ስለፍርሃት ምርጥ ነገር ብሏል፤ ጋሽ ስብሐት። “ፍርሃቴን ወድደዋለሁ፤ በአጉል ድፍረት ከማፈራው ጠላት ይልቅ ወዳጀ ብዙ ሆኛለሁና።” ብሏል። (ዕረፍቱ መልካም ይሁንለትና) በትምህርትና በስራ ባህሪውም፣ ከፈሪዎቹም ከአስፈራሪዎቹም ጋር ዝንባሌያቸውን አይቷል፤ በክፋታቸው ወርዷል ፤ በማንነቱ ወጥቷል። ይህን ያልኩት ለመነሻ ያህል ነው። ፍርሃት፣ ከግለ-ባህሪ የሚመነጭ ብዙ ጊዜ ሰበብ የማያጣው፣ በጥቂቱ ከትንሽ እውነት የሚመነጭ በሰው ልጅ ላይ የሚታይ ነባር ጠባይ ነው፤ ቁምነገሩ ፍርሃታችንን እንደምንፈታበት መንገድ የተለያየ መሆኑ ነው።
የፈሪ ሰው የፍርሃቱ መነሻ ልዩ ልዩ ነው። ከግል ገጠመኙ ሊነሳ ይችላል፤ ድንገተኛና ክፉ ድርጊያ ሊያስነሳው ይችላል፤ የልጅነት ክፉ ትርክት ሊቀሰቅስበት ይችላል፤ ልዩ ጫናም ወደፍርሃት ሊከትተው ይችላል። ይህንን ያልኩት ያለምክንያት አይደለም። በርካታ ሰዎች ይህንን ከሰማሁ በኋላ እና ያንን ካወቅሁና ካየሁ በኋላ፣ እንዲህና እንዲያ ሆንኩ ሲሉ ይደመጣሉና ነው።
አንዱን የዕድሜ ልምዴን ላውጋችሁ፤ ከዚህ በፊት ተጠቅሜበትም ከሆነ “አፉ በሉኝና” ተከታተሉኝ። ወጣት ልጆች ሆነን ሳለ፣ ከመካከላችን የነበረ አንድ ጓደኛችን፣ እኛ በቀላሉ ይሆንልንና እናወጋ የነበረውን የፍቅር ታሪክ ንዴትና እጦት መዘጋትና መከዳት … ወዘተ እርሱ አያወራም፤ አይደነቅም ወይ ሁለመናው በድብርት ይዋጣል። ግራ ግብት ሲለን ፣ አንተ የሴት ጓደኛ የለህም እንዴ፣ ስንል ጠየቅነው። እኔ እንዲህ ያለ ነገር አላውቅም አለን። አብረን አድገን ፣ አብረን እየገባንና እየወጣን ሲመሽ ብቻ እኮ ነው፤ የምንለያየው፣ እና እንዴት እንዲህ ልትሆን ቻልክ፣ አሁን ማ ይሙት እንዳንተ ያለ መልከ-ቀና ልጅ እንዴት አላውቅም ይለናል፤ አልነው። በጥቅሉ ፈራለሁ፤ ይደብረኛል፤ እንደዚህ ዓይነት ወሬ.. አለን። በጨዋነት እንዳልሆነ ይገባናል፣ ግን ይጨንቃል።
ምንድነው የምትፈራው? ከሴት ጋራ መቀራረብ እፈራለሁ። ለምን ትፈራለህ ? ፈራለሁ አልኩ ፈራለሁ፤ ብሎ ምንጭቅ ብሎ ተነሳ። ከመካከላችን ነገር ማብረድ የሚችለው ግርማ የተባለ ጓደኛችን ፤ “በቃ ፈራለሁ” ብሏል፤ ተዉት አለንና ፤ ለዚያ ቀን ተውነው። በሌላ ጊዜ ከሰፈራችን ወረድ ብሎ ወደምንንቦራጨቅበት ወንዝ አብረን ወርደን ሳለ እያዋዛሁ ጠየቅኩት። ዘጠኝ አመቴ መሰለኝ፤ 2ኛ ወይም 3ኛ ክፍል እያለሁ እኛ ቤት የነበረች ሰራተኛ ነበረችና ወንድና ሴት ምን መሆኑን አሳየችኝ ፤ አለኝ። በጣም በልጅ ስሜት ጓጓሁ። እናስ አልኩት። እና በዚያም ጊዜ ፣ አንተ ባሌ ነህ ትለኛለች ፤ ትስመኛለች ስማታለሁ፤ እኔም ባሏ እንደሆንኩ አስባለሁና፣ አንድ ቀን ከትምህርት ቤት መጥቼ ደብተሬን ጥዬ ወደጫወታዬ ላመራ ስል ፤ ዛሬ የምትወደውን መክሰስ አዘጋጅቼልሃለሁና ብላ አለችኝ። እኔም ያለጥርጣሬ ወደእርሷ ክፍል ስትወስደኝ ሄድኩና በላሁ። ከዚያ በሰዓቱ ማንም በቤት አልነበረምና ፤ በልቼ ለመውጣት ወደበሩ ስሄድ በሩ ተቆልፏልና አትልፋ ብላኝ። ባልና ሚስት እኮ አብሮ ይተኛል፤ አለችኝ። እና አብረን እንተኛ አለችኝ ። ከዛስ በፍጥነት ፣ ልብሴን አወላለቀችና ያለችውን አደረገች። ሁሉም ነገር ህልም ነው፤ የመሰለኝ። ተነስታ በሩን ስትከፍት የሆነውን ማመን አልችልም፤ እርቃኔን እንደሆንኩ ወንድሞቼና እህቶቼ መጡ ። ምንድነው አሉኝ። የሆነውን አላውቅምና ፤ ምንም አልኩኝ! ምን ሆነህ ነው? ራቁትህን ነህ፤ ደሞም ከተዘጋ በር ውስጥ እየወጣህ ነው፤ ደግሞ “ደሙ” ምንድነው? …. የምን ደም ነው? እኔ እንጃ! ፊታቸው መቆም አቃተኝ። ይህች ባልና ሚስት ነን፤ ያለችኝ ልጅ ምን አድርጋኝ እንደሆነ ምን አውቃለሁ? እርቃኔን ወደዋናው ቤት ሮጥኩ፤ የለችም። ተጣራሁ ወይ አላለችኝም።
እስከወዲያኛውም እኛ ቤት አልተመለሰችም። በጣም አለቀስኩ፤ ፈራሁ። ትንሹዋ ልቤ ልትፈነዳ ደረሰች። ከእህትና ወንድሞቼ ጋር፣ ከዚያ ጊዜ በኋላ ግንኙነቴ ሁሉ ተበለሻሸ። እና አሁን፣ ሴቶች ሁሉ እንደዚያ ነው ፤ የሚመስሉኝ ስለዚህ ፈራቸዋለሁ፤ አለኝ።
ይህንን እንዴት ነው የማስረዳው። ግራ ገባኝ፤ ሰኞ ደርሶ፣ ግን ትምህርት ቤት ስንሄድ እንደቀልድ ለተማሪዎች ምክር አገልግሎት “መምህራችን” ነገርኳት ። ያኔ፣ ትልልቅ ጎረምሶች ነን። አንድ ነገር ታድርግ ብዬ የነገርኳት መምህር ፤ እኔንም ሊፈራና ላይጠጋኝ ስለሚችል ለሌላ ወንድ መምህር እነግረውና ቀርቦ ያነጋግረዋል፤ አለችኝና ተለያየን ። በኋለኛው እድሜያችን እንኳን አለማግባቱን አስታውሳለሁ። እንዴት ሆኖ ይሆን ? በልጅነት ወራት፤ ልጅን ጨወታና ቀልድ እንጂ የአዋቂዎች ዓለም ጭቃ ሲለጠፍበት የፍርሃት ግንብ በህጻኑ ልብ ውስጥ መገንባቱና እንግዳ ስሜት መፍጠሩ አይቀርም። እና እንደፈራ ቀርቶ ይሆን … ህይወት አለያይታናለች።
ሌላው በህይወት የሌለው፣ ዓለማየሁ የተባለ የልጅነት ጓደኛዬ ነው፤ የልጅነት ጓደኛዬ፤ በጣም ተደባዳቢና ነገር ፈላጊ ነው። ባንተ የተነሳ ትምህርት ቤት መገረፍ ሰልችት ነው ያለኝ እኮ። ክፍል ውስጥ ነውጥ ከተነሳ አንተ አለህበት፤ በሌለህበትም ትኖርበታለህ። ከልጅነት እስከ ጉርምስና ባለፍንበት ህይወት አንተ ካለህ ፀብና ግጭት ስላለ ሁሌ ገሸሽ እል ነበረ። የምትገርም ልጅ ነህ ፤ ስለው አንተ ፈሪ ነህ አለኝ። አሳዘነኝ፤ ፈሪው ግን እርሱ ነበረ፤ ነውም። ህይወትን በቀና እና ገንቢ መልክ አይቷት አያውቅም። የሁሉም ነገር መፍቻ ጉልበተኛነት ብቻ ነው። ግን ለምንድነው በስለት መሞሻለቅ እንኳን የማያስፈራህ? ስለው፤ ትንሽ ልጅ ሆኜ ነው፤ አባቴ እናቴን ዓይኔ እያየ በስለት ደጋግሞ ወግቶ የገደላት። የዚያን ቀን ነው፤ በመስኮት ዘልዬ እንደወጣሁ የቀረሁት። ከትውልድ ሰፍራችን እግሬ ወዳደረሰኝ ወጥቼ ሄድኩ፤ እዚህ ጥሩ ቤተሰብ አግኝቼ ትምህርቴን የመማር እድል ባገኝም፣ ፀብ ከተነሳ አቅመቢስ እናቴን እያሰብኩ፣ ቀድሜ መምታት እንጂ መመታት አልወድም፤ በዚያ ላይ “ጎበዝ ጎበዝ”፣ የሚለኝ የሰፈር ልጅ ሲበዛ ልክነቴን እያረጋገጠልኝ መጣና እንዲህ ሆንኩልህ። እናም ቀድሜ እማታለሁ፤ ስመታም እያንዳንዱ ቡጢ እናቴን የተበቀለልኝ ነው፤ የሚመስለኝ። ስለዚህም ደጋግሜ እማታለሁ፤ ለዚህ ነው፤ እንዲህ የሆንኩት አለኝ። ፍርሃት፣ ቁጣና በቀል ተጋብተው ሰውን እንዲህ ጨካኝ ባህሪ ያላብሱታል። ትንሽ እንስሳ ብጤ ነገር ያደርጉታል።
እናም አሁን እያየን ያለነውን ሀብት ደምሰሳ፣ ንብረት ዘረፋና ጭካኔ ምንጭ ሌላ ምንም ሳይሆን በወጣቶቹ ልብ ሌላውን በአውሬነትና እንግዳነት ባህሪ ሲሞላ በነበረ የአስፈራሪነት ባህሪ ነው። ያም፣ ፍርሃት የወለደው፣ የመገፋትና የተጎጂነት ቁጣ ነው። እገሌ ሀብት ያፈራው ዘር ማንዘርህን በድሎ ነው፤ ደሃ የሆንከው እንቶኔ የተባለው ዘር ስለበደለህ ነው፤ እና የመሳሰሉት ትርክቶች በወጣቱ አእምሮ እየተጠቀጠቁ ስለኖሩ ነው፤ ወጣቶቹ እንዲህ የሆኑት። በደልና ምዝበራ ብዝበዛና ዘረፋ ተፈጽሞብሃል ሲባል የኖረ ወጣት የተዘራበትን ዘር ነው፤ ማፍራት የሚችለው። የቤት ሰራተኛቸው የሰራችበት እንግዳ ነገር፣ ያስደነገጠው ልጅ፣ እናቱን በአባቱ እጅ ያጣው ህጻንና የአሁኖቹ ልጆች ድርጊያ ተመሳሳይነት የክፉው ሙሌት ውጤት ነው። እኛም ብዙዎቻችን ይህንን ትርክት ለማፍረስ መነቃነቅ አልቻልንም፤ ወይም አልፈለግንም። ስለዚህ ክፉው የመመቀኛኘት ዘር ምቹ መሬት አገኘ። እናም በየስፍራው ያየነው ክፉ ነገር ሁሉ ሆነ። በየስፍራው ችግሩ የደረሰባቸው ሰዎች የሚናገሩትን ሲቃና ሳግ የተቀላቀለበት ድምጽ መስማት ይዘገንናል።
እንዲያውም ይህንን በቀጥታ ሳቀርበው ትምህርት ሚኒስቴርን እከስሳለሁ። የሐገር ልጅ የሚሰራባቸው ሥርዓተ-ትምህርቶች የሚቀመሩበት፣ መጻህፍት የሚዘጋጁበት፣ አጋዥና ዋቢ መጻህፍት የሚጠቀሙበት፣ የመቀመሚያ ቤታችን ነው። ይኼ ቤት ሚናውን በሥርዓት አልተወጣም፤ በጥንቃቄ አልሰራም፤ ስለዚህ ትምህርት ቤቶች የነውር መዝሪያ ማሳዎች ፣ መጻህፍቱ ክፋትን የመጠቅጠቂያ መዳመጫዎች ሆነውብን ኖረዋል፤ ስለዚህ ላለፉት ብዙ መቶ ዓመታት በሐገራችን ለተፈጠረው ችጋር፤ ድህነትና ረሐብ የነጻነት እጦትና እርዛት ምክንያት አንድ ዘር እንደሆነ ተደርጎ በተኮናኝነት የቀረበባቸው የመርዝ ማጉረሻ ማንኪያዎች ነበሩ። ይሁንናም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በየደረጃው ዝም ብሏል፣ ወይም እንዳቅሙ እና እንደሚገባው ለኢትዮጵያዊነት አልሰራም። በየትምህርት ቤቶቻችን እንኳን የሰንደቅዓላማ ማውጫና ማውረጃ ሥነ-ሥርዓት ቀርቷል፤ ወይም ይሁን ተብሎ እንዲረሳ ተደርጓል። እናም ለዚህ የኔም አስተዋጽኦ አለበት።
መምህር በነበርኩበት ወቅት ይህንን የሰንደቃ’ላማ መዝሙር ቢሆነን ብዬ ጽፌ ነበረ። “የውድ ሐገራችን ኢትዮጵያ፤ ታሪካዊ ዓርማችን፣ አረንጓዴ ፣ ቢጫ፣ ቀይ ሰንደቅዓላማችን!! የዜግነት ክብር ውል ማሰሪያ፣ የገድላችን ሁሉ ድል ማብሰሪያ፣ በምድር ዙሪያ ላለን ኢትዮጵያውያን፣ ነሽ መመኪያ አለኝታ ጥንት እስካሁን። ልምላሜ ጽናት ተስፋ ገድል፣. ምልክትሽን አይቶ ማይወላውል፣ በየዘመናቱ ጀግኖች አፍሪ፤ ነሽና ኢትዮጵያ ሁሌም ኩሪ….እያለ ይቀጥላል።
ለማ መገርሳ፣ በአንድ ወቅት እንዳሉት ያለፉትን ሃያ ምናምን ዓመታት ልጆቻችንን በየትምህርት ተቋሙ “ስንግታቸው የነበረው የጥላቻ መርዝ” ነው። ይህ ግን ማብቃት አለበት ፤ አያኗኑረንምና። ስለምወደውና ድርጊታችንን ከልብ ስለሚያስታውሰኝም፣ የምወደውን አባባል ልጠቀመው፣ “አውሎ ነፋስን የዘራ ማዕበል ያጭዳል” የሚለውን አባባል መጽሐፍ ቅዱስ ሰጥቶኛልና ማመስገንም እወዳለሁ። አዎ ፣ አውሎ ነፋስ እየዘራን ነው፤ ክፋትን እየዘራን ነው፤ ቁጭትን እየዘራን ነው። ለዚህም ነው፤ ሁላችንም ቂምና ቁርሾ ዘርተናል፤ እናም ውድመትና ግድያን አጭደናል።
አሁን በቀደም ዕለት በተቀሰቀሰው ረብሻ የ30 እና 40 ዓመት ልፋትና ስኬት በአንድ ቀን አዳር ባለቤቶቹን “በረንዳ አዳሪ” ወንጀል ፈጻሚዎቹን “አክባሪ” ድርጊት፤ ተፈጽሟል። ይህ በልዩ ልዩ የሀገራችን ክፍሎች፣ በተለይም በምእራብ አርሲ አንዳንድ አካባቢዎች የተፈጸመ ጥቃት በአእምሯቸው የተረበሹ፣ በክፉ ወሬ የተከፉና በዘር ቁጭት የተቀሰቀሱ (መደራጀታቸውን ሳንዘነጋ) ወጣቶች የተፈጸመ ጥቃት መሆኑ ቀርቶ የሆነ ዘር እና የሆነ የሃይማኖት ክፍል የሰራው ተደርጎ መቅረቡ ትናንትን መድገም ነው፤ ይህንን ትርክት ካመንን ግን ከጀርባችን የቀመሩልን አካላት ወደፈለጉት ቀለበት ውስጥ እያስገቡን ነውና፤ መጠንቀቅ አለብን።
ይልቅ ራሳችንን እንመርምር የት ጋ ነበረ ፤ ስህተታችን እንበል። የስህተታችንን አረም በመንቀል ወደፊት ለመሄድ ግን አሁንም አልመሸም፤ አሁንም አልረፈደም። ይህ ጊዜ፣ ለሰላም ጥሩ ጊዜ አይደለም ፤ አይባልም። ሁሉም ጊዜ ለጦርነትና ግጭት ጥሩ እንዳልሆነ ሁሉ ለሰላም ግን ማለዳው ጥሩ ነው፤ ምሽቱም እንዲሁ መልካም ነው። ሁላችንም በመስማማት ስህተትን ነቅሶ ለማውጣት ምቹ ጊዜ የለም ፤ ማለት አንችልም። በሁሉም ሰው ልብ ውስጥ የሚገኘውን እንጥፍጣፊ ፍቅር እንጠቀምበት።
ፍርሃታችን ክፉ እንዳይመጣ እንጂ፤ ክፉ ለማምጣት ከሆነ ወዮ ለፈሪዎች። ፍርሃታችን ልዩነትን ላለማራገብ ከሆነ መልካም ነው፤ “ልዩ ነን፤ አንስማማም፣ አብሮነት አያዋጣንም ፤ ቅንጅት አይረባንም፤” ለማለት ከሆነ ግጭትን እያሞካሸን ፣ ንትርክን እያፋፋንና ጦርትን እየጠራን ነውና ሊታሰብበት ይገባል። ምክንያቱም በጦርነት ያተረፈች ሐገር በግጭት ውስጥ አልፋ፣ የከበረች ምድር የለችም፤ ጥፋትና ውድመት እንጂ። እርስ በእርሳችን ከተቆራቆስንና ወደግጭት ከገባን ቀሪው ምድር ለባዕድ እንጂ ለራስ አይሆንም። ይህንን ጠንቅቀን መገንዘብ ይገባናል። ለባእድ የተገዛ ወትሮም የትምክህቱ ምንጭ ራሱ አይደለምና እጅ መስጠቱ አይቀርም ፤ እኛ ግን ከሀገራችን በላይ ማንም የለንምና የምንቆመውም የምንወድቀውም ለእርሷ ስንል ነው። አኩራፊዎችን ልባቸው ቢመለስ አሰየው፤ ባይመለስ ግን እያጠፉ ያሉት ሀገራቸውን ነውና ለልጆቻቸውና ለልጅ ልጆቻቸው የሚነግሩት ሐገርም ወገንም እንደሌላቸው ከወዲሁ ማወቅ ይገባቸዋል። አውቀውትም የሚያደርጉት ከሆነ ፈውሱን ይስጣቸው። ፈውሱ ደግሞ ያለው መደማመጡ ላይ ነው፤ ፈራ ተባው ላይ አይደለም። “ኬሩኒ፣” ይላል ሲዳማ ፤ “ኬር ይሁን”፤ ይላሉ ጉራጌ ዘመዶቻችን።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 25 ቀን 2012 ዓ.ም
አሳምሬ ሣህሉ