ቅድመ – ታሪክ
ልጅነቱን ያሳለፈው እንደ ዕድሜ እኩዮቹ ዘሎና ፈንጥዞ ነው። አካባቢው ከከተማ ወጣ ያለ መሆኑ ለልጆች ውሎ ምቹ የሚባል ነበር። የዛኔ የካ አባዶ እንደአሁኑ በቤቶች የተሞላ አልነበረም። ጫካማው ስፍራ የጅቦች ጩኸትና የአውሬዎች ኮቴ ሲሰማበት ይውላል።
የደጀኔ ወላጆች ልጃቸው እንደ ከተሜ ልጆች እንዲማርላቸው ይሹ ነበር። ደብተር አስይዘው ትምህርት ቤት ሲልኩትም አንድ ቀን የልባቸውን እንደሚሞላ ተማምነው ነው። እነሱ ባይማሩም በልጆቻቸው ቀለም መቁጠር ህይወትን መለወጥ እንደሚቻል ያውቃሉ።
የደጀኔ ታላቅ ወንድም እምብዛም በትምህርት አልገፋም። ከመማር ይልቅ ግብርናን መርጦ ወላጆቹን ያግዛል። ለእሱ ትምህርት ይሉት ጉዳይ ትርጉም ሰጥቶት አያውቅም።
ደጀኔ በወላጆቹ ድጋፍ ለገጣፎ እየተመላለሰ ሲማር ደስተኛ ሆነ። የዕድሜ እኩዮቹ ከሰፈራቸው ርቀው ይማራሉ። እሱም ቢሆን ይህን ማድረጉ አልከበደውም። ደስተኛ እንደሆነ ውሎ ይመለሳል። አብዛኞቹ ከራሳቸው አልፈው የወላጆቻቸውን ተስፋ ለመሙላት የሚማሩ ናቸው።
ከዚህ ቀድሞ በትምህርት የተጉ የአካባቢው ልጆች መልካም ደረጃ ላይ እንዳሉ ሰምቷል። ዛሬ እነሱ በታላላቆቻቸው ጎዳና ከተጓዙ ይህን ዕድል እንደማያጡት ገምተዋል።
ደጀኔ ከባልንጀሮቹ ጋር እየተመላለሰ የሚማረው ትምህርት ፍሬ ቢይዝ ወላጆቹ ተደሰቱ። አንደኛ ደረጃን አጠናቆ ወደ ቀጣዩ ምዕራፍ በደረሰ ጊዜም የሁልጊዜው ህልማቸው ሊፈታ መቃረቡን ገምተው ፈጣሪያቸውን አመሰገኑ። ነገን በበጎ እየሳሉ ያሻውን ሲፈጽሙለትም ከልባቸው ሆነ።
መንገድ መሳት
ደጀኔ የስምንተኛ ክፍልን አጠናቆ ወደ ዘጠነኛ ተሻገረ። ይህ ዕድሜው ልጅነቱን ጨርሶ አፍላነቱን የጀመረበት ነውና ጉርምስናውን ያሳብቅበት ያዘ። ከእኩዮቹ ጋር ሲውል ትኩረቱ እንደቀድሞው ትምህርት ብቻ አልሆነም። ጨዋታው ባህርይውና አዋዋሉ ተለወጠ።
ዘጠነኛ ክፍልን አጠናቆ ወደ አስረኛ ሲሻገር አብሮት የኖረው የትምህርት ፍላጎት ቀነሰ። ቀድሞ የነበረው የቀለም ፍቅር ከውስጡ ተሟጦ ልቡን ከፈለው። ይህኔ የነበረውን ዕቅድ ትቶ አቅጣጫውን ቀየረ። አመታት የለፋበትን ትምሀርቱን አቋርጦ ቤት መዋልን መረጠ። ይህን ያስተዋሉ ወላጆቹ ለምን ? ሲሉ ጠየቁ። ከእንግዲህ መማር እንደማይፈልግ አብራርቶ ነገራቸው።
ከጠዋት አስከማታ ቤት መዋል የጀመረው ተማሪው ደጀኔ ከወላጆቹ እጅ ሊወድቅ ግድ አለው። ጠዋት ተነስቶ የሚበላውን መጠየቅ፣ በየቀኑም ጥያቄውን መድገም ልማዱ ሆነ። ይህ እውነት ለወላጆቹ አይቀሬ መሆኑን ሲያውቅ ደግሞ በሀሳብ ይጨነቅ ያዘ። ውሎ አድሮ ግን ከአንድ ውሳኔ ደረሰ። እርፉን ጨብጦ የወላጆቹን እርሻ ለማረስ ተነሳ።
የትናንቱ ተማሪ ዛሬ ጥሩ ገበሬ ለመሆን በወሰነ ጊዜ ወላጆች አልተቃወሙም። ከድካማቸው ያሳርፋቸው ዘንድ መሬቱን ሰጥተው የምርቱን ፍሬ ጠበቁ። ደጀኔ ደብተር መያዝ በለመዱ እጆቹ መሬቱን እየገመሰ ከእርሻ መዋሉን ቀጠለ። ግብርናው ስላደገበት አልከበደውም። እያረሰ ውሎ ቤቱ ሲገባ በወላጆቹ ምርቃት እፎይታን ያገኛል።
ደጀኔ የትምህርቱ አለመሳካት ከቤት ቢያውለው ገበሬ ለመሆን ተገዷል። ቤተሰቦቹ የሚያልሙት ይህን መሰል ህይወት አልነበረም። እሱም ቢሆን በጠዋቱ ከትምህርት ውሎ ቀለም መቁጠሩ ለዚህ ግብ እንዳልነበረ አሳምሮ ያውቀዋል።
አዲስ ሀሳብ
ወጥቶ በቀንስራ ሊሰማራ ወሰነ።
ደጀኔ የቀን ስራ ለመግባት መነሻ የሆነው ታላቅ ወንድሙ በላቸው ነበር። በላቸው በአካባቢው እየሰራ በሚያገኘው ገንዘብ ራሱን በሚገባ እንደለወጠ ያውቃል። ሁሌም ስራ የማይጠፋበት አካባቢ ለእሱና ለጓደኞቹ የሚሆን ገንዘብ አሳጥቷቸው አያውቅም።
የነ ደጀኔ አካባቢ አሁን ከቀድሞው ተለውጧል። ጫካ ሆኖ የኖረው ስፍራ በቤቶች ተተክቶ ከተማው በእጅጉ ደምቋል። ገና በጊዜ የጅብ ድምጽ የሚሰማበት መንደር ዛሬ በመኪኖች አጀብ ግራ ያጋባ ይዟል። የቤቶች ግንባታን ተከትሎ የበረከተው የቀንስራም ለብዙዎች የእንጀራ ማግኛና የገንዘብ ምንጭ መሆን ጀምሯል።
ደጀኔ ልጅነቱን በቡረቃ ያሳለፈበት የመንደሩ ሜዳ ዛሬ በዘመናዊ ቤቶች ተሸፍኗል። ለአካባቢው መዘመን ዋንኛ ሰበብ የሆነው የኮንዶሚኒየም ግንባታም ለበርካታ የአካባቢ ነዋሪዎች የስራ ዕድልን ፈጥሯል። ይህ መሆኑ በርካታ ወጣቶች በጉልበታቸው ድካም፣ በላባቸው ወዝ እንዲያድሩ መንገድ ሆኗል።
ደጀኔ የደረሰበት የአፍላነት ዕድሜ ሀይል ሆኖት በጉልበት የሚከወኑ ስራዎች ላይ ይውላል። እሱን መሰል ወጣቶች ተሰባስበው በጋራ የሚሰሩት ከተገኘም ከመሳተፍ አይቦዝንም። አሁንም ኑሮው ከወላጆቹ ጋር ነው። እንደግብርናው ሁሉ ዛሬም ቤተሰቦቹን ለማገዝ እጁ ወደኋላ አይልም።
አንዳንዴ ስራ በተገኘ ጊዜ ከታላቅ ወንድሙ ጋር በእኩል ይሰራል። መቆፈርና መሸከም፣ ረዳት ሆኖ መስራትና ሌላም የጉልበት ስራ ከነ ደጀኔ ዓይን አያመልጥም።
የነ ደጀኔ መንደር ወጣቶች ትብብር በስራ ብቻ አይገለጽም። በአካባቢው የሚፈጠር ጠብና አለመግባባት ቢኖር አብዛኞቹ ችግሩን የጋራ ያደርጉታል። አጋጣሚ ሆኖ ከመንደሩ ወጣቶች አንዳቸው ቢጎዱ ጉዳዩን ከጥቃት ቆጥረው በጋራ ይጋፈጣሉ። ዕለቱን ባያደርጉት እንኳን ቀን ጠብቀው፣ ቦታ ለይተው ለመበቀል ወደ ኋላ አይሉም።
የደጀኔ ታላቅ ወንድም በላቸውና ባልንጀሮቹ ሰፈራቸውን ለመጠበቅና ስማቸውን ለማስከበር ጉልበትን እንደ አማራጭ ይጠቀማሉ። የሌላ አካባቢ ልጆች ከእነሱ መንደር ወጣቶች ጋር የሚፈጥሩት አለመግባባት በአሸናፊነት ካልተቋጨም ቁጭታቸው አብሯቸው ይከርማል። ዳግም ቀን ጠብቀው ብድር እስኪመልሱ በአይናቸው ዕንቅልፍ አይዞርም።
አንድ ቀን …
ከቀናት በአንዱ ቀን የነ ደጀኔ ሰፈር ልጆች ከሌሎች ወጣቶች ጋር ጠብ ገጠሙ። ድብድቡ ልቆ ግርግሩ ሲያይል የወዲያኛው ሰፈር ወጣቶች ጉልበት በረታ። ይህኔ ከነ ደጀኔ ሰፈር ልጆች ጥቂቶች ተጎዱ። ያመለጡት አምልጠው ጠቡ እንደተቋጨ ከተደባዳቢዎቹ መሀል የአንድ ወጣት ህይወት ማለፉ ተሰማ። ወጣቱ ከነ ደጀኔ መንደር የተገኘ ልጅ ነበር።
ይህ ታሪክ በነ ደጀኔ መንደር ነዋሪዎች ዘንድ ሀዘን አጥልቶበት ከረመ። ተደባዳቢዎቹ በፈጸሙት ያልተገባ ጠብ የሰው ህይወት እንደዋዛ ማለፉ ብዙዎቹን አሳዘነ።
ደጀኔ ወላጆቹን በጉልበት ማገዙን አልጠላውም። ይህን በማድረጉ የእነሱን ትከሻ ከድካም እንዳሳረፈ ገብቶታል። ያም ሆኖ ግን እስከመጨረሻው የበሬ ጭራ እየተከተለ ከጥቁር አፈር መታገልን አልወደደም። ውሎ ሲያድር ሌሎች ዕቅዶችን አሰበ። አንዱን ሀሳብ በሌላው እየተካም ከአንድ ጫፍ ደረሰ። በመጨረሻ ከግብርናው
አስቆጨ። በሌላ መልኩ የደጀኔ ወንድም በላቸውና የጓደኞቹ ስሜት ከሀዘን አልፎ ቂም በቀልን ወለደ።
እስከ ዛሬ በተራ ድብድብና ጠቡን ተከትሎ በሚመጣ ሽንፈትና ድል ስሜታዊ የሚሆኑት ወጣቶች ይህ ክፉ አጋጣሚ አይሽሬ ጠባሳ ጣለባቸው። ጠዋት ማታ በቀልን እያሰቡ ቂማቸውን የሚወጡበትን ስልት መንደፍ ያዙ። በስራ ሰበብ ሲገናኙ ጨዋታቸው ደም በመመለስ የተዋዛ ሆነ። የሁሉም ቋንቋ በአንድ ተቃኝቶ ቀንና አጋጣሚን ሲጠብቁ ከረሙ።
ከሁሉም ባልንጀሮች የበላቸው ስሜት በእጅጉ ይለያል። አንዳንዴ ለስራ በአካባቢው ብቅ ባለ ጊዜ ከወራት በፊት ህይወቱን በግድያ ያጣውን የመንደራቸውን ወጣት ያስታውሳል። ይህኔ ውስጡ በቁጭት ግሎ በእልህ ይንቀጠቀጣል። አፉን ገጥሞ ጥርሶቹን እያፋጨ፣ እጆቹን አጋጭቶ ራሱን ይወዘውዛል።
ድርጊቱን ማን እንደፈጸመው ጠንቅቆ የሚያውቀው ወጣት ስለበቀሉ ሲል የቅርብ ሰው እንኳን ቢያገኝ እንደማይምር እየደጋገመ ለራሱ ቃል ገብቷል። እሱና ጓደኞቹ የሰፈራቸውን ልጅ ደም፣ መልሰው በቀሉን በደም መወጣት ካልቻሉ አሁንም ዕንቅልፍ የላቸውም።
መጋቢት 18 ቀን 2004 ዓም
ደጀኔና ወንድሙ ከሌሎች የሰፈር ልጆች ጋር ሰሞኑን የጀመሩትን ስራ ለመጨረስ በጠዋቱ ተቃጥረዋል። ወጣቶቹ እንዲህ አይነቱን ስራ ባገኙ ጊዜ በጋራ ሰርተው የድርሻቸውን እኩል መካፈል ልማዳቸው ነው።
እነ ደጀኔ በአካባቢው የሚቆፈረውን ጉድጓድ አጠናቀው ለማስረከብ የበረታ ጉልበት አስፈልጓቸዋል። ስራውን ለአራት ሆነው ከጀመሩትም ቀናት ተቆጥረዋል። ዛሬም በማለዳው የመገናኘታቸው ምክንያት ይህ የጉድጓድ ቁፋሮ ሆኗል።
አራቱም የያዙትን አካፋና ዶማ ከጉድጓዱ እያስገቡ አፈርና ድንጋይ ያወጣሉ። ከእነሱ መሀል የደጀኔ ወንድምና አንዱ ባልንጀራው በአይን መተያየት ጀምረዋል። በስራው መሀል ቀና እያሉ በሀሳብ ይግባባሉ። ሁለቱም አካላቸው እንጂ ልባቸው በስፍራው እንደሌለ ያስታውቃል።
ጥቂት ቆይቶ ባልንጀሮቹ የያዙትን አካፋና ዶማ አስቀምጠው ከነበሩበት ጉድጓድ ወጡ። ወዲያውም ለሁለቱ ወጣቶች ተመልሰው እንደሚመጡ ተናግረው መንገድ ጀመሩ። ሁለቱም ወፈር ያለ አጣና ይዘዋል።
ደጀኔና ባልንጀራው ጥያቄ ከማቅረባቸው በፊት ሁለቱም ጎረምሶች ከስፍራው መራቃቸውን አወቁ። እነሱ ከሄዱበት አስኪመለሱም በእጃቸው የያዙትን ዶማ ወደ ጉድጓዱ ሰደው ቁፋሯቸውን ቀጠሉ።
ጥቂት ቆይቶ በአካባቢው ደማቅ ጩኸት ተሰማ። ስፍራው በግርግር ተናውጦ ትርምሱ ሲያይል ከጉድጓዱ የነበሩት ሁለት ወጣቶች የያዙትን ጥለው ወደ ስፍራው ገሰገሱ። ደጀኔ ከአካባቢው እንደደረሰ ታላቅ ወንድሙን ከሰዎች መሀል ለየው። በላቸው በአንድ እጁ ድንጋይ በሌላው ወፍራም ዱላ እንደያዘ ነው። ከጎኑ ያለው
ጓደኛው ደግሞ ተመሳሳይ ዱላ ጨብጦ አንድ ወጣትን በጋራ ይደበድባሉ።
ደጀኔ ይህን ሲያረጋግጥ እየሮጠ መሀላቸው ገባ። ወጣቱን ሲመለከት ከወራት በፊት የተገደለውን ባልንጀራቸውን አስታወሰ። ንዴት ብሽቀትና በቀል ተመላለሱበት። ተደብዳቢው የገዳዩ የሰፈር ልጅ መሆኑን ሁሉም ያውቃሉ። ጓደኛቸውን የገደለው እሱ ባይሆንም ሊምሩት አልፈለጉም። ለበቀል የተነሳው ልባቸው በጭካኔ እንደተመላ ዙሪያውን ከበቡት።
በላቸው ዱላውን እንደያዘ ወደወጣቱ ቀረበ። ጊዜ አልሰጠውም። እያጣደፈ ወገቡ ላይ አሳረፈበት። ይህኔ ወጣቱ የተመታበትን ዱላ ይዞ ለማስለቀቀቅ ሞከረ። ትግሉ ቀጠለ። ደጀኔ ሁኔታውን እንዳየ ወንድሙን ለማገዝ ተንደረደረ። ከመሬት ያገኘውን ድንጋይ አንስቶም ወደ ወጣቱ ወረወረ። አልሳተውም። ድንጋዩ አሁንም ወገቡን አገኘው።
እሱን ተከትሎ ወንድምየው እጁን ሰነዘረ። ፊቱን በጥፊ እያጮለ ጭንቅላቱን በቴስታ ደጋገመው። ምቱ ሲብስ የአስቻለው ጓደኛ ከመሀል ገባ። ግርግሩን ተጠቅሞ በጥፊ አጣደፈው።
ወጣቱ እንዲምሩት እየለመነ ከባድ ጩኸት አሰማ። ጩኸቱን ከሰሙት መሀል አንድ መንገደኛ ቀርቦ እንዲተውት ጠየቀ። ደጀኔ የሰውየው ንግግር አልተመቸውም። ለጥያቄው ምላሽ ይሁን ያለውን ሌላ ጥፊ ወጣቱ ፊት ላይ አሳረፈ። ወደሰውዬው መለስ ብሎ በ‹‹አያገባህም›› ቁጣ አፈጠጠበት።
ገላጋይ ጠፍቷል። የደቦኞቹ ጉልበት በርትቷል። እነ ደጀኔ ብቻውን ያገኙትን ወጣት በዱላና ድንጋይ እየደበደቡ አዳክመውታል። የጓደኛቸውን ሞት ሀይላቸውን አፈርጥመው ጉልበታቸውን አጠንክረው እየተበቀሉለት ነው። አሁንም ወጣቱ በተዳከመ ድምጽ መማጸኑን ቀጥሏል። የሰማው አልነበረም።
ሀይሉ መዳከም፣ ትንፋሹ ማጠር ሲጀምር ሁለቱ ባልንጀሮች ፊትና ኋላ እየተሯሯጡ ከስፍራው አመለጡ። ደጀኔ መለስ ብሎ ከወጣቱ ኪስ የወደቀውን ሞባይል አነሳና ከኋላቸው ሩጫውን ተቀላቀለ።
የፖሊስ ምርመራ
ፖሊስ ጥቆማ ደርሶት ከአካባቢው ሲገኝ የወጣቱ ህይወት አልፎ ነበር። አስከሬን ከማንሳቱ በፊት አስፈላጊውን የቴክኒክና ታክቲክ ማሰረጃዎችን ሰብስቦ መረጃዎችን ለማደራጀት የምስክሮችን ቃል ሊቀበል ግድ ነበር። በምክትል ሳጂን ሲሳይ ተሾመ የሚመራው ቡድን ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ ጥብቅ ክትትሉን ቀጠለ።
ሶስቱ ተጠርጣሪዎች ወንጀሉን በፈጸሙበት ዕለት ራሳቸውን ለመሰወር ከአካባቢው መራቃቸውን ያወቀው ፖሊስ በመዝገብ ቁጥር 621/04 በከፈተው ዶሴ የዕለት ሁኔታዎችን እያሰፈረ ክትትሉን ቀጠለ። በዕለቱ ከሟች ኪስ የወደቀውን ሞባይል ስለወሰደው ደጀኔ በቂ መረጃ በማግኘቱም በስልኩ ተጠቅሞ ወደ እርሱ ደወለ።
ደጀኔ የስልኩን መጥራት እንዳወቀ ‹‹ሀሎ! ማንልበል ›› ሲል ምላሽ ሰጠ። ፖሊስ ድምጹን እንደሰማ ጊዜ አላጠፋም። የራሱን ዘዴና ስልት ተጠቅሞ ተጠርጣሪው ካለበት ደርሶ በቁጥጥር ስራ አዋለው።
ደጀኔ በህግ ጥላ ስር እንደዋለ የሆነውን እውነት ሁሉ አንድም ሳያስቀር ዘረዘረ። ሁለቱ ተጠርጣሪዎች ያሉበትን እንዳማያውቅ ጠቅሶም በፈጸመው ድርጊት መጸጸቱን ተናገረ። ፖሊስ በቂ ማስረጃዎች ደጀኔን ለዓቃቤ ህግ ክስ አሳልፎ ሌሎቹን ማሰስ ጀመረ። ለጊዜው አላገኛቸውም።
ውሳኔ
ግንቦት 9 ቀን 2007 ዓ.ም በችሎቱ የተሰየመው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በነፍስ ማጥፋት ወንጀል የተከሰሰውን ግለሰብ የመጨረሻ ውሳኔ ለማየት በሰአቱ ተገኝቷል። ፍርድ ቤቱ ተከሳሹ ከሌሎች ግብረአበሮቹ ጋር በመሆን በፈጸመው ድርጊትም ጥፋተኛ ስለመሆኑ በበቂ ማስረጃዎችና መረጃዎች አረጋግጧል። በዕለቱ ባሳለፈው ውሳኔም እጁ ከተያዘበት ጊዜ አንስቶ በሚታሰብ የአስራስድስት ዓመት ከአምስት ወራት እስራት ይቀጣልኝ ሲል ብይኑን ሰጥቷል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 13/2012
መልካምስራ አፈወርቅ