ባለፈው ሳምንት እትማችን ≪ወላጆች ልጆቻቸውን እንዴት ማሳደግ አለባቸው≫በሚል ርዕስ አስነብበናል። ዛሬ ደግሞ ወላጆች ለልጆቻቸው ምን ማስተማርና እንዴት መምራት እንዳለባቸው ዶክተር አልማዝ ባራኪ የላኩልንን ጽሑፍ እናስነብባለን።
ልጆች ብዙ ጊዜ አብረው የሚያሳልፉትን (በቅርበት የሚያዩትን) ሰው ይመስላሉ። ከሱስ፣ ከጥላቻ ንግግሮች፣ ከስንፍና፣ ከጭካኔ፣ ከእምነት ማጉደል፣ ወዘተ ከመሳሰሉት እኩይ ተግባራት የጸዱ ወላጆች፣ ባልተጠበቀ አጋጣሚ ካልተደናቀፈባቸው በስተቀር ልጆቻቸው በእውቀት፣ በክህሎትና በሥነምግባር የታነጹ ዜጎች ይሆናሉ። ብዙጊዜ የምትሳተዋ መስመር የራስን ፍላጎት መሰዋት አለመቻል ናት። ምርጡን ለልጆቻችን ለመስጠት ስንል የምንከፍለው መስዋዕትነት በልጆቻችን አስተዳደግ ላይ ጉልህ ሚና ይኖረዋል።
በአንድ አካባቢ በልጆች አስተዳደግ ሂደት ውስጥ የማህበረሰቡ ሚና ብዙም ወላጆች ከሚያደርጉት የተለየ አይሆንም። ዜጋነት የሚባለው አንድ ልጅ መጀመሪያ የራሱ፣ የቤተሰቡ፣ የማህበረሰቡ እና የአገሩ ነፀብራቅ ነው ይባላል። ስለዚህ ዋናው ሚና አርአያነቱ ስለሆነ ልጆች ራስን የመውደድና የመንከባከብ፣ ወላጆቻቸውን የመውደድና የመንከባከብ፣ ጓደኞቻቸውን የመውደድና የመንከባከብ፣ ማህበረሰቡን የመውደድና የመንከባከብ፣ ሰፋ ያለ ራዕይ ኖሯቸው ደግሞ አገራቸውን የመውደድና የመንከባከብ አቅም እንዲኖራቸው ማድረግ ነው። ማህበረሰብ የቤተሰብ ድምር ውጤት ስለሆነ እያንዳንዱ ቤተሰብ በልጁ አስተዳደግ ላይ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ በአጠቃላይ በአንድ አካባቢ በሚኖሩ ልጆች አስተዳደግ ላይ የሚጨምረው ወይም የሚያጎድለው ነገር አለ።
መምህራን ከስጦታዎች ሁሉ ውድ ስጦታ የሆኑትን የብዙ ሰዎች ልጆች ተቀብለው የሚያሳደጉ ናቸው። በዚህም የተነሳ ለሚከተለው የልጆች አስተዳደግ ችግር ሙሉ በሙሉ ተጠያቂ ሆነው ይቆጠራሉ። እውነቱ ግን በተለይ ወላጅና መምህር በልጆች ጉዳይ ላይ የጋራ አጀንዳ ቀርጸው በማይወያዩበት ሁኔታ መቆጠር ያለባቸው የአንድ ባለድርሻ አካል ሚና እንዳላቸው ነው። የልጆች እድገት መሠረት የሚጣለው ትምህርት ቤት ከመግባታቸው በፊት ባሉት ጊዜያት ነው። ከዚያ በኋላ ያሉት ጊዜያት የማስተካከያና የማረቂያ ናቸው።
እንደአንድ የባለድርሻ አካል የመምህራን ሚና ተማሪዎች ለደረጃቸው የሚመጥን ግን ምጡቅ አእምሮ እንዲኖራቸው የሚረዳ እውቀት እንዲያገኙ ማገዝና ማስተማር፤ እኔ ያልኩትን ብቻ ተቀበል ሳይሆን እንድታውቅ ላግዝህ በሚል እሳቤ የተግባቦት ክህሎታቸው እንዲዳብር ማገዝ፣ ጠያቂ፣ ተመራማሪና በምክንያት የሚያምኑ እንዲሆኑ መርዳት፣ ለራሳቸው፣ ለጓደኞቻቸው፣ ለሚኖሩበት ማህበረሰብ፣ ለአካባቢያቸው፣ ለአገራቸውና በአጠቃላይ ለእንስሳትናእፅዋት የሚያስቡና የሚቆረቆሩ እንዲሆኑ ማገዝ ነው።
ሌላው አርአያ የመሆኑ ጉዳይ መምህራን ላይ ሚዛን ሊደፋ ይገባል። ልጆች በተለይ ከቅድመ መደበኛ እስከ አንደኛ ደረጃ መጨረሻዎቹ አካባቢ መምህራንን ሁሉ ነገር አድርጎ የመቁጠር አዝማሚያ አለ። መምህሩ የሚሉትን፣ የሚያደርጉትን ሁሉ መከተልና ትክክል አድርጎ መቁጠር ይስተዋላል። ስለዚህ መምህራን እነሱም ምጡቅ አእምሮ ያላቸው፣ የተግባቦት ክህሎታቸው የዳብረ፣ ጠያቂ፣ ተመራማሪና በምክንያት የሚያምኑ፣ ለራሳቸው፣ለጓደኞቻቸው፣ ለሚኖሩበት ማህበረሰብ፣ ለአካባቢያቸው በአጠቃላይ ለአገራቸው እንዲሁም ለእንስሳት፣ለእፅዋት የሚያስቡ፣ የሚቆረቆሩ መሆን ይጠበቅባቸዋል። ይሄንን የመምህሩን መልካም ተግባር እየተከታተለና እያየ ያደገ ተማሪም ከመምህሩ በተሻለ ቀናነት ያዳብራል። ስለዚህ መምህራን ለተማሪዎቻቸው የመልካም ምሳሌ አርአያ መሆን ይጠበቅባቸዋል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 19 ቀን 2012 ዓ.ም