የትዳር አጋርነታቸው ይበልጥ እንዲተጋገዙ ረድቷቸዋል። በፍቅር እና በአክብሮት የሚያሳልፉት ጊዜም በርካታ መሆኑን ይናገራሉ፤ በዚህም ስራቸውን ከማሳደግ ባለፈ ለሌሎችም መትረፍ የቻለ ዘርፍ ላይ መሳተፍ ችለዋል። የሚያውቁትን ለማሳወቅ እንደማይሰስቱ እና በከፈቱት ድርጅት ውስጥ ሙያቸውን ጭምር እያካፈሉ እንደሚሰሩ ደግሞ የሚያውቋቸው ይመሰክራሉ። ጥንዶቹ ወይዘሮ ሰናይት አብደና እና ኢንጂነር ዮሴፍ መለሰ ይባላሉ።
ወይዘሮ ሰናይት አብደና የተወለዱት በአዲስ አበባ ከተማ ሽሮሜዳ አካባቢ ነው። ሰባት ልጆች ባሉበት ቤት የመጨረሻ ልጅ ናቸው። አባታቸው መምህር ሲሆኑ እናታቸው ደግሞ የቤት እመቤት ናቸው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን እንጦጦ አምባ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል። ሁለተኛ ደረጃን ደግሞ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ቀጥለዋል።
ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት በኋላ የመምህርነት ስልጠና ወስደው ህጻናት መዋያ ውስጥ መምህር ሆኑ። ፈረንሳይ ለጋሲዮን አካባቢ በሚገኝ ራፊዲየም ዩዝ አካዳሚ በተሰኘ መዋዕለ ህጻናት ትምህርት ቤትም በ1997 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ ሲቀጠሩ በ200 ብር የወር ደመወዝ እንደነበር በፈገግታ ያስታውሱታል። በመዋዕለ ህጻናቱም ለሰባት ዓመት ሲሰሩ እስከ ርዕሰ መምህርነት ደረጃ ደርሰው እንደነበር አይዘነጉትም።
በመምህርነት ስራቸው ወቅት ግን የቢሮ ፀሐፊነት ሙያን ተምረው ነበርና በመጨረሻ ትምህርት ቤቱን ለቀው በቴክኒክና ሙያ ኤጀንሲ ስር በፀሐፊነት ተቀጠሩ። በኤጀንሲው በሚሰሩበት ወቅት ደግሞ ሶስተኛ ልጃቸውን መገላገላቸውን ያስታውሳሉ። እናም ልጅ ለማሳደግ በሚል ሶስት ዓመት ከሰሩበት ተቋም ተሰናብተው በቤት ውስጥ ጊዜያቸውን ማሳለፉን ተያያዙት።
ለሁለት ዓመታት ልጆችን በመንከባከብ ቤት በሚያሳልፉበት ወቅት ግን የግል ስራ ጀምረው መንቀሳቀስ እንዳለባቸው ማሰብ ጀምረዋል። እናም መስራት ስለሚኖርባቸው ነገር ከባለቤታቸው ጋር መምከር ጀመሩ።
ባለቤታቸው ኢንጂነር ዮሴፍ መለሰ ይባላሉ። በኬሚካል ኢንጂነርነት ሙያቸው ኢትዮ ፕላስቲክ ድርጅት ውስጥ ለስድስት ዓመታት አገልግለዋል። በመቀጠልም የኢንዱስትሪ እና ማዕድን ልማት በተሰኘ ተቋም ስር እና ዲኤች ገዳ ፋብሪካ ላይ በተለያዩ ቦታዎች ከአስር ዓመታት በላይ መስራታቸውን ይናገራሉ። ለአንድ ዓመት ደግሞ ብሩንዲ ላይ የፋበሪካ ተከላ ላይ ተሳትፈዋል።
አቶ ዮሴፍ የኬሚካል ኢንጂነሪንግ እውቀታቸውን አዋጭ ወደሆነ የግል ስራ ለመቀየር ሃሳብ ነበራቸው። እናም ባለቤታቸው ወይዘሮ ሰናይት ምን እንስራ የሚል ሃሳብ ሲያመጡ ተመካከሩና የሳሙናና እና የጽዳት ምርቶችን እያዘጋጁ ቢያቀርቡ ውጤታማ መሆን እንደሚችሉ ተስማሙ።
ጥንዶቹ ከዚህ በኋላ ወደኋላ ማለት አልፈለጉም። በመሆኑም የተወሰኑ ኬሚካሎችን ገዙና ቤታቸው ውስጥ ፈሳሽ ሳሙናዎችን ለመስራት ሙከራ አደረጉ። ሙከራቸው ደግሞ ጥሩ ስለነበር ለሚያውቋቸው ሰዎች ሞክሩት እያሉ ሰጧቸው፡፡ ተቀባይነትም አገኙ። በርካቶችም ማምረት ሲጀምሩ ገዥ በመሆን እንደሚያግዟቸው አበረታቷቸው።
ባለትዳሮቹም አዲስ አበባ 18 በተባለ አካባቢ አነስተኛ አንድ ክፍል የቆርቆሮ ቤት ተከራይተው ፈሳሽ ሳሙና ለማምረት የሚያስችላቸውን ፈቃድ አወጡ። በትንሿ ቤት ውስጥም ኬሚካሎችን እያቀላቀሉ ፈሳሽ ሳሙናውን በ2008 ዓ.ም ላይ ማምረት ጀመሩ።
በወቅቱ መነሻ ካፒታላቸው 56 ሺህ ብር እንደነበረ የሚናገሩት ጥንዶቹ አንድ ሰራተኛ ቀጥረው እንደነበር ያስታውሳሉ። ምርታቸውንም ደረጃ መዳቢዎች ወስደው ጥራቱን ካስፈተሹ በኋላ ሳሙናው መመረት ሲጀምር ግን እንገዛችኋለን ያሉ ሰዎች ሁሉ ድምጻቸውን በማጥፋታቸው የገበያ ችግር ገጠማቸው።
ገበያው ሲጠፋ ደግሞ የገንዘብ እጥረትም በመከሰቱ ትልቅ ችግር ውስጥ ገቡ። ፈሳሽ ሳሙናውንም ከገበያ በሚገዟቸው የፕላስቲክ ማሸጊያዎች ካኖሩ በኋላ ወደተለያዩ ሱቆች በመዘዋወር ገበያ ማፈላለጉንም
ተያያዙት። አንድ የሽያጭ ባለሙያም ቀጥረው የገበያ አማራጫቸውን ለማስፋት ጥረት ማድረግ ጀመሩ። የቤት መኪናቸውንም ጭምር በመጠቀም ምርቶቻቸው ወደማከፋፈሉ ስራ ተሰማሩ። ቀስ በቀስም ደንበኞች እያፈሩ ስራቸውን ፈር ማስያዝ ቻሉ።
ገበያውም እየተገኘ ምርቶች በብዛት መሸጥ ሲጀምሩ ግን በቤት መኪና ብቻ ማመላለሱ አዋጭ ስላልሆነ አቅማቸውን አጠናክረው የጭነት ተሽከርካሪ ገዙ። ከዚህ በኋላ <<ፒናክል>> ብለው የሰየሙትን ማምረቻቸውን ሳሙናዎች በተመቻቸ ሁናቴ በተሽከርካሪ ለገበያ ማቅረብ ጀመሩ። ተጨማሪ ሰራተኞችንም ቀጥረው ስራቸውን አስፋፉ። በዓመታቸውም ከፈሳሽ ሳሙና በተጨማሪ በረኪና፤ የመስታወት ማጽጃ እና የመጨዳጃ ቤት ማጽጃ / ዲቶል/ ወደ ማምረቱም ተሸጋገሩ።
ጥሩ ገበያ በነበረበት ወቅት በዓመት እስከ 200 ሺህ ብር ድረስ ያገኙ እንደነበር የሚያስታውሱት ጥንዶቹ፤ በሚያገኙት ገንዘብ የተለያዩ ማሽኖችን በመግዛት በእጅ ብቻ ይሰራ የነበረውን የምርት ደረጃ ወደማሽነሪ አሸጋገሩ። በተለይ ኬሚካል የማደባለቁን ስራ እና ወደማሸጊያዎች የመሙላቱን ተግባር በማሽን መከወን በመቻላቸው የስራው ፍጥነት ከማደጉ በላይ ምርቶቻቸውን በብዛት ማቅረብ ቻሉ። የበረኪና ምርታቸውን ማሸግ ስራ በሀገር ውስጥ በተሰራ ማሽን መከወን በመቻላቸው ጥራቱንም ብቻ ሳይሆን አቅርቦቱንም ማሳደግ አስቻላቸው።
ምርቶቻቸውንም ለክፍለ ሃገር ጅምላ ተረካቢዎች፣ ለሸማች ማህበራት እና ለተለያዩ ሱፐር ማርኬቶች በማቅረብም ተጨማሪ የጭነት ተሽከርካሪ ገዙ። ስራው እየተስፋፋ ሲመጣ ግን በኪራይ የሚሰሩበት ግቢ ሊበቃቸው አልቻለም። የቤቱን ግማሽ ክፍል ለኬሚካል ማከማቻ ሲያደርጉ ግማሹን ደግሞ ለማምረቻ እና ምርት ማከማቻ አድርገውት በጠባብ ቦታ ላይ መፈናፈን አቃታቸው። ይህም ችግር የኋላ የኋላ አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል በመገንዘባቸው ስራቸው እንዳይቋረጥ በሚል የተከራዩትን ቦታ አድሰው ለማዘመን ሞከሩ።
ይሁንና የሚያገኙት ገንዘብ ለተሻለ የምርት ጥራት የሚያግዙ ስራዎች ላይ የሚያውሉት እኒሁ ጥንዶች ቤቱን አስፋፍተው ለማደስ የሚያስችል ገንዘብ እጃቸው ላይ አልነበረም። ገንዘብ ባይኖራቸውም ግን መስዋዕትነት በመክፈል የመኖሪያ ቤታቸውን ሸጠው የተከራዩበት የስራ ቦታቸውን ወደማደሱ ስራ ገቡ። ደረጃውን በጠበቀ መልኩ በብሎኬት አስፋፍተው የኪራይ ቤቱን ካሰሩ በኋላ በመጠኑም ቢሆን ማጽጃ ፈሳሾቹን በስፋት ለማምረት እድል አገኙ።
የመስሪያ ቦታ እጥረቱ በየጊዜው እየፈተናቸው መሆኑ ያሳሰባቸው ጥንዶቹ ግን ዘላቂ መፍትሄ ለማግኘት በሚል ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ላይ በየጊዜው ጥያቄ ማቅረባቸው አልቀረም። ይሁንና ሰሚ ጆሮ ሳያገኙ ዓመታትን አሳለፉ፡፡
በክፍለ ከተማቸው ወረዳ 9 ስር በየጊዜው ምርጥ አምራች ድርጅት በሚል እንደሚሸለሙ የሚናገሩት ጥንዶቹ ፤ ይሁንና መስሪያ ቦታ ሲባል ግን የሚያውቃቸው ሁሉ መልስ እንደማይሰጣቸው ያስረዳሉ። በዚህም ምክንያት በዓመትም እስከ 250 ሺህ ብር ኪራይ ለመስሪያ ቦታ ያወጣሉ።
በዚህ ምክንያት አሁንም ድረስ ኬሚካሎችን እና ምርቶችን በተጣበበ ቦታ በማስቀመጣቸው መስራት እየቻሉ ምርት ለማሳደግም ሆነ ሰራተኛ ቁጥር ለማብዛት አለመቻላቸው የሚያስቆጫቸው ጉዳይ ሆኗል።
ከዚህ ባለፈ ግን የግብዓት እጥረቱም ቢሆን ሌላው ፈታኛ መሆኑን ያነሳሉ። ይሁንና ጥንዶቹ ችግር ከፊታቸው ሲጋረጥባቸው በጋራ በመመካከር እና በመተጋገዝ አሁን ያሉበት መድረሳቸውን ይናገራሉ።
አሁን ላይ ሰባት አይነት ምርቶች እያመረቱ የሚገኙት ባለትዳሮቹ ሶስት የኬሚካል ማቀላቀያዎችን /ሚክሰሮችን/ በመጠቀም በአንድ ሺፍት ብቻ 10ሺህ ሊትር ፈሳሽ ሳሙናዎችን የማቅረብ አቅም ገንብተዋል። ገበያው ከቀንም በቀን እስከ 30ሺህ ሊትር ሳሙና ማቅረብም ይችላሉ። አምስት ሊትሩን ፈሳሽ የልብስ ሳሙና በ135 ብር የሚያቀርቡት ጥንዶቹ የእጅ ፈሳሽ ሳሙያ ደግሞ በ27 ብር እንዲሁም 500 ሚሊ ሊትር ዲቶሉን ደግሞ በ50 ብር ለገበያ ያቀርባሉ።
ሰባት አይነት የጽዳት ምርቶችን የሚያቀርበው የባለትዳሮቹ ድርጅት ከብዙ ፈተናዎቸ ጋር እየታገለ በስሩ 14 ቋሚ ሰራተኞችን ያሉት ሲሆን፤ ከስድስት እስከ ስምንት የሚደርሱ ጊዜያዊ ሰራተኞችን ስራ በሚበዛበት ወቅት ያሰማራል። በማምረቻው ስር አንድ ኤክስፐርት እና የጥራት ደረጃዎችን የሚፈትሽ ባለሙያም አላቸው። ሰራተኞችን በማሰልጠን ጭምር ወደስራ የሚያስገቡ በመሆናቸው አሁን ላይ ስራውን በሚገባ የለመዱ ባለሙያዎችን ማፍራታቸው ደግሞ ለእነርሱ ኩራት ነው።
ከስራቸው ጎን ባለትዳሮቹ ለትምህርቱን ትኩረት ሰጥተዋል። በዚህም ወይዘሮ ሰናይት የማኔጅመንት ዲግሪያቸውን ያገኙ ሲሆን፤ ኢንጂነር ዮሴፍ ደግሞ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና ከደቡብ አፍሪካ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም በማኔጅመንት እና ቢዝነስ አድሚኒስተሬሽን ሁለተኛ ዲግሪ የደረሰ የትምህርት ጊዜ አሳልፈዋል። ይህም ስራቸውን በጋራ ለማቃነት በእጅጉ እንደረዳቸው ይመሰክራሉ።
ጥረት ዋነኛው የስራችን ባህሪ ነው የሚሉት ወይዘሮ ሰናይት እና ኢንጂነር ዮሴፍ፤ በቀጣይ ደግሞ ብድር ካገኙ አምራች ኢንዱስትሪውን በሰፊው በመገንባት በርካታ ሰራተኞችን ለመቅጠር አስበዋል። ጥንዶቹ በየጊዜው ምርቶቻቸውን ለማሳደግ ከሚያደርጉት ጥረት አንጻር የሳኒታይዘር ምርት ለማዘጋጀትም ሙከራ አድርገው ነበር።
የኬሚካል ኢንጂነር የሆኑት ኢንጂነር ዮሴፍ ከባለቤታቸው ጋር በመሆን ሳኒታይዘሩን በጥሩ ሁኔታ ለሙከራ ማምረት ቢችሉም እስካሁን ግን ለማምረት የሚሆን ፍቃድ የሚሰጣቸው አካል አለማግኘታቸውን ይገልጻሉ። ለዚሁ ጉዳይ የሚመለከታቸው ቢሮዎች ዘንድ ቢያቀኑ ፍቃድ መስጠት አቁመናል የሚል ምላሽ በማግኘታቸው ጉዳዩን በአጽንኦት እየተከታተሉት መሆኑን ያስረዳሉ። ፍቃድ እንዳገኙ ሳኒታይዘር በማምረት በኮሮና ምክንያት የሚመጣውን ችግር ለመከላከል የአቅማቸው ለማበርከት ጥረት እንደሚያደርጉ ጥንዶቹ ተስፋ አድርገዋል።
በቤት ውስጥ ሙከራ የተጀመረው የሳሙና እና ማጽጃ ምርቶች ማዘጋጃ ድርጅታቸው አሁን ላይ ሃብት መፍጠር መቻሉ ትልቅ ደስታ የሚሰጣቸው ጥንዶቹ ከማምረቻው ባለፈም የማማከር ስራ የሚያከናውን ድርጅትም አላቸው። ኢንጂነር ዮሴፍ የሚመሩትም ሰኒዮ ቢዝነስ ፒኤልሲ የተባለ አማካሪ ተቋም አላቸው።
በማኔጅመንት ዘርፍ ለተለያዩ ተቋማት እና ግለሰቦች ከማማከር ባለፈ የተለያዩ ሙያዊ ስልጠናዎችን ይሰጣሉ። በአማካሪው ድርጅት ስር ሁለት ኤክስፐርቶች ቀጥረዋል። ማማከሩ እና ስልጠናው በሚኖርበት ወቅት ደግሞ የተለያዩ ባለሙያዎችን ቀጥረው ያሰማራሉ። ሁልጊዜም ስራ ላይ የሚገኙት ጥንዶቹ ነገን በተሻለ የኢንቨስተርነት ደረጃ ደርሰው ለሀገርም የተሻለ አበርክቶ እንደሚያመጡ እምነታቸው ነው።
ስራ ማለት ለእነርሱ ልክ እንደ ልጅ ነው። ልጅ ይወለዳል እየተንከባከቡትም ያድጋል፤ ስራም ማለት ከሃሳቡ ጀምሮ እስከ እድገቱ ድረስ ካልተንከባከቡት ፍሬ አያፈራም። በመሆኑም ማንኛውም ወጣት ነገውን የተሻለ ለማድረግ ዛሬ ላይ ስራውን እያሻሻለ እና ጥረት አክሎበት ሊንቀሳቀስ ይገባል የሚል እምነት አላቸው። በተለይ ወጣቶች አልባሌ ቦታ እየዋሉ ቤተሰብን ከማስቸገር ይልቅ አቅማቸው የሚችለውን ዘርፍ መርጠው ከእራሳቸው አልፈው ለሌችም የሚተርፍ ገቢ የሚያመጣ ስራ ላይ መሰማራት ይጠበቅባቸዋል። እንደሀገር አመረቂ ውጤት ለማምጣት ጊዜን በአገባቡ መጠቀም ያስፈልጋል የሚለው ደግሞ ምክራቸው ነው። ቸር እንሰንብት!!
አዲስ ዘመን ሐምሌ 11, 2012
በጌትነት ተስፋማርያም