ዓለማቀፉ የቀይ መስቀል ድርጅት፣ በአንድ ወቅት ባወጣው መግለጫ በዋናዋ ሶማሊያ ግዛት በእርስ በርስ ውጊያው ላይ በአንዳንድ ስፍራዎች ጦርነቱ ከፈጠረው መፈናቀልና ስደት ሌላ ድርቅና ረሐብ ገብቶ ስለነበረ “የማርያም መንገድ“ አግኝተን እርዳታውን ለማድረስ በገባንባቸው ጊዜያት ያስቸገረን ነገር የሰዎቹ በዘር መከፋፈል ነበረ፤ ይላል።መሪሐኑ፣ ከኢሳው፣ ገደቡርሲው ከሌላው ጋር ስለሚገፋፋና ስለሚጠፋፋ የእርዳታ መድሃኒትና ምግብ ለማቅረብ የሚገቡ ሰራተኞቻችን በቅርብ ርቀት ላይ ያሉትን ሌሎች ሰዎችን ለመድረስ መጀመሪያ ያገኘናቸው ጎሳዎች ፈቃድ ያስፈልገን ነበረ።ያንዳቸው እጣ በሌላኛው ጫማ ስር ነበረ፡፡
እኛም አንዳች ነገር ከማድረሳችን በፊት የዓለማአቀፍ ቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃን ዓላማና መርሆዎች፣ ተልእኮና እሴቶች ለጎበዝ አለቆቹና አጃቢዎቻቸው ማስረዳት ይጠበቅብን ነበረ። ይህም ሆኖ ማለፊያ መጠየቃችን አይቀርም ነበረ።እጅጉን ፈታኝ የነበረው ሁኔታ አንድ ቋንቋ እየተናገሩ አንድ እምነት እና አምልኮ ዘዴ ይዘው ለመደማመጥ አለመቻላቸው ነው። እያወራህ አለመደማመጥ እየተነጋገርክ አለመረዳዳት ደግሞ ስምየለሽ አደጋ ነው። ሁሉም እልኸኛና ሁሉም ኃይለኛና እኔ ያልኩት ካልሆነ ባይ ነው። ባገኘው አጋጣሚ ራሱን የበላይ አድርጎ የሚያሳይበትን እድል መፍጠር ደግሞ የሚናፍቁት ነገር ነው፡፡
እርዳታችንን በተገቢ ሁኔታ የሰጠናቸው አካላት ወደሚቀጥለው ቀበሌ ወይም ወረዳ ለመጓዝ መኪናችንን ስንቆሰቁስ የሚነግሩን አንደኛ የፀጥታ ስጋት ያለ መሆኑን፣ ሁለተኛ በቂ እርዳታ ከሌሎች የተሰጣቸው መሆኑን እናም መድሃኒቱን ካገኙ መልሰው ለእነርሱ ሊሸጡላቸው እንደሚችሉ በማሳሳት መረጃ ይሰጡን ነበረ።እንደምንም ብለን እንያቸውና እንመለስ በማለት፣ አስተርጓሚያችንን ይዘን ስንሄድ (እነርሱ ለሁለት ጉዳይ ነው የሚጠቀሙባቸው) እንደዚሁ የተዛባ መረጃ በማቅረብ ወደር የሌለው ጨካኝ ስራ ይሰሩ ነበረ፡፡
የጎሳና የነገድ ልዩነትን የሚፈጥሩት እነዚያ ሶማሊያውያን የልዩነታቸው ገመድ የሚያጠቡት እስከ ቤተሰብ ድረስ በመውረድ ነው፤ ማቆሚያ የለውም። የአባታቸው ልጅ ወንድምና እናታቸው አንድ አይደሉም፤ ስለዚህ የእኛ ወገን ናቸው ለማለት ያስቸግራል፤ ነው የሚሉት።እኛ ሰፈር አንድ ሰሞን የሚያስቸግሩን “እነዚህ ዲቃላዎች” ናቸው፤ እንዳሉት ማለት ነው።
እኛ ቋንቋና ባህላቸውን የማናውቅ ሰዎች ልንረዳቸው ከዓለም ዙሪያ እርዳታ አሰባስበን ልንሰጣቸው ስንገባ ሥራውን ከማቅለል ይልቅ በማካበድ፣ የነገድና የጎሳ ልዩነታቸውን ተንተርሰው ሲከላከሉ እንደማየት አሳዛኝ ነገር የለም። አንድ ቋንቋና አንድ አንድ እምነት፣ (98.9 ከመቶ ገደማ) ያላቸው ሆነው ሳለ ዘር ቆጠራ ውስጥ ገብተው እርስ በእርሳቸው ምግብና መድኃኒት እስከ መከላከል የደረሰ ጥላቻ ምንጩ አረማዊነት ነው። መነሻው ልክ እንዳለመሆኑ ውጤቱም ልክ አይሆንም፤ ይልና ዘገባቸው፤ እንኳንስ የተራበ ህጻን ያልተራበም ቢሆን ፖለቲካ አይገባውም። እነርሱ ግን እነዚህን ሁሉ የህብረተሰብ አካላት የልዩነታቸው አካልና የጥላቻ ጅራፋቸው ተካፋይ አድርገው ይስሏቸዋል፤ ሲል ይቀጥላል፡፡
ይህንን ሀሳብ እዚህ ላይ ገታ ላድርገውና ወደ ሀገራችን ስንመጣ፣ እኛ ራሳችን ልዩ ልዩዎች ነን። ባለህብረ ቋንቋ፣ ባለብዙ ባህል፣ ባለብዙ ወግ፣ ባለብዙ ቀለም ግን አንድ እናት ያለችን ዥንጉርጉር ኢትዮጵያውያን ነን። ይህንን ብዙነታችንን ብቻ በሰላም ለሽያጭ ብናበቃው ብቻ እንከብራለን። ራሳችንን ለእያንዳንዳችን መቼ አቅርበንና ገልጠን አበቃን ? ራሳችንን ለሌሎቻችን መቼ በስርዓት አሳይተን መቼ ጨረስን፣ ገና ብዙ የሚገለጥ ውብ ነገሮች ያሉን ህዝቦች ነን፡፡
ልዩ ልዩ አለባበስ፣ አጋጌጥ፣ አሞሻሸር፣ የሰርግ ስርኣት፣ የምግብ አዘገጃጃት፣ የለቅሶ መንገድ፣ የአስተራረስ ዘዴ፣ ዘይቤዎች፣ እንቆቅልሾች፣ ፈሊጦች ተረትና ምሳሌዎች ወዘተርፈ ያለን ነን። መቼ ተያይተንና ተጠናንተን አበቃን? ኧረ ብዙ ብዙ አለን፤ ጎበዝ፡፡
ባለፉት ሶስት አስርት ዓመታት ግን ከውቡ ቀለም ይልቅ አስፈሪ ቀንዶቻችንን ስናለካካ፣ በልባችን ማሳ ላይ ደግሞ የጥላቻ አረሞች ስንተክልና ስናሳብብ ቆይተን የድህነታችን ምንጭ፣ የችጋራችን ምክንያት ይህ ወይም ያኛው ቋንቋ ተናጋሪ ነው፤ የሚል እሳቤ በልባችን ተዘርቶና አብቦ፣ ፍሬው በአስፈሪ ሁኔታ ባለፉት 20 ወራት ውስጥ በአለፍ ገደም እየፈነጠቀ በዚህ ዓመት ብቻ የተመዘገበ፣ ከ250 በላይ ወገን አሳጥቶናል። አስከሬኑ ደብዛው የጠፋውን ቤትና እናቱ ትቁጠረው፡፡
የቅርቡ ዘረፋና የንብረት ውድመት ምክንያት ደግሞ የሃይማኖት ጭንብል መልበሱ “የአሳማጮቹን” ተስፋ መቁረጥ ጉልህ በማድረግ፣ ሙጣጭ እድሎቻቸውን በመጠቀም ጥፋትና ውድመቱን በማስፋት፣ በአካባቢው ያለውን የጎረቤት አጥፊ ኃይል፣ ስር-ሰደድ ጥፋት ለማስፈፀም የታቀደ መሆኑን አመላካች ነው። ለመሆኑ አሳማጮቹ ትዳር ያማጡ ህብረት የፈጠሩ ግባቸውን የመቱ ይመስላቸዋልን? የፈጠሩት እኮ ቂምና ቁርሾ ነው፤ ነገ የባነኑ እለት ወደ እነርሱ እንደሚዞር አላስተዋሉ ይሆን? ወይስ አሁንም ምኒሊክ ጡት ቆረጡብህ እያሉና እያስባሉ ሰው አንገት እንደእንስሳ ያስቆርጣሉ? የጥፋታቸውንስ ጥልቀት ልብ ብለውታልን? ይህ ጥፋት ትናንት ሐገሪቱን ትልቅ እስር ቤት አድርገው ከፈጸሙትና ካስፈጸሙት ግፍ የላቀ የጠራራ ፀሐይ ውንብድና ነው። ይህ በአንዳችን ወይም በተወሰነ የህብረተሰብ ክፍል ላይ የተፈፀመ ክፉ ግፍ በሁላችንም ላይ የሆነ ነው።
በዩጎዝላቪያ የእርስ በእርስ ጦርነት ወቅት በሰርቢያ ሄርዞጎቪና እንዲሁም በሰርብሬኒካ የተፈጸሙት ግፎች ሰርቢያን ከእስልምና የማጽዳት የስም ኤጤሬዎች ክፉ ግፍ ነበረ።ቀን ሲያልፍ ታዲያ ተኳሾቹም አስተኳሾቹም ካሉበት ስፍራ ተይዘው ናዚዎች በቀረቡበት በዓለማቀፉ የፍትህ ችሎት ቀርበው ቅጣታቸውን ተቀብለዋል። ያንን ግፍ ስፈጸመው ሰው ራሱን በመደበቅ መነኩሴ መስሎና ጺሙን አንዠርግጎ የመነኮሳቱን ቀሚስ ለብሶ ጨዋ መስሎ ሲመላለስ ነው፤ የተያዘው። የንጹሃን ደም መቼም መደበቂያ ኤሴትምና።ግን ፍርድ ቤት ሲቀርብ እኔ አንዲትም ነፍስ አላጠፋሁም፤ ማንም ታጣቂ የፈጸመውን ግፍ በእኔ ላይ አታላክኩ ነው፤ ያለው።የግፍ ጽዋ ስትሞላ ግፈኛውን እባዘነች ማስያዟን ታሪክ ደጋግማ አሳይታናለች፡፡
እንዲሁም ይህንን የዘረፋና የውድመት ታሪክ ከቀናዎቹ የጥቁሮች አመጽና የሰራተኞች የመብት ጥያቄ ጋር በማዛመድ ሊያስተያዩ የሞከሩ ሰዎች አሳዛኞች ናቸው። መንግስትን መቃወም እንደተጠበቀ ሆኖ የተቃጠሉት ግን መከላከያ የሌላቸው ምስኪን ሲቪልና ነጋዴ ሰዎች ንብረት መሆኑ “ከአህያውን ፈርቶ ዳውላውን” ያነሰ ተረት ካለ እንድታውሱኝ የሚያስጠይቅ ነው።ሲቪሎች ብቻም አይደሉም፤ በእምነታቸውና በሌላ ቋንቋ ተናጋሪነታቸው ተለይተው ነው ጥቃት የተፈጸመባቸው፡፡
የትኛው የጥቁሮች ዓመጽ ነው፤ የነጮችን መኖሪያ ቤት እየፈለገ፤ የነጮችን መኪና እየመረጠ፣ የነጮችን ሆቴልና ሞቴል እያሳደደ ያጠቃው? ከቶውንም አይደለም። ጥፋትና ውድመት ተፈጽሟልን አዎ ተፈጽሟል ግን ያገኙትንና በሰልፋቸው ትይዩ የመጣውን ቤትና ንብረት አቃጥለዋል፤ ሱፐርማርኬቶች ተዘርፈዋል፤ ግን የነጭ ስለሆነ ይውደም፤ የጥቁር ስለሆነ ይትረፍ አልተባለም።ቁጣው የፈጠረው ጥፋት ተፈጽሟል።ይህንን አምስሎት ለመስጠት መሞከር ለቅሶ ቤት ገብቶ እንደመዝፈን ያለ ድንገቴ ነው። ለቅሶ ቤት ኦርኬስትራ ተይዞ ተገብቶ አይዘፈንማ !! በተደራጀ በተጠናና በታቀደ መልኩ የነ እነእንትና መኖሪያ ቤት፣ ትምህርት ቤት፣ ክሊኒክ፣ ሆቴል የገበያ አዳራሽ ይውደም፤ ተብሎ በአጀብና በጩኸት ወጥቶ ማፍረስ ትግሉን ወደየትም ደረጃ ከፍ አያደርገውም። አደራጆቹንና አሰማሪዎቹን እንቅልፍ የሚነሳና ነጥብ ያስጣለ፣ የተሰማራባቸውን ጋሻ የለሽ ወገኖች የሚያሳዝንና የአጥፊያቸውን ማንነት ያሳያ ክስተት ነው፡፡
እንዲህ ዓይነቶቹ ጥፋቶች በዓለም የፍትህ አደባባይ ማስቀረብ ብቻ ሳይሆን ታሪክ ይቅር የማይለው ጥፋትም መፈጸም ነው። አዎ፣ ልጆቻችን ይህንን ታሪክ ይህንን ውድመት እየቀረጹ ነው፤ ልጆቻችን ይህንን ጥላቻ ይህንን አግላይነት እያዩ ነው። በባዶ ትርክት የመጣ ጥቃት ሳሆን በተጨባጭ ማን በመሆናቸው እየተፈጸመ ያለ ጥቃት ነው። ይህንን ጥፋት እንዲፈጸም የሚያደርጉ ሰዎች ለማስፈጸም ያላቸው ብቃት ለማሳየት አስበው ከሆነ “እንኳን ደስ ያላቸው” ይኸው 170 ሰዎችና ግምት በብዙ መቶ ሚሊዮን የሚቆጠር “የሌላ ዘር” ንብረት ወድሟል።አሁን “ዘራፍ” ብለው የሚፎክሩበት ነገር በወገን ላይ በተፈጸመ ጥቃት ከሆነ፣ መሳሳታቸውን ለመንገር ምስክር አንጠራም። የሚገርመው ሙስሊም ያልሆኑትን ወገኖቻችንን በማጥቃት ሌላው ወገን ብሩካን በሆኑት ድንቅ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ላይ ሌላው ህዝብ እንዲነሳ መሞከር የተበላ ቁማርና ነውረኛ ሐሳብ ነው። አታስቡት፤ ትናንት በተለያዩ አውደ ውጊያዎች፣ የእውቀት መስኮች፣ የስፖርት ሜዳዎች፣ የህክምና ተቋማት፣ በኪነጥበብ ዘርፎች (ያሻችሁን የሙያ ዘርፍ ጥሩ) ድንቅ አበርክቷቸውን ለዚህች ውድ ሐገራቸው ያበረከቱትንና ዛሬም ቀጥለው፣ በዓለም የመገናኛ ብዙሃን ለሐገራቸው እውቀታቸውንና ተቆርቋሪነታቸውን ሳይሾሙ ቆመው፣ ሳይጠሩ ራሳቸውን ጠርተው የቆሙትን ሙስሊም ወንድሞቻችንና እህቶቻችንን ሌላው ህዝብ ይጠላቸዋል ብሎ ማሰብ ዘበት ነው። ከጀግና ኡመር ሰመተርን፣ ከጠቢብ እነዶክተር የሱፍን፣ ከአዋጊ እን ጄኔራል አብዱላሒን፤ ከአድዋ ሙሐመድ ዓሊን (ንጉስ ሚካኤልን)፣ ከንግር አዋቂዎች ኡስታዝ ጀማልን፣ ኡስታዝ አቡበከርን የማይረሱትን ውድ እህቶቻችንን እነሻኪርን፣ እነ አል አሩሲን እና ሌሎችን መጥራት ይቻላል።በኢትዮጵያ የባለታሪክነት ወንዝ ላይ ከንግድ እስከ ታላላቅ የእውቀት ደብር ድረስ ሌሎችንም ስማቸውን መጥራት ይቻላል። ከኢትዮጵያውያን ወንድሞቻቸው የሆኑትን በመሆን ያልተሳተፉበት መስክ ያልተዋደቁበት ዓውድ የለም። እናም ….ውድ አስተኳሾች ሆይ፣ ጥይቶቻችሁ ዒላማ ስተዋል፤ ቀስቶቻችሁ አለት መትተው ተቆልምመዋልና እረፉ። ባታርፉም ትርፉ ድካም ነው፡፡
እና አንዳችንን ያገለለና ሌሎችን ያቀፈ፤ ሌሎችን ያገለለና አንዳችንን ብቻ ያቀፈ ነገረ ሥራ በዚህች በሐውርታዊ ባለታሪክ ሐገር ላይ በመፍጠር ለብቻ መደሰት አይቻልም፤ ለብቻ ሰላም አይገኝም፤ ለብቻ ብልጽግና አይታሰብም።ስለዚህ ሁላችንም እርስ በእርስ በመናበብ እና በመመጋገብ ነው ልናድግና ልንበዛ ልንበለጽግ የምንችለው፡፡
እዚህ ላይ ስደርስ ደስታው ጨርሶ ያልወጣልኝ የትናንቱ የአባይ የመጀመሪያ ደረጃ ሙሌት ሥራን ማንሳት ወደድኩኝ። ይህ ሙሌት የመጀመሪያው ይባል እንጂ የፍጻሜውም ማመላከቻ ትልቅ ቅስት ነው። ከግድቡ እየተገማሸረ ሲወርድ የነበረውን ውሃ ሲያዩ የነበሩ አይኖቼ እንባ ከማውረድ አልታቀቡም። አዎ ደስታም ያስለቅሳል፤ አዎ ግርምትም ያፍነከነካል፡፡
ይህ ደስታ የሁሉም ልበ ቀና ኢትዮጵያውያን ሁሉ ነው።ከቤንሻንጉል ጀምሮ፣ ጋምቤላን ይዞ ጢስ አባይንና የበላዩን ጨብጦ የሙስጠፌን የትውልድ ቀዬ የሶማሌን የኦሮሚያንና አፋሩን በጥቅሉም የሁልም ህዝብ ደስታ ነው።አባይ ለብልጽግና አስተዋጽኦ መዘጋጀት አባይን የሀገር ውስጥ ፖለቲካ ፓስታ አውሰብሳቢዎችንም ጭምር የሚጠቅም ነው፤ ቢያውቁበት፡፡እንኳንስ የሀገሬ ሰው ግብጽና ሱዳንም ካወቁበት የግድቡ መሰራት እና ሙሌቱ ለጥቅማቸው ነው፤ ጎርፍና ደለል በመቀነስ ያገለግላቸዋልና!! እስከዛሬ የበይ ተመልካች የሆንንበት ሁነት በመለወጡ ደስሊላቸው ይገባል።ሲለሙ አትልሙ አላልናቸውም፤ ልትለሙ አይገባም ካሉን የስደተኞች ፍልሰት ከካርቱም አደባባይ ወደ ኦንዱርማንና ሌሎች ከተሞቻቸው ካይሮና እስክንድሪያ ድረስ ያጥለቀልቃቸዋል። ይህንን ደግሞ የሚወዱት አይመስለንም። መልማታችን እናንተንም ይረዳል ያበለጽጋል ብለን ስንል፤ ተጨማሪ የመብራት ኃይልና የኢንዱስትሪ ልማት ታገኛላችሁ፤ ማለታችን ነው፡፡
ለአንዳችን የመጣ ብልጽግና ለሁላችንም ነው፤ ለሁሉ ካልሆነ ጊዜያዊ እንጂ ዘለቄታዊ እንደማይሆን ሳይታለም የተፈታ ነው።የእኛ ቤት መልከኛነትና ውበት ብቻውን ሰፈሩን አያደምቀውም፤ በአሮጌ ጨርቅ ላይ የተጣፈ አዲስ ጨርቅ ነው፤ የሚያስመስለው። ስለዚህም ከጎረቤት ተማክሮ ቀለም ተዋውሶ ማድመቅ ሁሉንም ያሳምራል። እንዲህ ካላሰብን እንዲህም ካልተጋን ነገር አይሳካም፤ ውብትም አይደምቅም፡፡
ስለዚህ ነው ለሁላችንም ያልሆነ ለአንዳችን አይሆንም የምለው። ግብጽ ስትበለጽግ እውቀትና ልምድ ቀሰማ እንደቀደመው ጊዜ በሰላም ሄደን እንወስዳለን። የሐይድሮሎጂ ትምህርት ቤታችንን እናበለጽጋለን፤ ሜትሮዎቿን (የምድር ውስጥ ባቡር) የሰራችበትን ጥበብ እንዋሳለን። ናይል የኪነጥበብ ሥራዎቿ ምንጭ የሆነበትንም ጥበብ እንቀስማለን። የጀልባ ሽርሽር የቱሪስት ኢንዱስትሪዋን አሰራር እንቀዳለን። የሱዳንን ታላላቅ እርሻና ኢንዱስትሪ ልማት እንማረዋለን።ይህ በእርስ በእርስ መግባባት የሚገኝ መመጋገብ በጋራ ያበልጽገናል። እኛ ብቻ እንልማና ስደተኞች ሆናችሁ እናስጠልላችሁ፤ ተርባችሁ እናብላችሁ፤ ካላችሁ ግን አይሳካም፤ አያስኬድም።
ስለዚህ እኛም እንልማ፤ ጎበዝ ለዚህ ነው ውሃ ያለው ውሃውን፣ ለሌላ በማቀበል፤ ጤፍ ያለው ጤፉን፣ በርበሬ ያለው በርበሬውን፣ ቅመም ያለው ቅመሙን፣ ወርቅ ያለው ወርቁን፣ እምነበረድ ያለው እምነበረዱን፣ ቡና ያለው ቡናውን የቀንድ ከብት ያለው ሰንጋውንና ጥጃውን እየተቀባበልን እና እየተመጋገብን ከምድር ውስጥና ከምድር በላይ ያለውን ሀብት በመካፈል እንጓዛለን እንጂ፤ እኔ ልብላ አንተ ተራብ፤ እኔ ልብራ አንተ ጥፋ፤ በዚህ ዘመናዊ ዘመን አይሰራም። አሜሪካ ከዓለም በተሰበሰበ የለማ ጭንቅላት፤ ሌላውም በሌላው ጭንቅላት የበለጸገ እውቀት እየተካፈሉ ነው፤ ያደጉት። በሁላችንም ያልሆነ በብቻችንም አይበለጽግም። ብልጽግናስ ጣዕሙ መካፈልም አይደል? ለአሁን አበቃሁ!
አዲስ ዘመን ሐምሌ 18/2012
ከአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ