ቅድመ- ታሪክ …
ከስልጤ ሜዳማ ስፍራዎች በአንዱ ሲቦርቅ ያደገው ሁሴን መሀመድ ልጅነቱን ያጣጣመው ከመንደር እኩዮቹ ጋር ነበር። በወቅቱ ከእሱ መሰል ባልንጀሮቹ ጋር ትምህርትቤት ገብቶ ፊደልን ቆጥሯል።ስድስተኛ ክፍል ሲደርስ ግን ሁኔታዎች ተለወጡ።ወላጆቹ መኖሪያቸውን መለወጥ ፈለጉና አዲስአበባ ይዘውት ገቡ።
አዲስ አበባ ለነሁሴን ቤተሰብ እንደታሰበው አልሆነችም።የኑሮ ውድነት፣የቤት ኪራይና መሰል ወጪዎች ፈተና መሆን ጀመሩ። እናት አባት ህጻናት ልጆቻቸውን ይዘው ኑሮን መታገል ያዙ። በየእለቱ የሚገጥማቸውን ችግር መሸከም አልሆነላቸውም።
ባልና ሚስትና ህጻናት ልጆቻቸው በየቤትኪራዩ ተንከራተቱ። እነሱን አብልቶ ለማሳደር በቂ ገቢ ቢጠፋ ሁሴንና ወንድሙ ትምህርታቸውን ሊያቆሙ ግድ አለ። ቤት መዋል የጀመሩት ልጆች ችግር በዚህ ብቻ አልተፈታም። የሚበሉትና የሚለብሱትን ለመሙላት ወላጆች መልፋትና መድከም ግድ አላቸው ።
ከገጠር አዲስ አበባ የገባው ቤተሰብ ችግር እያየለ ሲሄድ ጥንዶቹ ስለልጆቻቸው ነገ ይበጃል ባሉት ጉዳይ መከሩ ። በምክራቸው ሚስት አረብ ሀገር ሄዳ ብትሰራ እንደሚሻል ተማመኑ።እሷ ባህር ተሻግራ ዓመታትን ብትቆይ የጎደለው ሞልቶ የጨለመው እንደሚበራ አመኑ ። በዚህ ምክር የደረጀው ዕቅድ ስር ሰዶ የጉዞ ሂደቱ ተጀመረ። በደላሎች ሩጫና በብድር ገንዘብ የተወጠነው የስደት ጉዳይ ተጣድፎም እናት ርቃ ለመሄድ ጓዟን ሸከፈች።
ሚስት የእንቦቃቅሎቿን ግንባር እየሰማች ስለልጆቿ አደራውን ለባሏ ሰጠች።ሆድ ቢብሳትም ዕምባዋን ጠርጋ ህጻናቱን አሳመነች። ከስደት ስትመለስ የምታመጣላቸውን እየነገረች፣ ከስፍራው ስትደርሰ በምትልክላቸው ልብሶች እየደለለች በሽኝት ተሰናበተች።
አባትና ልጆች…
አባወራው ባለቤቱን ወደ ዓረብ አገር ከሸኘ በኋላ አራት ልጆቹን ይዞ የተለመደውን ህይወት ቀጠለ።ለሆድ እንጂ ለስራ ያልደረሱት እነሁሴን አባታቸውን መርዳት አልቻሉም ። ጠዋት ማታ በስራ የሚባትለው ጎልማሳ የፍላጎታቸውን ሞልቶ ቤቱን ማሳደር አልሆነለትም። ውሎ እያደር ኑሮ ከበደው። ትናንትና የበዛውን ጎዶሎ የምትሸፍነው ሚስት ዛሬ ከጎኑ ያለመኖሯ የችግሩን ቀዳዳ አሰፋው። ለጥቂት ጊዜ ህጻናትን ይዞ መንገዳገድ የጀመረው አባት ህይወት እንደቀድሞው አልሆነለትም ።ወዳጅ ዘመድ በሌለበት አገር ያለእናት እጅ፣ ሚስት አልባ ልጆቹን ማሳደግ በእጅጉ ከበደው።እናም ጊዜ ወስዶ ቆም ብሎ አሰበ። አስቦም ከአንድ ውሳኔ ደረሰ።
ከዚህ በኋላ አዲስ አበባ መኖሩ እንደማይበጅ ገብቶታል።በሰው አገር ከነልጆቹ ከሚንገላታ አገሩ ገብቶ እያረሰ መኖርን ወዷል። አባወራው ከራሱ መክሮ ከውሳኔ መድረሱ መንገዱን አፋጠነው። ለጉዞ የተነሳው ልቡም ትናንትና አስቋጥሮ ያመጠውን ጓዝ ዳግም አሸክፎ በመጣበት ሊመልሰው ተዘጋጀ። ልጆቹን ይዞ የተከራየውን ቤት ቁልፍ ለአከራዩ እንደመለሰ ሁሴንና ወንድሙ በቅርብ አለመኖራቸውን አወቀ ። ይህኔ ሁለቱን ሴት ልጆች ስለወንድሞቻቸው ጠየቀ ።
የሁለቱ ውሳኔ…
ሁሴንና ታናሽ ወንድሙ አባታቸው ወደገጠር ሊመለስ መሆኑን ካወቁ ጀምሮ ዕንቅልፍ የላቸውም። የከተማ ህይወት ባይመቻቸውም ጣዕሙን ከነችግሩ ከተላመዱት ቆይተዋል። የነበሩበትን የገጠር ህይወት ደግመው ማየት የማይሹት ወንድማማቾች የአባታቸው ውሳኔ ቁርጥ መሆኑን ሲረዱ ለራሳቸው ዕቅድ ነድፈው እሱን ተከትለው ላለመሄድ ወሰኑ ። አባት የልጆቹን ገጠር አለመመለስ ባወቀ ጊዜ ለምኖና አሳምኖ ለመወስድ ሞከረ፤አስቀድመው ከውሳኔ የደረሱት እነሁሴን ግን የልመና እጁን ገፍተው ‹‹እምቢኝ›› ሲሉ ተቃወሙ ። አባትና እህቶቻቸውን ሸኝተውም አዲስአበባ ለመኖር መቁረጣቸውን ነገሩት ።
አባወራው ሁለት ወንድ ልጆቹ ሊከተሉት ባይወዱ ሴት ልጆቹን ይዞ ገጠር ተመለሰ። ይህን ሲያደርግ ከልብ ቢከፋም የልጆቹን ውሳኔ መቃወም አልቻለም። ግማሽ ልቡን ከእነሱ ትቶ ቅር እንዳለው ከቀዬው ገባ ። እንደትናንቱም መሬት ጭሮ፣ በሬ ስቦ ሊያድር ግብርናውን ቀጠለ ።
ህይወት በጎዳና…
ወንድማማቾቹ አባታቸውን እንደሸኙ የጎዳና ኑሮን ጀመሩ።በጊዜው እነሱን የሚረዳ ባለመኖሩ ከዚህ ሌላ ምርጫ አላገኙም፡፤ስቴድየም ዙሪያ ካሉ ልጆች ጋር ሲላመዱ የጎዳናን ህይወት አወቁት። ጠዋት ማታ ከሚያርፉበት ግንብ ስር የተገኘውን እኩል ተቃምሰው፣ የሚሸቀል ሲገኝ ሮጠው፣ ለጊዜው ለራሳቸው ሆኑ። ሁሴንና ወንድሙ አንዳንዴ የታክሲ ረዳት ሲሆኑ የተሻለ ገቢ ያገኛሉ።ይህ ባልቀና ጊዜ ግን ርሀብና ጥማቱን ችለው፤ከሌሎች ተጋርተው ያድራሉ።
ሁሴን በየጊዜው ገንዘብ ማግኘት ቀላል እንዳልሆነ ከገባው ቆይቷል፡፤ እሱም እንዴሎች ሌላ አማራጭ ፍለጋ መሮጥ አለበት። ይህን አማራጭ ተብዬ ብዙ የጎዳና ልጆች ሞክረውት አትርፈውበታል። ‹‹አዩኝ አላዩኝ›› ተብሎ በሚፈጸመው የመኪና ዕቃ ስርቆት ካልተነቃና መረጃ ካልተገኘ ዳጎስ ያለ ገንዘብ ያስገኛል ። ሁሴን ሌሎችን ተከትሎ የጀመረው አዲስ ስራ ለጊዜው ስኬታማ ሆነለት። ብልጣብልጥ ዓይኖቹ ከፈጣን እግሮቹ ተዳምረውም ዳጎስ ያለ ገንዘብ መያዝ ጀመረ። ለእሱና ለወንድሙ ፣ለባልንጀሮቹ ጭምር መትረፍ ሲጀምር ስርቆቱን እየጣመው ደጋገመው። ሁሴን አሁን ጉርምስና ላይ መድረሱ ከሌሎች ያጋጨው ጀምሯል።ከመስማማት መደባደብን መምረጡም ለፖሊስ ጣቢያ እስር ሲዳርገው ቆይቷል ።የስርቆት ውሎው ደግሞ ሁሌም የተሳካ አይሆንም ። አንዳንዴ ሁኔታውን የጠረጠሩ ከእጃቸው ባስገቡት ጊዜ በዋዛ አይለቁትም። እንዳይሆን ደብድበው ለህግ አሳልፈው ይሰጡታል። እንደስራ የያዘው የመኪና ዕቃ ስርቆት ለአራት ጊዚያት አስከስሶ ለእስር ዳርጎታል። ደጋግሞ መታሰሩ ያልበቃው ሁሴን ግን ተመልሶ በቦታው ሲገኝ ጥቅሙን ብቻ ያስባል ። በለመደው ዘዴና ልምድ ተጠቅሞም የመኪና ዕቃዎችን እየፈታ ለሽያጭ ያውላል ።
የስራ አጋሮች…
ሁሴን ከእስር ከተፈታ በኋላ መሰሎቹን ተጠግቶ በሌላ የስራ መደብ መስረቅ ጀምሯል። እነዚህ ቡድኖች በተገናኙ ጊዜ ነጥቀውና ሰርቀው ስለሚያገኙት ጥቅም ያወጋሉ ። ቀን በጫት ውሎ ያሳለፉትን ውሳኔም ምሽት በመጠጥ እያወራረዱ ስለቀጣዩ ዕቅድ ይነድፋሉ ። ሁሴንና ባልንጀሮቹ ጨለማን ተተግነው የሚፈጽሙት ዝርፊያ ከግብ ሲያደርሳቸው ቆይቷል። በጎናቸው የሚሽጡት ስለትም ብዘዎችን ማርኮ ያሰቡትን እንዲወስዱ አግዟቸዋል። እነሱ ለዝርፊያ በተሰማሩ ጊዜ ምህረት ይሉትን አያውቁም ።ከሰው ህይወት ይልቅ ገንዘብና ንብረትን ያስቀድማሉ
የካቲት 28 ቀን 2005 ዓም…
ጨለማው አይሏል፡፤ሰዓቱ ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ከሰላሳ እያለ ነው ። ከስራ ወደቤት እየገቡ ያሉት አባወራ ቤት ደርሰው ስለሚከውኑት እያሰቡ ይጓዛሉ። የደረሰቡት አካባቢ ሠዋራና ድንጋያማ ነው። ሰፈራቸው በመሆኑ ግን የሰጉ አይመስልም ።በእጃቸው በያዙት ትልቅ ባትሪ እየታገዙ ጠመዝማዛውን መንገድ አጋምሰውታል። ሰውዬው እንዲህ እንደዛሬ በሚያመሹ ጊዜ ከወገባቸው ወሸቅ የሚያደርጉት ሽጉጥ አይለያቸውም። እሱን በያዙ ጊዜ ብዙዎች የሚሰጉበት ጉዳይ ጉዳያቸው አይሆንም። ዙሪያገባውን እየቃኙ በጨለማው መሀል ያለፍርሀት ይጓዛሉ ።
የዛን ቀን ምሽት ሁሴንና ሦስት ጓደኞቹ ቦሌ ‹‹እፎይታ›› ከሚባል ስፍራ ቆይተዋል ። በቦታው የመገኘታቸው ምክንያት ያሰቡትን ቅሚያ ለመከወን ነበር። አጋጣሚው ቀንቷቸው የያዙትን ይዘው ‹‹እግሬ አውጭኝ›› እንዳሉ ሁሉም ከመንደሩ መሀል ደርሰዋል ። በጨለማው እየሮጡ ፣በመታጠፊያው እያቋረጡ፣ ከመንደሩ ጥግ ሲደርሱ ከነበሩበት አካባቢ ስለመራቃቸው እርግጠኞች ነበሩ። አራቱ ነጣቂዎች እግራቸው የቆመበት ስፍራ ድቅድቅ ጨለማ መሆኑ እንደሁልግዜው አግዟቸዋል።በእጃቸው የገባው ሲሳይ ደግሞ በሳቅ እያጀባቸው ነው ።
እነሁሴን በመንደሩ አንደኛው ቅያስ እንደደረሱ ከርቀት የሚታይ ደማቅ የእጅ ባትሪ በአይናቸው አንጸባረቀ ። ድንገቴው ክስተትም ለአፍታ አስደነገጣቸው፡፤ወዲያው ግን ሀሳባቸውን ሰብስበው በምልክት ተናበቡ።የሁሉም ዕቅድ አንድ ሆነና እየሮጡ ደርሰው መንገደኛውን አባወራ ከበቡ ።
አንድ ለአራት…
ሰውዬው የሚያዋክቧቸውን ዘራፊዎች ላለመያዝ የአቅማቸውን ሞከሩ።ከኋላቸው የዞረው አንዱ ጎረምሳ ግን አንገታቸውን አንቆ አላላውስ አላቸው።የተቀሩት ኪሳቸውን እየፈተሹ፣ ጎናቸውን እየዳበሱ ሊጥሏቸው ታገሉ።አባወራው በዋዛ አልተረቱም። እሳቸውም የሞት ሽረት ትግል ቀጠሉ። የመንገደኛውን ብርታት ያዩ ዘራፊዎች ተረባርበው አጠቋቸው፡፤ከባልንጀሮቹ መሀል አንደኛውም ትልቅ ድንጋይ አንስቶ ግንባራቸውን መታው።ሌላው እሱን ተከትሎ በመሰል ትልቅ ድንጋይ ማጅራታቸው ላይ አሳረፈ።
ሰውዬው እየዞረባቸው ሦስቱን ጎረምሶች እንደያዙ ከመሬት ወደቁ ። ትግሉ ሲቀጥል ፍተሻው ተከተለ።ዘራፊዎቹ ሰውዬው መሳሪያ እንደያዙ በገባቸው ጊዜ ማህደሩን በስለት ቆርጠው ሽጉጡን በእጃቸው አስገቡ ። ተረጋግተውም አንድ ሁለት ብለው ስምንት ጥይቶችን ቆጠሩ። ከኪሳቸው ያገኙትን ሞባይል፣ግምቱ አራትሺህ ብር የሚገመት ሶላር የእጅባትሪና ገንዘብ ወስደው በመጡበት ፍጥነት ተሰወሩ።
ዘራፊዎቹ ጥቂት አለፍ ብለው የእጅባትሪውን ከአንድ የትምህርትቤት ጣራ ላይ ወረወሩት።ገንዘብና ሽጉጡን ይዘውም ለሁለት ተከፍለው ተለያዩ።ሁሴን አብሮት ከሄደው ጓደኛው ጋር አድሮ ሲነጋ መሳሪያውን ለመሸጥ ገበያ አፈላለጉ ። አጋጣሚው ቀንቷቸው ለአንድ ገዢ በስምንትሺህ ብር አስረክበው ገንዘቡን ለሁለት ተካፈሉ። ሌሎች አጋሮች ይመጣሉ ብለው ጠበቁ። ከቀናት በኋላ ሲገናኙ እነሁሴን መዘነጣቸውን አይተው መብታቸውን ጠየቁ ። በቅጡ የመለሰላቸው አልነበረም።ሁለቱ አጋሮች በንዴት እንደጨሱ ጥርሳቸውን ነከሱ።
የፖሊስ ምርመራ…
ከፖሊስ ጣቢያው ተገኝተው ቃላቸውን የሰጡት አባወራ በዛን ቀን ምሽት የተፈጸመባቸውን ድብደባና ዝርፊያ አንድ በአንድ አስረዱ። ፖሊስ በወቅቱ የሚያስታውሱትን ምልክት ያስረዱት ዘንድ ጠየቀ፡፤ ተበዳዩ የሰዎቹን አለባበስ ድምጽና መልክ በማስታወስ ለመናገር ሞከሩ ። ፖሊስ የተዘረፈባቸውን ከሀያሺህ ብር በላይ የሚገመት ንብረት በአስረጂነት መዝግቦ ተጠርጣሪዎችን ማደኑን ቀጠለ።
በዋናሳጂን ፍቅሬ ታንቱ የሚመራው ቡድን ሌት ቀን አሰሳውን ቀጥሏል። ተደጋጋሚ ወንጀለኞችን ለይቶም በእጁ አስገብቷል ። ተበዳይ ከተያዙት በርካታ ተጠርጣሪዎች መሀል ዘራፊዎችን ለይተው እንዲያሳዩ ተነገራቸው። ሰውዬው በእጃቸው የባትሪ ብርሀን ያስተዋሏቸውን ዘራፊዎች አልዘነጉም። መደዳውን ከቆሙት መሀል ሁለቱን ብቻ ነጥለው አወጧቸው። ሁሴንና የመሳሪያቸውን ማህደር በስለት ቆርጦ ያወጣው ባልንጀራው አብዱርአዛቅ ነበር።
ከሚፈለጉት መሀል ሁለቱን ዘራፊዎች በእጁ ያስገባው ፖሊስ ተፈላጊ ምርመራዎችን አጠናቆ ጉዳዩን ወደ ዐቃቤ ህግ የክስ መዝገብ አዛውሮታል።ክሱ በሚገባ ተደራጅቶ የደረሰው የፌዴራል ዓቃቤህግም ጉዳዩ በወንጀል እንደሚያስጠይቅ አጣርቶ ፍትህ ይሰጥበት ዘንድ ወደ ፍርድቤት ችሎት አድርሶታል።
ውሳኔ…
የካቲት 23 ቀን 2007 ዓም በችሎቱ የተሰየመው የልደታው ከፍተኛ ፍርድቤት በሁለቱ ተከሳሾች ላይ የመጨረሻውን የፍርድ ወሳኔ ለማሳለፍ በቀጠሮው ተገኝቷል።ፍርድቤቱ በተከሳሾቹ ላይ የቀረበውን የተደራጀ የክስ መዝገብ በበቂ ማስረጃና መረጃ ሰንዶም ጥፋተኛ መሆናቸውን አረጋግጧል።በዕለቱ ባሳለፈው ውሳኔም ሁሴን መሀመድና ጓደኛው አብዱርአዛቅ ይመር እያንዳንዳቸው እጃቸው ከተያዘበት ጊዜ ጀምሮ በሚታሰብ የዘጠኝ ዓመት ጽኑ አስራት እንዲቀጡ ሲል በይኗል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 25 ቀን 2012 ዓ.ም
መልካምስራ አፈወርቅ