስ ዘመን ሐምሌ 26/2012
ዳግም ከበደ