አዲስ አበባ ፡- በሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት አንዳንድ ወረዳዎች የደንጊ በሽታ ወረርሽኝ ምልክቶች መታየታቸውንና ሕዝቡ ራሱንና ቤተሰቦቹን ከበሽታው ለመጠበቅ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አሳሰበ ።
የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር እና የሕዝብ ጤና ድንገተኛ አደጋዎች ስጋት መከታተልና ቁጥጥር አስተባባሪ ዶክተር በየነ ሞገስ ትናንት በጽህፈት ቤታቸው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት፤ የደንጊ በሽታ ወረርሽኙ የተከሰተው በፊቅ ዞን ሲሆን፣በዞኑ ለገሂዳ ወረዳም በአንድ ሳምንት 60 ሰዎች በበሽታው ተጠቅተዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል 41ዱ ህፃናት ናቸው።
በሽታው ከስድስት ወራት በፊት በዞኑ በዶሎ ኦዶ ወረዳ ተከስቶ በ331 ሰዎች ላይ ምልክቶች ታይቶ እንደነበር ዶክተር ሞገስ አስታውሰዋል፡፡ ካለፈው ሳምንት ወዲህ የታዩትን የደንጊ በሽታ ወረርሽኝ ምልክቶች ለመቆጣጠር የክልሉ ፈጣን ምላሽ ሰጪ ቡድን የዳሰሳ ጥናት እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፣ የኢንስቲትዩቱ ህክምና ቡድንም ወደ ሥፍራው መላኩን አስታውቀዋል።
በሽታው ትኩሳት፣ ከፍተኛ ራስ ምታት፣ የጡንቻና የመገጣጠሚያ ቦታ ህመም ማቅለሽለሽና ማስታወክ ምልክቶች እንዳሉት ያስረዱት ዶክተር በየነ ፣ በሽታው መድሃኒት እንደሌለውና ክትባቱም በዓለም አቀፍ ደረጃ በአብዛኛው ጥቅም ላይ አለመዋሉን አብራርተዋል።
እንደ ዶክተር በየነ ገለጻ፤ በሽታው በወባ መሰል ትንኝ የሚተላለፍ ሲሆን፣ ትንኞቹ የሚናደፉት ቀን ላይ ነው፤ ለመራባት ሞቃት ወይም ሐሩር ቦታዎችን ይመርጣሉ፡፡ ኅብረተሰቡ ራሱንና ቤተሰቡን ለመከላከል የታቆሩ ውሃዎች እንዳይኖሩ ማድረግ፣ ርጥበት አዘል ቆሻሻ ነገሮችን ማስወገድ፣ ሰውነትን ሙሉ ለሙሉ በመሸፈን መንቀሳቀስ እና ህፃናትን በአጎበር ማስተኛት ይገባል፡፡
የበሽታውን አስተላላፊ ትንኞች ለመከላከልም የመከላከያ መድሃኒት ርጭት እንደሚደረግ ጠቅሰው፣ በሽታው ደንጊ ነው ብሎ ለማረጋገጥ ከታማሚዎች የደም ናሙና ተወስዶ በሴኔጋል ዳካር ምርመራ እንደሚደረግም ገልፀዋል።
በሽታውን ለመከላከል ቅድመ ትንበያ ተሰርቶ አንደነበር አስታውሰው፣በሽታውን መከላከል ግን አልተቻለም ብለዋል፡፡ ኢንስቲትዩቱ ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለው የደንጊ በሽታ የላቦራቶሪ ምርመራ ለማድረግ የሚረዱ የመመርመሪያ መሣሪያዎችን ለማስገባትና የላቦራቶሪ ሥርዓቱን ለመዘርጋት አቅሙን ገንብቶ ከዓለም ጤና ድርጅት ጋር እንደሚሰራም አስታውቀዋል፡፡
የደንጊ በሽታ ከ2005- 2006 ዓ.ም ጀምሮ በድሬዳዋ ፣ከ2007- 2008 ዓ.ም በድሬዳዋ እና ጎዴ ባለፈው ዓመት ደግሞ በዶሎ አዶ ተከስቶ እንደነበር የኢንስቲትዩቱ መረጃ ያመለክታል።
አዲስ ዘመን ጥር 18/2011
በኃይለማርያም ወንድሙ