ካለፉት ሁለት ሳምንታት ጀምሮ የ‹‹ዋይ ፋይ›› ኢንተርኔት አገልግሎት ተለቅቋል። የሞባይል ዳታ ስለሌለ መደበኛው የማህበራዊ ገጾች ጫጫታ የለም። በውጭ አገር የሚኖሩ እና በሆቴል አቅራቢያ ያሉ ሰዎች ብቻ ናቸው የሚጠቀሙ። በሌላ በኩል ፌስቡክ በተፈለገው ልክ አይሰራም። የአንዳንድ ተቋማትና መገናኛ ብዙኃን የፌስቡክ ገጾች ናቸው መረጃ የሚለጠፍባቸው። የግለሰቦች ቁጥር ቀንሷል።
አንድ ሁለት ቀን የዋይ ፋይ አገልግሎት ያለበት ቦታ ሆኜ ወደ ፌስቡክ መንደር ጎራ አልኩ። በእውነቱ በጉጉት ነበር የገባሁት። የጓጓሁበት ምክንያት ሁለት ነው። የመጀመሪያውና ዋናው የአካውንቴን ደህንነት ለማረጋገጥ ነው። እንደሚታወቀው በእንዲህ አይነት አጋጣሚ (ሎግ አውት ሳናደርግ ለብዙ ጊዜ ከቆየ) አካውንታችን ችግር ያጋጥመዋል። የአይ ሲ ቲ ባለሙያዎች እንደሚመክሩት ሎግ አውት መደረግ አለበት። ሳላደርግ ስለነበር የጠፋው እሱንም ለማረጋገጥ ነበር። ሁለተኛው ጉጉቴ ግን ምን አዲስ ነገር ይኖር ይሆን የሚለውን ለማየት ነው።
አንዳንዶቹ ቀልድ ናቸው። ‹‹ስልኬን ቻርጅ ካደረኩ ይህን ያህል ሳምንት ሆነኝ፣ ከቤተሰብ ጋር መጫወት ጀመርኩ፣ እዚያው ቤት ተወልደው ያደጉትን ልጆች ‹ይሄ ደግሞ የማነው ልጅ› ብዬ ሳቁብኝ….›› የሚሉ ቀልዶች ናቸው። የሁሉም ቀልዶች መልዕክት ፌስቡክ ባለመኖሩ የሆኑትን ነው። እንዲያውም የአንዳንዶቹ መልዕክት ወደ ማህበራዊ ህይወት መመለሳቸውን የሚያመሰግንም ነው።
አንዳንዶቹ ደግሞ ያንኑ የተለመደውን ብሽሽቅ አጠናክረው የቀጠሉ ናቸው። ‹‹ፌስቡክ ተከፍቶልኝ ተሳድቤ!›› ብለው በፉከራ የቆዩ ይመስላል። ለእነዚህ ሰዎች አጸፋ ለመስጠት ‹‹እባካችሁ በእናንተ ምክንያት ነው የተዘጋብን›› በማለት የአታዘጉብን ተማጽኖ የሚያቀርቡ ናቸው።
ዶቸቬለ ‹‹የማህበራዊ ሚዲያ ቅኝት›› በተሰኘው ፕሮግራሙ የተለያዩ ሰዎችን አስተያየት አሰባስቦ ነበር። ከአገር ደህንነት አይበልጥም ይዘጋ ያሉ ብዙዎች ናቸው። አንዳንዶቹ ደግሞ መዝጋት አፈና እንደሆነም ተናግረዋል፤ በመዝጋት አገር ማስተዳደር አምባገነናዊነት ነው ያሉም አሉ። ያው እንግዲህ ሰዎች የተለያየ አስተያየት ይኖራቸዋል።
እስኪ ቆም ብለን እናስበው! ከአገር ደህንነትና ኢንተርኔት ከሚዘጋ የቱ ይሻላል? እርግጥ ነው ሁለቱም ለምርጫ የሚቀርብ አልነበረም፤ ለምርጫ እንዲቀርብ ያደረገው የራሳችን የአጠቃቀም ችግር ነው። ‹‹የተሻለውን ሰይጣን ምረጥ›› እንደሚለው የፈረንጆች አባባል የተሻለውን ችግር ምረጡ ቢባል መዘጋቱ ይሻላል፤ ምክንያቱም ከአገር ደህንነት አይበልጥም። የተፈጠሩትን ነገሮች አይተናቸዋል፤ እነዚያ ነገሮች የተፈጠሩት ኢንተርኔት ተዘግቶ ነው፤ ኢንተርኔት ቢኖር ኖሮ ምን እንደሚፈጠር አስባችሁታል? ብጥብጡ በመላው አገሪቱ ይሆን ነበር ማለት ነው። ቀጥታ የብሄር ስም እየጠሩ ‹‹በለው!›› ሲባል ነበር።
አሁን ምርጫው የተጠቃሚው ነው። ይዘጋ ወይስ እንስተካከል? መቼም ያንን ጉድ እያየ መንግስት ዝም ይበል ማለት የማይታሰብ ነገር ነው። በነገራችን ላይ በኢንተርኔት መዘጋት መንግስት ቀዳሚው ተጎጂ ነው። ግን ከገንዘብ ጥቅም ህይወት ስለሚበልጥ ነው። መንግስት ፀጥታ የማስከበር ኃላፊነት እንዳለበት የታወቀ ቢሆንም ለእያንዳንዱ ግለሰብ ፖሊስ ማቆም ግን የማይቻል ነው። በዚያ ላይ ሚሊዮን ፖሊስ ቢሰማራ ‹‹በለው! ቁረጠው! ፍለጠው!›› የሚለው ካልቀረ የፖሊስ ሥራ መታኮስ ብቻ ሊሆን ነው ማለት ነው። ሰላም የሚሰፍነው ደግሞ በፖሊስ ተኩስ ሳይሆን በህዝቡ ህግ አክባሪነት ነው።
ግጭት ቀስቃሽ ነገሮችን ስናራግብ እየጎዳን ያለነው የራሳችንን ወገኖች ነው። ኢንተርኔት እኛ ለመዝናኛ እንጠቀመው ይሆናል፤ ለብዙዎች ግን እንጀራቸው ነው። እነዚህ ወገኖች የገቢ ምንጫቸው ይሄው ብቻ ነው። ለምሳሌ ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 በሰራው ዘገባ ራይድ የትራንስፖርት ድርጅት ግማሽ ሚሊዮን ብር አጥቷል። ይሄ ትልቅ ድርጅት ስለሆነ የዕለት ጉርስ አያጣ ይሆናል። ለኢንተርኔት ካፌ ህንጻ ውስጥ ተከራይተው የሚሰሩ ግን የዕለት ጉርስ እስከማጣት ይደርሳሉ። የህንጻ ውስጥ ኪራይ ደግሞ ዋጋው እንኳን ቀላል አይደለም። እነዚህ ሰዎች ሌላ መተዳደሪያ የላቸውም። እንግዲህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ኢንተርኔት የቅንጦት ሳይሆን የህልውናም ጉዳይ ሆነ ማለት ነው። ኢንተርኔት የሚዘጋበትን ምክንያት ስናጯጩህ የእንዲህ አይነት ወገኖችን እንጀራ እየዘጋን ነው።
የኢንተርኔት ተጠቃሚው ማህበረሰብ በከፊልም ቢሆን ‹‹የተማረ›› የሚባለው ወገን ነው። በዚህ የተማረ በሚባለው ማህበረሰብ አገር ሲቃወስ ማየት አሳፋሪ ነው። ካፌ ውስጥ ሆነው ማኪያቶ እየጠጡ ‹‹በለው!›› ይላሉ፤ ምስኪን ወጣት እየሄደ ይማገዳል። የራሱን ወገን ንብረት ያጠፋል። የአገር ፍቅር ማለት ግን ምን ማለት ይሆን?
መንግስት እነዚህን ወገኖች ‹‹የጥፋት ኃይል›› ሲል ብዙ ወቀሳ ደርሶበት ነበር። ለምን የጥፋት ኃይል ይላል እየተባለ። ምናልባት ጥፋተኛ ያልሆኑትን ሲል ይወቀስ እንጂ የወገን ንብረት የሚያወድምና የሚያስወድም ታዲያ ምን ሊባል ነው?
‹‹ኢትዮጵያ ኢንተርኔት ዘጋች›› ተብሎ በብዙ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ተሰራጭቷል። አንድ የአገር ፍቅር አለኝ የሚል ኢትዮጵያዊ ይሄን ሲሰማ ምን ይሰማዋል? አገራችን በበጎ ነገር ስሟ ሲጠራ እንኮራለን። አትሌቶቻችን በዓለም አደባባይ የኢትዮጵያን ባንዲራ ሲያውለበልቡ የምናለቅሰው አምስት ሳንቲም የምናገኝ ሆኖ አይደለም። ለዝና ከሆነም አትሌቱን እንጂ እኛን የሚያውቀን የለም። ሳግ የሚተናነቀን አገራዊ ኩራት ስለሚፈጥርብን ነው። በዚያው ልክ የአገራችንን ስም የሚያጠለሽ ዜና በዓለም ሲሰራጭ እናዝናለን። እንግዲህ የአገሪቱ ስም መጥፋት የሚያስደስተው ካለ እሱ የአገሪቱ ጠዪ ነው ማለት ነው። አገሩን የሚጠላ የጥፋት ኃይል ካልተባለ ታዲያ ምን ሊባል ነው?
የተማረ በሚባለው ወገን ሌላም ችግር አለ። አንብቦ የመረዳት ችግር አለብን። ፌስቡክ ኢትዮጵያ ውስጥ ግጭት የሚያስነሳው በጸሐፊዎች አላዋቂነት ብቻ ሳይሆን በአንባቢዎችም አላዋቂነት ነው። የሥልጣኔ ማማ ላይ ናቸው በሚባሉት አገራት ሳይቀር ስድብና ዛቻ አለ። ልዩነቱ ግን አንባቢዎቻቸው አሳቢ ናቸው። ካፌ ውስጥ ቁጭ ብሎ ‹‹እገሌ ሌባ!›› የሚል ጽሑፍ ቢያገኝ ለእሱ መረጃ ብቻ ነው። እንደ እኛ አጣና እና ድንጋይ ፍለጋ አይሄድም። ቆም ብሎ ያስባል። ብሄር ተኮር የግጭት ቅስቀሳ ግቡን የሚመታው አፍሪካ አገራት ውስጥ ነው።
በገጠር አካባቢ የማውቀው አንድ ጥሩ ባህል አለ። በመንደሩ የሆነ አሉቧልታ ይነሳል። ለምሳሌ እገሌ ከእገሌ ሚስት ጋር ወሰለተ ወይም እገሌ እንዲህ አደረገ ሲባል ወሬውን እንደ አዲስ የሰማ ሰው ‹‹ማነው ያለው?›› ብሎ ይጠይቃል። የነገሩን እውነትነት የሚያረጋግጠው በተናጋሪው ማንነት ነው። ተናጋሪውን ሲነግሩት ‹‹ውይ! እሱ ነው እንዴ!›› ብሎ ውሸት መሆኑን ያረጋግጣል። ተናጋሪው እውነት በመናገር የሚታወቅ ከሆነም እውነት ነው ብለው ይቀበላሉ።
የተማረ የሚባለው ወገን ግን ከእነዚህ ወገኖች አንሷል። ማነው የለጠፈው ብሎ አይጠይቅም። እንኳን የፌስቡክ መረጃ ዋናዎቹ መገናኛ ብዙኃን (ሜይንስትሪም ሚዲያዎች) የዘገቡትን ራሱ ማነው ያለው ብለን መጠየቅ አለብን።
አሁን ምርጫችን ኢንተርኔት ይዘጋ ወይስ እኛ አጠቃቀማችንን እናስተካክል የሚለው ብቻ ነው። ከዚያ ውጭ የራሱን ኑሮ አመቻችቶ ምስኪን ድሃ በእሳት እያስጋየ መኖር አያዛልቅም። መንግስትም ዝም ብሎ አይመለከትም፤ ቢያንስ ቢያንስ ኢንተርኔት ይዘጋል። ኢንተርኔት ሲጠፋ ምን ያህል እንደተቸገርን አይተነዋል። ኢንተርኔት ዘጊውም ሆነ ከፋቹ መንግስት ሳይሆን እኛው ነን። እኛ ከተስተካከልን ኢንተርኔት አይዘጋምና እንስተካከል!
አዲስ ዘመን ሐምሌ 22/2012
ዋለልኝ አየለ