በደመ ግቡ ፊታቸው ላይ ትህትናቸው ታክሎበት ልዩ መገለጫቸው ሆኗል። ተግባቢና ሰራተኞቻቸውን በፍቅር መያዙ የሚችሉ ሰው መሆናቸውን ደግሞ ባልደረቦቻቸው ይመሰከራሉ። ከ20 ዓመት በላይ አብረዋቸው ከሰሩ ሰራተኞቻቸው ጋር ደግሞ ቅርበታቸው ልክ እንደቤተሰብ ነው ። በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ተሰማርተው ውጤታማ የሚባል የንግድ ጉዞን አካሂደዋል። በስራ አጋጣሚ ያወቋቸው ደግሞ በጥንካሬያቸው ለበርካታ ሴቶች አርአያ መሆን የሚችሉ እንስት መሆናቸውን ይናገራሉ። የዛሬው እንግዳችን ወይዘሮ መንበረ አለሙ ይባላሉ።
ወይዘሮ መንበረ የተወለዱት የንጉስ ተክለ ሐይማኖት መቀመጫ በሆነችው ደብረማርቆስ ከተማ ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ ንጉስ ተክለሐይማኖት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርትቸውን ተከታትለዋል። በወቅቱ አቡኑ ሰፈር በሚባለው መንደር የነበረው የቤተሰባቸው ግቢ ሰፊ እና በአረንጓዴ ተክሎች የተሞላ እንደነበር ያስታውሳሉ። በተለይም ግቢያቸው ውስጥ የምንጭ ውሃ ጭምር ነበር። እናም ወይዘሮ መንበረ በግቢያቸው በሚገኘው አጸድ ውስጥ ማንበብ እና መዝናናት ያስደስታቸው ነበር።
የአስኳላ ቆይታቸው በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ሲቀጥል ድብዛ በተሰኘው ትምህርት ቤት ገቡ። በጊዜው ከሰፊው ግቢያቸው ለቀው ደብረማርቆስ ከተማ መሃል ወደሚገኝ ሌላ ቤት ከቤተሰባቸው ጋር መሸጋገራቸውን ያስታውሳሉ። ትምህርት ቤቱም ለመኖሪያቸው ቅርብ ሲሆን፤ ከትምህርት መልስም በአብዛኛው ጥናት ላይ ያሳልፉ እንደነበር አይዘነጉትም። በትምህርት ቤት ቆይታቸው ደግሞ ኮሜርሻል የትምህርት ዘርፍ የተባለውን መርጠው ነበርና ለጸሐፊነት የሚያበቃቸውን ትምህርት መከታተል ቀጠሉ።
ከፀሐፊነት ሙያ ትምህርቱ ጋር የሚሰጠው የ12ኛ ክፍል ትምህርት ከመጠናቀቁ ጥቂት ወራት በፊት ግን ትዳር መያዛቸውን በፈገግታ ያስታውሱታል። ያኔ ወደትዳር ሲገቡ ደግሞ ገና የ18 ዓመት ወጣት ነበሩ። ይሁንና ብልህ እና ነገሮችን በቶሎ መገንዘብ የሚችሉ በመሆናቸው የትዳር ህይወታቸውን ለማስተዳደር እንዳልተቸገሩ ይናገራሉ።
ትዳር ከያዙ በኋላ ደግሞ ትምህርታቸውንም ሳያቋረጡ የ12ኛ ክፍል ፈተናን ወሰዱ። በዚያው ክረምትም ወይዘሮ መንበረ አዲስ አበባ መጥተው ስራ ማፈላለግ ጀመሩ። ወዲያውም ስራ ተገኘ። በወቅቱ ደግሞ ባል እና ሚስት በአንድ ቦታ መመደብ የሚችሉበት አሰራር ነበርና ባለቤታቸው ወደሚገኙበት ወሎ ሄደው በወባ መቆጣጠሪያ ተቋም ውስጥ እንዲሰሩ ተመደቡ። በወባ መቆጣጠሪያ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በ1967 ዓ.ም በፀሐፊነት ሲቀጠሩ የወር ደመወዛቸው 230 ብር እንደነበር አይዘነጉትም።
ከጥቂት ዓመታት በኋላ ደግሞ ከባለቤታቸው ጋር አዲስ አበባ በሚገኘው የወባ መቆጣጠሪያ ድርጅት ተዘዋውረው የፀሐፊነት ስራቸውን ቀጠሉ። በመጨረሻም ለአራት ዓመታት ተኩልም ከሰሩበት ድርጅት ለቀው፤ መገናኛ እና ትራንስፖርት ሚኒስቴር ይባል ወደነበረው ተቋም በፀሐፊነት ተቀጠሩ። በዚያም ለአራት ዓመታት ካገለገሉ በኋላ ወደባህርና ትራንዚት ተቋም ተሸጋገሩ። በወቅቱ የሚያገኟትን ጥቂት ገቢ ቢሆን ለመቆጠብ እና ለቁም ነገር ለማዋል የሚጥሩት ወይዘሮ መንበረ ከባለቤታቸው ጋር ተፍጨርጭረው ባገኙት ገንዘብ አዲስ አበባ ላይ ቤት ሰሩ።
ባህር ትራንዚት እያሉም የደርግ መንግስት ሊወድቅ የተቃረበበት ጊዜ መጣ። አንዳንድ የመንግስት ግርግሮችን ሲያዩም በኢሠፓ ውስጥ ይሳተፉ የነበሩት ባለቤታቸው አንድ ቀን ስራ ሊያጡ እንደሚችሉ በማሰብ ወደፊት አማትረው አዩ። እናም መኖሪያ ቤታቸውን በጥሩ ገንዘብ ሸጠው በአነስተኛ ወጪ ኮተቤ አካባቢ ባዶ መሬት ገዙ። መንግስትም ተቀይሮ ኢህአዴግ ወደስልጣን ሲመጣ ወይዘሮ መንበረ ያሰጋቸው ነገር አልቀረምና ባለቤታቸውም ከስራ ተሰናበቱ። ከስራ መሰናበት ብቻ አይደለም ለእስርም ጭምር ተዳረጉ። ባለቤታቸው ደግሞ በእስር ወቅት በነበሩበት ጊዜ አብረዋቸው ከታሰሩ ሰዎች መካከል ጥሩ ጓደኞችን አፈሩ። በእስር ቤቱ ያገኟቸው ጓደኛ ደግሞ የኬሚካል ኢንጂነር ባለሙያው ናቸው። ጓደኛማቾቹ ከእስር ሲወጡ የእራሳቸውን ስራ መስራት እንዳለባቸው ሲማከሩ የኬሚካል ኢንጂነሩ በሙያቸው የመጠጥ ማምረቻ ላይ መሰማራት እንደሚችሉ ገለጹ።
በዚህ ወቅት ታዲያ ወይዘሮ መንበረ ጋር ከቤት ሽያጭ የተገኘ ገንዘብ መኖሩን የሚያውቁት ባለቤታቸው የኬሚካል መሃንዲሱ ጓደኛቸው እና ባለቤታቸው ንግዱን ሊከውኑ እንደሚችሉ በማሰብ አስተዋወቋቸው።
ከአምስት ወራት የእስር ቆይታ በኋላ የወይዘሮ መንበረ ባለቤት በነጻ ሲፈቱ ወደስራቸው እንዲመለሱ መደረጉን ያስታውሳሉ። ከዚያም ከእስር ጓደኛቸው ጋር በመሆን ለሽርክና ስራ ከወይዘሮ መንበረ ጋር ስምምነት አደረጉ። በወቅቱ ወይዘሮዋ ከመኖሪያ ቤት ሽያጫቸው ያገኙት ገንዘብ በአግባቡ በማስቀመጣቸው በሽርክና ለስራው የመጠጥ ማምረቻ ፋብሪካ ግንባታ ዋነኛ የፋይናንስ ምንጭ መሆን እንደሚችሉ አስመሰከሩ።
በመጀመሪያ ስለመጠጥ ማምረቻ ፋብሪካ የሚያስፈልጉ ጉዳዮች ከተለዩ በኋላ ወይዘሮ መንበረ ለማምረቻ ማሽኖች ግዥ ወደኬንያ እንዲሄዱ ተመረጡ። ኬንያ ከሚገኙ ዘመዶቻቸው ጋር በመሆን የገዟቸውን 150ሺህ ብር የሚያወጡ የተለያዩ ማሽኖችን እና መለዋወጫዎችን በአውሮፕላን አስጭነው በጥቂት ቀናት ተመለሱ።
ወይዘሮ መንበረ ኮተቤ አባባቢ በገዙት ባዶ መሬት ላይ ተጨማሪ ብድር ከዘመድ አዝማድ ወስደው የማምረቻውን መስሪያ ቦታ እንዲዘጋጅ አደረጉ። ማሽኖችም ተተክለው የተለያዩ አልኮል መጠጦች በዘመናዊ ማሽኖች መመረት ጀመረ። በተለይ ጂን፣ የሎሚ እና የተለያየ ቃና ያላቸው አረቄዎች እና አፕሬቲቭ የተሰኘውን መጠጥ አሽገው ማቅረብ ጀመሩ።
በዚህ ወቅት ግን ወይዘሮ መንበረ የፀሐፊነት ስራቸውን ሙሉ በሙሉ አላቋረጡትም ነበር። ይልቁንም የሶስት ወራት ፈቃድ ወስደው የአዲሱ ፋብሪካቸውን የምርት ሽያጭ ስራ መከወን ጀመሩ። በኪዮስኩ እና በየሱፐር ማርኬቱ እንዲሁም በየሆቴሎች በመዘዋወር የፋብሪካውን ምርቶች ማሻሻጡን ተያያዙት። አንዳንዴም ከመጠጦቹ በማስቀመስ ጭምር ገበያውን ሰብረው ለመግባት ሰፊ ጥረት ማድረጋቸውን ያስታውሳሉ።
ከሶስት ወራት የሽያጭ ስራ ቆይታቸው በኋላ አዳዲስ ሰራተኞችን ካለማመዱ በኋላ እርሳቸው ወደፀሐፊነት የቅጥር ስራቸው ተመለሱ። ከስራቸው በሚያገኙት ትርፍ ሰዓትም ድርጅቱ ዘንድ እየመጡ ከባለቤታቸው ጎን ስራውን ይቆጣጠሩ ነበር። በእንዲህ ሁኔታ ለአንድ ዓመት እንደቆዩ ጥሩ ገቢ በመገኘቱ ወይዘሮ መንበረ የላኪነት ንግድ ላይ ለመሳተፍ አቀዱ።
አዳማ ከተማ መጋዘኖችን ተከራይተው ቦሎቄ ምርት ወደውጭ ለመላክ የሚያስችላቸውን ዝግጅት አደረጉ። በወቅቱ ለስራ ደርሰው የነበሩ ሁለት ልጆቻቸውም አብረዋቸው ተሰለፉ። ከነጋዴዎች ላይ የተረከቡትን ቦሎቄም ጥራቱን ጠብቀው በማዘጋጀት በመጀመሪያ ጊዜ አንድ ኮንቴይነር ቦሎቄ መቀመጫውን ፈረንሳይ ላደረገ ገዥ አቀረቡ። በዚህ ስራ በአንድ ጊዜ 200 ሺህ ብር ማትረፍ በመቻላቸው ተበረታተው በላኪነቱ ስራ ቀጠሉበት። በየጊዜውም የሚልኳቸውን ምርቶች በማሳደግ ከቅባት እህሎች ጀምሮ እስከ ጥራጥሬ እና የዝንጅብል ምርቶችን ወደተለያዩ ሀገራት መላካቸውን ያስታውሳሉ።
ወይዘሮ መንበረ የመጠጥ ፋብሪካ ከተቋቋመ አምስት ዓመት ሲሞላው ግን የባህር ትራንዚት የፀሐፊነት ስራቸውን ለቀው በዋናነት የግል ስራዎቻቸው ላይ ማተኮሩን መረጡ። በአስመጪነቱ ስራ ተሰማርተውም ከቻይና የቫዝሊን ምርቶችን ወደማከፋፈሉ ስራ ገቡ። ቫዝሊኑ በበርሜል ገብቶ በጅምላ ለነጋዴዎች የሚሸጥ በመሆኑ ብዙም የሚያዋጣ ትርፍ እንዳላስገኘ ያስታውሳሉ። በመሆኑም የቫዝሊን ንግዱን አቁመው ወደላኪነቱ ስራ አተኮሩ።
የኤክስፖርቱ ስራ ግን በተለያየ ምክንያት ይስተጓጎል ገባ። በርካታ ላኪዎች ጥራት የሌለው ምርት በማቅረብ፣ በኮንትሮባንድ ንግድ በመሳተፍ እና ገበያውን ፍትሃዊ እንዳይሆን በማድረጋቸው ችግር ተፈጠረ። ከዚህ ይባስ ብሎ ደግሞ ወይዘሮ መንበረ በላኪነቱ የሚያግዟቸው ልጆቻቸው ወደውጭ ሀገራት በመሄዳቸው ስራውን ለማቆም ወሰኑ። እናም ለ16 ዓመታት በጥንካሬ ከሰሩበት እና የውጭ ምንዛሬ በማስገባታቸው የዋንጫ ተሸላሚ ከሆኑበት የላኪነት ዘርፍ እራሳቸውን አገለሉ።
ወዲያውም የአልኮል መጠጦች ማምረቻ ፋብሪካው ላይ ሙሉ ትኩረታቸውን አደረጉ። ፋብሪካውን ለማስፋፋት በማሰብ ከስምንት ዓመት በፊት ኮተቤ አካባቢ የሚገኝ ሰፊ መሬት ገዙ። የተለያዩ ግንባታዎችን በማከናወንም ከሁለት ዓመታት በፊት የፋብሪካቸው ማስፋፊያ አደረጉ። የተለያዩ ማሽኖችንም ከባለቤታቸው ጋር በመሆን ከቻይና አስመጥተው በሚሊዮኖች ብር የፈሰሰበትን ማምረቻ በተጠናከረ መልኩ ወደስራ አስገቡ።
የኢታኖል ምርት ከፊንጫ ስኳር ፋብሪካ በመረከብ በቀን ከ9 ሺ እስከ 12 ሺ ሊትር የአልኮል መጠጦችን እና የእሳት አልኮል የማምረት አቅምም ፈጠሩ። በዚህ ስራቸው አምስት ትላልቅ ተሽከርካሪዎችን አሰማርተው ምርቶቻቸውን ማከፋፈሉን ተያያዙት። አንድ ተጨማሪ ቦታ ገዝተውም ያማረ ህንጻ ገንብተው ማከራየት ጀመሩ። በሚሊዮኖች የሚቆጠር ሃብት አደራጅተው ለ50 ቋሚ እና ጊዜያዊ ሰራተኞች የስራ እድል መፍጠር ችለዋል። በማምረቻቸው ውስጥም በሺዎች የሚቆጠሩ የጠርሙስ ማሸጊያዎችን ከእጅ ንክኪ ውጪ የሚያጥቡ ማሽኖችን አስተክለዋል።
ወይዘሮ መንበረ አሁን ላይ ሶስት ልጆቻቸውም ውጭ ሀገር ናቸው። ባለቤታቸውም ጤናቸው በመታወኩ እርሳቸው ሙሉ በሙሉ ድርጅቱን የመቆጣጠር ኃላፊነት ወስደዋል። ሴት ልጅ ሰርታ ማሰራት ትችላለች የሚለውን ሃሳብም በተግባር በማሳየት ከሰራተኞቻቸው ጋር በፍቅር እና በሰላም ጊዜያቸውን እያሳለፉ ይገኛሉ። በስራቸው ላይ ግን አንድ እክል ገጥሟቸዋል። እንደ ሃገር ያለው የኢታኖል ምርት እጥረት መጠጦችን እንዳያመርቱ አግዷቸዋል።
በተለይ በአሁኑ ወቅት ለተከሰተው የኮሮና ቫይረስ መከላከያ የሚሆን የሳኒታይዘር ምርት በማስፈለጉ የኢታኖል አቅርቦቱ ለተወሰኑ የሳኒታይዘር አምራቾች ብቻ እየቀረበ ይገኛል። እርሳቸውም በችግሩ ምክንያት በሽታውን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የሳኒታይዘር ምርት ማዘጋጀት ጀምረው የነበረ ቢሆንም የኢታኖል ምርቱ ቀጣይነት ስላልነበረው በብዛት ማምረት እንዳልቻሉ ይናገራሉ።
በቀጣይ ቀናት ኢታኖሉን ከመንግስት አግኝተው ወደምርት እንደሚገቡ ተስፋ አድርገዋል። ይሁንና እንደሃገር ያለውን ችግር ለመቀነስ ከሸንኮራ ብቻ ሳይሆን ከድንች እና ከሌሎችም ሰብሎች የሚዘጋጅ የኢታኖል ምርት በባለሃብቶች በሰፊው ቢቀርብ ለበርካቶች መፍትሄ እንደሚሆን ይገልጻሉ።
ችግሩን ተቋቁመው የድርጅቱን ቀጣይነት ለማረጋገጥ ስራዎቻቸውን ልጆቻቸው እንዲረከቡ የሚፈልጉት ወይዘሮ መንበረ ውጪ ሃገር የሚገኙ ልጆቻቸው በቀጣይ ማምረቻውን ማስፋፋት አቅም እንዳላቸው እምነት ጥለዋል። በተለይ በስፋት ከሸንኮራ ፋብሪካዎች የሚገኘውን የሞላሰስ ምርት በመጭመቅ የኢታኖል ምርት በመሰብሰብ የፋብሪካውን ስራ ማስፋፋት እንደሚችሉ በልጆቻቸው ላይ ተስፋ ሰንቀዋል። ለቀጣዩ ትውልድ ሊያስተላልፉ ያሰቡት ፋብሪካ ነገ ላይ ደግሞ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰራተኞችን አቅፎ የሚጓዝ ትልቅ ድርጅት እንደሚሆን ወጥነዋል።
ስራ ማለት ለወይዘሮ መንበረ ልክ እንደመዝናኛ ነው። ሁልጊዜም በስራ ላይ ቢሆኑም አይሰለቻቸውምና ቀኑን ሁሉ በስራ ያሳልፋሉ። ሰዎች ስራቸው ላይ ውጤታማ ለመሆን በተለይ በንግዳቸው ትርፋማ ለመሆን በመጀመሪያ የሚከውኑት ጉዳይ ላይ ፍቅር ሊኖራቸው ይገባል የሚል እምነት አላቸው። በዚህ መንገድ ወጣቶች ስለሚሰሩት ስራ ፍላጎት ካላቸው ሁልጊዜም ስራቸውን ለማሳደግ የሚያስችል ብርታትን ማዳበር ይችላሉ። ጥረቱ ሲጠናከር ደግሞ ከእራስ አልፎ ለሌሎችም መትረፍ የሚያስችል ውጤት ማምጣቱ አይቀርምና ጊዜን በአግባቡ ማሳለፉ ከመቼውም በላይ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል የሚለው ደግሞ ምክራቸው ነው። ቸር እንሰንብት!!!
አዲስ ዘመን ሐምሌ 18/2012
ጌትነት ተስፋማርያም