ከማረሚያ ቤት እስከ ሆቴል እና ዩኒቨርሲቲዎች ጓዳ በመግባት በርካቶችን የመመገብ ዕድል አግኝተዋል። በወጣትነታቸው የገቡበት የንግድ ሥራ ጠንካራ አድርጓቸዋል፡፡
ከደሴ ጦሳ ተራራ ሥር በተመሠረተው ህይወታቸው ሌሊት ተነስተው ሲውተረተሩ ይውላሉ፤ ማታም ከሥራ መልስ የቤተሰብ ሃላፊነቱ አይቀሬ ነው። ይህን ብርታት የተመለከቱ ደግሞ እንስቷ ለአካባቢያቸው ወጣቶች ሁሉ አርአያ የሚሆን የሥራ ተምሳሌት ናቸው በማለት ያሞካሿቸዋል። ባለታሪካችን ወይሮ ፍሬህይወት እሸቱ ይባላሉ።
ወይዘሮ ፍሬህይወት እሸቱ የተወለዱት በአማራ ክልል ከደሴ ከተማ 60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው አምባሰል ወረዳ ልዩ ስሙ እጓ ተክለሐይማኖት በተባለ ቦታ በ1974 ዓ.ም ነው። ለወላጆቻቸው የመጀመሪያ ልጅ ሲሆኑ ከእርሳቸው በታች ደግሞ አንድ ወንድም አላቸው። ቤተሰባቸው በንግድ ሥራ የሚተዳደሩ በመሆናቸው ገና በልጅነት እድሜያቸው ነበር የቤተሰባቸውን ሥራ እያዩ ወደ ንግድ ሥራ የተሳቡት።
በተለይ እናታቸው ጠንካራ ነጋዴ እንደነበሩ ወይዘሮ ፍሬህይወት ያስታውሳሉ። የተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎችን እና የቤት ውስጥ መገልገያዎችን ለመነገድ በአብዛኛው እናት ወደገበያ ስለሚሄዱ የቤት ውስጥ ሥራው ደግሞ ለሴት ልጃቸው ነበር ሃላፊነቱ የሚተወው። በተለይ የወይዘሮ ፍሬህይወት ታናሽ ወንድም በእግሩ መዳህ ሲጀምር የበኩር ልጃቸው ፍሬህይወትም የወንድሟ ተንከባካቢ እና የቤት ውስጥ ሥራዎችን ከዋኝ ዋነኛ ባለሙያ እንደነበሩ ያስታውሳሉ።
ለቀለም ትምህርት ልዩ ፍላጎት የነበራቸው ወይዘሮ ፍሬህይወት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን እዚያው ደሴ ከተማ ላይ በሚገኘው እቴጌ መነን ትምህርት ቤት ከአንደኛ እስከ አራተኛ ክፍል ተምረዋል። ከዚያም እስከ ስምንተኛ ክፍል ድረስ ያለውን ደግሞ ቅዳሜ ገበያ በተሰኘው ትምህርት ቤት ተከታትለዋል።
በወቅቱ ከትምህርት መልስ በቀጥታ ወደቤት በማምራት እንደሚያሳልፉ የሚያስታውሱት የደሴዋ ነጋዴ ለጨዋታ የሚሆን እና ከመንደር እኩያ ህፃናት ጋር ለማሳለፍ የሚሆን ጊዜ እንዳልነበራቸው ይናገራሉ። ይልቁንም ከቤት ሥራቸው ባለፈ አልፎ አልፎም ቢሆን ወደቤተሰባቸው የንግድ ሱቅ በመሄድ አንዳንድ ሥራዎችን ለማገዝ ይጥሩ ነበር።
እንዲያ እንዲያ እያሉ የመጀመሪያ ደረጃ የአስኳላ ጊዜያቸውን አጠናቀው ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ደግሞ ሆጤ የተሰኘው ትምህርት ቤት ገቡ። በወቅቱ ለሒሳብ ትምህርት ያላቸው ፍላጎት ከፍተኛ እንደነበር የሚያስታውሱት ወይዘሮ ፍሬህይወት ምናልባት ለዚህ ዝንባሌያቸው የቤተሰባቸው የንግድ ሥራ ከፍተኛ ተጽዕኖ አድርጎባቸው ሊሆን እንደሚችል ይናገራሉ።
ከ12ኛ ክፍል በኋላ በቀጥታ ያመሩት ወደወይዘሮ ስህን ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ተቋም ነበር። በዚያም የአካውንቲንግ ትምህርታቸውን መከታተል ጀመሩ። ትምህርት ላይ እያሉ ደግሞ ገና በአፍላው የወጣትነት እድሜያቸው ወደትዳር ህይወት ገቡ።
የትዳር አጋራቸው ደግሞ በተለያዩ የኤሌክትሪክ ማሽን ምርት ሥራዎች ላይ የተሰማሩ ባለሙያ ነበሩና ወይዘሮ ፍሬህይወት የእርሳቸውን ንግድ ፍላጎት እና የባለቤታቸውን ሙያ አጣምረው አንድ ሥራ መሥራት እንዳለባቸው አሰቡ። አስበውም አልቀሩ ባለቤታቸውን አማክረው የዳቦ መጋገሪያ ማሽን እንዲያዘጋጁላቸው በማድረግ የዳቦ ቤት ንግድ ሥራ ላይ ተሰማሩ።
በወቅቱ የ19 ዓመት ወጣት የነበሩት እንስት ከባለቤታቸው ጋር ተጋግዘው በከፈቱት የንግድ ሥራ ሁለት ሠራተኞችን ቀጠሩ። ሠራተኞቹ በወቅቱ 102 ብር የተገዛውን 50 ኪሎግራም ዱቄት አቡክተው ሲጋግሩ ወይዘሮ ፍሬህይወት ደግሞ በየሱቁ እየዞሩ ዳቦውን ማከፋፈል ጀመሩ።
በ1990ዎቹ መጀመሪያዎች ላይ አንዱን ዳቦ በ25 ሳንቲም በየሱቁ የሚያከፋፍሉት ነጋዴ ማታ ላይ ደግሞ በየሱቁ እና በየሱፐርማርኬቱ እየዞሩ የቀጣይ ቀን የገበያ ፍላጎት መጠየቅ እና የጠዋት ሂሳብ የመሰብሰብ ሥራ ላይ ነበር የሚጠመዱት።
ይህ የሥራ ሂደት ግን እጅግ አድካሚ እና አሰልቺ ቢሆንም ጥንካሬን ተላብሰው በየዕለቱ የሚያሳልፏትን እያንዳንዷን ጊዜ ለቁም ነገር ያውሉ እንደነበር አይዘነጓትም። በዚህም ጥንካሬያቸው ከትርፋቸው የሚያገኟትን ገንዘብ በመያዝ በሳምንት የአንድ መቶ ብር ዕቁብ ይጥሉ እንደነበር በፈገግታ ያስታውሱታል።
እራሳቸውን ለማሻሻል በጀመሩት የዳቦ ንግድ ለሁለት ዓመታት እንደሠሩ ግን ደሴ ላይ አንድ በንግድ ግንኙነት/ በኔትወርክ/ አማካኝነት የሚሠራ ንግድ እንዳለ ይሰማሉ። ሥራው ሰዓት እና ኤሌክትሮኒክስ ምርቶችን ከሌሎች በመረከብ ማሻሻጥ እና ከበታቻቸው ደግሞ ተጨማሪ የሽያጭ ባለሙያዎችን ካመጡ ገቢያቸው ከፍ የሚልበት አይነት ንግድ ነበር። እናም ትምህርታቸውን አጠናቀው ነበርና ስለ ሥራው በቂ ሥልጠና ለማግኘት በሚል 10 ሺህ ብር ከፍለው ወደኬንያ የሚያመሩበት ዕድል ተፈጠረ።
ኬንያ የነበረው ሥልጠና ግን አጠቃላይ ህይወታቸውን የቀየረ እና ስለንግድ አሠራር በቂ ግንዛቤ ያስጨበጣቸው እንደነበር አይዘነጉትም። በኬንያ ለ21 ቀናት ሲቆዩ ቀድሞ የሚሠሩትን ንግድ እንዴት ባለመልኩ አከናውነው ውጤታማ መሆን እንደሚችሉ በተግባር የተደገፈ እውቀት ሸምተው ነበር። እናም ወደሀገራቸው ሲመለሱ ምንም ነገር ቢሆን እችላለሁ የሚል የሥራ መንፈስን አጠናክረው ነበር የተመለሱት።
ከስልጠናው በኋላም ወይዘሮ ፍሬህይወት የንግድ ፈቃድ አውጥተው የምግብ አቅርቦት ሥራ ላይ መሰማራት የሚያስችላቸውን ዝግጅት አደረጉ። እናም ደሴ ሪፈራል ሆስፒታል ላይ ጨረታ አሸንፈው ምግብ የማቅረብ ሥራ ጀመሩ። ለሠራተኞች እና ለታካሚዎች የተለያየ ምግብ አሠርተው በማቅረብ ጥሩ ተቀባይነት ማግኘት እንደቻሉ በተመሳሳይ ጊዜ ደግሞ አጣዬ ሆስፒታል ላይ የምግብ ማቅረብ ሥራን አሸንፈው መሳተፍ ጀመሩ።
እናም ከደሴ አጣዬ ድረስ እየተጓዙ እየተቆጣጠሩ ያሠሩ እንደነበር አይዘነጉትም። ለአንድ ዓመት አጣዬ ሆስፒታል ላይ ከሠሩ በኋላ ደሴ ማረሚያ ቤት ደግሞ ለታራሚዎች የሚቀርብ ምግብ ለመሥራት ተስማምተው ወደሥራ ገቡ። በወቅቱ የማረሚያ ቤቱ ሥራ እጅግ ሰፊ ስለነበር በቦታው ብቻ 40 ሠራተኞችን ቀጥረው ነበር።
በየቀኑም ለአንድ ሺህ አምስት መቶ ሰዎች በማረሚያ ቤቱ ውስጥ ቁርስ ምሳ እና እራት ምግብ በማቅረብ የሥራ ቅልጥፍናቸውን በሰፊው አሳዩ። በተለይ እራሳቸው ለምግድ ዝግጅቱ የሚሆኑ አትክልቶችን እና የተለያዩ ግብዓቶችን ከገዙ በኋላ ከሠራተኞቻቸው ጋር አብረው በመሥራት የሚያቀርቡበት ጊዜ በርካታ በመሆኑ የበርካታ ሰዎችን የሥራ መንፈስ በማነቃቃት ረገድ ጉልህ ድርሻ እንደነበራቸው አይዘነጉትም።
ከማረሚያ ቤቱ ምገባ ሥራ ጠቀም ያለ ገቢ ያገኙት ወይዘሮ ፍሬህይወት ሰፋ ያለገበያ ለማግኘት በሚል ወደአዲስ አበባ መምጣታቸውን ያስታውሳሉ። በተለይ 22 ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የአንድ ኮሌጅ የካፌ አገልግሎትን ይዘው ለመሥራት ቢሞክሩም እንዳሰቡት አዋጭ ስላልሆነላቸው ተመልሰው ወደደሴ ማምራታቸውን ይናገራሉ። ይሁንና በቀጣይ ጊዜ ወደመዲናዋ ተመልሰው እንደሚመጡ ተስፋ አድርገዋል።
በደሴ ከተማ ላይ የምግብ ማቅረብ ሥራውን አጠናክረው በመቀጠል በተጓዳኝነት ደግሞ ጃኖ የተሰኘ ካፌና ሬስቶራንስ ቤት ተከራይተው ይሠሩ እንደነበር ይናገራሉ። የተለያዩ ምግቦችን ለተጠቃሚዎች በማቅረብ ንግዱን እያጧጧፉት ሳለ ግን አከራዮቻቸው ንግዱን ሊቀሟቸው አሰቡ። ለሁለት ዓመታት እንደሠሩ የንግድ ቦታውን ለቀው እንዲወጡ ከአከራዮቻቸው ተነገራቸው።
ወይዘሮ ፍሬህይወትም ገንዘብ ልጨምር አሊያም የምትፈልጉት ምንድነው ብለው ቢጠይቁም ሰሚ ጆሮ በማጣታቸው ካላመዱት የንግድ ቦታቸው እንዲለቁ ተደረገ። ይሁንና አከራዮቻቸው ልናድሰው ነው ብለው ያስለቀቋቸው ቤት ውስጥ እራሳቸው ገብተው በተሟሟቀ ቤት ውስጥ ሥራውን ቀጠሉት።
ወይዘሮ ፍሬህይወት በዚህ ቢናደዱም ተስፋቆርጠው ግን አልቀሩም፤ ይልቁንም የምግብ አቅርቦት ጨረታዎችን በማሸነፍ በተለያዩ ቦታዎች መሥራታቸውን ቀጠሉ። በተለያዩ ቦታዎች ምግብ በማቅረባቸውም ሥራውን በሚገባ የሚያውቁት የንግድ ሰው ቦሩ ሜዳ ሆስፒታል ለሠራተኞች እና ለታካሚዎች የሚሆን ምግብ በየዕለቱ አሠርተው ያቀርቡ ነበር።
በዚህ ጥረት ላይ እያሉ ግን የኮሮና ቫይረስ በሽታ ወደኢትዮጵያ ገባ። ቦሩ ሜዳ ሆስፒታልም ለማቆያነት አገልግሎት በመዋሉ ምግብ የሚሠሩላቸው ተቀጣሪዎቻቸው ወደሥራ እንደማይመጡ አሳወቋቸው።
ይህ ወቅት ለወይዘሮ ፍሬህይወት እጅግ ከባድ እንደነበር ይናገራሉ። ምክንያቱም ሥራው እያለ ሠራተኛ ከማጣት በላይ የሚያስጨንቅ ጉዳይ የለምና። በመሆኑም እራሳቸው እና ቤተሰቦቻቸውን ሰባስበው ምግብ በማብሰል ለሆስፒታሉ ማቅረብ ጀመሩ። በዚህ ተግባራቸው አማካኝነት እየተጠነቀቁም ቢሆን መሥራት ይቻላል የሚለውን ትምህርት ከሥራ ገበታ ለራቁ ሠራተኞቻቸውን በተግባር አሳዩ። እንዲህ እንዲህ እያሉ ጥቂት ባለሙያዎችን ጨማምረው የጀመሩትን የምግብ አቅርቦት ሥራ አስቀጠሉ።
በአሁኑ ወትቅም በየቀኑ 200 ሰዎችን የሚመግብ ሥራ ላይ ናቸው። በተለያዩ ቦታዎች የምግብ አቅርቦት ሥራ በሚኖርበት ወቅት በአንድ ጊዜ ከስልሳ እና ከሰባ ሠራተኞች በላይ እንደሚያሰማሩ የሚናገሩት የንግድ ሰው፤ በየጊዜው ምን መሥራት አለብኝ በማለት አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን የመፍጠር ፍላጎት እንዳላቸው ይናገራሉ።
የተለያዩ የሥራ መስኮች ላይ ተሰማርቼ ንግድን አይቼዋለሁ የሚሉት ወይዘሮ ፍሬህይወት፤ በአንድ ወቅት የስቴሽነሪ ንግድ ላይም ተሠማርተው እንደነበር ያስታውሳሉ። ይሁንና ለመቆጣጠር አስቸጋሪ ስለሆነባቸው አንድ ፊታቸውን ወደምግብ ሥራው ማዞራቸውን ይናገራሉ። በአሁኑ ወቅት በዚሁ ሥራ አማካኝነት ሁለት የሥራ ተሽከርካሪዎች እና አንድ የቤት መኪና ባለቤት መሆን እንደቻሉ በመግለጽ አዲስ አበባ ላይ እና ደሴ ላይም ዘመናዊ ቤቶችን መገንባታቸውን ይገልፃሉ።
ለዚህ ሁሉ ውጤት ያበቃቸው አልሸነፍ ባይነት እና ተስፋ ሳይቆርጡ ጊዜን በሥራ ማዋላቸው መሆኑን በመጥቀስ በቀጣይም ዘመናዊ ሆቴል እና ሬስቶራንት ለመክፈት ውጥን እንዳላቸው አልሸሸጉም። በተለይም ወደአዲስ አበባ በመምጣት ከደሴው ሥራ ባለፈ በመዲናዋ ዘመናዊ የሆቴል ንግድ ላይ ለመሰማራት እራሳቸውን በአቅም እያጠናከሩ ይገኛሉ።
የሦስት ልጆች እናት የሆኑት የንግድ ሰው ከሥራ መልስም የቤተሰብ ሃላፊነቱ አለባቸው እና ልጆችን መንከባከብ እና መርዳቱን አላስተጓጎሉም። ነገ ልጆቻቸውም ደርሰው እንደእርሳቸው ጥሩ ሥራ እንዲኖራቸው ልጆቻቸውን ማስተማራቸውን ቀጥለዋል።
ሥራ ማለት ለእኔ የግዴታ ያክል ልክ አንድ ሰው ምግብ እንደሚበላው ሁሉ በየዕለቱ መከወን ያለበት ጉዳይ ነው የሚሉት ወይዘሮ ፍሬህይወት፤ ማንኛውም ወጣት ለስንፍና ቦታ ሳይሰጥ የሚያገኛትን ጊዜ ለቁምነገር ስለማዋል ሊያስብ እንደሚገባ ይናገራሉ። ንግድን በተመለከተም እየወደቁ እና እየተነሱም ቢሆን ማደግ ስለሚቻል በሩቆ እከስራለሁ በሚል ስሜት ከመፍታት ይልቅ እየሞከሩት ችግር እና መፍትሄውን እያወቁ መሥራቱ ለውጤት ያበቃል የሚለው ደግሞ ምክራቸው ነው። ቸር እንሰንብት!!!
አዲስ ዘመን ሰኔ 20/2012
ጌትነትተስፋማርያም