አመለ ሸጋ ነው፤ ተግባቢ እና ለንግድ የሚሆን ባህሪ እንዳለው ደግሞ በስራ አጋጣሚ የሚያውቁት ሰዎች ይመሰክራሉ። ለማደግ እና ሰርቶ ለመለወጥ የሚያደርገው ጥረት ከእርሱ አልፎ በዙሪያው የሚገኙ ሰዎች በህይወታቸው የተሻለ ነገር እንዲያደርጉ የሚያነሳሳ ሃይልን የማጎናጸፍ አቅም አለው። በ30ዎቹ መጀመሪያ የእድሜ ክልል ላይ የሚገኝ ወጣት ቢሆንም ህይወት ያለስራ ትርጉም አልባ መሆኗን እንደተረዳ ይናገራል። ታዲያ ለመኖር ከሚያደርጋቸው ክንውኖች መካከል ዋነኛውና ትርጉም የሚሰጠው በየቀኑ በንግድ ቦታው ላይ የሚያሳለፈው ጊዜ እንደሆነ አልሸሸገም። የዛሬ ባለታሪካችን ወጣት ፈድሉ ረሺድ ይባላል።
ወጣት ፈድሉ የተወለደው በጉራጌ ዞን ጉመር ወርቃ ዘር በተባለው አካባቢ ነው። ወላጆቹ ስምንት ልጆችን ሲወልዱ እርሱ ደግሞ ስድስተኛ ልጃቸው ነው። በሰፊ ቤተሰብ ውስጥ እየዳኸ ያደገው ፈድሉ የሀገሩን ባህል እና አኗኗር ጠብቆ እንዲያድግ ቤተሰቦቹ ያደረጉት ጥረት መልካም ነበር።
በጉራጌ ማህበረሰብ ዘንድ ለስራ የሚሰጠው ግምት ከፍተኛ ስለሆነ ወላጆቹም ሲያድግ ለሀገሩም ለወገኑም ሸክም ሳይሆን ደጋፊ የሚሆን ጠንካራ ሰራተኛ እንዲሆን ምክርም ሆነ ተግባራዊ ትምህርትን ይለግሱት እንደነበር ያስታውሳል። ገና አምስት እና ስድስት ዓመት በሆነው ጊዜ እንኳን በአቅሙ ምን አይነት የቤት ውስጥ አንዳንድ ተግባራትን እንዲከውን በማድረግ ለስንፍና ቦታ እንዳይሰጥ የበኩላቸውን መፍትሄ ያበጁ ነበር።
ፈድሉ በለምለሙ የጉራጌ ምድር ለስምንት ዓመታት ገደማ ካደገ በኋላ ግን ትምህርት ቤት መግባት እንዳለበት ቤተሰቡ ወሰነ። በዚህ ወቅት ታዲያ ታላቅ ወንድሙ አዲስ አበባ ከተማ መጥቶ የግሉን ስራ ይሰራ ነበርና ፈድሉም ወደወንድሙ ዘንድ ሄዶ ትምህርቱን እንዲከታተል ተላከ። አዲስ አበባ ላይ መሳለሚያ በተሰኘው አካባቢ ከወንድሙ ጋር እየኖረ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን አባድር ትምህርት ቤት መከታተል ጀመረ። የአስኳላ ጊዜውን በጥሩ ሁኔታ ቀጥሎ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን አወሊያ በተሰኘው ትምህርት ቤት መከታተል ችሏል። አስረኛ ክፍልን እንዳጠናቀቀ ግን ትምህርቱን የሚቀጥልበት ሁኔታ ባለመፈጠሩ በቀጥታ ወደስራ የሚገባበት እድል ተፈጠረ።
ወንድሙ ደግሞ በጌጣጌጥ ስራዎች ንግድ ላይ ተሰማርቶ ነበርና ወጣት ፈድሉም ከና በ19 ዓመት እድሜው የእጅ እና አንገት ጌጣጌጥ ንግድ ስራው ላይ ከወንድሙ ጋር አብሮ መስራት ጀመረ። ወንድሙ የተለያዩ ከብር እና ከወርቅ የሚሰሩ ጌጣጌጦችን ሲያዘገጃጅ ፈድሉ ደግሞ በሽያጭ ሰራተኝነት በሱቁ ውስጥ ይሰራል። አልፎ አልፎ የሚመጡ ስባሪ ያጋጠማቸውን የወርቅ እና ብር ጌጣጌጦችን መጠገን እና የቆሸሹትንም በማጠብ ሙያውን ለመልመድ ጥረት ማድረግ ቀጠለ። ከስራ መልስ አብረው ወደመኖሪያቸው የሚያቀኑት ታናሽና ታላቅ ታዲያ ልክ እንደሚዋደዱ አባት እና ልጅ ያክል ቅርበታቸው ጠንካራ ነው።
ፈድሉ መርካቶ ላይ በተከፈተው የወንድሙ ሱቅ ውስጥ ሙያም ገንዘብ አያያዝም እየተማረ መጣ። ከሽያጭ ስራ እና ጥቃቅን የጥገና ስራዎች በዘለለ ግን የጌጣጌጦች ዲዛይን ስራ ላይ አልተሳተፈም። በዚህ ምክንያት ከጌጣጌጥ ማዘጋጀት ስራው ይልቅ ብር እና ወርቆቹን ስለመነገድ ነበር ልምድ ማካበት የፈለገው። ለአስር ዓመታት በዚህ መልኩ በሽያጭ ስራው ሲሰራ ከብዙ ነጋዴዎች እና ሙያተኞች ጋር ትውውቅን መፍጠር ቻለ።
በወንድሙ ላይ ሸክም ሆኖ መኖር መቀጠሉ እየከበደው ስልመጣ ግን በግሉ ንግዱን ለመሞከር ማሰብ ጀመረ። ፈድሉ ታዲያ ጌጣጌጦቹን በግሉ ስለመነገድ ሲያስብ ደግሞ በጥቂቱም ቢሆን እራሱን በፋይናንስ ማዘጋጀት እንደጀመረ ያስታውሳል። በመጨረሻ ከብዙ ልፋት በኋላ በሚያውቃት እና የንግድ ማዕከል በሆነችው መርካቶ ውስጥ ለንግድ የሚሆን አነስተኛ የንግድ ሱቅ አገኘ። ሱቋን በወር ስምንት ሺህ አምስት መቶ ብር ለመከራየት ከተስማማ በኋላ የእራሱን የጌጣጌጥ መሸጫ ሱቅ ለመክፈት የሚያስችለውን ዝግጅት አጠናከረ። ከአሮጌ ዕቃዎች መሸጫ ቦታ ጭምር በመሄድ አንዳንድ እቃዎችን ካመጣ በኋላ በማደስ ለሱቁ አገልግሎት ማዋል ጀመረ።
ቀድሞ ከወንድሙ ጋር ሲሰራ በነበረበት ወቅት የሚያውቁት ሰዎችም የተለያዩ ጌጣጌጦችን በማዋስ ጭምር ሰርቶ እንዲከፍል እድሉን ሰጡት። ወንድሙም በሃሳብ እና በምክር ከጎኑ ሳይለይ አንዳንድ ድጋፎችን አደረገለት እና ፈድሉ ሱቁን ከፍቶ መስራት ቻለ። በመጀመሪያ የግል ንግድ ስራው ለሽያጭ ያቀረበው ጌጣጌጥ የአንገት ሃብል እንደሆነ የሚያስታውሰው ወጣት ፈድሉ ጌጡን ለአንዲት ሴት በሰማንያ አምስት ብር ከሁለት ዓመታት በፊት እንደሸጠ ደግሞ አይዘነጋውም። ይህ አጋጣሚ ለጀማሪው ነጋዴ ትልቅ የሞራል ስንቅ ሆነለትና ይበልጥ እንዲጠነክር ረዳው። ይሁንና ንግድ በጀመረ ጥቂት ቀናት ውስጥ ከገቢዎች ቢሮ የመጡ ሰዎች ቫት ማሽን እንዲያስገባ እና ቫትን ጨምሮ እንዲሸጥ ማስጠንቀቂያ በሰጡት ወቅት ትልቅ ስጋት ውስጥ ከቶት እንደነበር ያስታውሳል።
ጀማሪ ነጋዴ በመሆኑ የቫት አሰራሩ ኪሳራ ውስጥ እንደሚከተው በመስጋቱም ፈተና ውስጥ ገብቶ ነበር። ይሁንና ዘርፉ በሚጠየቀው አሰራር በማለፍ ጠንካራ ነጋዴ መሆኑን በወጣትነቱ ማሳየት ችሏል። ለዚህ ደግሞ መንድሙ ብቻ ሳይሆኑ በሙያው የተሰማሩ ሌሎች ባልደረቦቹም ያደርጉለት የነበረው የመንፈስ ማበረታቻ ፈተናውን እንዲያልፈው አግዘውታል። መርካቶ ላይ መስራት ትልቅ ጥቅም አለው የሚለው ወጣቱ በተለይ በአካባቢው የሚገኙ ነጋዴዎች መረዳዳትን እና አብሮ መስራትን የለመዱ በመሆናቸው ለእርሱም እንዳገዘው ይናገራል።
በተለይ ሱቅ ሲከፍት እንመርቅለት ብለው ጌጦቹን በመግዛት እና የተለያዩ ምርቶችን አቅርበውለት ከሸጠ በኋላ እንዲከፍላቸው እድሉን የሚያመቻቹለት ሰዎች በቅርበት በመኖራቸው ብቸኝነት ሳይሰማው ስራውን እንዲያሳድግ እንደረዳው አልሸሸገም። ልክ እንደእርሱ አይነት ንግድ ውስጥ ለተሰማራ እና መርካቶ ውስጥ ሰርቶ ለማደግ የሚፈልግ ሰው ታማኝነት እና ለንግድ የሚሆን መልካም ጸባይ ወሳኝ ነውና ወጣት ፈድሉም በውሰት የመጡለትን ጌጦች ገበያ ሲያገኝ በመሸጥ ገንዘቡን ለባለቤቶቹ መመለሱን ለአፍታም አልሳተም። በዚህ አይነት አሰራር ደንበኞቹን ሳያስከፋ በመስራት የሚያገኘው መጠነኛ ትርፍ እያጎለበተ ከስምንት ወራት በኋላ ከብር ጌጤጌጦች ንግድ አልፎ የወርቅ ጌጣጌጦችንም ወደመሸጡ ተሸጋገረ።
ከተለያዩ አረብ ሀገራት እና ከሀገር ውስጥ ጭምር ሰዎች የገዙትን ወርቅ መልሰው መሸጥ ሲፈልጉ በመግዛት በየጊዜው ሱቁን መሉ አደረጋት። በአቅሙ የገባትን እቁብም በመያዝ እና በየጊዜው በጌጣጌጥ ንግዱ ላይ የሚያገኘውን ገንዘብ በማጠረቃቀም መልሶ ለንግድ ሱቁ ማጠናከሪያ ማዋሉን ተያያዘው። የጋብቻ ቀለበቶች፣ ዲስክ እና ገመድ የተሰኙትን ዲዛይን የያዙ የአንገት ጌጦች፣ ምላጭ ቅርጽ ያለው የወርቅ እና የብር የአንገት ጌጥ እንዲሁም በሙያው አጠራር ጫት ጌጥ የሚባለውን እና ሴቶች ከሀበሻ ባህል ልብስ ጋር የሚያጌጡባቸውን ያማሩ እና ከፍተኛ ሙያዊ ጥበብን የሚጠይቁ የጆሮ ጌጦችን ለገበያ በማቅረብ ትርፉን ከቀን ወደቀን በማሳደግ ወጣት ፈድሉ በመርካቶ ታዋቂ ወርቅ ቤት ባለቤት ለመሆን ብዙ ዓመታት አልፈጀበትም።
ከ14 ካራት እስከ 21 ካራት የጥራት ደረጃ ያላቸውን ወርቆች በሱቁ በማቅረብ ይነግዳል። የተለያየ ዲዛይን ያላቸው የብር ጌጦችን በግራም በአማካይ 55 ብር እየሸጠ ይገኛል። በወርቅ ንግዱ ደግሞ አንደኛ ደረጃ የሚባለውን ወርቅ በአማካይ በግራም 2ሺህ 200 ብር ሲሸጥ፣ ሁለተኛ ደረጃውን ደግሞ በአንድ ሺህ 900 ብር ያቀርባል። የካራት መጠኑ ዝቅ ያለውን እና ባለ 14 ካራቱን ወርቅ ደግሞ በግራም አማካይ ከስድስት መቶ ብር እስከ ስምንት መቶ ብር ለገበያ በማቅረብ ንግዱን አጠናክሮ ቀጥሏል። በየጊዘው የሚያገኘውን ትርፍ ለተጨማሪ ጌጤጌጥ ግዥ በማዋል ሱቁን ለማሟላት የሚጥረው ወጣት ገቢ ብቻ ሳይሆን ወጪም አለበትና በወር 12ሺህ 500 ብር የሱቅ ኪራይ እየከፈለ፤ ለግል ህይወቱም የሚሆን ወጪ እየሸፈነ ኑሮውን በተረጋጋ መልኩ እየከወነ ይገኛል።
ወጣት ፈድሉ አሁን ላይ በመርካቶው ሱቁ ውስጥ ግማሽ ሚሊዮን ብር የሚያወጣ የጌጣጌጥ ንብረቶችን ለገበያ በማቅረብ ላይ ነው። ከጀማሪነት ተነስቶ በሁለት ዓመታት ውስጥ እዚህ ደረጃ መድረስ የቻለው ግን ስንፍናን ተጠይፎ በየቀኑ ስራ ላይ በማሳለፉ መሆኑን የሚያውቁት ይመሰክራሉ። በዚሁ ከቀጠለ ወጣቱ ነገ ላይ ከፍተኛ ባለሃብት የማይሆንበት መንገድ እንደሌለ አካሄዱ ማሳያ መሆኑን ደንበኞቹ ሳይቀር ይመሰክራሉ። በንግድ ሱቁ ውስጥ የለም የሚለውን ቃል የማያዘወትረው ፈድሉ ደንበኞች የፈለጉትን ዲዛይን ጌጣጌጥ ከሌሎች ነጋዴዎች ላይ ጭምር በመዋስ እያቀረበ በመርካቶ ሰርቶ መለወጥ እንደሚቻል በተግባር እያሳየ ነው።
ወጣት ፈድሉ በቀጣይ የንግድ ሱቁን አስፋፍቶ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ሃብት የያዘ ቢዝነስ እንደሚኖረው ተስፋ አድርጓል። ለዚህ ደግሞ ከሱስ የራቀ እና ቁም ነገር ላይ ያተኮረ ህይወትን ከንግዱ ስራ ጎን ለጎን እየተከተለ ይገኛል። ያለስራ ከመዋል ይልቅ ያለምግብ መዋል ይሻላል የሚለው ወጣቱ ስራ ማለት ለህይወት ችግሮች ሁሉ አማራጭ የሌለው መፍትሄ ነው ይላል። አሁን ላይ መስራት ያልቻለ መኖር አይችልምና የሌሎችን እጅ ጠባቂ ከመሆን እውነተኛ ህይወት ለመምራት የግል ጥረትን ማድረግ ዋናው ተግባር ሊሆን እንደሚገባ እምነቱ ነው። በተለይ በታዳጊ ሀገር ላይ እየኖሩ በጥንካሬ መስራት ካልተቻለ ወድቆ መቅረትም አለና በስራ ድርድር አላውቅም ይላል።
ስራ የሚሰራ ሰው ይከበራል፤ ማንም ቤተሰብ ደግሞ ልጁ ውጤታማ እንዲሆንለት ከፈለገ እና ተከበሮ እንዲያስከብራቸው ምኞት ካለው የልጃቸው እጅ ለስራ እንዲታነጽ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው ወጣት ፈድሉ ይናገራል። በዚህ ረገድ ቤተሰቦቹ ለእርሱ ያደረጉት አስተዋጽኦ የኋላ ኋላ ጠቅሞታልና ለቤተሰቡ ምስጋና ያቀርባል።
በየጊዜው የተወለደበት ቀዬ ዘንድ እየሄደ ቤተሰቦቹን ለአረፋ የመጠየቅ ልምድ ቢኖረውም ግን ዘንድሮ በኮሮና ምክንያት የተነሳ አዲስ አበባ ላይ ለማሳለፍ ምርጫውን አድርጓል። በዓሉን በሰላምና በፍቅር ሲያከብር ግን ከእራሱ ልምድ በመነሳት ለወጣቱ የሚያስተላልፈው መልዕክት አለ። ማንኛውም ወጣት ሙያዬ ብሎ የያዘውን ነገር ላይ ትኩረት በመስጠት በጥንካሬ መስራት ከቻለ ነገ ላይ መለወጥ የማይችልበት ምክንያት የለምና ሁሉም ኢትዮጵያዊ ጊዜውን በአግባቡ ሊጠቀምበት ይገባል የሚለው ደግሞ ምክሩ ነው። ቸር እንሰንብት!!
አዲስ ዘመን ሐምሌ 25 ቀን 2012 ዓ.ም
ጌትነት ተስፋማርያም