የዘመናዊ ትምህርት ፍላጎት እያደገ መምጣት የጀመረው በ19ኛው መቶ አመት ነው። ትምህርት የምዕመናን ማፍሪያ አይነተኛ መሳሪያ ነው ብለው የገመቱ ሚሲዮናውያን ትምህርት ቤቶች በመክፈትም ሆነ ጎበዝ ጎበዞችን ተማሪዎች ወደ ውጭ ሀገር ለትምህርት በመላክ በዚህ ረገድ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል። አጼ ቴዎድሮስ በአውሮጳ ቴክኖሎጂ በተለይም በዚያ ቴክኖሎጂ ወታደራዊ ጥቅም ተማርከው ወጣት ኢትዮጵዮጵያውያን በእጅ ሙያ የሚሰለጥኑበት ትምህርት ቤት ጋፋት ላይ አቋቁመው ነበር። ከአድዋ በኋላ ኢትዮጵያ ከአውሮጳና ከአውሮጳውያን ጋር ያላት ግንኙነት እየተጠናከረ ሲሄድ ዘመናዊ ትምህርት ለመስፋፋት አመቺ ሁኔታዎች ተፈጠሩ። …” የኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ አባት ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ፤ “ የኢትዮጵያ ታሪክ ከ1847 እስከ 1983 “በተሰኘው መጻፋቸው ይነግሩናል። መርስኤ ኀዘን ወ/ ቂርቆስ “ የሐያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ “ ደራሲ ደግሞ፤ “በዳግማዊ ምኒልክ ስም የመጀመሪያው የቋንቋ ተማሪ ቤት በሶስት ግብጻውያን አስተማሪዎች በ1899 ዓም ተከፈተ። “ ሲሉ ይነግሩናል።
ከ150 አመታት በላይ የዘለቀው የሀገራችን ዘመናዊ ትምህርት በታሪኩ እንደ ዘንድሮ ያለ ከፍተኛ ፈተና ገጥሞት አያውቅም። ከመጋቢት 7 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በኮቪድ 19 አደገኛ ወረርሽኝ የተነሳ በ26 ሚሊዮን ተማሪዎቻቸው ላይ ወደ 40ሺህ የሚጠጉ ትምህርት ቤቶች፣ ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች ደጃቸውን ዘግተዋል። ምን አልባት በሀገሪቱ የምዘና ስርዓት ለመጀመሪያ ጊዜ ከስምንተኛና ከ12ኛ ክፍል ተማሪዎች በቀር ወደ ቀጣዩ ክፍል እንዲዛወሩ ተወስኗል። አለማቀፉ የትምህርት ሁኔታም ከዚህ ያልተለየ መሆኑን የታይም መፅሔት ዘጋቢ ሜሊሳ ጎዲን ታትታለች። በመላው አለም የሚገኙ ሀገራት በኮቪድ -19 ዘመን ትምህርት ቤቶችን መልሶ ለመክፈት በየፊናቸው ጥረት እያደረጉ ነው። በ186 ሀገራት ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች 60 በመቶ ያህሉ ተዘግተዋል። በዚህም 1ነጥብ 5 ቢሊዮን ተማሪዎች ቤት ለመዋል ተገደዋል። በተለይ በአሜሪካ ወረርሽኙ በመባባስ ላይ መሆኑ ትምህርት ቤቶችን የመክፈት ጉዳይ አወዛጋቢ ሆኗል። ከምንም ነገር በላይ 2ኛው ፕሬziዳንታዊ ምርጫ ስለሚያስጨንቃቸው ዶናልድ ትራምፕ እያንዳንዱ ውሳኔያቸው ፖለቲካዊ ነጥብ ማስቆጠር ላይ ያነጣጠረ ነው። የዘርፉ ልሒቃንን ምክርና ሳይንሳዊ መረጃዎችን ችላ በማለት ኢኮኖሚው እና ከተሞች በመከፈታቸው ወረርሽኙ በአስደንጋጭና ለማመን በሚከብድ ሁኔታ ሊዛመት ችሏል። ዛሬም ከዚህ ሀቅ መማር ስላልፈለጉ ትምህርት ቤቶች እንዲከፈቱ በመወትወት ላይ ይገኛሉ።
ትምህርት ቤት በማይከፍቱት ላይ የሚደረግላቸው ድጎማ እንደሚቋረጥ በማንገራገሩ ላይ ይገኛሉ። የትምህርት ሚኒስትሩ ቤትሲ ዳቮስ የፕሬዝዳንቱን ሀሳብ ይጋራሉ። ለነገሩ ቢቃወሙ ነበር የሚገርመው። የተማሪዎችን፣ የመምህራንና የወላጆችን ጤና ለወረርሽኙ ሳያጋልጡ እንዴት ነው ትምህርቱን ማስጀመር የሚቻለው በሚል ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ግን ሚኒስትሯ መልስ መስጠት እንዳልቻሉ የፎሪን ፖሊስ መፅሔት ዘጋቢ ላውሬ ጋሬት ትናገራለች። ሚኒስትሯ ወረርሽኙን ለመከላከል የሚያስችል መመሪያም ሆነ የገንዘብ ድጋፍ አላቀረቡም። ሆኖም ትምህርት ቤቶች የየራሳቸውን የጥንቃቄ ስልት መቀየስ ይኖርባቸዋል ሲሉ ከማሳሰብ አልቦዘኑም። ሚኒስትሯ ከሲኤንኤን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ “ህጻናት በትምህርት ገበታቸው ላይ በአካል መገኘት ይኖርባቸዋል። “ ሲሉ ቀጭን ትዕዛዝ አስተላልፈዋል። ዳሩ ግን በሀገሪቱ የሚገኙ አብዛኛዎቹ ከተሞች በትምህርት ዘመኑ የማስጀመሪያ መርሀ ግብሩ መሰረት እንደማይከፈቱ ከወዲሁ እያሳወቁ ነው። በ
ምህጻሩ ሲዲሲ በመባል የሚታወቀው የበሽታዎች መቆጣጠርና መከላከል ማዕከል በበኩሉ የትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ የመክፈት ጉዳይ በትምህርት ቤቶች ወረርሽኙን ሊያስፋፋ እንደሚችል እያስጠነቀቀ ነው። ሆኖም አብዛኛዎቹ ትምህርት ቤቶች ወረርሽኙን ወደ ተማሪዎች፣ መምህራንና ወላጆች በማያጋባ መንገድ ለመጀመር አማራጮችን እያማተሩ መሆኑን የታይም መፅሔት ዘገባ ያትታል። ምን አልባት የሌሎች ሀገራትን ተሞክሮ ቀምሮ ከሀገራዊ ተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር ማዋሀድ አንዱ መላ ሊሆን ይችላል ትላለች ሜሊሳ በመጣጥፏ። በክፍል የተማሪዎችን ቁጥር መቀነስ፣ ማህበራዊ ፈቀቅታን መጠበቅ፣ ምርመራን ማሳደግ እና የመሳሰሉትን እርምጃዎች ትምህርት ቤቶችን ለመክፈትም ሆነ ላለመክፈት የውሳኔ ግብዓት በመሆን ሊያገለግሉ ይችላል። የተቀመጠው አቅጣጫ ለሀገራችንም ሊበጅ ይችላልና በተሳካ ሁኔታ ተማሪዎቻቸውን ወደ ፊደል ገበታቸው የመለሱ ሁለት ሀገራትን እና ያለ በቂ ቅድመ ዝግጅትና ጥንቃቄ ትምህርት ቤቶችን በመክፈቷ ውድ ዋጋ የከፈለች ሀገርን ለአብነት እንመልከት።
ዴንማርክ ፦ በፓርላማዋ ይሁንታ፤ ትምህርት የልጆች መብት ነው ብሎ በሚያምነው መንግስቷ አነሳችነት፤ ከአንድ ወር ሙሉ በሙሉ የእንቅስቃሴ እቀባ በኋላ፤ ከምዕራባውያን ሀገራት ቀድማ ትምህርት ቤቶችን ሚያዚያ መጀመሪያ ላይ በመክፈት ፋና ወጊ የሆነችው ዴንማርክ ናት። እድሜያቸው ከ2 እስከ 12 የሚደርስ አስራ ሁለት አስራ ሁለት ህጻናትን የያዙ አነስተኛ ቡድኖች ይመሰረታሉ። የመጀመሪያው ቡድን “ ተከላካይ አረፋ “ በመባል ይታወቃሉ። የቡድኑ አባላት ወደ ትምህርት ቤት የሚመጡት በተናጠልና በጊዜ ልዩነት ነው። ምሳቸውን ለየብቻ ይመገባሉ፤ ለእያንዳንዳቸው የየራሳቸው የመጫዎቻ ቦታ አላቸው፤ በየሁለት ሰዓቱ እጃቸውን ይታጠባሉ፤ ጭምብል ለመልበስ አይገደዱም፤ በተማሪዎች ዴስክ መካከል የሁለት ሜትር ርቀት ሲኖር፤ የትምህርት መርጃ መሳሪያዎች ቢያንስ በቀን ሁለት ጊዜ ይጸዳሉ፤ በተቻለ መጠን ትምህርት ከክፍል ውጭ እንዲሆን ይበረታታል፤ ወላጆች የትምህርት ቤቱን ቁሳቁስ እንዲነኩ አይፈቀድም። እነዚህ እርምጃዎች እስካሁን ውጤታማ የሆኑ ይመስላል። ትምህርት ቤቶች በመከፈታቸው በወረርሽኙ የተያዙ ተማሪዎች፣ መምህራንና ወላጆች አልተገኙም። ዴንማርክ በዚህ ውጤት በመበረታታት ከግንቦት መጀመሪያ ወዲህ ደግሞ እድሜያቸው ከ12 እስከ 16 የሆነ ተማሪዎችን ከፍ ብለን በተመለከትነው አግባብ ወደ ትምህርት መልሳለች። ይህ የዴንማርክ ፈለግ የተከተሉት ጀርመንና ፊላንድ ውጤታማ መሆን እንደቻሉ የታይም መፅሔት ዘገባ ያወሳል። ዴንማርክ ከመጋቢት ጀምሮ ሙሉ ለሙሉ እንቅስቃሴን መገደቧ እና በወረርሽኙ የተጠቁ ዜጎቿ አኃዝ ዝቅተኛ መሆኑ ለስኬታማነቷ ሌሎች ምክንያቶች ናቸው። ይሄን ባለአምስት ኮከብ ሊባል የሚችል ጥንቃቄ አይደለም ኢትዮጵያ አሜሪካም መፈጸም ይቸግራታል። ሆኖም ወደ አለን አቅም አውርደን ልናላምደው እንችላለን።
ደቡብ ኮሪያ ፦ በደቡብ ኮሪያ ትምህርት ለመጀመር የተቆረጠው ቀን አምስት ጊዜ ተራዝሟል። ከተከፈቱ በኋላ በዋና ከተማዋ ወረርሽኙ እንደገና ካገረሸ እና ቫይረሱ ተማሪዎችን ማጥቃት በመጀመሩ ትምህርት ቤቶች እንደገና ተዘጉ። ዛሬ ትምህርት ቤቶች እንደገና ተከፍተዋል። በር ላይ ሙቀታቸው እየተለካ፤ ማህበራዊ ርቀታቸውን ጠብቀው፣ የአፍንጫ ተአፍ መሸፈኛ ጭምብል ለብሰው እና እጃቸውን ደጋግመው እየታጠቡ ትምህርታቸውን ይከታተላሉ። አንዳንዶቹ በፈረቃ ሲያስተምሩ ሌሎች ትምህርት ቤቶች ደግሞ የክፍሉን ገጽ ለገጽ ትምህርት ከኦን ላይን አዳቅለዋል።
እስራኤል ፦ በሚያዚያ ወር መጨረሻ ላይ ትምህርት ቤቶች በአንድ ክፍል የሚማሩ ተማሪዎችን ቁጥር በመቀነስ ተከፈቱ። ከሁለት ሳምንት በኋላ የተማሪዎች ቁጥር ቀድሞ ወደ ነበረበት ተመለሰ። ተማሪዎች ወደ ቤት ከሄዱ በኋላ ሙቀቱ በከፍተኛ ሁኔታ ሲጨምር ጭምብላቸውን እንዲያወልቁ ተፈቅዶላቸው ነበር። ዳሩ ግን ትምህርት ቤቶች ከተከፈቱ አንድ ወር በኋላ ሰኔ ላይ 2026 ተማሪዎች፣ መምህራንና ድጋፍ ሰጭ ሰራተኞች በኮቪድ -19 ተጠቅተው በመገኘታቸው፤ 28 ሺህ 147 ተማሪዎች በአስገድዶ ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ ተደረገ። በአንድ ትምህርት ቤት 130 ተጠቂዎች ተገኙ። ትምህርት ቤቶችም እንደገና ተዘጉ። ትምህርት ቤቶች ከመከፈታቸው በፊት በቀን 50 የነበረው የተጠቂዎች ቁጥር ከተከፈቱ በኋላ ወደ 1,500 አሻቀበ። እንደ እስራኤል መንግስት መረጃ ከሆነ በሰኔ ወር ከተመዘገበው ከፍተኛ የተጠቂዎች ቁጥር ትምህርት ቤቶች በ2ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። በእስራኤል ሁለተኛው የወረርሽኙ ማዕበል እንዲቀሰቀስ ያደረገው የትምህርት ቤቶች ያለ በቂ ዝግጅት መከፈት እና የበዛ እንዝህላልነት መኖሩ ነው። የእስራኤል ትምህርት ሚኒስቴር ከዚህ በኋላ ትምህርት ቤቶችን ለመክፈት መነሻ የሚያደርገው ሀገር አቀፉን የወረርሽኝ ስርጭት አኃዝ ሳይሆን የየከተሞችን ወቅታዊ መረጃ ነው። በቀጣይ እያንዳንዱ ትምህርት ቤት የሚከፈተው በከተማው ነባራዊ ሁኔታ ላይ ተመስርቶ ይሆናል።
እንደቀብድ
ከእነዚህ ሶስት ሀገራት በአዎንታም ሆነ በአሉታ ተሞክሮ ቀምሮና ከሀገራዊ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር አዋህዶ ትምህርት ቤቶች የሚከፈቱበትን መመሪያ ለማዘጋጀት ግብዓት በመሆን ሊያገለግሉ ይችላሉ። የኢፌዲሪ ትምህርት ሚኒስቴርም ሆነ የከፍተኛ ትምህርትና የሳይንስ ሚኒስቴር ትምህርት ቤቶችና ዩኒቨርሲቲዎች እንዴት መከፈት እንዳለባቸው ጥናት እያደረጉና መመሪያዎችን እያሰናዱ ይሆናሉ ብዬ ስለማምን፤ ወላጆችና የትምህርት ማህበረሰቡም በጥፍሩ ቆሞ እየተጠባበቀ ስለሆነ፤ እነዚህ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችም የደረሱበትን ውሳኔም ሆነ ያዘጋጇቸውን መመሪያዎች ስራ ላይ ከማዋላቸው በፊት የዘርፉ ተዋንያን እንዲያወያዩ ለማበረታታት የሚከተሉት የሀሳብ ቀብዶች አሲዛለሁ።
1ኛ . ትምህርት ቤቶችንና ዩኒቨርሲቲዎችን በሀገር አቀፍ ደረጃና በተመሳሳይ ጊዜ ወጥ በሆነ አግባብ ከመክፈት ይልቅ እንደየ ክልሎችና አካባቢዎች ተጨባጭ ሁኔታ በሂደትና ደረጃ በደረጃ መክፈት፤
2ኛ . የቫይረሱ ስርጭት ከፍተኛ በሆነባቸው እንደ አዲስ አበባና መሰል ከተሞች ትምህርት ቤቶችን ተጣድፎ መክፈት መዘዙ የከፋ ሊሆን ስለሚችል ጥንቃቄ ማድረግ ያሻል።
3ኛ . ትምህርት ቤቶችንም ሆነ ዩኒቨርሲቲዎችን ከመክፈት በፊት የምርመራ አቅምን ማሳደግ እና ተማሪዎችን፣ መምህራንና ሰራተኞችን በስፋት መመርመር ግድ ይላል። ፈጣሪ ሀገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ከዚህ አደገኛ ወረርሽኝ ይጠብቅ ! አሜን።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 25 ቀን 2012 ዓ.ም
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን) fenote1971@gmail.com