የጋራ ማንነት አገርን ይገነባል። አገር ደግሞ በአንድነት ማንነቱን የሚገልፀው ህዝብ ሉአላዊነት መገለጫ ትሆናለች። ኢትዮጵያ ለዘመናት የተናጠልና የጋራ ማንነት ያላቸው ህዝቦች መገኛ ሆና ቆይታለች። አሁንም እንደቀጠለች ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን ብሄራዊ ኩራት፣ ክብርና አልበገር ባይነትን ተላብሳ እንድትቆም ያስቻላትን ድሎችም በነዚህ ዘመናት አጣጥማለች።
በጦርነትና በእጅ አዙር ሙከራ ውብ ድብልቅ ማንነት ያላቸውን ህዝቦች ቀለበት ውስጥ ለማስገባት ተሞክሮ በተደጋጋሚ ሲከሽፍ መቆየቱን ታሪክ ያወሳናል። አሁንም ድረስ ይህን መሰሉ ድርጊቶች መሰረት ሲያጡና በህዝቦች አንድነት ሲከሽፉ እናስተውላለን።
በመግቢያችን ካነሳነው ሃሳብ ጎን ለጎን አገር በባህል፣ የጋራ ስነልቦና፣ ታሪክ፣ ቋንቋ፣ መልክአ ምድርና በሌሎች ተጨማሪ እሴቶች ትገነባለች። ከሁሉ በሚልቅ መልኩ ግን አገር በጠቢባን ያላሰለሰ ጥረት ፈር ትይዛለች። በተለይ የአንድን አገር የጋራ እሴቶች አጉልቶ ከማሳየትና የተሳሰረ ድር ከመፍጠር አንፃር ፀሃፍት የአናብስቱን ድርሻ ይወስዳሉ። በታሪክ፣ ትርክት፣ በልብ ወለድ ስራዎች የህዝቦች ማንነት፣ ባህላዊ እሴቶች በመቅረፅ የማህበረሰቡን የማይነጣጠል ስነ ልቦና በጉልህ በሚታይ መልኩ ወደ አደባባይ የማውጣት ትልቅ አቅም አላቸው።
እነዚህ የማህበረሰቡ ‹‹ራስ›› የሆኑት ጠቢባን በማይታየው የሃሳብ መስመር ጠንካራ ድንበር የመስራት አቅማቸው ድንቅ ነው። በስነ ፅሁፍ፣ ስነ ጥበብ፣ ኪነ ጥበብ ፈጠራዎቻቸው ልብ ውስጥ ተሰንቅሮ ለዘላለሙ የሚቀር ብሄራዊ ኩራት፣ አልበገር ባይነት፣ አገር ወዳድነትና የጋራ እሴት ይገነባሉ። በረብጣ ገንዘብና የቴክኖሎጂ ውጤት ከሚገነባ የወታደር አቅም በላይ ሉአላዊነትና ማንነትን የሚያስጠብቅ፤ ደረቱን የሚሰጥ ዜጋን ለመፍጠር የጥበብ ተሰጦን የተላበሱ መንገድ ጠራጊዎች የጥበብ ሰዎች ከምንም በላይ አቅም አላቸው።
ለዛሬ በዘመን ጥበብ የእሁድ ገፅ አምዳችን ላይ ይህን ርእሰ ጉዳይ በጠንካራ አመክንዮ የሚያስረዱልን ሃሳቦችን ለማንሸራሸር ወደናል። የሁሉንም የጥበብ ዘርፎችና ጠቢባን በማንሳት ጉዳዩን ከመለጠጥ ይልቅ በስነ ፅሁፍ ዘርፉ ላይ ብቻ ለማተኮርም ፈልገናል። በዚህ ርእሰ ጉዳይ ላይ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን ከመቅረፅ፣ ያለውንም አጉልቶ ለአደባባይ ከማብቃት አንፃር በስነ ፅሁፍ ዘርፉ በየዘመናቸው አንቱታን ያተረፉትን ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድን እንዲሁም አንጋፋው ደራሲ አዳም ረታን ማጠንጠኛችን አድርገናል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪና መምህሩ ፕሮፌሰር ቴዎድሮስ ገብሬ የጸጋዬ ገብረመድህንና የአዳም ረታን ስራዎች ዋቢ በማድረግ ስለ ብሔርተኝነትና አገር ግንባታ አንድ ጥናት ሰርተዋል። በጥናታቸው የስነ ፅሁፍን አበርክቶ በሰፊው ከመዳሰሳቸው ባሻገር እነዚህን ሁለት ጠቢባን ስነ ፅሁፋዊ ፍልስፍና ዙሪያ የግል ምልከታቸውን አመላክተዋል።
በቅድሚያ ግን በኢትዮጵያ ስነ ፅሁፍ ውስጥ ግዘፍ የነሳ ስራ ለመስራታቸው አገሬው የሚመሰክርላቸውን ጉምቱ ደራሲዎች ስጦታ ምንነትና የአገር ግንባታ አሻራ ከመመልከታችን በፊት ‹‹አገር ግንባታ›› የሚለው ጉዳይ በራሱ ምን አይነት ብያኔ እንዳለው ለማንሳት እንሞክር።
አገር ግንባታ – ስነ ፅሁፍ
ፕሮፌሰር ቴዎድሮስ ገብሬ አገር ግንባታ ወይም የብሄራዊ ስሜት ምህንድስና ‹‹የሀሳብ፣ የእምነትና የ የመርህ ጣጣ ነው›› ይሉታል። እንደርሳቸው እሳቤና ፍልስፍናዊ እይታ ያስቀመጧቸው ሶስት ጉዳዮች ረቂቅ አሊያም በእንግሊዘኛው አገባብ (Metaphysical) መሆናቸውን ይናገራሉ። በዚህ የተነሳ ሁሉም ውክልና ‹‹representation›› እንደሚፈልጉ ይገልፃሉ። ይህን ለማድረግ ደግሞ ዋናውን ሚና የሚጫወተው ጥበብ በተለይ ደግሞ ስነ ፅሁፍ መሆኑን ያነሳሉ።
እንደ ፕሮፌሰሩ ገለፃ ውክልና በኪነት ወይንም በስነ ጽሁፍ ውስጥ ሁለት መልክ አለ። የመጀመሪያው እራሱ ‹‹ውክልና›› ሲሆን በዚህ ውስጥ ‹‹የተጠራና ያልተጠራ›› እንደሚኖር ይጠቁሙናል። ሁልጊዜም ቢሆን በአገር ወይም (nation) ግንባታ ላይ የሚያከራክረው ጉዳይ አፈታሪክ የሚያስፈልገው፤ መወከል ያለበት ወገን
አሊያም ሰብዓዊ እሴት በአግባቡ ሳይካተት ሲቀር መሆኑን ይናገራሉ። በመሆኑም በአንድ እራሷን በቻለች፣ ባህል፣ ወግና ስርዓት ባላት አገር ውስጥ በሁሉም አቅጣጫ ያለ ወገን ውክልናውን በስነ ፅሁፍ አሊያም በኪነት ውስጥ ሊንፀባረቅ ይገባል ይላሉ።
‹‹የሀሳብ፣ የእምነትና የመርህ ጣጣዎችን ተጠንቅቀን፤ ሁሉንም በሚወክል መንገድ ሰርተናል ብንል እንኳን አዲስ ትውልድ ሲመጣ ከነበረው የተለየ እሴትና ፍላጎት ይዞ ስለሚመጣ ማደስ ያስፈልጋል›› የሚሉት ፕሮፌሰር ቴዎድሮስ ገብሬ፤ ይህን ሃላፊነት ለመወጣት ስነ ጽሁፍ ጥሩ አውድ ይሰጣል ይላሉ።
ሁለተኛው የውክልና መንገድ በራሳቸው አገላለፅና ‹‹አስተማስሎ›› መሆኑን ይናገራሉ። አስተማስሎ ማለት ደግሞ በእንግሊዘኛ (abstract›› እና ‹‹complex) የሚባሉትን ቃላት የሚተካ እንደሆነ ይገልፃሉ። ወደ ዋናው ፈትለ ነገር ሲመጡም ይህ የአስተማስሎ የውክልና አይነት ረቂቅ፣ የማይዳሰሱና ለመግለፅ የሚያስቸግሩ ሃሳቦችን በምስል ማቅረብ ማለት እንደሆነ ያብራራሉ።
‹‹ከሃምሳዎቹና ስድሳዎቹ ጀምሮ የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት (Nationalism) ታውኳል። እስካሁንም እንደታወከ ነው›› የሚሉት ፕሮፌሰሩ ቴዎድሮስ፤ በዚህ ምክንያት ብዙ ጥያቄዎች እንደተነሱበት ይናገራሉ። ከዚህ ባለፈም በርካታ እሴቶች በምስቅልቅሉ መነሻ መጥፋታቸውን ይጠቁማሉ። እንደ እርሳቸው እይታ ባጠፏቸው እሴቶች ምትክ ምንም አይነት አዲስ እሴት አልተገነባም። ይሄ ደግሞ አደገኛው ጉዳይ ነው።
ትውልድ ተለዋውጧል። ነባሩ ትውልድ በነቀለው እሴት ምትክ አዲስ ስላልገነባ አዲሱ ትውልድ ያለ በባዶ ነው የተቀመጠው የሚሉት ፕሮፌሰሩ፣ ተነቅለው በተጣሉ ነባር እሴቶች ላይ ነው ብሄርተኝነቱ (nationalism) የተመሰረተው ይላሉ። ያ ደግሞ በጊዜው ከነበረው እሴቶች ጋር የነበረው ፍቅር ሲያበቃ አብሮ ያበቃለት መሆኑን ያነሳሉ። እንደ መፍትሄ ሲያስቀምጡም አዲሱ ትውልድ አዲስ ብሄራዊ ማንነት እሴት ያስፈልገዋል የሚል መደምደሚያ ላይ ይደርሳሉ። እንደእርሳቸው እሳቤ ለትውልዱ ይሄንን የሚሰሩለት ደግሞ ከያንያን፣ የጥበብና የስነ ፅሁፍ ሰዎች ናቸው።
የሌሎች አገራት ልምድ
በአንዳንድ ጠንካራ ብሄራዊ መግባባት ባለባቸው አገራት ከያንያን ስኬታማ ናቸው። በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ግን እነዚህ ወሳኝ አካላት ተዳክመው ይታያሉ። ፕሮፌሰር ቴዎድሮስ ስለዚህ ጉዳይ ሲያነሱ ‹‹ለምን? የቋንቋ መብዛት እርግማን ሆኖብን ይሆን? እንደዛም እንዳይባል ፓፕዋ ኒው ጊኒ የምትባል ሃገር 3 ሚሊየን ሕዝብና 700 ገደማ ቋንቋ አላት። ሆኖም በመተሳሰብና በአንድነት ይኖራሉ›› የሚል ጠንካራና ሞጋች ጥያቄ ያነሳሉ።
ሌላኛዋ በምሳሌነት የሚያነሷት አገር ህንድ ነች። ከአንድ ሺህ በላይ ቋንቋና ከአራት በላይ አገር በቀል ሃይማኖቶች አሏት። እምነት ላይ የተመሰረት ካስት ሲስተም የሚባል ስርአትም እንዲሁ። ሕንድም በግጭትና በመከፋፈል የታወቀችበት ጊዜ ነበር። ይህን የመቃቃርና የመታመስ ዘመን የስነ ፅሁፍ አባት፣ ገጣሚ፣ ሙዚቃ አቀናባሪ ብሎም ሰዓሊ የነበረው ታጎር የተባለ ሰው ሊቋጨው ችሏል። በታጎር አማካይነት አገሪቷ ታሪኳን፣ ባህልና እሴቶቿን የጠበቀችና በስነ ፅሁፍ የዳበረ ታሪክ ያላት እንድትሆን ድርሻውን ተወጥቷል። ታዲያ እነሱ ጋር መልስ የተገኘለት የቋንቋ በሽታ እኛ ጋር ለምን አልተፈወሰም? ይሄ ጥያቄ የፕሮፌሰር ቴዎድሮስ ነው።
የስነ ፅሁፍ ወካይ መሃንዲሶች
‹‹የኢትዮጵያን የስነ ጽሁፍ ቀኖና ብንሰራ ከላይ ከሚቀመጡት ሰዎች ውስጥ እንደ ስብሃት ገ/ እግዚያብሔር፣ ጸጋዬ ገብረመድህን፣ በዓሉ ግርማና ሰለሞን ደሬሳ የመሳሰሉት አፋቸውን የፈቱት በአማርኛ ቋንቋ አይደለም›› የሚሉት ፕሮፌሰሩ ሆኖም ግን ስለ ብሄርተኝነትና አገራዊ ስሜት በአማርኛ መፃፍ መምረጣቸውን ያነሳሉ። ያለ እነዚህ ጉምቱ ደራሲያን ስራ የአማርኛ ስነ ፅሁፍ ‹‹literature›› ኢትዮጵያዊ መሆን ይችል እንዳልነበርም ይገልፃሉ። ፀሃፍቱ ይህን ቋንቋ ምርጫቸው አድርገው ስራዎቻቸውን ለትውልድ ስነምግባር፣ እሴት መገንቢያ ያዋሉት የባህል ተጽዕኖ ስለነበረባቸው ሳይሆን ነፃ ፍላጎታቸው ስለነበረ ነው። ያ ባይሆን ኖሮ በእንግሊዝኛ እና በፈረንሳይኛ ችሎታቸው የተነሳ ስራዎቻቸውንም ሆነ ምልክቶቻቸውን ያደርሱ
ነበር።
‹‹በፖለቲካ ዲስኩር መስራት አይቻልም። Politics ሊሰራ የሚችለው ሀሳብን በሃሳብ ማስረዳት ነው። Art ግን ሃሳብን ፈርክሶ ቀለም እና ቅርጽ ኖሮት ሰው እንዲኖርበት አድርጎ ነው የሚሰራው›› በማለት የሰሩትን ጥናት ውጤት የሚያብራሩት ፕሮፌሰር ቴዎድሮስ ገብሬ፤ በኢትየጵያ ዘመናዊ ስነ ፅሁፍ ላይ ጠንካራ አሻራ አሳርፈዋል ያሏቸውን አዳም ረታንና ፀጋዬ ገብረመድህንን በንፅፅር በማንሳት ‹‹ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነትን›› እንዴት በስነ ፅሁፍ መገንባት እንደሚቻል በስፋት ያብራራሉ።
ለኢትዮጵያ ብሄርተኝነት-አዳምና ፀጋዬን በንፅፅር
ፕሮፌሰሩ ሁለቱንም የአገራዊ ማንነትን፣ ብሄርተኝነትን በሚገነባና በሚገልፅ ጉዳይ ላይ ‹‹mythical thinking›› አሊያም እሳቤ የሚማረኩ ናቸው ይሏቸዋል። ሆኖም የየራሳቸው ልዩነት እንዳላቸው በማንሳት እንደሚከተለው ያስቀምጧቸዋል።
ጸጋዬ የግጥም አሊያም የድርሰት ስራዎቹን ሲያዘጋጅ ተሰርቶ ያለቀ ምልክት ‹‹symbol›› ይፈልጋል። የጸጋዬ በስነ ፅሁፍ ስራዎቹ ኢትየጵያዊ ብሄርተኝነትና ትርክት ‹‹national myth›› ለመገንባት ሙከራ ሲያደርግ በግዙፋን እሴቶች ለምሳሌ ያህልም በአባይ፣ በአዋሽ፣ በምኒልክ፣ በዓድዋ፣ በቴዎድሮስና በዘርዓይ ታሪክ ላይ ይመሰረታል። እዛ ተንተርሶ የሚፈልገውን ይሰራል ይላሉ።
‹‹ጸጋዬን ጨምሮ ነባር ከያኒያን ጀግና ሲሰሩ የሚመርጧት እናት በተለመደው የ feminine value የተሟላች መሆን አለባት›› የሚሉት ጥናት አድራጊው፤ ይህቺ እናት ንጹህ ቦታ የተገኘች፣ ከማሕጸን ጀምሮ የተጠበቀች በመሆኗ እንደሚያምኑ ይገልፃሉ። የአዳም ገፀ ባህሪ ግን ጉልት ላይ የምትውል፣ እግሯ ንቃቃት የተሞላ፣ ከነባሮቹ ባሮች የከፋ ድህነት ያላት ይሆንና እሷም ግን እንደነባሮቹ በድንግልና ትወልዳለች።
ፕሮፌሰሩ ‹‹ጸጋዬ አባይን ይጠልፍና ከአባይ የ Ethiopian identity ያሰግራል›› ይሉታል። አባይ ትልቅና ጠንካራ እንደሆነ እየገለፁ። አዳም ደግሞ በተቃራኒው የስነ ፅሁፍ ስራውን ሲሰራ ጤፍ እንደሚወስድ ይገልፃሉ። ጤፍ ማለት ከሰብሎች ሁሉ ትንሿ እንደሆነች አንስተውም ደራሲው ግን በሚያስገርም ሁኔታ ከዚህች ‹‹አንድ ፍሬ ጤፍ አብራክ እንጀራ እንደሚከፈለው ሁሉ›› አዳምም ኢትዮጵያዊነትን ልክ እንደ ጤፍ ሊከፍል ይሞክራል በማለት ሁኔታውን በጥልቀት ለማስረዳት ይሞክራሉ።
‹‹ጸጋዬ ጠንካራ ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ሊሰራ ሲፈልግ የጋራ ጠላት ይመለምላል›› የሚሉት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህሩ፤ ይህ አይነት እሳቤ በብዙ አገሮች ጥንታዊ ታሪክ ላይ ‹‹national myth›› ወይም ‹‹national literature›› መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑን ያነሳሉ። በተለይ የውጪ ጠላት ሲመጣ ዜጎችን ለአንድ ዓላማ ለመሰብሰብ ትልቅ ሃይል እንዳለውም ያስረዳሉ። ስለዚህ ለብሄራዊ ማንነት ‹‹national identity›› ግንባታ የፀጋዬ አይነት የስነ ፅሁፍ ዘይቤ እንደሚመከር ይናገራሉ። ቴዎድሮስ፣ ምኒልክ፣ ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት የተሰኙት የቲያትርና የግጥም ስነ ፅሁፍ ስራዎች በዚያ መንፈስ መሰራታቸውንም ይናገራሉ።
ፕሮፌሰሩ ሌላኛውን የኢትዮጵያ እንቁ የስነ ፅሁፍ ሰው በሙያ መነፅራቸው ሲመለከቱት ‹‹አዳም ከዚህ ተቃራኒ ነው›› የሚል ድምዳሜ ላይ ይደርሳሉ። እርሱ ‹‹የኛ ጠላት ራሳችን ነን›› የሚል እሳቤ እንዳለው ይገልፃሉ። በዚህ ምልከታውም እንደ ማሕበረሰብም፣ እንደ ግለሰብ ራሳችንን እንድናሸንፍ በስራዎቹ ይረዳናል በማለት ያስቀምጡታል።
እንደ መውጫ
በፕሮፌሰሩ እይታ የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት ‹‹Nationalism››ጉዳይ የጊዜ ጥልቀት time depth ይፈልጋል። ጸጋዬና አዳም ደግሞ ይሄን ቁልፍ ጉዳይ በሰላ ብእራቸው መስራት ችለዋል። በተለይ ለአዳም ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት በጊዜ ውስጥ አይደለም የተፈጠሩት። ከጊዜ ጋር አብረው እንጂ። ሁለቱም በየዘመናቸው እንደ ብርቅዬ የአገር ፈርጦች የሚታዩት የስነ ፅሁፍ ሰዎች ለጠንካራ የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት ግንባታ ጉልህ አስተዋፆ ያስቀመጡ ናቸው። ይሄ ደግሞ በምሁሩ ቴዎድሮስ አገላለፅ ለአገር ግንባታ ጥሩ ማዳበሪያ fertile አፈር ነው››
አዲስ ዘመን ሰኔ 14/2012
ዳግም ከበደ