ከስነጥበብ ጋር ጥብቅ ቁርኝት ባለው የስራ ዘርፍ ተሰማርታ ውጤታማ መሆን ችላለች። በሴትነቷ ካለባት የቤተሰብ ሃላፊነት ባለፈ በከፈተችው ድርጅት አማካኝነት ደግሞ በርካታ ወጣቶችን ሰርታ እያሰራች ትገኛለች። የዛሬዋ እንግዳችን ኢንቲሪየር ዲዛይነር ወይዘሮ ሚስጥር ጎሳዬ ትባላለች ።
የተወለደችው በአዲስ አበባ ከተማ ተክለሐይማኖት አካባቢ ነው። ወላጅ አባቷ በንግድ ስራ የተሰማሩ ሲሆን እናቷ ደግሞ የመንግስት ሰራተኛ ናቸው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን የተከታተለችው ናዝሬት ስኩል በተሰኘው እና ሴቶችን ብቻ በሚቀበለው ትምህርት ቤት ነው።
በልጅነቷ አባቷ ወደ ንግድ ስራው ከምታዘነብል ይልቅ ትምህርቷ ላይ አተኩራ እንድትገፋበት ድጋፍ ያደርጉላት እንደነበር ታስታውሳለች። እርሷ ግን ወደ ስነጥበቡ ዘርፍ መሳብ የጀመረችው ገና በአፍላዎቹ የልጅነት እድሜዋ ነበር። በትምህርት ቤት በተለይ የስዕል፤ የሙዚቃ እና የስፌት ትምህርት ክፍለ ጊዜዎችን በንቃት ትከታተል እንደነበር አትዘነጋውም። ቤት ውስጥም ቢሆን በእርሳስ የተለያዩ ስዕሎችን በማዘጋጀት የስነጥበብ ፍላጎቷን ለማሳደግ ትጥር ነበር።
የስነጥበብ ዝንባሌዋን እንድታሳድግ ደግሞ እናቷ በይበልጥ ያግዟት እንደነበር ታስታውሳለች። ይህን ዝንባሌዋን የተመለከቱ ቤተዘመዶችዋም ለስዕል የሚሆኑ ግብዓቶችን በስጦታ መልክ ሲያበረክቱላት ይበልጡኑ በነጭ ወረቀት ላይ ለምታሰፍረው ጥበብ መሳቧ አልቀረም።
ይሁንና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ስትጀምር ግን ይበልጡኑ ወደ አስኳላው ትኩረቷን አደረገች። በውስጧ ያለውን የጥበብ ፍላጎት በውስጧ ይዛ ምርጫዋ ያደረገችውን የማህበራዊ ሳይንስ የመሰናዶ ትምህርቷንም ቀጠለች።
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን በጥሩ ውጤት አጠናቃ የከፍተኛ ትምህርት ዝግጅቷን ስታደርግ ሰመራ ዩኒቨርሲቲ መመደቧን አወቀች። ይሁንና በሚሊኒየሙ ክብረበዓል ወቅት ወደአፋር አቅንታ ለመማር በምታቅድበት ወቅት በወቅቱ ጀማሪ በነበረው ዩኒቨርሲቲው በኩል በርካታ ያልተሟሉ ጉዳዮች መኖራቸውን ተረዳለች። እናም ወደሰመራ አቅንታ መማሩ አስቸጋሪ እንደሚሆንባት በመገንዘቧ አዲስ አበባ ቀርታ የግል ኮሌጆች ትምህርቷን ለመቀጠል ወሰነች።
በአዲስ አበባም ሂልኮ የተሰኘው የኮምፒውተር ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ኮሌጅ ገብታ የኮምፒውተር ሳይንስ ትምህርትን ማጥናት ጀመረች። ለሶስት ዓመታት የተከታተለችው ትምህርት ማጠናቀቂያ ዓመት ላይ ግን በቀጣይ በዲዛይን ስራው ዘርፍ የግድግዳ ጌጣጌጦችን ዲዛይኖችን እያመረተች እንደምትሰራ ወስና ነበር። ይሁንና ከምረቃዋ በኋላ የግል ስራዋን ለመጀመር መነሾ የሚሆናት በቂ ገንዘብ ባለመኖሩ ተቀጥራ የመስራቷ ጉዳይ የግድ ሆነ።
ስራ ስታፈላልግ ደግሞ በጸሃፊነት ሙያ የምትቀጠርበት እድል አገኘች። እናም በአንድ የቻይና ድርጅት ውስጥ ጸሃፊ ሆና በሁለት ሺህ ብር የወር ደመወዝ ተቀጠረች። ባገኘችው ስራ እስከመጨረሻው የህይወት ዘመኗ ለመቀጠል እቅድ ባይኖራትም ለቤት ውስጥ እና ለተለያዩ ታቋማት ዘመናዊ የግድግዳ ጌጦች ስራ መነሻ የሚሆናትን ገንዘብ ለማግኘት ግን እንደሚረዳት በመገንዘቧ ከምታገኘው ገንዘብ ላይ በአቅሟ መቆጠቡን ተያያዘችው።
ከምታገኘው ገንዘብ ላይ የተወሰነውን ወስዳ ጥቂት የስዕል ብሩሾችን እና ቀለም በመግዛት የስዕል ሸራዋን ወጠረች። እናም ለግድግዳ ማስዋቢያ የሚሆኑ በ3ዲ ጥበብ የሚከወኑ ስዕሎችን በቤቷ ማዘጋጀት ጀመረች። ይህን ስታደርግ በቤቷ በሚገኝ አንድ ጠባብ ክፍል ውስጥ የሚገኙ እቃዎችን ወደአንደ ጎን በመሰብሰብ ለስራዋ የሚሆናትን ቦታ ካዘጋጀች በኋላ ከጸሃፊነት ስራዋ ባለፈ በቤቷ የግድግዳ ጌጦችን ለማምረት የሚያስችላትን ዝግጅት አደረገች።
በመጀመሪያ የሰራችው ደግሞ በ3ዲ ጥበብ የታዘገ የዛፍ ምስል ነበር። ስዕሉ በእጅ መዳሰስ የሚችል እና የተለያዩ የወዳደቁ እቃዎችን በመለጣጠፍ የሚሰራ የስነጥበብ አይነት ነበር። እናም የመጀመሪያዋ ስራዋን የቤታቸው ግድግዳ ላይ ሰቀለችው። በዚህ ወቅተ አባቷ በመደሰታቸው ለስነጥበብ ፍላጎቷ እድገት እንዲረዳት በሚል የአምስት ሺህ ብር ሽልማት አበረከቱላት።
በሽልማቱ የተበረታታችው ወይዘሮ ሚስጥር ለስራዋ የሚያግዟትን እንደ ቆዳ ፤ መቁረጫ እና ሌሎች ለስራዋ የሚረዱ ቀላል የእጅ መሳሪያዎችን አሟላችበት። ከዚያም በዶቃ፣ በተለያዩ የምግብ አዝርዕቶች እና የተለያዩ ዕቃዎችን በመጠቀም በስዕል ሸራ ላይ በመለጣጠፍ የሚዘጋጁ የግድግዳ ማስዋቢያዎችን ማዘጋጀቷን ተያያዘችው። ምርቶቹንም በፍሬም ካስዋበች በኋላ አንድ በአንድ እያዞረች ለፈላጊዎች በማቅረብ ደንበኞችንም ማፍራት ጀመረች።
በወቅቱ ግን በከተማው ለግድግዳ ማስዋቢያ የሚሆኑ ምርቶች ሰፊ እጥረት መኖሩን እና በፍሬም የተዘጋጁ ማስዋቢያዎች በውጭ ምንዛሬ ከተለያዩ ሀገራት የሚገቡ መሆኑን በመረዳቷ በግሏ ቢሮ ከፍታ ለመስራት ያላት ፍላጎት ጨመረ። ጥቂት ጊዜያትንም ለሬስቶራንቶች እና በተለያዩ አውደ ርዕዮች ላይ ምርቶቿን ስታቀርብ በደንበኞች በኩል ፍላጎቱ ከፍተኛ መሆኑን ተረዳች። እናም ስራውን በስፋት መከወን እንዳለባት በማመን ስናፕ ፕዛዛ የተሰኘው የገበያ ማዕከል ላይ ቢሯን ከፍታ ዳዴ ይል የነበረውን የግል ንግድ ስራዋን ወደማጠናከሩ ተሸጋገረች።
ለቢሮ ኪራይም 12 ሺ ብር በወር ከከፈለች በኋላ የተወሰኑ የእጅ ጥበብ የታከለባቸው ስራዎቿን ስታቀርብ ጥቂት ወራት የገበያ ችግር አጋጥሟት እንደነበር አትዘነጋውም። ቀስ በቀስ ግን የምርቶቿን የስነጥበብ ደረጃ እና ውበት የተመለከቱ በርካታ ደንበኞችን ማፍራቷ አልቀረም። ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት ገደማ በተከፈተው እና በስሟ ሚስጥር ብላ በሰየመችው የቤት ውስጥ እና የተለያዩ ተቋማት ማስዋቢያ የግድግዳ ጌጦች ማምረቻ ድርጅት ስር ባህላዊ ይዘት ያላቸውን የጥበብ ውጤቶች መሸጧን ቀጠለችበት።
በዚህ ስራዋ በተለይ የእንዝርት እና የጥጥ ፈትልን ከወዳደቁ መዳብ ሽቦዎች ጋር በማጣመር የምታዘጋጃቸው በፍሬም የተሰሩ የግድግዳ ማስዋቢያዎች በበርካቶች ዘንድ ተወዳጅነታቸው ከፍ እንዳሉ ወይዘሮ ሚስጥር ትናገራለች። በተለይ ትክክለኛውን የእንዝርት እና የተፈተለ ጥጥ በፍሬም አድርጋ የምታቀርብበት የግድግዳ ማስዋቢያ በብዙዎች ዘንድ ጥሩ ተቀባይነት ያተረፈ በመሆኑ ለበርካቶች በ1ሺህ 400 ብር ማቅረብ መቻሏን ታስታውሳለች።
በተለያዩ የጥበብ ፈርጆች የተሰሩ ማስዋቢያዎችን ለተለያዩ ደንበኞቿ በማቅረብ ጥሩ ተቀባይነትን ማትረፍ ቻለች። ወይዘሮ ሚስጥር ባህላዊ ይዘት ካላቸው የግድግዳ ጌጦች ስታመርት የወዳደቁ እና በቆሻሻነት ተፈርጀው የተጣሉ ቁሶችንም መልሳ ለጥቅም በማዋል ትታወቃለች።
በተለይ የወዳደቁ ፌስታሎችን በመሰብሰብ በፍሬም ለምታዘጋጃቸው እውነተኛውን የጀበና አቀማመጥ የሚያሳየው የግድግዳ ማስዋቢያዎች ላይ የጀበናው ማስቀመጫ አድርጋ ፕላስቲኩን በግብአትነት ተጠቀማበታለች። በሌላ በኩል ደግሞ የወዳደቁ የመዳብ ሽቦዎችን እና የተሰባበሩ መስታወቶችን በመጠቀም ለተለያዩ የ3ዲ ስዕል ስነጥበብ ስራዎቿ ታውላለች።
በስራዎቿ አማካኝነት የአካባቢ ብክለትን በመቆጣጠር ረገድ የበኩሏን ጥረት በማድረጓም በዓለም ባንክ በተደገፈ የአየር ንብረት ለውጥ ውጤታማ ስራዎች ላይ ድጋፍ የሚያደርግ ተቋም የ30 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ሽልማት አበርክቶላታል። ይህ ሽልማት ስራዎቿን በማስፋፋት ንግዷን በሁለት እግሩ እንዲቆም እንዳገዘው ትናገራለች።
በሽልማቱ ይበልጥ በመበረታታቷም የተለያዩ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ መሳሪያዎችን ገዝታ በባህላዊ የኢትዮጵያ ዕቃዎች እና ሀገርኛ ክንውኖች ላይ ያተኮሩ የግድግዳ ማስዋቢያ የስነጥበብ ምርቶችን በማምረት ገፋችበት። ከእርሷም አልፋ የተለያዩ ሰራተኞችንም ቀጥራ ማሰራቱን ተያያዘችው።
ሲያሻት ከቀንድ ፤ሌላ ጊዜ ደግሞ ከሸክላ እና ከቅል ዲዛይን ተደርገው የተሰሩ ማስዋቢያዎች የምታዘጋጀው ስራ ፈጣሪ አንድን የቤት ውስጥ አካል ሊያሳምር የሚችል ሃሳብ ካገኘው ወደተግባር ትለውጠዋለች። ማስዋቢያውም በመጀመሪያ በወረቀት ላይ በአግባቡ ንድፉ ከተቀመጠ በኋላ አሊያም በስዕል መልክ ወይም በቅርጻቅርጽ መልክ ተሰርቶ በፍሬም ይዘጋጃል። በዚህም አብረዋት የሚሰሩት ሰዎችም በየጊዜው አዳዲስ ሀሳቦችን እየተማሩ ይሄዳሉ።
ስራዬ ከሰሌን፣ ከቆዳ፣ ከቀርከሃ እና ለተለያዩ የእደጥበብ ውጤቶች አምራቾች ጋር የተሳሰረ ነው የምትለው ወይዘሮ ሚስጥር፤ ለዲዛይን ስራዋ የሚውሉ በርካታ ግብዓቶችን ከአነስተኛ አምራቾች በመግዛት ለእራሷ የሚሆናትን ስታገኝ ለአቅራቢዎቹ ደግሞ የተሻለ የገበያ ትስስር መፍጠሯን ትናገራለች።
በዚህ መንገድ የበርካታ ባለሙያዎች እጅ ያረፈባቸው በፍሬም የተዘጋጁ የማስዋቢያ የስነጥበብ ውጤቶችን ለበርካታ የግል እና የመንግስት ተቋማት ማቅረብ ችላለች። በተለይ በአዲስ አበባ የሚገኙ ባለ አራት እና አምስት ኮከብ ሆቴሎች እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዲሁም የቀዳማይት እመቤት ጽህፈት ቤቶች ውስጥ የሚስጥር ምርቶች በብዛት እንደሚገኙ ነው የምታስረዳው።
ወይዘሮ ሚስጥር እራሷ ዲዛይን አድርጋ ከምታዘጋጃቸው የግድግዳ ማስዋቢያዎች ባለፈ ደግሞ በፈርኒቸር ምርቱም ውስጥ አምርቶ የመሸጡን ስራ ከጀመረች ጥቂት ዓመታት ተቆጥረዋል። ዘነበወርቅ አካባቢ በሚገኘው ማምረቻ ቦታዋ ላይ ዘመናዊ ሶፋዎችን፣ መመገቢያ ጠረጴዛዎችን እና የወጥ ቤት የእንጨት ምርቶችን እንዲሁም የተለያዩ የእንጨት ውጤቶችን ለገበያ በማቅረብ ላይ ትገኛለች።
በማምረቻው የተለያዩ የመሰንጠቂያ፣ የእንጨት ቅርጽ ማውጫ እና የቤት እቃዎች ማዘጋጃ ማሽኖችን በመግዛት ምርቶችን በጥራት ታዘጋጃለች። ለአብነት ከዋንዛ እንጨት የሚዘጋጀው ጠረጴዛ በዘጠኝ ሺህ ብር በማቅረብ ገበያው ላይ አሻራዋን እያሳረፈች ነው።
ከዋንዛ በተጨማሪ የቀርከሃ ምርቶችንም የምትጠቀመው ወይዘሮ ሚስጥር፤ የስነጥበብ ችሎታዋን በመጠቀም በየጊዜው ከደንበኞቿ የሚቀርቡላትን የቤት ውስጥ እና የሆቴል የፈርኒቸር ምርቶችን ለማዘጋጀት ከጥራት በተጨማሪ ውበትንም ያማከለ ስራ ለመከወን ጥረት እንደምታደርግ ትናገራለች።
ተመጋጋቢ የእንጨት ምርቶችን ለሚጠቀሙት የዲዛይን እና የፈርኒቸር ምርቶቿ ከዓለም ዓቀፍ ተቋማት የፍትሃዊ ንግድ /የፌይር ትሬድ/ ሰርተፍኬት በማግኘቷ በቀጣይ ወደውጭ ሀገራት ምርቶቿን ለመላክ ሰፊ እድል እንደሚሰጣት አምናለች። የፍትሃዊ ምርት ሰርተፍኬቱ፤ ተገቢውን ዕቃ የመጠቀም፤ ተገቢውን የሰራተኛ ክፍያ የመክፈል እና ሌሎች ሀቀኛ አሰራርን ስለመተግበር ግምገማ የሚደረግባቸው በመሆኑ ለወጪ ንግዱ ገበያ ተቀባይነት ወሳኝነት አለው።
በየቀኑም አዳዲስ የስዕል ጥበብ ላይ የተመሰረቱ የግድግዳ ማስዋቢያዎችን ለማዘጋጀት ደፋ ቀና የምትለው እንስት በፈርኒቸር ሙያው ደግሞ ከውጭ የሚገቡትን ምርቶች የሚወዳደር ሀገር በቀል እውቀት የታከለባቸው ዕቃዎችን እያመረተች መሆኗን ትናገራለች።
የስነጥበብ ችሎታዋን ወደአምራች ንግድ የቀየረችው እንስት ከዘነበወርቁ ማምረቻ ቦታዋ እና ከስናፕ ፕላዛ የገበያ ማዕከሉ መሸጫዋ ባለፈ ደግሞ በአዲስ አበባ ሴነቸሪ ሞል በተሰኘው የገበያ ማዕከል ተጨማሪ ቢሮ ከፍታለች። ከአዲስ አበባ ወጣ ብላም በሀይቆች በተከበበችው በቢሾፍቱ ከተማ በተገነባው ኩሪፍቱ ሪዞርት ውስጥ ተጨማሪ የምርት ማሳያ ከፍታለች።
በአጠቃላይ የወይዘሮ ሚስጥር በጥበብ ስራ ላይ የተመሰረተው ንግድ በአሁኑ ወቅት 34 ሰራተኞችን ይዟል። አብዛኛዎቹ ሰራተኞቿ ደግሞ እዚያው እራሷ ማምረቻ ውስጥ ሰልጥነው እራሳቸውን እያሳደጉ የመጡ ወጣቶች ናቸው። በተለይ ለወጣት ሴቶች በምታደርገው እገዛ ሙያ ከማልመድ ባሻገር እራሳቸውንም በገንዘብ እንዲደግፉ የሚያደርግ ስራ መፍጠር በመቻሏ ደስተኛ ነች።
በአጠቃላይ የስነጥበብ ስራዎቿ ሩዋንዳ ላይ ከአፍሪካ ምርጥ ስራዎች ውስጥ በመካተቱ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ጭምር በተካፈሉበት መድረክ ተሸላሚ መሆን መቻሏ ለእሷ ሆነ ለሃገሯ ኩራት ነው። ይሁንና ከዚህም በላይ ስራዎቿን በማሳደግ ለበርካታ ወጣቶች ስራ የሚፈጥሩ ባህላዊ እደጥበብ ምርቷን ወደውጪ የመላክ ውጥን እንዳላት አልሸሸገችም። በተገኘው ስኬት ከመኩራራት ይልቅ ለተሻለ ውጤት የንግድ አድማሷን በማስፋት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሃብቶችን ወደሃገሯ ለማምጣት አቅዳለች።
ስራ ማለት ለወይዘሮ ሚስጥር ጥረት የታከለበት እና ለሌሎችም የሚተርፍ ክንውን ነው። በዚህ ረገድ በርካታ ወጣቶች ዛሬ ላይ የተሰጣቸውን ጊዜ በአግባቡ ተጠቅመው ስለነገው ህይወታቸው መቃናት ደከመኝ፤ሰለቸኝ ሳይሉ ጥረት ካደረጉ ውጤታማ የማይሆኑበት ምክንያት የለም የሚለው ደግሞ ምክሯ ነው። ቸር እንሰንብት!!
አዲስ ዘመን ሰኔ 6/2012
ጌትነት ተስፋማርያም