ድሬ ያችን ሰዓት!
ያችን ሌሊት እንደምን አድርጎ ይርሳት? ከላይ ሰማይ እንደራበው ጅብ ሲያጓራ፣ ሲስገመገም፤ የመብረቅ ብልጭታ ሲያስጓራ፤ የሰዎቹ ዋይታና እሪታ በአዕምሮው ውስጥ እየተመላለሰ እንደምን ሊረሳት ይችላል? ያች ‹‹የበርሃ ንግስት›› አይታና ሰምታ በማታውቀው ማዕበል ስትናወጥ ለዚያውም በእኩለ ሌሊት ማንን ድረሱልኝ ብላ ትማፀን?
አዎ! አቶ በያን ይህን ሁሉ አስከፊ ክስተት በዓይኑ በብረቱ ተመልክቷል። ልጅ ከእናቱ ባል ከሚስቱ በሞት ሲነጠቅ፤ ሰው ከነንብረቱ በደራሽ ጎርፍ ሲፈናቀል ሰዎች ዕድሜ ልካቸውን ያፈሩትን አንጡራ ሀብታቸውን በደቂቃ ውስጥ ተነጥቀው ያጡ የነጡ ድሃ ሆነው ሲገኙ አይቶ ልቡ በኀዘን ተሰብሯል። ስድስት ቤተሰቦቹንም አጥቶ በኀዘን ተቆራምዷል። በዕለተ ቅዳሜ ሐምሌ 29 ቀን 1998 ዓ.ም ከሌሊቱ 8 ሰዓት ተኩል ድሬዳዋን ባጥለቀለቃት ጎርፍ።
በዚያን ነፍስ ውጭ ነፍስ ግቢ ግብግብ ውስጥ ታዲያ ሀብት ንብረት ሲወሰድባቸው ሰዎች ዛፍ ላይ እየተንጠላጠሉ ነብሳቸውን ማዳናቸውን ሲመለከት ግን የፈጣሪን ምህረት ያስታውሳል። ሰው ዛፍን አሳደገ፣ ዛፍ ደግሞ የሰው ሕይወትን ታደገ፤ ይህ አጋጣሚ አስተሳሰቡን ሁሉ ለወጠው። ከዚህን ጊዜ ወዲህ ዛፎች በመትከል አሻራውን ለማኖር ወሰነ፤ ይኸው ሥራዬ ብሎ እስከዛሬ ድረስ ከችግኝና ዛፎች ጋር ተወዳጅቶ ይኖራል። የወደፊት ትልሙም ይህ ነው የዛሬው ‹‹እንዲህም ይኖራል እንግዳችሁ›› አቶ በያን ተሰማ።
የቀቤናው ልጅ
በያን ተሰማ ይባላል። የተወለደው በአሁኑ አጠራር ጉራጌ ዞን በሚባለው ቀቤና አካባቢ ነው። አሁን በድሬዳዋ 06 ቀበሌ ነዋሪ ነው። ስድስት ልጆች አሉት። በትምህርት ዓለም ብዙም አልገፋበትም፤ በእርግጥ ለመማርም ዕድሉንም አላገኘም። ከስድስተኛ ክፍል በላይ አልዘለቀም። ዛሬ ወደሚኖርባት ድሬዳዋ በ1974 ዓ.ም መጨረሻዎቹ ላይ የአስራ ሦስት ዓመት ታዳጊ ሆኖ ነው የመጣው።
በወቅቱ በርካታ ሰዎች ከአካባቢው ሄድ ብለው ጥሪት አፍርተው ቤተሰብ ሲያግዙ ይመለከት ስለነበር እርሱም በአጋጣሚ ከሰዎች ጋር ሄዶ ድሬዳዋ ከተመ። ሊስትሮ ሥራ እየሰራ ራሱን ለማስተዳደር ሞከረ። ከሊስትሮ ወደ ‹‹ጀብሎ››ንግድና እና ሌሎች ሥራዎች ተሸጋረ። በቂ ገንዘብ ባላገኘም ጊዜ አልፎ አልፎም በረንዳ ያድር ነበር። በርካታ ውጣ ውረዶችን እያለፈ በሂደት ወደ ንግዱ ገባ። በተለይም ከጅቡቲ ድሬዳዋ ባቡር ይመላለስ ስለነበር ‹‹ኮንትሮባንድ›› ዕቃዎችን ለመነገድ ቀልቡ ተነሳሳ። ልባሽ ጨርቆችንና ሌሎችንም በመነገድ ሕይወቱን ይመራ ጀመረ። አንዳንዴ ገንዘብ አጠር ሲለውም በእምነት ዱቤ እየተቀበለ ሸጦ ለውጦ ገንዘብ መቋጠር ጀመረ።
ነፍስን የታደገች ዛፍ
ሐምሌ 29 ቀን 1998 ዓ.ም በዕለተ ቅዳሜ ከሌሊቱ 8፡30 ድንገተኛ ጎርፍ ድሬዳዋን አጥለቀለቃት። ከከዚራ አካባቢ የተነሳው ጎርፍ ያገኘውን ሁሉ እየደረመሰና እያፈረሰ ድሬዳዋን አጥለቀለቀ። እርሱም ያኔ በዓይኑ ያየውን ለማመን ይከብደዋል። በርካታ ሰዎች እርቃናቸውን ይወጡ ነበር። ያልቻለው ደግሞ ከጎርፍ ጋር ግብ ግብ ገጥሞ ነብሱን ለማዳን ይታገል ጀመር። በዚህ ወቅት አንድ ሌላ ወንድሙ ከእርሱ ሰፈር ራቅ ብሎ ነበር ያለው። ታዲያ ይህ ወንድሙና ሁለት ልጆቹ ጎርፉን ያመለጡት ዛፍ ላይ ወጥተው ነበር። ያኔ! ከጎርፍ የዳነው አንደኛው ልጅ በአሁኑ ወቅት ድሬዳዋ ሲሚንቶ ፋብሪካ ውስጥ መካኒክ ነው።
ችግሩ ካለፈ በኋላ ብዙ ሰዎች ዛፍ ላይ እየወጡ ራሳቸውን ማዳናቸውን ሰማ። በአላህ ሥራም በእጅጉ ተገረምኩ ይላል። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ታዲያ አዕምሮው አንድ ነገር ለመሥራት ወሰነ። አላህ ፈቃዱ ከሆነ ዛፍ መትከል ሥራዬ ይሆናል ሲል ወሰነ። የአጋጣሚ ነገር ሆኖ
ታዲያ በ2000 ዓ.ም ‹‹ሁለት ዛፍ በደጄ›› በሚል መፈክር እንደ አገር አዋጅ ሆኖ ሰዎች ሁሉ ዛፍ ተካይ ሆኑ።
እርሱም በወቅቱ የድሬዳዋ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ከሆነው ሁሴን አብዱረሃማን የሚባል ሰው ዘንድ ሄዶ 2000 ችግኞች ይሰጠኝ ብሎ ጠየቀ። ይህ የተቀደሰ ሃሳብ ነው በሚል በፈገግታ ጭምር ዛፎቹን ሰጡት። እርሱም ድሬዳዋን ጎርፍ ያጎረፈባትን እና የቆሻሻ ክምር መጣያ ስፍራ የነበረና ማንም ሰው የማይጠቀምበትን ስፍራ ለችግኝ መትከያ ምቹ ነው ሲል ወሰነ። የጎርፍ መሄጃ ስለነበርም እከለከላለሁ የሚል ፍርሃት አላደረበትም። በአንድ ጀንበር ሁለት ሺህ ችግኞችን ተክሎ ጨረሰ።
ታዲያ እነዚህን ችግኞችን ለማሳደግ ፍዳ ማየት ጀመረ። ድሬዳዋ ከውሃ እጥረቷ ጋር ተያይዞ ለችግኞቹ ውሃ ማፈላለጉ፤ መኮትኮቱና መንከባከቡ ፈተና ሆነ። ግን ዓላማ ነበርና ቀጠለበት። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ከዛፍ ጋር ተወዳጀ። ለአረንጓዴ ልማት ‹‹የቁም እስረኛ›› ሆንኩ ይላል። በአሁኑ ወቅት ሁለት ሄክታር ተኩል መሬት ላይ 21ሺ ቋሚ ዛፎችን ተክሏል። ይህን ቦታ የጎርፍ መሄጃ
ስለነበር ከፈጣሪ እንጂ ከሰው ፈቃድ አልጠየኩበትም ይላል። ታዲያ ሰዎችም ቢሆን ስፍራው የተለየ ጠቀሜታ ስለማይሰጣቸው የከለከለው አካል አልነበረም።
በእርሱ አጠራር ከቦታው ጥበትና ከመሬቱ አቀማመጥ ብሎም ከዛፎቹ መጠጋጋት የተነሳ ‹‹ትንሿን አማዞን›› መስርቻለሁ ብሎ ያምናል። በቀጣዮቹ ጥቂት ዓመታትም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞችን የመትከል እቅድ ሰንቋል። ከዛሬ አስር ዓመታት በፊት የበያን እጅ የተከላቸው ችግኞች ዛሬ ከዛፍነት አልፈው ጫካ ሆነዋል። ዋንዛ፣ ዝግባ፣ጃካራንዳ፣ የውጭ አገር ዛፎች፣ በብዛት ይገኛሉ። በጥብቅ ሁኔታ መጠበቅ ያለባቸው ዛፎች ውስጥ ስድስቱ ከጫካው ውስጥ ይገኛሉ። ችግኝ ሲፈልግ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን፤ ግብርና ጽሕፈት ቤት ያግዙታል። እርሱም የራሱን የችግኝ ጣቢያ አቋቁሟል። መንገድ ላይ ዘር ካገኘም ይለቅምና ወደ ችግኝነት ይቀይራል።
‹‹አበደ አሉኝ››
አቶ በያን አዳሩም ውሎውም ሁሉ ነገሩ ዛፎቹ ዘንድ በመሆኑ ለቤተሰቡ የሚሠጠው ብዙ ጊዜ የለውም።
ጥቂቶችን ከማገዝ አገርን ማገዝ ይበልጥብኛል ሲል ከራሱ ቤተሰብ በላይ ለማህበረሰብና ለአገር ማሰብ ይጠቅመኛል ሲል የቤተሰቡ ሕይወት ላይ ብቻ ከማተኮር ሰፋ አድርጎ ማሰብ ጀመረ። ሁሉም ነገሩ ችግኝ መትከልና መንከባከብ ሆነ።
ሰዎች ሀሜት ጀመሩ። ‹‹ቤተሰቤም ጭምር ይህ ሰው አበደ፣ ወደ ሕክምና ይወሰድ፤ አዕምሮውን እየሳተ ነው›› ሲሉ ግራ በመጋባት የጤናው ሁኔታ ያሳስባቸው ጀመር። በያን ግን ጤነኛ ነበር። እርሱን ጤና የሚነሳው በረሀዋን ንግስት በአንድ ሌሊት እንዳልነበር ያደረገውን ጎርፍ ሲያስብ ነው። ያ! ክፉ ቀን ጥቁር ጠባሳ ጥሎበት አልፏና ዳግም ማየት አይፈልም። ከፈጣሪ ጋር የተቻለውን ሁሉ ሠርቶ ኃላፊነቱን መወጣት ይፈልጋል። በእርግጥ አበደ ቢባል ብዙም ላይገርም ይችላል። በሁኔታው ግራ የተጋባው የመጀመሪያ ልጁም ትምህርት አቋርጦ የቤተሰቡን ሕይወት ለመታደግ ሥራ መጀመሩንም ያስታውሳል።
ታዲያ ያኔ ይህ ሰውዬ አበደ የሚሉ ሰዎች አሁን ጫካውን ሲያዩት ያበድነው እኛ ወይስ እርሱ ነው ሲሉ ራሳቸውን መጠየቅ መጀመራቸውን ይናገራል። ቤተሰቦቹ ያ ሁሉ ልፋቱ ለምን እንደሆነ አሁን ተረድተውታል፤ እንዲያውም ያግዙታል። ባለፈው ዓመት ደግሞ አዳማ ላይ አገር አቀፍ ሽልማት ወስዷል። በወቅቱ ለሥራው የሚያግዙት የተለያዩ ግብዓቶችንና የምስክር ወረቀት ተሰጥቶታል። በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርና ከተለያዩ ጽሕፈት ቤቶችም የተለያዩ 18 የምስክር ወረቀቶችም ተበርክተውለታል።
ክብረ ወሰን ለመስበር
በዓለም ላይ ብዙ ዛፎችን በመትከል ሪኮርድ የተያዘው የኬንያ ዜጋ በሆነችው ዋንጋሪ ማታይ ነው። ታዲያ በያን ይህን ክብረ ወሰን በግማሽ ሚሊዮን ዛፎችን በማሻሻል በዓለም ክብረ ወሰን ስሙን ለማፃፍና የኢትዮጵያን ስም ከፍ አድርጎ የማስጠራት እቅድ አለው። በዘንድሮ ዓመት 240ሺ ችግኞች በግቢ ውስጥ አፍልቷል። በሚቀጥለው ዓመት አንድ ሚሊዮን ለማፍላት ዝግጅት አጠናቋል። በሚቀጥሉት አራት ዓመታት ውስጥ 3ነጥብ5 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል ክብረወሰኑን ለመቆናጠጥ ወስኗል።
በአሁኑ ወቅት በሁለት ተኩል ሄክታር ላይ ያበቀለውን ጫካ ‹‹ኢሊናም›› ወይንም ኢትዮጵያ ለምለም ናት የሚል ሥያሜ ሰጥቶታል። ታዲያ በ2000 ዓ.ም ችግኝ መትከል ሲጀምር የወለዳትን ልጅ ስያሜ ልጅም ‹‹ኢሊናም›› የሚል ስም አውጥቶላታል። በአጋጣሚ ሆኖ ‹‹ኢሊናም›› በቀቤና አካባቢ አነጋገር እንደ ሰብል የሚል ትርጉም አለው።
በያን ዛሬም እንቅልፍ የለውም። ‹‹ዛፍ ትከሉ ከፍቷል ዘመኑ›› እያለም ዞሮ ይለፍፋል። በጉራጊኛ፣ ኦሮምኛ፣ አማርኛ፣ ትግርኛ፣ ሱማሊኛ፣ ወላይትኛ፣ በሀደርኛ፣ እና በመሳሰሉት 18 ቋንዎችም ዛፍ ትከሉ እያለ ሰዎችን እየዞረ ይቀሰቅሳል። ታዲያ በአንድ ወቅት ይህ ሰው አበደ ይሉት የነበሩት አሁን ፈገግ ብለው እውነቱን ነው ዛፍ እንትከል እያሉ የአረንጓዴ ልማትን እየተቀላቀሉ ነው። እርሱም ይህን ለውጥ ሲመለከት ልቡ በሃሴት ትሞላለች።
አግዙኝ
አቶ በያን ተሰማ ዛፍ መትከል የሕይወቱ አካል አድርጎ ለመሄድ ወስኗል፣ የሚጠበቅበትን እያደረገ ነው። ታዲያ መንግሥት ጥቂት ነገር እንዲያግዘኝ እፈልጋለሁ ይላል። በኢትዮጵያ ማንኛውም ቦታ ሄዶ ዛፍ ሲተክል ቢኖር ቅር እንደማይለው ይናገራል። የአረንጓዴ ልማት ሥራው ብዙ ፈተናዎች ተጋርጠውበታል። ድሬዳዋ የውሃ እጥረት አለ። የከርሰ ምድር ውሃን አውጥቶ ለመጠቀም ደግሞ አቅም የለውም። ታዲያ በዚህ ላይ የሚያግዘኝ አካል እፈልጋለሁ ባይ ነው። ለዛፍ መትከያ የሚሆን ቦታ እጥረት ገጥሞታል። በተለይም አንድ ቋሚ የሆነ እና ሰፊ ቦታ ቢሰጠኝ ለሥራው ቅልጥፍ፣ ለመከታትልና ለመቆጣጠር ያስችለኛል ይላል። መንግሥትም ከምንም በላይ በዚህ ጉዳይ ቢተባበረኝና ባለሙያዎች በእውቀት ቢያግዙኝ ሲልም ይማፀናል።ታታሪው የአረንጓዴ ልማት አርበኛ በያን ተሰማ።
አዲስ ዘመን ሰኔ 20/2012
ክፍለዮሐንስ አንበርብር