ኢንጅነር ታከለ ኡማ በአዲስአበባ ከተማ አስተዳደር በምክትል ከንቲባ ማዕረግ ሲመደቡ ጀምሮ የዕለት ውሏቸው በሩጫ የተሞላ ነው:: ከተማዋን የሸፈናትን ድህነት ለመግፈፍ እንደባተሉ ነው:: ይኸን ጥረታቸውን የሚያደንቁና የሚያግዙ እጅግ በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች የመኖራቸውን ያህል፤ የረገጡትን ሁሉ እየተከተሉ ሲነቅፉ የሚውሉም የትየለሌ ናቸው:: አንዳንዶቹ የእሳቸውን እንቅፋት በማሳየትና ነጥብ በማስቆጠር የጥላቻ ፖለቲካን ለመዝራት ላባቸውን የሚረጩ ናቸው::
ሰሞኑን በአዲስአበባ መሬት ወረራ ነግሷል ተባለ:: ለአንድ ብሔር እየተመረጠ መሬት ይታደላል የሚል ወሬ ናኘ:: ቀጠለናም በርካታ የኮንዶሚኒየም ቤቶች እንዲሁ ለተመረጡ የአንድ ብሔር ሰዎች እየተሰጠ መሆኑን ማህበራዊ ሚዲያው ያራግብ ገባ:: ከእነታከለ ወገን ዝምታው ረጅም መሆን ብቻ ሳይሆን ለትችቶቹ መልሱ እንደቴሌዋ ሴትዮ «ጥሪ አይቀበልም» መሰለ::
ያው እንደምናውቀው አዲስአበባ ከተማ ለዜጎቿ አንገት ማስገቢያ ነፍጋ የኖረች ከተማ ናት:: በ2005 ዓ.ም በአዲስአበባ ከተማ በተካሄደው ድጋሚ ምዝገባ ከ900 ሺ በላይ ነዋሪ የኮንዶሚኒየም ቤት ፈላጊነት ተመዝግቧል:: ዛሬ ይኸ ቁጥር በብዙ እጥፍ መጨመሩ አያጠያይቅም:: እንደቀድሞ «ቦታ ተመርቼ፤ ቤት ሠርቼ…፤ወልጄ ከብጄ እኖራለሁ» የሚል ተስፋ ለአብዛኛው ወጣት የቅንጦት ጥያቄ መሰሎ መታየት ከጀመረ ቆየ:: ለምን ቢባል የመጀመሪያው ጉዳይ ቦታ (መሬት) ማግኘት የሚቀመስ ባለመሆኑ ነው:: ሌላው ደግሞ በአንዳች ተአምር ቦታው ቢገኝ እንኳን በዋጋ ንረት ጣሪያ የነካውን የኮንስትራክሽን ማቴሪያል ወጪ ችሎ ቤት መስራት እጅግ ከባድ የመሆኑ ጉዳይ ነው::
ቤት ኪራይም ቢሆን በተለይ ለወርሃዊ ደመወዝተኛ ከግማሽ በላይ ገቢውን የሚወስድ መሆኑ የኑሮ መናጋትን የሚያስከትል አድርጎታል:: እስቲ ይታያህ፤ መሀል አራት ኪሎ አንድ ባለአንድ መኝታ ቤት ለመከራየት ከ8 እስከ 9 ሺ ብር ትጠየቃለህ:: ከፍ ይበልልኝ ብለህ ባለሁለት መኝታ ቤት ብትጠይቅ ገንዘብህን ይጭነቀው እንጂ ከ13 እስከ 15 ሺ ብር በወር ኪራይ እና በትንሹ የሦስት ወር ቅድመ ክፍያ እንድትከፍል ይነገርሃል:: ወፍራም ደመወዝተኛ ነህ ቢባል እንኳን ይህን ያህል ብር ለቤት ኪራይ አውጥተህ በምን ወሩን ትዘልቃለህ? እናም ጥቂት የማይባሉ ወጣቶች ዛሬም የወላጆቻቸው ጡረተኛ ለመሆን የተገደዱት ወደው አይምሰልህ::
ዛሬም በተወለዱበት አልጋ ለመተኛት የተገደዱና የነገን ብሩህ ቀን ለማየት በተስፋ የፋፉ ወጣቶች ቁጥር ቀላል አለመሆኑን መንገር ለቀባሪ ማርዳት እንዳይሆንብኝ እሰጋለሁ:: እናም ትውልዱ እጅግ ከከፋ ተስፋ አልባነት የመለሰው የመንግሥት የኮንዶሚኒየም ፕሮግራም ነበር ቢባል አልተጋነነም::
ወደ መነሻችን እንመለስ፤ ባለፈው ሐሙስ ዕለት ጠ/ ሚኒስትር ዐብይ በተገኙበት የሸገር ዳቦ ማምረቻ ተመረቀ:: ኢንጅነር ታከለ ኡማም እንደወትሮው ምረቃውን አደናንቀው በሥራው የተሳተፉትን በማህበራዊ ሚዲያ (በፌስቡክ) ገጻቸው አመሰገኑ:: ጥቂት የማይባሉ ሰዎች የሰጧቸው አስተያየቶች በአመዛኙ በመሬት ወረራውና በኮንዶሚኒየም እደላ ወሬው ላይ የተንጠለጠሉ ነበሩ:: ጥቂት የማይባሉ ሰዎች በሰሙት መረጃ መቶ በመቶ እርግጠኛ ሆነው አስተያየት የሰጡ ናቸው:: ለምን እርግጠኛ ሊሆኑ ቻሉ? የሚለው ጥያቄ ራሱን ችሎ በስፋት የሚያነጋግር ነው::
በዚህ ጸሐፊ ዕይታ፤ አንዱና ዋናው ምክንያት በአሉባልታም ይሁን በሌላ መንገድ ለሚነሱ ወሬዎችና የሕዝብ ቅሬታዎች በከተማ አስተዳደሩ በኩል ፈጣን
ምላሽ አለመስጠቱ ቀዳሚው ምክንያት ነው ብዬ አስባለሁ:: ለማስተባበልና ወይንም ለመልስ ከመሮጥ የተሻለው መንገድ መረጃን ፈጣን በሆነ መልክ የሚመግብ አጥቂ የኮሙኒኬሽን ስትራቴጂ ቢኖር ነበር::
ሌላውና ሁለተኛው ምክንያት የ13ኛው ዙር ኮንዶሚኒየም ቤቶች እና የ2ኛ ዙር የ40 በ60 ቤቶች ከአንድ ዓመት በላይ ለባለዕድለኞች መተላለፍ አለመቻሉና በመካከል ግልጽ መረጃ በመጥፋቱ ለተጨማሪ ሐሜትና አሉባልታ ተጋልጦ የመቆየቱ ጉዳይ ነው::
በወቅቱ ምን ያህል ቤቶች ነበር በዕጣ የተላለፉት? የካቲት 27 ቀን 2011 ዓ.ም 51 ሺህ 229 የጋራ መኖሪያ ቤቶች (ኮንዶሚኒየም ቤቶች) ዕጣ ማውጣት ሥነ ሥርዓት ተከናውኗል::
ዕጣ ከወጣባቸው ቤቶች ውስጥም 32 ሺህ 653 ቤቶች የ20/80 ቤቶች ሲሆኑ፣ ቀሪዎቹ 18 ሺህ 576 ደግሞ የ40/60 ቤቶች ናቸው። በዚህም መሠረት የ20/80 ፕሮግራም ኮንዶሚኒየም ቤቶች ውስጥ 1 ሺህ 248 ስቲዲዮ፣ 18 ሺህ 823 ባለ አንድ መኝታ፣ 7 ሺህ 127 ባለ ሁለት መኝታ እና 5 ሺህ 455 ቤቶች ደግሞ ባለ ሦስት መኝታ ክፍሎች ናቸው። በእነዚህ የ20/80 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ ውስጥ የሚካተቱት በ1997 ዓ.ም ተመዝግበው በ2005 ዓ.ም በነባር መደብ የተመዘገቡና በ2005 ዓ.ም የአዲስ ባለ ሦስት መኝታ ክፍል ተመዝጋቢዎች መሆናቸው መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል::
ከዚሁ ጋር ተያይዞ ከአንድ ዓመት በፊት በተለይ በኮዬ ፈጪ ኮንዶሚኒየም ዕጣ ከወጣባቸው ቤቶች ጋር ተያይዞ በእነጃዋር መሐመድ አንቀሳቃሽነት በአዲስአበባ ነዋሪ ላይ ዛቻ መፈጸሙ፣ በሌላ በኩል የአዲስአበባ ከተማ አስተዳደር ለጉዳዩ እልባት ሳይሰጥ በዝምታ ተሸብቦ መቆየቱ ተጨማሪ ምክንያት ሆኖ ነዋሪውን ላልተገባ ጥርጣሬና ስጋት አጋልጦት ስለመቆየቱ በስፋት የተነገረ ነው::
እናም በእነዚህ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ የሚነሱ ወሬዎች ወዲያውኑ በሕዝብ ውስጥ ተአማኒነት የሚያገኙት ቀድሞውንም እምነትን የሚሸረሽሩ እና መግባባት ላይ ያልተደረሰባቸው ወይንም ግልጽነት ያልተያዘባቸው ጉዳዮች በመኖራቸው ነው:: በሕዝብ ውስጥ ጥርጣሬ በመንገሱ ነው:: እናም እንዲህ ዓይነቱን ችግሮች መቅረፍ የሚቻለው ዕለት በዕለት መረጃ ለሕዝብ በመስጠትና
ግልጽነትን በማስፈን ብቻ ነው:: ሥራችን ይናገራል ብሎ መተው ወይንም የሚነገረውን መናቅ የማታ ማታ ከበድ ያለ ዋጋ ሊያስከፍል ይችላል::
ይህ ርዕሰ ጉዳይ ሌላ አንድ ጉዳይ አስታወሰኝ:: በምርጫ 97 በምርጫ ዋዜማ ነው፤ ህወሓት/ኢህአዴግ የግሉን ፕሬስ አብዝቶ ይንቅና ያጣጥል ነበር:: የግሉ ፕሬስም በአመዛኙ የኢህአዴግን ሽንፈት ቀድሞ ሟርት በሚባል ደረጃ ያስተጋባ ነበር:: ህወሓት/ኢህአዴግ ግን «የእኛ መሠረት አርሶአደሩ ነው:: ከ85 በመቶ በላይ አርሶአደር አሳምሮ ይመርጠናል:: 15 በመቶ ገደማ ከተሜው መረጠ፣ አልመረጠም አያሳስበንም» በሚል አፋቸውን ሞልተው የሚናገሩ ከፍተኛ አመራሮች ነበሩት:: እና ምን ሆነ? የተናቀ ያስረግዛል የሚባለው ብሂል በኢህአዴግ ላይ ደረሰ::
በወቅቱ እነአቶ በረከት ስምኦንን የመሰለ ከፍተኛ አመራሮች ከእንቅልፋቸው ተቀስቅሰው የሽንፈት ዜና ተረዱ:: ይህ ትንሽ ነው የተባለው 15 በመቶ ከተሜ ገጠሩን ጭምር የማንቀሳቀስ አቅም እንዳለው የታወቀው በምርጫ 97 ውጤት ሆነ:: «ገተር ፕረስ» እየተባሉ ሲዘለፉ የኖሩት ጋዜጦችና መጽሔቶች ተጽዕኖ መፍጠር እንደሚችሉ የታወቀው ተቃዋሚዎች በገጠር ሳይቀር በዝረራ ጭምር ለማሸነፍ ሲበቁ ነው::
እናም የሕዝብ ግንኙነት ሥራ ወይንም የኮሙኒኬሽን ሙያ በሚገባ መጠቀም እና አለመጠቀም በራሱ ከሕዝብ ጋር የሚኖርን የግንኙነት ደረጃ ይወስናል:: ሚዲያ (ሶሻል ሚዲያውን ጨምሮ) ትልቅ አቅም ነው፣ አራተኛ መንግሥት ነው የሚባለው ለዚህ ነው:: ሕዝብን በክፉም ሆነ በደጉ የማሳመን አቅሙ ከፍተኛ ነው::
እርግጥ ነው፤ ኢንጅነር ታከለ ኡማ እጅግ ዘግይቶም ቢሆን የተናፈሰውን ወሬ አስተባብለዋል:: ሐሙስ ሰኔ 18 ቀን 2012 ዓ.ም ማምሻውን በጽ/ቤታቸው የፌስቡክ ገጽ ተከታዩን መረጃ አስነብበው ነበር::
«የከተማ አስተዳደሩ በተለያዩ ክልሎች ለሚገኙ የመንግሥት ሠራተኞች የጋራ መኖሪያ ቤቶችን እየሰጠ ነው በሚል እየተሰራጨ ያለው መረጃ ፍፁም ከእውነት የራቀ ነው።
የከተማ አስተዳደሩ እያስገነባቸው የሚገኙ የጋራ መኖሪያ ቤቶች በሕጋዊ መንገድ ተመዝግበው ለሚገኙ ነዋሪዎች እንጂ ለተለያዩ ክልል ሠራተኞችም ይሁን ግለሰቦች የሚሰጥበት አሠራር የለውም።
በ13ኛው ዙር ዕጣ የወጣላቸውና የወሰን ችግር የሌለባቸው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለነዋሪዎች እየተላለፉ ሲሆን ከትናንት በስቲያ ጀምሮ የቁልፍ ርክክብ እየተካሄደ ሲሆን በሁለት ሳምንት ውስጥም የቁልፍ ርክክብ የሚጠናቀቅ ይሆናል።
ከዚህ ውጪ በየትኛውም መንገድ የዕጣ ማውጣት ሂደት የተከናወነ አለመሆኑን ለማሳወቅ እንወዳለን።የከተማ አስተዳደሩ በተለያዩ ክልሎች ለሚገኙ የመንግሥት ሠራተኞች የጋራ መኖሪያ ቤቶችን እየሰጠ ነው በሚል እየተሰራጨ ያለው መረጃ ፍፁም ከእውነት የራቀ ነው።
የዚህ ዓይነቱ ፍፁም የሀሰት መረጃዎች የከተማ አስተዳደሩን በተለይ በግዙፍ ፕሮጀክቶች አፈፃፀም ላይ እያሳየ ያለውን እመርታ ለማጠልሸትና ጥርጣሬ ለመፍጠር እንደሆነ እንረዳለን። በመሆኑም ኅብረተሰባችን ይህንን ተረድቶ ራሱን ከሀሰት መረጃዎች እንዲያርቅ አደራ ለማለት እንወዳለን» ይላል::
ይኸ ዓይነቱ ማስተባበያ ግን ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ ዓይነት ነው:: ቀደም ሲልም እንደተገለጽኩት በኮሙኒኬሽን ሙያ ውስጥ ተከላካይ መሆን ከባድ ዋጋ የሚያስከፍል ነው:: ኮሙኒኬሽን ሁልጊዜ አጥቂ
እንዲሆን ምሁራን ይመክራሉ:: ቀድሞ መረጃ የሚሰጥ፣ ቀድሞ ተደራሽ ሲሆን ውጤቱ ያማረ ይሆናል:: ከተቦካ፣ ከተጋገረ፣ ብዙ ቦታ ከተዳረሰ በኋላ ማስተባበያ መስጠት (የቱንም ያህል እውነት ቢያዝ) ሙሉ በሙሉ የተባለውን ማጥፋት፣ ወደቀድሞ ቦታ መመለስ አዳጋች ይሆናል::
በሌላ በኩል አንድ የተነገረ ወሬ ስለተስተባበለ ብቻ ሕዝብ ትክክል ነው ብሎ ይወስዳል ተብሎ አይገመትም:: ሕዝብ አዋቂ ነው፤ ያመዛዝናል:: ሲያሳምነው ይቀበላል:: በሌላ በኩል አንድ ወሬ ሳይስተባበል ዝም ስለተባለ ብቻም ወሬው ትክክል ነው ማለት አያስደፍርም:: ግን ትልቁ ችግር ታመነም፣ አልታመነም የወሬው መስፋፋት በኅብረተሰብ ውስጥ ውዥንብር መፍጠሩ አይቀሬ ነው:: አንዳንዴ ውዥንብሩ ያልተገባ ውጤት ላይ ሊያደርስ መቻሉ አስከፊ ውጤቱ ነው::
እናም የኮሙኒኬሽን መንገዱ ምን ይሁን የሚለው ሰፋ ተደርጎ መታየት ያለበት ርዕሰ ጉዳይ ይመስለኛል:: ጉዳዩ በአዲስአበባ ብቻ ሳይሆን እንደሀገርም ሰፊ ችግር ያለበት ነው:: በርካታ የመንግሥት መ/ቤቶች በመገናኛ ብዙኃን የመረጃ ነፃነት አዋጁ ድንጋጌ መሠረት መረጃ የመስጠት ግዴታ የተጣለባቸው ቢሆንም ብዙዎቹ በሰበብ አስባቡ ወገቤን የሚሉ መሆናቸው ተደጋግሞ የተነገረ ነው:: አንዳንድ የሕዝብ ግንኙነት ሰዎች ባለሙያ አለመሆናቸው ዘርፉን ጭምር ጎድቶታል:: አንዳንዶች መረጃ ለመስጠት ፍላጎት ቢኖራቸውም ቅሉ ከገዛ ድርጅታቸው መረጃ የማግኘት አቅማቸው ደካማ በመሆኑ ለመተባበር ሲቸገሩ ይታያል:: ይህ ችግር ደረጃው ይለያይ እንጂ እስከላይኛው የመንግሥት መዋቅር ድረስ የሚንጸባረቅ ነው:: ችግሩ በከፍተኛ አመራር ደረጃ ያሉትን ሰዎችን የሚያካትት መሆኑ ከበድ ያደርገዋል::
አሁን አሁን ጠ/ሚኒስትሩን እና ጽ/ቤታቸውን ጨምሮ ከፍተኛ አመራሮችም በግል በማህበራዊ ሚዲያ የየተቋማቸውን መረጃዎች እንዲለቁ እየተደረገ መሆኑ በአዎንታ የሚታይ መልካም ጅምር ነው:: ባለፉት አንድ ዓመት በግሌ የጠ/ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ፣ የኢንጅነር ታከለ ኡማ የፌስቡክ እና የቲውተር ተሳትፎ ማየት መቻሌና ከትኩስ መረጃቸውም መቋደሴ ለአርአያነታቸው ተገቢውን ዋጋ እንድሰጥ አድርጎኛል:: በዚህም አጋጣሚ አመሰግናቸዋለሁ:: ይህም ሆኖ ግን ቁንጽል ተደርገው የሚለቀቁ መረጃዎች ግን ብዙውን ጊዜ ለመደበኛ ሚዲያው ሰፋ አድርጎ እንዲሰራው ቲፕ ከመስጠት ያለፈ የሚጠቅሙ የማይሆንበት ጊዜ አለ::
በዚህ ጊዜ የሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎች እና የሕዝብ ግንኙነት ሰዎች በሚዲያ ሰዎች ይጨናነቃሉ:: እነዚህ ጥያቄዎች በወቅቱ ምላሽ ማግኘት ባልቻሉ ቁጥር በሕዝብ ውስጥ ሆን ብለውም ይሁን በቅንነት የሚሰራጩ አሉባልታዎች አየሩን ሊሞሉት የግድ ይሆናል::
መንግሥትም ሥራውን በወቅቱ ካለመስራቱ ጋር ተያይዞ በየዕለቱ ለሚፈበረኩ ወሬዎች «ይኸ ወሬ ሐሰተኛ ነው፣ በሬ ወለደ ነው፣ በልማታችን የቀኑ ኃይሎች ሴራ ነው…» እያለ መልስ በመስጠትና በማስረዳት የተከላካይነት ሚና እንዲጫወት ይገደዳል:: እንዲህ ዓይነቱ የኮሙኒኬሽን ስትራቴጂ ከኪሳራ በስተቀር ትርፍ የለውም:: እናም ተቋሞቻችን በአጥቂነት ላይ የተመሰረተ የኮሙኒኬሽን ስትራቴጂ እንደባህርያቸው ቀርጸው በፍጥነት ወደመተግበር ቢሸጋገሩ ሕዝባዊ ቅቡልነታቸውን ለማሳደግ በብዙ መልኩ ይረዳቸዋል::
አዲስ ዘመን ሰኔ 20/2012
ፍሬው አበበ