ፈረንጆች ብረትን መቀጥቀጥና ማጣጠፍ እንደ ጋለ ነው የሚል ወርቃማ ይትበሀል አላቸው። ከአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ አሳዛኝ ግድያ በኋላ በመልካው፤ በአየሩ ጮኽው ከሚሰሙ፣ ጎልተው ከሚታዩ ርዕሰ ጉዳዮች አንዱ የሕግ የበላይነት ነው። የዛሬ መጣጥፌ እዚህ ላይ ስለሚያጠነጥን ነው ይትበሃሉን የተዋስሁት። “የሕግ የበላይነት” የአንድ ሀገረ መንግስት የማዕዘን ራስ ነው። ሁሉም የሚመሰረተውና የሚገነባው በእሱ ላይና ዙሪያ ነው። የሕግ የበላይነት እንደ ሀገረ መንግስቱ ማንነት ብያኔው አንጻራዊና የተለያየ ነው። እንደ ትህነግ/ ህወሃት እና ደርግ ላለ ሰው በላ፣ አረመኔያዊ፣ ፈላጭ ቆራጭና አምባገነን አገዛዝ፤ የህግ የበላይነት ከሕግ ፊት ማንኛውም ሰው እኩል ነው የሚለው ንኡድ ጽንሰ ሃሳብ ቦታ የለውም። ዜጎችን ረግጦ የመግዣ፣ የአንድን ቡድን ጥቅምና ፍላጎት ማስከበሪያና ስልጣን ላይ የመቆያ መሳሪያ ነው። ባህሪው እንደ ሀገረ መንግስቱ ግንባታ ሒደትና የሕዝቡ የሥነ ልቦና ውቅር ይለያያል። ከለውጡ ማግስት ጀምሮ እየተለማመድነው፣ እየሞከርነውና ልናዘለቅው የምንፈልገው የሕግ የበላይነት ዜጎች በሕግ ፊት ያለምንም ልዩነት እኩል መሆናቸውን በመርህ ደረጃ የሚቀበል ነው። ዜጎች በማንነታቸው፣ በሃይማኖታቸው፣ በጾታቸው፣ በፖለቲካዊ አመለካከታቸው፣ በመደባቸው ማለትም በሀብት መጠናቸው፣ ወዘተረፈ የተነሳ በሕግ ፊት አድልዎና ልዩነት እንደማይደረግ ዋስትና የሚሰጥ ሥርዓት ነው።
ሆኖም የሕግ የበላይነት በሕግ ፊት ሰዎች ያለ ልዩነት እኩል ሲታዩ በማንነታቸው፣ በሃይማኖታቸው፣ በስልጣናቸው፣ በሀብት መጠናቸው፣ በፖለቲካ አመለካከታቸውና በመደባቸው መድለዎ አለማድረግ ነውና በአንድ ጀምበር ወደ ሙላቱ /governing issue/ ሊመጣም ሆነ ሊረጋገጥ አይቻልም። ከ150 ዓመታት በሚሻገረው የኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ይቅርና በደርግና በቀዳማዊ ትህነግ /ኢህአዴግ የአገዛዝን፣ የፓርቲንንና የአንድ ቡድን የበላይነትን እንጂ የሕግ የበላይነት የማረጋገጥ ፍላጎቱም ሆነ አሰራርና አደረጃጀት አልነበረም። ከእነ ውስንነቱ ሀቀኛው የሕግ የበላይነት የማረጋገጥ ስራ አሀዱ ብሎ የጀመረው ከለውጡ ማግስት ወዲህ ነው ማለት ይቻላል። መሰረቱ ይጣል እንጂ ሒደትን የትውልድ ቅብብሎሽን፣ የተቋማትና የአሰራር ለውጥ እና ግንባታ እንዲሁም የፖለቲካ አመራሩን ቁርጠኝነት የሚጠይቅ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ራስና መገለጫ ስለሆነ ልዩ ትኩረት ይሻል። ለዚህ ነው የነገ ሀገር ተረካቢ ልጆችን ከታች ክፍል ጀምሮ ማስተማር፤ ገለልተኛና ነጻ ፍርድ ቤቶችን፣ የፍትሕ፣ ሚዲያን፣ የሲቭል ማህበረሰብ፣ የሰብዓዊ መብት፣ የእንባ ጠባቂ፣ የሙያ ማህበራት፣ ከፓርቲና ከግል ፍላጎት ይልቅ የሀገርንና የሕዝብ ፍላጎትን የሚያስቀድም አርዓያ መሪ ማብቃትን ይጠይቃል የሚባለው። በሌላ በኩል የሕግ የበላይነት የማስከበርና የማረጋገጥ ጉዳይ ለመንግስት ወይም ለአንድ አካል ብቻ የሚተው አይደለም። ከላይ ያነሳኋቸው ተዋንያንን ጨምሮ፣ መንግስት እና ሕዝብን በተንሰላሰለ አግባብ መስራትን ይጠይቃል። ከእነዚህ ባለድርሻ አካላት የአንዱ ተዋናይ ሙሉ በሙሉ አለመሳተፍ ይቅርና በንቃትና በአንክሮ ኃላፊነቱን አለመወጣት የሚፈለገውን ለውጥ ለማምጣት አዳጋች ያደርገዋል። የሕግ የበላይነት ሰፊ ጽንሰ ሃሳብና በሒደት እየጎለበተ የሚሄድ የሀቀኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የልብ ትርታ ነው። ይሁንና የዴሞክራሲ አባት የሆነችው ግሪክም ሆነች ደቀ መዛሙርቱ እንግሊዝና አሜሪካ ከ400 ዓመታት በኋላ የሕግ የበላይነትን ምልዑ – በኩሌ ላይ አላደረሱትም። ሒደት ነውና።
እስከዚያ ድረስ ግን የኢፌዴሪ መንግስት እጁን አጣጥፎ መቀመጥ አለበት ማለት አይደለም። ባሉት የሕግ የበላይነት ማስፈጸሚያ ተቋማት አማካኝነት ጊዜ የማይሰጡና በጣም አንገብጋቢ የሆኑ የሕግ የበላይነት ጥሰቶችን በጊዜ ማረምና ማረቅ ይጠበቅበታል። ዛሬ ለምንገኝበት ሁለንተናዊ ቀውስ የዳረገን በልበ ሰፊነት ስም የተከተልነው የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ዳተኝነት፣ ከልክ ያለፈ ማባበልና ትዕግስት ነው። ሸኔ ኦነግና ትህነግ እንደ ግብፅ ካሉ ታሪካዊ ጠላቶቻችን ጋር በማበር በተቀናጀና በተናበበ ጥምረት ሲሻቸው በተናጠልና የጥፋት ግንባር በመፍጠር ሕገ መንግስቱን እየጣሱ፣ ሀገረ መንግስቱን በሃይል ለማፍረስ፤ ሀገራችን እንደነ የመን፣ ሶማሊያ፣ ሊቢያና ሶሪያ እንደ ኩይሳ በቁም እንድትፈርስ፤ የጎበዝ አለቃ መፈንጫ፤ ሽብርተኝነትን እየጎነቆሉ፤ የእነ ግብፅ እኩይ ሴራ እውን እንዲሆን፤ የሕግ የበላይነት እንዳይረጋገጥ ያለ የሌለ አቅማቸውን እየተጠቀሙ ነው። ስለሆነም የኢፌዲሪ መንግስት የሕግ የበላይነትን የማስከበር ሕገ መንግስታዊ ኃላፊነት ስላለበት የሸኔ ኦነግንም ሆነ የትህነግን ጉዳይ በጥበብና በማስተዋል የማያዳግም እልባት ሊያበጅለት ይገባል። ከሕግ፣ ከሀገርና ከሕዝብ በላይ አለመሆናቸውን ሕጋዊነትን በተከተለ አግባብ ሊያረጋግጥ ይገባል።
አይናፋሩና ተሽኮርማሚው የሀገራችን የሕግ የበላይነት አይነ ጥላው ተገፎለት ከአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያና እሱን ተከትሎ በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ከተሞች ማንነትን አነጣጥሮ በተፈፀመ ዘግናኝ ግፍ፣ ዘረፋና ውድመት የተነሳ የራሱን የጸጥታ አካል፣ አመራርና በእብሪትና በማን አለብኝነት ወቢ ሲተፋቸው በዚህ የተነሳም ሕዝብ አይነኬ እስከማለት ደርሶ የነበሩትን ሳይቀር ለሕግ ቀርበዋል። ይህ የለውጥ ኃይሉ ውሳኔ ሀገርን ከለየለት ብጥብጥ፣ ቀውስና ትርምስ፤ ሕዝብን ተባብሶ ተጠናክሮ ሊመጣ ካለ ጥቃት የታደገ ነው። ሆኖም ከዚህ ጎን ለጎን “ የሕግ የበላይነት ተጣሰ “ እና “ የሕግ የበላይነት ይከበር “ ለማለት መግፍኤ የሆኑ ምክንያቶችና ሰበቦችን ከምንጫቸው ማድረቅ ይጠበቅበታል። ለሶስቱ ሰኔዎች፣ ለጅግጀጋው ግፍ፣ ጃዋር መሀመድ ተከበብሁ ካለ በኋላ ለተከተለው ጥፋት፣ ወዘተረፈ መነሻ የሆኑ ክፍተቶችን ከስረ ነገራቸው ማጥራት ይጠይቃል። የሕግ የበላይነት ሁከትን፣ ብጥብጥንና ቀውስን ከማስቆም በላይ ነው። የሕግ የበላይነትን ፈተና የሚጥሉ በርካታ ያደሩና ሲንከባለሉ የመጡ ችግሮች አሉ። የፈጠራ ትርክት ምርኮኛ የሆነው ትውልድ መበራከት፤ የመጠላለፍና የመበላላት፣ የደባና ያልሰለጠነው ፖለቲካ፣ አብዛኛው የፖለቲካ ታሪካችን መሰረት ሀገር በቀል ሳይሆን ሶሻሊስታዊ አይዶሎጂ መሆኑ የሃሳብ ብዝኀነትንና ልዩነትን የማያስተናግድ ሆኖ መቆየቱ እና ስራ አጥ የሆኑ የሚሊዮን ወጣቶች ሀገር መሆናችን የሕግ የበላይነትን የሚገዳደሩ አለመግባባቶችና ግጭቶች መላልሰው እንዲጎበኙን ምክንያት ሆነዋል።
ሀገሪቱ የወጣት ምድር እንደ መሆኗ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ወጣቱ የማይተካ ሚና አለው። ይሄን ሚናውን በቅጡ ተገንዝቦ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ማሳተፍ ላይ ውስንነት ስላለብን የሕግ የበላይነትን ለሚጥሱ ኃይሎች መጠቀሚያ እየሆነ ነው። ከለውጡ ማግስት ጀምሩ በተፈጸሙ የሕግ የበላይነት ጥሰቶች ሁሉ ግንባር ቀደም ተሳታፊው ወጣቱ ነው። የዲያስፖራና የሀገር ቤት አክቲቪስት እንዳሻው ቁጭ ብድግ የሚያደርገው ሆኗል። የአርቲስት ሃጫሉን ግድያ ተከትሎ በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ከተሞች በንጹሐን ላይ የተፈፀመ ዘግናኝና አረሜናዊ ግድያ፣ ዘረፋና የሀብት ውድመት የተፈፀመው በእነዚህ ኃይሎች ለወጣቶች በተሰጠ ስምሪትና ተልእኮ ነው። ሆኖም ሁሉም ወጣት የጥፋት ኃይል ተባባሪ ነው ማለትም አይደለም። የጥፋት ኃይሎች መጠቀሚያ የሆነው ወጣት በሙሉ ፈልጎና ወዶ ገብቶበታል ብሎ መደምደምም ይቸግራል። ተስፋውን የተነጠቀ ወጣት አይደለም ማንኛውም ሰው ተስፋ ሲቆርጥ የሚያደርገውን አያውቅም። ይህ ለጥፋቱና ለወንጀሉ ማላከኪያ /ኤክስኪውዝ/ ነው ማለት ግን አይደለም። ፋና ወጊው ምሁር ነጋድራስ ገብረህይወት ባይከዳኝ ከ 104 ዓመት በፊት፣ “መንግስትና የሕዝብ አስተዳደር” በተሰኘው ዘመን ተሻጋሪ የፖለቲካ ኢኮኖሚ መፅሐፋቸው፤ “…የሚበላውንና የሚጠጣውን ያጣ ድሃ የተወለደበትን አገር የሚወድበት ምክንያት ያጣና መንግስቱ ቢበረታ ወይም ቢጠፋ ግድ የለውም። ..” ሲሉ እንደ ነብይ አበክረው ተናግረዋል። የሚያሳዝነው የአጼው፣ የደርግና የቀዳማዊ ትህነግ መንግስታትም ሆነ ልሒቃን ሊሰሙት አልፈለጉም። የነጋድራስን ትንቢት ሰሚና ፈጻሚ ቢገኝ፤ የወጣቱንም ሆነ የቤተሰቡን ህይወት በመቀየር ተስፋው እንዲለመልም፤ የጥፋት ኃይሎች መጠቀሚያ እንዳይሆን ማድረግ ይቻላል። ለእሱ የስራ እድል በመፍጠር፣ የቤተሰቡን ገቢ የሚያሳድጉ የኢኮኖሚ አማራጮችን በማመቻቸት ህልም ያለው ማህበረሰብ መፍጠር ይቻላል። እየሆነ ያለው ግን ከዚህ በተቃራኒው ነው። በብዙ ሚሊዮን የሚገመቱ የዩኒቨርሲቲም ሆኑ የሌሎች የቴክኒክና ሙያ ምሩቃን ዛሬም ስራ የላቸውም። ስራ ያገኙትም ኑሮአቸው ከእጅ ወደ አፍ ከመሆኑ ባሻገር ተስፋ የሚያሰንቅ አይደለም። በቀን ሶስት ጊዜ እንኳ መብላት አልቻሉም። አምስት ሰዓት ላይ ቁርሳቸውንና ምሳቸውን በአንድ ላይ በልተው፤ ውጪ ገዝቶ ለመብላት አቅም ስለማይኖራቸው እዚያው መስሪያ ቤታቸው ከስራ ከመውጣታቸው በፊት 11 ሰዓት ላይ ያንኑ እህል ውሃ የማይል “ራታቸውን “ በልተው ውለው ያድራሉ። ይሄን ድህነት የወለደውን የሲቪል ሰረቫንቱን የኑሮ ዘይቤ
አምስት አስራ አንድ ይሉታል። ከዚህ የከፋው ሳይማር ያስተማራቸውን ቤተሰባቸውን ለመርዳትም ሆነ ለመጦር፤ ቤተሰብ መስርቶ ለመኖር ስለማይችሉ ለተለያዩ የሥነ ልቦና ችግሮች ይዳረጋሉ። ይህን የታዘበ ማህበረሰብ ለትምህርት የነበረው በጎ አመለካከት ይሸረሸራል። ዛሬ የምንገኝበት አሳሳቢ ኡደት ይህ ሆኖ እያለ ኢኮኖሚው ለተከታታይ 10 ዓመታት በሁለት አኃዝ ስለመመንደጉ፤ የሀገሪቱ ጥቅል ሀገራዊ ምርት GDP ሶስት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከሁለት ትሪሊዮን ወደ 3 ነጥብ 2 ትሪሊዮን ማደጉ ይለፈፋል። ምን ቢታለብ ያው በገሌ ያለችውን ውሮ ያስታውሷል። ፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም እንዲህ አይነት የእድገት አለቅላቂ አኃዞችን ባዶ፣ ሀሰተኛ /bogus/ ስታስቲክስ፣ ኮተን ካንዲ /cotton candy / ይሏቸዋል።
እንደ አደራ
በተያዘው የበጀት ዓመት መንግስት ለካፒታል ፕሮጀክቶች ከብድርና እርዳታ ውጭ ከ160 ቢሊዮን ብር በላይ በመመደብ በድምሳሳው ድህነትን ለመቀነስ እንደሚያግዝ ቢያወሳም፤ በቀጥታ የሕዝቡንና የወጣቱን ኑሮ ለመቀየር የተያዘ በጀት ስለመኖሩ ግልፅ አይደለም። የ27 ዓመቱ ሳያንስ ዛሬም ለሌላ 10 ዓመት ላም አለኝ በሰማይ እያለ እንዲጠብቅ የ10 ዓመት መሪ እቅድ ተዘጋጅቶለታል። ይቅርታ ይደረግልኝና መንግስት ከነባራዊ የሀገሪቱ ጉዳይ ጋር ዛሬም የተግባባ አይመስለኝም። ይህን ስል እዚህም እዚያም ለወጣቱ የስራ እድል ለመፍጠር የሚደረጉ ጥረቶችን ዘንግቼ አይደለም። ከችግሩ አንገብጋቢነት አንጻር በቂ እዚህ ግቡ የሚባሉ አይደለም ለማለት እንጂ። ወጣቱ ያለበት ነባራዊ ሁኔታ አይደለም የ10 ዓመት የአንድ ዓመት ሒደትን ለመጠበቅ እንኳ የማያስችል መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል።
ወጣቱ አቋራጭ፣ ፈጣንና ስር ነቀል መፍትሔ /intervention/ የሚያሻው መሆኑ ዛሬም የተዘነጋ ይመስላል። በሰዓታት ልዩነት እያሻቀበ ያለው የኑሮ ውድነት እና በሕገ ወጥ ነጋዴና ደላላ የተተበተበው ገበያ አይደለም ስራ ፈላጊ ወጣቱን ባለ አምስት አኃዝ ደመወዝተኛ የሆነውን” መካከለኛ ገቢ” ያለውን ዜጋ እያማረረ ይገኛል። ሌላው ግጭትን፣ ልዩነትን፣ መጠራጠርን፣ ጎጠኝነትንና ወንዜነትን የሚያበረታታው የፖለቲካ ሥርዓታችንም ሆነ የራስን እድል በራስ መወሰን እስከ መገንጠል የለጠጠውን ሕገ መንግስት መለስ ብሎ የመፈተሽ ጉዳይ አበክሮ ሊታሰብበት ይገባል። የአርቲስት ሃጫሉ ግድያና እሱን ተከትሎ የተፈፀመው ወንጀል የሕግ የበላይነት ከተጠባባቂነት ወደ የሞት ሽረት ጉዳይነትና ወደፊት አምጥቶታል። ከዚህ በኋላ ለአፍታ መዘናጋት አልያም ለምርጫ ሲባል የሚደረግ ማመቻመች ሀገሪቱን ወደማትወጣው የትርምስ አረንቋ ሊዘፍቃት ከመቻሉ ባሻገር በለውጥ ኃይሉ ላይ የተጣለውን እምነት ክፉኛ ይሸረሽረዋል። ሰሞነኛው የሀገራችን አዋዋል የሕግ የበላይነትን የነብር ጅራት አድርጎታል። ከያዙ የማይለቁት።
ሀገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን እንደ ሰሞኑን ካለ ጥፋት ፈጣሪ አብዝቶ ይጠብቅ ! አሜን።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 11, 2012
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን) fenote1971@gmail.com