ገና በወጣትነት እድሜያቸው ነው ወደንግዱ ዓለም የተቀላለቀሉት። የቅጥር ስራቸውን ትተው ወደ ንግድ ስራ በገቡበት ወቅተ እጃቸው ላይ ለመንቀሳቀሻ የሚሆን በቂ ገንዘብ ሳይዙ ቢሆንም ቀስ በቀስ ግን ውጤታማ መሆን ችለዋል። ይህንን ታሪክ የሚያውቁ ደግሞ ደፋር እና አልሸነፍ ባይነታቸውን ይመሰክሩላቸዋል። እኒህ ደፋርና አልሸነፍ ባይ አቶ ጥላሁን ጫላ ይባላሉ።
ባለታሪኩ አቶ ጥላሁን ጫላ የተወለዱት በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ጀልዱ ወረዳ ውስጥ ኦሶሌ በተባለ አካባቢ ነው። በደርግ ዘመነ መንግስት በ1974 ዓ.ም ሲወለዱም ቤተሰቦቻቸው የሚተዳደሩት በግብርናው ዘርፍ ነበር። ለቤተሰባቸው የመጀመሪያ ልጅ በመሆናቸው ደግሞ እድሜያቸውም ከፍ እያለ ሲመጣ ኃላፊነቱም በዛው ልክ እያደገ መምጣቱን ያስታውሳሉ። በዚህም ገና በልጅነታቸው ነበር የእርሻ ስራ ላይ በመሰማራት ወላጆቻቸውን ወደማገዙ እና ከብቶችን ወደማገዱ የተሸጋገሩት።
ከግብርና ስራ እገዛው ባለፈ ደግሞ የቀለም ትምህርት ለመከታተል የነበራቸው ጉጉት ከፍተኛ እንደነበር አይዘነጉትም። እናም ከእርሻ እገዛ ስራው ጎን ለጎን የአስኳላ ትምህርታቸውንም ለመከታተል ኦሶሌ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ገቡ።
በወቅቱ ከሌሊቱ 10 ሰዓት እና 11 ሰዓት ተነስተው ‹‹ወንፈል›› ወይም የደቦ ስራ ላይ ይሳተፋሉ። የጎረቤቶቻቸውን እርሻ ማረም እና ኩትኳቶ አሊያም አጨዳው ላይ ይሳተፋሉ። የትምህርት ቤት መግቢያ ሰዓት ሲደርስ ደግሞ ቁርሳቸውን በላልተው እና ደበተራቸውን ሸክፈው ወደ አስኳላ ያመሩ እንደነበር አይዘነጉትም።
ከትምህርት መልስም ስራው ይቀጥላል፤ ከብት ማገዱም ሆነ መላላኩ የእርሳቸው ድርሻ ነው። ማታ ደግሞ ወደ ጥናት ያመራሉ። በወቅቱ በአካባቢያቸው የኤሌክትሪክ መብራት ባለመኖሩ ደግሞ የሚወዱትን ትምህርታቸውን ለመቀጠል በኩራዝ ብርሃን ታግዘው ማንበባቸውን የግድ ነበር። እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ በኩራዝ ታግዘው በማንበብ ነበር ጥቂት ለመኝታ እረፍት የሚያደርጉት።
እንዲህ እንዲህ እያሉ በኦሶሌ የጀመሩትም ትምህርት በደልጁ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ቀጥለው 10ኛ ክፍልን አጠናቀቁ። ከ10ኛ ክፍል በኋላ ግን ጀልዱም ሆነ ኦሶሌ አካባቢ የሚያስተምሩ ተቋማት ባለመኖራቸው ወደ ሆለታ ሄደው የመማራቸው ጉዳይ የግድ ሆነ። ሆለታ ከተማ ላይም ከጓደኞቻቸው ጋር ቤት ተከራይተው ከቤተሰብ በሚላክላቸው ገንዘብ አማካኝነት ትምህርታቸውን መከታተሉን ቀጠሉበት።
ቤተሰብ ከገንዘብም አልፎ እህል ጭምር አስጭነው ሲልኩላቸው አቶ ጥላሁን እና ጓደኞቻቸው ደግሞ እራሳቸው እያበሰሉ እንጀራ ጋጋሪ ቀጥረው እስከ 12ኛ ክፍል ተማሩ። ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ሲያጠናቅቁ ደግሞ የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ውጤት በማግኘታቸው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሜርስ ትምህርት ቤት ተመደቡ።
በኮሜርስም የአካውንቲንግ ትምህርት የሚከታተሉበት እድል በመፈጠሩ ብዙም ወደማያውቋት አዲስ አበባ መጡ። በወቅቱ ደግሞ ዩኒቨርሲቲው በወር 120 ብር ለተማሪዎቹ ይሰጥ ነበርና አቶ ጥላሁንም ገንዘቡን ተቀብለው ቤት ከመከራየትም አልፈው የምግብ ወጪያቸውንም ይችሉ ነበርና የከፋ ችግር ሳይገጥማቸው ትምህርታቸውን መከታተሉን ተያያዙት። በመሃልም ትዳር መስርተው ጎጆ ወደ መቀለሱ ተሸጋገሩ።
በመጨረሻም ለሁለት ዓመታት የተከታተሉትን ትምህርት አጠናቀውም በዲፕሎማ ተመረቁ። ከምረቃው በኋላ ግን ስራ በቀላሉ ሊገኝ አልቻለም። ለስምንት ወራትም ከአዲስ አበባ ወደቤተሰባቸው መኖሪያ እየተመላለሱ ስራ ማፈላለጉን ተያያዙት፤ በወቅቱ ግን ቤተሰባቸው የተለያየ የሞራልም ሆነ የገንዘብ ድጋፍ ያደርጉላቸው እንደነበር አይዘነጉትም።
ከስምንት ወራት የስራ ፍለጋ ቆይታ በኋላ ግን አድአ በርጋ ወረዳ እንጭኒ ፋይናንስ ቢሮ ተቀጥረው የመንግስት ሰራተኛ ሆኑ። በጊዜው የወር ደመወዛቸው ደግሞ ተቆራርጦ እጃቸው ላይ 470 ብር ይደርሳቸው
እንደነበር ያስታውሳሉ። የወር ደመወዛቸውንም ከተቀበሉ በኋላ ብዙውን ገንዘብ የሚያውሉት ወደ አዲስ አበባ በመመላለስ የተሻለ ስራ ለማፈላለጊያነት እንደነበር አቶ ጥላሁን ይናገራሉ።
ለስምንት ወራት በቢሮው ከሰሩ በኋ ግን ኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ ውስጥ ስራ በማግኘታቸው አምቦ ከተማ ላይ ተመድበው መስራት ጀመሩ። ከስራቸው ጎን ለጎንም በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የአካውንቲንግ ትምህርታቸውን መከታተሉን ቀጠሉ።
በባንክ ስራቸው ላይ እያሉ ግን የስቴሽነሪ እቃዎች በብዛት በድርጅቶች እና በተለያዩ ተቋማት ተፈላጊ መሆናቸውን ይታዘባሉ። እናም ልክ ትምህርታቸውን አጠናቀው ሲመረቁ ሶስት ዓመት ተኩል ያክል ጊዜ ከሰሩበት ባንክ መልቀቅ እንደሚፈልጉ አሳወቁ።
በወቅቱ ግን በእጃቸው ያለው ጥቂት ገንዘብ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ቤተሰብም ሆነ የስራ አለቃዎቹ የባንክ ስራውን እንዳይለቁ ቢጠይቋቸውም አቶ ጥላሁን ግን አሻፈረኝ አሉ። ከባለቤታቸው እና አንድ ጓደኛቸውን ጋር በመሆንም ተደራጅተው መነገድ እንዳለባቸው በመወሰናቸው ከቅጥር ስራው በገዛ ፈቃዳቸው ተሰናብተው መስራት የሚፈልጉትን ጉዳይ ማውጠንጠን ጀመሩ። በኋላም የስቴሽነሪ ንግድ ስራ ቢጀምሩ አዋጭ እንደሚሆን በማሰባቸው አምቦ ከተማ ላይ ለስራ ማስኬጃ የሚሆን ገንዘብ ለማግኘት ከመንግስት ብድር ጠየቁ።
ተደራጅተው የጠየቁትን የብድር ገንዘብ በቀላሉ ሊያገኙ ባለመቻላቸው ግን ተስፋ አልቆረጡም ነበር። ይልቁንም በአንድ ወቅት ጋዜጣ ላይ ያዩትን የስቴሽነሪ ጨረታ ማስታወቂያ ይዘው ተወዳደሩ። ከውድድሩ በኋላ ጨረታውን በስልሳ ሺህ ብር ማሸነፋቸውም ተነገራቸው።
እጃቸው ላይ አይደለም 60 ሺህ ብር ግማሹንም እንኳን እንደሌላቸው የሚያውቁት አቶ ጥላሁን ግን ገንዘብ የለኝምና ማቅረብ አልችልም ብለው እጃቸውን አጣጥፈው እንዳልተቀመጡ ያስታውሳሉ። ምንም የሌለው ሰው ደፋር ነው የሚሉት ነጋዴው በእጃቸው ያለውን ስድስት ሺህ ብር ለሲፒኦ ወይም ለጨረታ ማስከበሪያ ዋስትና ማስያዣ ከፍለው የሚያውቋቸውን ዘመድ አዝማዶቻቸውን ብድር ወደ መጠያየቁን መሄዳቸውን ጊዜውን ወደኋላ ተመልሰው በፈገግታ ያስታውሱታል።
ሳይደግስ አይጣላም ነውና ዘመድ አዝማድ
አላሳፈራቸውም። በብድር መልክ ከቤተሰብ የሰበሰቡት ገንዘብ 30ሺህ ብር በመድረሱ ግማሹን የጨረታ እቃዎች ካስረከቡ በኋላ ገንዘቡ ሲሰጣቸው ቀሪውን ደግሞ በሁለተኛ ዙር አስረክበው መነሻ የሚሆን ትርፍ አገኙ።
በመጀመሪያ ስራቸው የተበረታቱት አቶ ጥላሁን አምቦ ላይ በከፈቷት አነስተኛ የስቴሽነሪ ሱቅ አማካኝነት ከስራ አጋሮቻቸው ጋር መንቀሳቀሱን ቀጠሉ። ለአንድ ዓመት በአምቦ እንደሰሩ ሰፋ ወዳለ የገበያ አማራጭ ለመግባት በማሰብ አዲስ አበባን ምርጫቸው አደረጉ።
ወደ አዲስ አበባ ሊመጡ ሲል ግን በዓምቦ አካባቢ የሚገኝ አንድ ወረዳ ላይ ስቴሽነሪ ጨረታ ለመወዳደር ሲሄዱ ለተደራጁ ሰዎች ሳይሆን ለአስመጪና ላኪዎች ነው ጨረታው ክፍት የሚሆነው የሚል ምላሽ ይሰጧቸዋል። እናም ወደ አዲስ አበባ መሄዴ ካልቀረ የአስመጪነት ፈቃድ ማውጣት አለብኝ ብለው በንዴት ይወስናሉ። የአስመጪነት ካፒታል ሲጠየቁም 50 ሺህ ብር አስመዝግበው ፍቃዱን በቀላሉ አገኙ። መርካቶ ላይም በ2003 ዓ.ም ሱቅ ተከራዩ።
ከዚህ በኋላ ግን ከውጭ ሀገራት ዕቃ ማስመጣት ሳይሆን ሱቃቸውን ወደ አዲስ አበባ መርካቶ ወደ ማዘዋወሩ ስራ ነበር የተጠመዱት። ቤተሰባቸውም ለጥቂት ጊዜያት አምቦ ከቆየ በኋላ እርሳቸው እየተመላለሱ በመነገድ የመርካቶውን ስቴሽነሪ ሱቃቸውን አደራጁ። ለአንድ ዓመታት በመርካቶ ከሰሩ በኋላ ግን ጥሩ ገቢ ሰበሰቡ። የንግድ ቦታው ከኢትዮጵያ የተለያዩ አቅጣጫዎች የሚመጡ ነጋዴዎች የሚሸምቱበት በመሆኑ ለአቶ ጥላሁንም ገቢ ማደግ አስተዋጽኦ በማድረጉ በዓመት 100 ሺህ ብር አተረፉ።
ትርፏን ይዘው ግን እቃ ለማስመጣት በሚል በስም ብቻ ወደሚያውቋት ቻይና ጉዟቸውን አደረጉ። ከመርካቶው ሱቃቸው ያተረፏትን ገንዘብ ግማሹን ለአየር ጉዞ ትኬት ሲያውሉ ግማሿን ደግሞ ለተለያዩ ወጪዎች በሚል ይዘዋት ነበር። ቻይና ሲደርሱ ግን የገጠማቸው ለየት ያለ ችግር ነበር።
ለአስመጪነቱ በቂ የገንዘብም ሆነ የሃሳብ ዝግጅት ባለማድረጋቸው እና ምግቡንም ለመልመድ ተቸገሩ፡፡ የገበያ ቦታዎችን ባለማወቃቸው ተንገላቱ። በመጨረሻም ከሳምንት ቆይታ በኋላ ታመው ወደሃገራቸው መመለሳቸው እርግጥ ሆነ። ከዚህ በኋላ ዕቃ ለማስመጣት በቂ ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባ በማመን ትምህርት ወስደው እራሳቸውን በዕውቀትም ሆነ በገንዘብ አቅም ካደራጁ ከዓመት በኋላ ደግሞ ወደ
ንግድ ማዕከሏ ዱባይ ከተማ አቀኑ።
ከዱባይም ጥቂት ኮምፒው ተሮችን እና የኮምፒውተር መለዋወ ጫዎችን በአውሮፕላን አስጨነው ወደሀገ ራቸው ተመለሱ። ከዚህ በኋላ ንግዱም እየተሳለጠ በመሄዱ የተለያዩ የስቴሽነሪ ምርቶችንም እያስመጡ ወደመሸጡ ስራ ዘልቀው ገቡ።
ከእስኪርቢቶ ጀምሮ የተለ ያዩ ወረቀቶችን እና የስቴሸነሪ እቃዎችንም በየጊ ዜው ከቻይና በማስመጣት ከእራሳቸውም አልፈው ለሌሎ ችም ስራ እድል መፍጠር ቻሉ። ስራዎች በሚኖሩባቸው ዓመታት በዓመት አምስት ጊዜ ያክል ወደቻይና ተጉዘው የስቴሽነሪ እቃዎችን ያመጡበት ጊዜ እነደነበር የሚያስታውሱት የንግድ ሰው አሁን ግን በኮሮና ምክንያት ስራው መቀዛቀዙን ነው የሚያስረዱት።
ስራው ጥሩ በሆነበት ወቅት በትላልቅ ጨረታዎች ላይ ለመሳተፍ ትኩረቱን ባደረገው ድርጅታቸው አማካኝነት በተለይ ከዩኒቨርሲቲዎች እና ከተለያዩ የመንግስት ተቋ ማት የሚወጡ የስቴሽነሪ ጨረታ ዎችን በማሸነፍ በሚሊ ዮኖች የሚቆጠሩ ምርቶችን ማቅረባቸውን ይናገራሉ።
የአቶ ጥላሁን የንግድ ድፍረት አሁን ላይ ውጤት እንዳመጣ እሙን ነው፤ በተለይ ማትረፍ እና አለማትረፋቸውን እንኳን እርግጠኛ ሳይሆኑ የቅጥር ስራቸውን ከለቀቁ በኋላ በርካቶች ይህ ሰው አደጋ ውስጥ ሊወድቅ ነው ብለው ስጋታቸውን ቢገልጹም እርሳቸው ግን በጥንካሬ አልፈው ውጤታማ ነጋዴ መሆን ችለዋል። አሁን ላይ እስከ 30 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ የስቴሽነሪ እቃዎችን የማቅረብ አቅምም መፍጠር መቻላቸውን ያስረዳሉ።
አቶ ጥላሁን በድርጅታቸው ስር በስቴሽነሪው ዘርፍ የሚገኙ ከእርሳስ እና ማርከር ጀምሮ እሰከ ስፒል እና ኮምፒውተር የደረሱ ወደ 100 አይነት የተለያዩ እቃዎችን በመግዛትና በመሸጥ ንግዳቸውን ይከውናሉ። አንድ ብሎ የጀመረው ስራቸውም አሁን ላይ ለአስር ቋሚ ሰራተኞች የስራ እድል መፍጠር ችሏል።
ከመርካቶች ሱቃቸው በተጨማሪም አሸዋ ሜዳ በሚባለው አካባቢ የምርት ማከማቻ ያቋቋሙት አቶ ጥላሁን፤ የድርጅታቸውን ዋና መቀመጫ ቢሮ ደግሞ ደንበል ህንጻ ላይ አድርገው ንግዳቸውን እየከወኑ ይገኛል።
ለስቴሸነሪው ዘርፍ የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ ነው የሚሉት የንግድ ሰው በተለይ ሀገር ውስጥ መመረት የሚችሉ በርካታ መጠቀሚያዎች ከውጭ በብዛት መግባታቸው ሀገርን ስለሚጎዳ ዘርፉን ወደአምራችነት ማሸጋገር ይገባል የሚል እምነት አላቸው። ለዚህ ደግሞ እራሳቸውም የበኩላቸውን ለመወጣት የወረቀት ማምረቻ ፋብሪካ ለመገንባት ዝግጅት በማድረግ ላይ መሆናቸውን ይናገራሉ።
በሆለታ አካባቢ ለፋብሪካ ግንባታው የሚሆን ቦታ ጥያቄ አቅርበው እስኪፈቀድላቸው ድረስ በመጠባበቅ ላይ ናቸው። ፋብሪካው ተገንብቶ ወደማምረቱ ሲሸጋገር ደግሞ የውጭ ምንዛሬን ከማዳን ባለፈ ለበርካቶች የስራ እድል እንደሚፈጥር ተስፋ አድርገዋል።
ስራ ማለት ለአቶ ጥላሁን ከፍተኛ ጥረት የታከለበት እና ተወዳዳሪነት ያለው ውጤታማ ክንውን ነው። ወጣቱ ትውልድም ስራን ሳይመርጥ ባለበት ዘርፍ ላይ ተወዳዳሪ እና ውጤታማ ለመሆን ቢጥር የስራው ፍሬ የማያገኝበት ምክንያት የለም፤ በመሆኑም ስራን ለነገ ሳይል ጊዜውን በአግባቡ መጠቀም የኖርበታል የሚልው ደግሞ ምክራቸው ነው። ቸር እንሰንብት!!
አዲስ ዘመን ሰኔ 13/2012
ጌትነት ተስፋማርያም