አዲስ አበባ፡- በገጠር ተደራሽነት መንገድ ግንባታ (URRP) በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን 90 ሺ ኪሎ ሜትር ለመስራት ቢታቀድም እስካሁን መፈጸም የተቻለው ግን 9 ሺ 957 መሆኑ ተገለፀ።
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ሰሞኑን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለከተማ ልማት ኮንስትራክሽንና የትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የባለስልጣኑን የስድስት ወር አፈጻጸም ባቀረበበት ዋና ዳይሬክተሩ ኢንጅነር ሀብታሙ ተገኝ እንደተናገሩት፤ ከፕሮግራሙ እስካሁን ማከናወን የተቻለው የእቅዱን 21 በመቶ ብቻ ነው።
እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ፤ አፈጻጸሙ ዝቅተኛ ሊሆን የቻለው ከፌዴራልም ሆነ ከክልል ለግንባታው የሚሰጠው ገንዘብ በበጀት እጥረት ምክንያት በመቋረጡ ነው። ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የተፈጠረውን የገንዘብ እጥረትና የስራ መቆም ለገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር፣ ለፕላን ኮሚሽንና ለሌሎች ለሚመለከታቸው አካላት ቢያሳውቅም እስካሁን የተገኘ በቂ ምላሽ የለም ብለዋል።
የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር የትምጌታ አስራት በበኩላቸው ፕሮጀክቱ በእቅዱ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ሊጠናቀቅ እንደማይችል ተናግረዋል። ኢንጅነር የትምጌታ እንደተናገሩት በመጀመሪያው እድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን የአንድ አመት ከፍተኛው አፈጻጸም ሀያ ሺ ኪሎ ሜትር ነበር። በቀጣዩ በጀት አመት ገንዘቡ ተገኝቶ የዚህን ያህል መስራት ቢቻል እንኳ በአጠቃላይ በእድገትና ትራንስፎርሜሽኑ ማጠናቀቂያ ሊሰራ የሚችለው የእስካሁኑን ጨምሮ ከ ሰላሳ ሺ ኪሎ ሜትር የበለጠ ሊሆን አይችልም። ይሄ እንዳለ ሆኖ ፕሮግራሙ ለሌሎት መሰረት ልማቶችና አጠቃላይ ለሀገሪቱ እድገት ወሳኝ በመሆኑ የገንዘብ ምንጭ የማፈላለጉና ባለው አቅም ለመስራት የሚደረገው ጥረት የሚቀጥል መሆኑን አመልክተዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 18/2011
በራስወርቅ ሙሉጌታ