ትናንት እና ነገ
የመስከረም ወር ለእኛ ለኢትዮጵያዊያን የወራት በኩር ነው። የብኩርና ክብርና መብት ደግሞ ምን ያህል የላቀ እንደሆነ ማሕበረሰባችን በሚገባ ይገነዘበዋል። በኩር ልጅ (ሴትም ሆነች ወንድ) ለወላጅ ጌጥና ኩራት መሆን ብቻ ሳይሆን የቤተሰብን ኃላፊነት በጫንቃ ላይ የመሸከም ግዴታንም ያካትታል። የመስከረም ወር ዐውድ ዓመትም ነውና አሥራ አንዱን የወራት እኩዮቹንና ሚጥጥዬዋን ጳጉሚትን ከኋላው አስከትሎ ሲመጣ ብዙ ይዘመርለታል፣ ይቀኙለታል፣ በተስፋ አብሳሪነቱም ይናፈቃል። መስከረም የልምላሜ ከፋይ ተጎናጽፎ፣ በተፈጥሮ ሜክ አፕ ተውቦና በመስቀል አበባ አሸብርቆ ብቅ የሚለው “እንቁጣጣሽ” እየተባለ እየተወደሰና “የአዲስ ዓመትን” ክብርና ሞገስ ተጎናጽፎ ጭምር ነው።
“ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ” ሆኖ አንጂ “ሮሽ ኻሻነህ” (Rosh Hashanah) እየተባለ በእስራኤላዊን ዘንድ የሚወደሰው የመስከረም ወር የዓመቱ ቁንጮ ወር ተደርጎ ብቻ ሳይሆን አዳምና ሔዋን (አደምና ሐዋ) እና ፍጥረታት በሙሉ የተፈጠሩበት ወር እንደሆነ በጽኑ እየታመነ ነው። ስለ መጻዒው “አዲሱ” የመስከረም ወር ለማሰብ ገና ነሐሴና ጳጉሚትን ስላልተሻገርን ቀድሞ መስከረምን ለማስታወስ ለምን አስፈለገ? የሚል ጥያቄ እንደሚነሳ ይገባኛል። እርግጥ ነው ያልተሻገርናቸው “የአሮጌ ዓመታችን አዳዲስ ቀናት” ከፊታችን እንደሚጠብቁን አልጠፋኝም። በግሌ የማምነው መጭዎቹ የነሐሴና የጳጉሜ ወራት በሀገራችንና በራሳችን ኃላፊና መጻኢ ጉዳዮቻችን ዙሪያ እያንዳንዳችን የጥሞና ጊዜ ወስደን ለማሰላሰል ብንጠቀምባቸው ይበጅ ይመስለኛል። የጽሑፌን አካሄድ የቃኘሁት በዚሁ አቅጣጫ ነው።
የመጭውን አዲስ ዓመት “አዲስ መስከረም” አቀባበል በተመለከተ የግል ሃሳቤን ወደኋላ ግድም በማጠቃለያ መልክ እንደማቀርብ በመጥቀስ ከትናንቷ የመስከረም ፀሐይ እስከ ዛሬዋ የሐምሌዋ ደብዛዛ ጀንበር በሸኘናቸው አሥራ አንድ ወራት ውስጥ የተከናወኑ ዐበይት ሀገራዊ የስኬት ማሳያዎችንና ተግዳሮቶችን በወፍ በረር ቅኝት ለመዳሰስ እሞክራለሁ።
ዓለም የተደመመባቸው ስኬቶቻችን፤
የ2012 ዓ.ም የመስከረም ወር በሀገራችን ታሪክ ለእኛ ለባለጉዳዮቹ ብቻ ሳይሆን አፍሪካና መላው ዓለም ጭምር አብሮን የፈነደቀበት ወር እንደነበር አይዘነጋም። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የኖቤል የሰላም ሽልማትን በአጭር ዓመታት የአመራር ስኬት መቀዳጀታቸው የሀገራችን የከፍታ ዘመን ጅማሮ በእርግጥም የሰመረ ለመሆኑ መልካም ማረጋገጫ ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትራችንን ለሽልማት ያበቃቸው ዋነኛ ጉዳይ ከኤርትራ ጋር ሻክሮ የነበረውን ግንኙነት ውለው ሳያድሩ ማደሳቸው ሲሆን የአጋጣሚ ጉዳይ ሆኖ ከስልሳ ሰባት ዓመት በፊት ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር የተዋሃደችው በ1945 ዓ.ም በመስከረም ወር በመጀመሪያው ቀን ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የኖቤል ሽልማታቸውን ከተቀበሉ በኋላ ባደረጉት ንግግር ውስጥ ከዛሬ 55 ዓመት በፊት በ1957 ዓ.ም፤ እሳቸው ራሳቸው አንኳ ባልተወለዱበት ዓመት፤ ዛሬ እየመሯት ያለችው ታላቂቷ ሀገራቸው ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ከፍተኛ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሽልማት ድርጅት ሽልማት ያበረከተችው እርሳቸውን ለሸለመው የኖቤል ድርጅት መሆኑን ባለማስታወሳቸው ይቆጫል። ለኖቤል ድርጅቱ የተበረከተውን ሽልማት በአካል ተገኝተው ከንጉሠ ነገሥቱ እጅ የተቀበሉት የወቅቱ የድርጅቱ ፕሬዚዳንት የነበሩት ፕሮፌሰር ቲ. ሲሲያስ ነበሩ። ከስምንት ኢትዮጵያዊያንና የውጭ ሀገራት ዜጎች መካከል አንዱ በመሆን ውድድሩን በማሸነፍ ፕሬዚዳንቱ ሽልማቱን መቀበላቸውን ጠቅላይ ሚኒስትራችን በንግግራቸው ውስጥ ቢያስታውሱ ኖሮ ምናልባትም ታሪኩ በድርጅቱ መዘክር ተቀዳሚ ሆኖ ለሁልጊዜም መጠቀሱ ብቻ ሳይሆን ያ አስደናቂው የኖርዌጂያኑ የኖቤል ሽልማት መቀበያ አዳራሽ በጭብጨባ በተንቀጠቀጠ ነበር። ዳሩ ለቁጭት ካልሆነ በስተቀር ነበር አያኮራ!
ሌላውና በሁለተኛነት የምጠቅሰው ስኬት የዓለም ሀገራት ዓይኖች ሁሉ ወደ ኢትዮጵያ እንዲንጋጠጥ ምክንያት የሆነበትን አንድ ክስተት ነው። በዚሁ ዓመት በታህሳስ ወር ሀገሬ ወደ ህዋ ያመጠቀቻት ሳተላይት ጉዳይ እንደዋዛ የሚታይ አልነበረም። ETRSS-1 የሚል ስያሜ የተሰጣት ይህቺ የስፔስ ሳይንስ ታሪካችን የበኩር “ልጅ” አገልግሎቷ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው ብቻ ሳይሆን ለሀገራዊ የገጽታ ውበት ማድመቂያነትም በጥሩ አብነት ሊታወስ ይገባ ይመስለኛል። ሳተላይቷን በማምጠቅ ሂደትም ሆነ በመጠቀችበት ዕለት በጨረቃ ላይ ከተንፈላሰሰችው የአሜሪካኗ አፖሎ 17 ጋር ተያያዥ የሆነውን አንድ አስገራሚ ሀገራዊ ታሪክ ባለመታወሱ ትንሽ ቅር አሰኝቶኝ ነበር። ታሪኩ ቢጠቀስ ኖሮ ምናልባትም የበርካታ ሚዲያዎችን ቀልብ ስቦ የሀገራችንን ስም ከፍ ማድረግ በተቻለ ነበር። የናሳዋ አፖሎ 17 ወደ ጠፈር መጥቃ ጠፈርተኞቹ በጨረቃ ላይ እየተራመዱ ዓለምን ለግርምት የዳረጉት ዲሴምበር 7 ቀን 1972 ዓ.ም ነበር። የመንኮራኩሯን የጠፈር ጉዞ ከሌሎች መሰል ጉዞዎች ለየት የሚያደርገው በወቅቱ ከሀገራዊ የሉዓላዊነት ነፃነት ጋር ተያይዞ በከበረና በሩቅ ዘመን ታሪክ መስፈርትነት ሀገሬ ተመርጣ አንድ ሁኔታ መከናወኑ ነበር። ከዓለም ሀገራት መካከል ክብርት ኢትዮጵያ አንዷ ሆና በመመረጥ የብሄራዊ ኩራቷና ክብሯ መገለጫ በሆነው በአርንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ሕብረ ቀለማት የተዋበው ብሔራዊ ሰንደቅ ዓለማዋ ከአፖሎ መንኮራኩር ጋር ወደ ጨረቃ ተጉዞ “ጉብኝት” አድርጎ መመለሱን ብዙ ዜጎች የሚያስታውሱ አይመስለኝም።
እርግጠኛነቱን ለማጣራት ጊዜ ቢያስፈልግም ከብሔራዊ ሰንድቅ ዓላማችን ጋር የነፍሰ ሄሩ እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት የሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ወካይ የጥበብ ሥራና የሀገራችን የወቅቱ ቅንስናሽ ሳንቲሞችም አብረው እንደተጓዙ በስፋት ይወራ ነበር። እውነታውን ወደፊት አጣራለሁ። በነገራችን ላይ ከኖቤል ፕሬዚዳንቱ ጋር በ1957 ዓ.ም የመጀመሪያውን የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሽልማትን ካሸነፉት መካከል አፈወርቅ ተክሌ አንዱ ነበሩ። ለማንኛውም ወደ ጨረቃ ተጉዞ በክብር የተመለሰውን ጠፈርተኛ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማችንን ሐምሌ 8 ቀን 1965 ዓ.ም ለቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ከጨረቃ ላይ ከመጣው ደንጊያ ጋር በክብር ያስረከቡት በወቅቱ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩት ሚስተር ሮስ አዴር እንደነበሩ በዚሁ ታሪካዊ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ በማግሥቱ ዜናው በስፋት ተዘግቦ ነበር።
ሌላውና የዓለምን ሕዝቦች ብቻ ሳይሆን ተፈጥሮን ራሷን ጭምር “በአንድ እግር አቁሞ” ያስደመመው ስኬታችን የታላቁ የህዳሴ ግድባችን የውሃ ሙሌት መጀመሩ ነው። ዓለም ከተፈጠረ፣ ዘመን ከተቆጠረ ጊዜ ጀምሮ “አባ ከና” ሳይባል እየተከዘ በመንጎድ ሌሎች ሀገራትን ሲያለማ፣ ሲያረሰርስና ሲያበለጽግ የኖረው የግዮን ወንዛችን ለመጀመሪያ ጊዜ ከቤት እንዲውል የተደረገው በዚሁ በተያያዝነው የሐምሌ ወር ውስጥ ነበር። የወንዛችን መከተር ጠላታቸውን እስኪበቀሉ ድረስ የፀሐይን ዑደት በተዓምር ካስቆመው ከሙሴ ደቀ መዝሙር ከኢያሱ ታሪክ ጋር ቢመሳሰል አይበዛበትም። ምስክርነት በሦስት ስለሚጸና በዓመቱ ውስጥ ያኮሩንን እነዚህን ዐበይት ሀገራዊ ስኬቶች ቆነጠርኩ አንጂ መታወስ የሚገባቸው ሌሎች ትሩፋቶችም ነበሩ።
ዓለም ስለ እኛ የታመመባቸው አሳዛኝ ክስተቶች፤
መቼም ሕይወት በተቃርኖ የተሞላ ስለሆነ ለደግ ደጉ ስኬቶቻችን የምንዘምረውን ያህል ለክፉ ክስተቶችም በግልጽነት መቆጨት ያለብን ይመስለኛል። በዚሁ በተያያዝነው ዓመት በተለይም በጥቅምትና በሰኔ ወራት በሀገራችን በርካታ አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶች፣ መፈናቅሎች፣ የንጹሐን ሞትና የሀብት ውድመቶች ታሪካችንን ያቆሸሹ ክፉ እድፎች ነበሩ። በዘር ካንሰር በታመሙ እኩያን የመንጋ ጥርቅም በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎቻችን ሕይወት በከንቱ ተቀጥፏል፣ ብዙዎችም ቆስለዋል ክፉኛም ተጎድተዋል። በሺህዎች የሚቆጠሩትም በክፋት አረቄ በሰከሩ ልበ ስውራን እርጉማን ተፈናቅለዋል። በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር የዜጎች ንብረትም የእሳት ሲሳይ ሆኖ ወድሟል። ይህን መሰሉ የሞት፣ የመፈናቀልና የውድመት መርዶ ሁላችንንም የሀዘን ማቅ አልብሶ ማለፉ ብቻ ሳይሆን የዓለምን ማሕበረሰብ ጭምር አንገት ያስደፋ ነበር። የሰላም አየር እየማጉ ባሉ ሀገራት መካከል መኖራቸውን እንደ መመከቻ ጋሻ በመቁጠር የዘረኝነትን ወረርሽኝ እየላኩ ጤና የሚነሱን ወበከንቱዎች የሚጮኹባቸውን እርባና ቢስ የተቃውሞ ጩኸቶች አስመልክቶ፤ “እነዚህ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ነን ባዮች በገዛ ሀገራቸው ልማትና ስኬት ይቀናሉ ማለት ነው? ከዘረኝነት ደዌስ መቼ ነው የሚፈወሱት? እኛንስ ባይረብሹንና በዕለት እንጀራቸው የሥራ ሰዓታት ላይ ባያላግጡ ምን ነበረበት?” እያሉ የየሀገራቱ ዜጎች እንደናቋቸውና እንቱፍ በማለት አንቅረው እንደተፏቸው ማን በነገራቸው። ለመሆኑ ህመሙ ከእኛም ተርፎ ለሌሎች ሀገራትም ጥዝጣዜ መፍጠሩን ህሊና ላለው ሰው ማመዛዘን እንደምን ይከብደዋል።
ከዓለም ሕዝብ ጋር አብረን የታመምንባቸው ጉዳቶቻችን፤
ዘር፣ ቋንቋ፣ ባህል፣ ብልጽግና ወይንም ድህነት፣ ዝና አለያም ተራ ዜግነት፣ መሪነት ወይንም ተመሪነት፣ ከምሥራቁም ሆነ ከምዕራቡ፣ ከሰሜኑም ሆነ ከደቡቡ የዓለማችን ክፍሎችና ዜጎቻቸው ጋር የኮቬድ 19 ወረርሽኝ የተገዳደረን፣ ግራ ያጋባንና ያስተከዘን በእኩል ደረጃና ስሜት ነው። ወረርሽኙ ለጊዜው ይህ ነው በተባለ የምርምር መፍትሔ ገና ሰላልተገራ በደዌው የሚለክፋቸው የፕላኔታችን ሕዝቦችና ሕይወታቸውን የሚነጥቃቸው ዜጎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ ሲያሻቅብ እንጂ ሲቀንስ አናስተውልም። በሌሎች ዘንድም ሆነ በእኛ ቀዬ ወረርሽኙ በትሩን እያሳረፈ ያለው ያለ አድልዎ በእኩል ደረጃ ነው። ልጆቻችን ከትምህርት ገበታ ተለይተው በቤታቸው ግቢ ውስጥ ከቆለፍንባቸው ወራት ተቆጥረዋል። የቤተ እምነት ደጃፎች ተዘግተው ምዕመናን በነፍስ ርሃብ መሰቃየት ከጀመሩም ሰነባብቷል። ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ የስፖርት፣ የኪነ ጥበባት፣ የተማሪዎች ምረቃና በርካታ ማሕበራዊ ዝግጅቶቻችን ተሰርዘው በእህህታ መነፋረቅ ከጀመርን እነሆ የዓመት እኩሌታችንን ልንዘክር ቀናት ናቸው የቀሩን። የፖለቲካ ህመምና የኢኮኖሚ ማፋሸኩም እየባሰበት እንደሚሄድ እያስተዋልን ነው። ይህ ክፉ ወረርሽኝ ዓለምን በእጁ መዳፍ አስገብቶ እያዳሸቀ ያለው መጠኑንና ዓይነቱን አስፍቶ እንጂ ወደ መረታት ተቃርቦ አይመስልም። ስለዚህም የታመምነው፣ የተጎዳነውና የምንማቅቀው ለብቻችን ሳይሆን ከዓለም ሕዝቦች ጋር በእኩል ደረጃ ነው።
በግል ያስቆዘሙን ሀገራዊ ክስተቶች፤
በክፉ ድርጊት ፈጻሚ እኩያን ተግባራት ጥፋትና ውድመት ደጋግሞ እንደፈተነን ቀደም ሲል ጠቅሻለሁ። ባጋጠሙን ሀገራዊ ተግዳሮቶች ምክንያትም ዓለም እኛን በትዝብት እኛ ራሳችን እርስ በእርስ ለመጠፋፋት በሚፈጸሙ ጥፋቶች ለትዝብት መደረጋችን ምን ያህል አሳፋሪ እንደሆነ ለሁላችንም ግልጽ ነው። ከዚሁ ጎን ለጎን በብሔራዊ ምርጫ መራዘም መንስዔ የተፈጠሩ ሀገራዊ እንኪያ ሰላንትያና አታካራዎች በፍጹም የሚዘነጉ አይደለሙ። “ምርጫ ምን ሲደረግ ይራዘማል” እየተባለ ዜጎች ዘገር እየነቀነቁ፣ ሰይፋቸውን እየመዘዙ ለአመፅ እንዲዘጋጁና እንዲሞሻለቁ በመርዝ የተለወሱ በርካታ ጥሪዎች ሲተላለፉ መክረማቸው አይዘነጋም። “ምከረው፣ ምከረው እምቢ ያለ እንደሆነ መከራ ይምከረው” የሚለው ብሂል በእምቢ ባዮቹ ሞገደኞች ላይ ተግባራዊ ሆኖ የወህኒ በሮች እንደ አዲስ መከፈት እንደጀመሩ እያስተዋልን ነው። “አርፋችሁ የፖለቲካ ጨዋታችሁን በሰላም ተጫወቱ” እያለ ሲለማመጥ የከረመው መንግሥት በትዕግሥቱ ርዝመት ጨጓራችን መላጡ ገብቶት ነው መሰል መረር ያለ እርምጃ በመውሰዱ ያሸለበ የሚመስለውን የፍትሕ ሥርዓት ሲቀሰቅስ እያስተዋልን ነው። ቢዘገይም ደግ አደረገ!
ዘመነ ኮቪድ በሀገር ሁለንተናዊ መልክ ላይ ማዲያት ማልበሱ እንደተጠበቀ ሆኖ “ከእጅ ወደ አፍ” የሆነውን የብዙ ዜጎች ሌማት ያለ አዋይ ባዶ እያስቀረ እንደሆነም እየተመለከትን ነው። የኑሮ ወድነቱ ንሮ ሰማየ ሰማያት በመመንጠቁ የምንታዘበውና የምንቆዝመው ሽቅብ በማንጋጠጥ ከሆነ ሰነባብቷል። ቢያንስ በመለስተኛና በትንንሽ የንግድና የአገልግሎት የሥራ መስክ ላይ የተሰማራው ወገን ወረርሽኙ ባስከተለው መቀዛቀዝ ክፉኛ ተጎድቶ ስለቆሰለ የንግድ ፈቃዱን በመመለስ ሱቁንና ቢሮዎቹን እየከረቸመ ቤት በመዋል መተከዙን ተያይዞታል። “የገቢዎች አምባሳደር” የሚል ሀገራዊ የአገልግሎት ኃላፊነት እንደተሰጠው አንድ ዜጋ የሀገሪቱን ገቢዎች የሚመራውና የሚቆጣጠረው ግዙፍ ተቋም ከንግድ ሥርዓቱ እያነከሱ በመውጣት የንግድ ፈቃዳቸውን ለመመለስ የሚራኮቱትን ዜጎች ሕመም ተረድቶ በልዩ መስተንግዶ ማከም እንጂ ባያስጨንቃቸው እመክራለሁ። “ሕግ ሕግ ነው!” እያለ መመሪያ በመጥቀስ ተስፋ በቆረጡ ዜጎች ላይ ጅራፍን ማሳረፍና በቢሮክራሲው ሰንሰለት ጠፍሮ ከማስለቀስ ይልቅ ክፉው ጊዜ እስኪያልፍ ድረስ ቢያግዛቸው አይከፋም። ያለበለዚያ፤“መከራው አብቅቶ ኮቬድ ይጠፋና፣ ያስተዛዝበናል ይሄ ቀን ያልፍና።” ተብሎ እንዳይተረትበት በርህራሄና በኃላፊነት የማገዝ ሥራውን ቢያከናውን ታሪኩ የሚሰምር ይመስለኛል። ለንግድ ሥራም ሆነ ለመኖሪያነት ቤቶቻቸውንና ቢሮዎችን የሚያከራዩ ግለሰቦችና ተቋማትም ቢሆኑ ቀን በጨለመባቸው ግፉዓን ላይ ይበልጡኑ ተስፋቸውን አጠልሽተው ወደ ሞት እንዳይነዷቸው በርህራሄ ቢያስቧቸው አይከፋም። እነዚህ ጥቂት ማሳያዎች ዜጎችን በግል እንዲያነቡ የሚያስቆዝሙ ሀገራዊ ሀዘኖቻችን ናቸው።
የመጭውን መስከረም ፀሐይ እንዴት እንሙቅ? መልሴ አጭር ነው። በተስፋ፣ በብሩህ ስሜት፣ በደማቅ ፀሐይነቷ፣ በሀሴትና በፈካ ሰብእና፣ ተንገድግዶም ቢሆን መቆም እንዳለ በመረዳት፣ ጨለምተኝነትን ከአእምሮ በማስወገድ፣ ወድቆ መነሳት የተፈጥሮ ሕግ መሆኑን በመቀበል፣ በመረዳዳትና በመደጋገፍ ቢሆን ሰብእናችንም ሆነ ታሪካችን ትዝብት ላይ እንደወደቀ ሳይቀር ፈጥነን ልናገግም እንችል ይሆናል። የመጨረሻው ማሳረጊያና መሰናበቻዬ መዝሙር ነው። መዝሙሩ የቀድሞዎቹ የዝዋይ ሕጻናት አምባ ዕምቡጥ አበባዎች ከሦስት ዐሠርት ዓመታት በፊት የዘመሩት ነው። ዛሬም ድረስ ከሕጻናት እስከ ጎልማሶችና አረጋዊያን ድረስ ዜማው በመንፈሳችን ውስጥ ታትሞ በሕያውነት ስላለ የማስታውሰው ግጥሙን ብቻ ይሆናል። እንጉርጉሮውን ለአንባቢያን ትቻለሁ። ፀሐዬ ደመቀች፤ ደመቀች፣ ብርሃኗን ለእኛ ማለት አወቀች። ፀሐይ ብርሃን ፈንጥቃ፣ ከአድማስ ወደ እኛ መጥቃ፣ ጊዜው ደመቀ ጠራ ሰማይ፣ በእናት ሀገር በእማይ። አሜን! ብሩህ ዓመት ከፊታችን አለ። ሰላም ይሁን!
አዲስ ዘመን ሐምሌ 25 ቀን 2012 ዓ.ም
(ጌታቸው በለጠ – ዳግላስ ጴጥሮስ) gechoseni@gmail.com