ዓለም በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ነበልባል ሳያንሳት በዘረኝነት ረመጥ እሳትም መንደዷንም እየተመለከትን ነው። ከሰሞኑ አሜሪካዊው ነጭ ፖሊስ ጥቁር አሜሪካዊውን ጆርጅ ፍሎይድን አንገቱን ከመሬት አጣብቆ ትንፋሽ እስኪያጥረው ድረስ ለአስር ደቂቃዎች ያህል ተንበርክኮበት በመቆየቱ ሕይወቱ አልፏል።
ዓለምም ጆርጅ ፍሎይድ ሕይወቱ እንድትተርፍ ሲማፀን፣ የሞቱ እናቱ እንዲደርሱለት ሲጣራ፣ የመጨረሻ እስትንፋሱን እንዲሁም ሕይወት አልባ ሰውነቱን ተመልክቷል። የጆርጅ ፍሎይድ ሞት በአገሪቷ ውስጥ ያለውን ለበርካታ መቶ ዓመታት የቆየውን መዋቅራዊ ጭቆና፣ ታሪካዊ ኢ-ፍትሐዊነት፣ የፖሊስ ጭካኔና ሌሎችም መሠረታዊ ችግሮችን ፍንትው አድርጎ ያሳየ ክስተት ሆኗል ሲል የቢቢሲ የአማርኛው የዜና ክፍል ዘግቧል።
ሚሊዮን ጥቁር አሜሪካውያን በማረሚያ ቤቶች በሚማቅቁባት፤ አገሪቱ ያወጣቻቸው ሕግና ሥርዓቶች መዋቅራዊ ጭቆና ያደርሳሉ ወይ? እስቲ አገሪቱ ፍትህን በማስፈንና ወንጀልን በመቆጣጠር ዘርፍ ረገድ በጥቁር አሜሪካውያን ላይ የሚፈፀሙ መድሎዎችን የትየለሌ ናቸው።
ይኸው በሚኒያፖሊስ እንደ እንስሳ የተገደለው ጆርጅ ፍሎይድ አሟሟት አሜሪካን ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም የሚገኙ ጥቁሮችን እንዲሁም የመብት ታጋዮችን ቁጣና ተቃውሞ አቀጣጥሏል። ብዙዎችም ጥቁር አሜሪካውያን በባርነት ንግድ በግዞት ከመጡበት ዕለት ጀምሮ እየደረሰባቸው ያለውን ግፍ፣ ለነፃነት የተደረጉ ትግሎችን እንዲሁም አሜሪካ በጥቁር ዜጎቿ ላይ እስካሁንም ድረስ የምትፈፅምባቸውን ለጆሮ ሰቅጣጭ የሆኑ ግፎች በርካቶች እየተናገሩም እየፃፉም ይገኛሉ።
ሚሊዮን ጥቁር አሜሪካውያን በማረሚያ ቤቶች በሚማቅቁባት፤ አገሪቱ ያወጣቻቸው ሕጎች እጅግ የተወሳሰበ መዋቅራዊ ጭቆና ሲያደርሱ ማስተዋል የዕለት ተዕለት ተግባር ነው። አገሪቱ ፍትህን በማስፈንና ወንጀልን በመቆጣጠር ዘርፍ ረገድ የዓለም ቁንጮ ነኝ ብትልም ነገር ግን በዚህ ሽፋን በጥቁር አሜሪካውያን ላይ የሚፈፀሙ መድሎዎች ፍፁም ኢሰብዓዊ ናቸው። ከታዳጊዎች ጀምሮ በተለያዩ ዕድሜ የሚገኙ ጥቁር አሜሪካውያን በተለያዩ ጊዜያት በፖሊስ ጥይት ቆስለዋል፤ እንዲሁም ተገድለዋል። መገደላቸው ብቻ አይደለም እጅግ አሳማሚው ጉዳይ። የሰው ልጅ የሞተ ዕለት ነው ሟች የሆነው። እንደ ውሻ መሞት ግን ምናልባትም ከውሻ ባነሰ መንገድ የጥቁሮች ደም እንደዋዛ በየጎዳናው ሲፈስ መመልከት ከአንዴም የሁለት ጊዜ ሞት ነው። የፖሊስ ጭካኔ ከግብሩም በላይ ነው። ገድሎህ ከንፈሩን አይመጥልህም። እንኳንስ በሕይወትና በሞት መካከል ሆነህ እስትንፋስ አጥሮህ «መተንፈስ አልቻልኩም» እያልክ ባለ በሌለ አቅምህ ብትጣራ ብትለምን ሊሰማህ ፍቃደኛ አይደለም። ገድሎህም ከአስከሬንህ ላይ መነሳት ይከብደዋል። ይኸ በሽታ ነው። ከኮሮናም የባሰ ወረርሽኝ።
በአስራዎቹ የዕድሜ ክልል የሚገኙ ጥቁር ታዳጊዎችም በፖሊስ በተገደሉባቸው ወቅቶችም ፖሊሶች «ለሕይወታችን ፈርተን ነው፤ ሽጉጥ ሊያወጡ መስሎን ነው» የሚሉ ምላሾች ሲሰጡም ተሰምተዋል። ይህንንም መሠረት በማድረግ የአሜሪካ ፖሊሶች ተጠርጣሪ ናቸው ብለው ጥይት የተኮሱባቸውን ሰዎች በምናጤንበት ወቅት ጥቁር አሜሪካውያን በፖሊሶች በጥይት መመታት ወይም የመገደላቸው ዕድል ከፍተኛ ነው።
በአሜሪካ ውስጥ የአደንዛዥ ዕፅን መጠቀም በነጮችና በጥቁር አሜሪካውያን ተመሳሳይ ሁኔታ ቢኖረውም፤ ጥቁር አሜሪካውያን አደንዛዥ ዕፅ ይዘው ከተገኙ ዘብጥያ ይወርዳሉ። ሌላው ቀርቶ የኮሮና ሟቾች ቁጥር እንኳ ወደ ጥቁሮች ያደላ እንደነበር በርካታ የመገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል። ይህን ስትመለከት ለመሆኑ የጥቁር ነፍስ ዋጋ ስንት ነው ብለህ እራስህን ለመጠየቅ ትገደዳለህ።
ለምሳሌ በጎርጎሮሳውያኑ 2018 የተደረጉ እስሮችን እንደ ማጣቀሻ ብናይ፤ በጥቁር አሜሪካውያን ዘንድ ያለው እስር 750 ከመቶ ሺህ ሲሆን ለነጭ አሜሪካውያን ደግሞ 350 ከመቶ ሺህ ነው። ነገር ግን ብሔራዊ የአደንዛዥ ዕፅ አጠቃቀም ላይ ከጎርጎሮሳውያኑ 2018 በፊት በተደጋጋሚ የወጡ ቁጥሮችን ብናይ በነጭ አሜሪካውያንና በጥቁር አሜሪካውያን ዘንድ የዕፅ አጠቃቀም ልማድ ተመሳሳይ ነው።
የአሜሪካ የሲቪል መብቶች ህብረት ባደረገው ጥናት ጥቁር አሜሪካውያን ድንገት ዕፀ ፋርስ ይዘው ቢገኙ ያለምንም ምህረት በቁጥጥር ስር እንደሚውሉ ይፋ ያደረገ ሲሆን ይህም ከነጮች ጋር ሲወዳደር 3.7 እጥፍ እንደሆነም መረጃው አመላክቷል። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አሜሪካውያን በጥቃቅን ወንጀሎች እስር ላይ እንደሚገኙ የተለያዩ መረጃዎች ያሳያሉ።
በተለያዩ ጊዜያትም አሜሪካ ጥቁርና ላቲን ሕዝቦቿን ወደ እስር ቤት በመወርወር ለነፃ የጉልበት ሥራ ዳርጋቸዋለች፤ እንዲሁም የተለያዩ ኩባንያዎችም የእስር ቤት ጉልበትን በመጠቀም ላይ እንደሚገኙ የሚያመለክቱ በርካታ ጽሑፎች ወጥተዋል። በእስር ላይ የሚገኙ ጥቁር አሜሪካውያን ከነጮች ጋር ሲወዳደር አምስት እጥፍ እንዲሁም ከላቲን አሜሪካውያን ጋር ሲወዳደር ደግሞ በእጥፍ ይበልጣል።
ምንም እንኳን ባለፉት አስር ዓመታት በእስር ላይ የሚገኙት ጥቁር አሜሪካውያን ቁጥር ቢቀንስም፤ አሁንም ከሌሎች ዘሮች በበለጠ ጥቁር አሜሪካውያን በእስር ይገኛሉ። ይህንኑ የበደልና የግፍ ትርዒት እዚያው አሜሪካ ኖሮበት ለዓመታት እስኪያንገሸግሸው ያስተዋለው አንድ ሱራፌል የተባለ የሀገሬ ልጅ ልብን በሚሰብር መልኩ ያካፈለኝን እንደሚከተለው ላጋራችሁ።
«ለስድስት ዓመታት የተማርኩባት ሚኒያፖሊስ ከተማ እሳት ፈጥራለች። እሳት ሆናለች። ወላፈኑ በመላ አሜሪካ ተሰራጭቷል። በጆርጅ ፍሎይድ ግድያ። በጥቁሩ ጆርጅ ፍሎይድ አሰቃቂ ሞት። በነጩ ፖሊስ የማን አለብኝ ገዳይነት።
ነጩ ፖሊስ የጥቁሩ ጆርጅ አንገት ላይ ተንደላቆ የተንበረከከበት፥ ጆርጅ «ኧረ የትንፋሽ ያለህ! ኧረ በናትህ መሞቴ ነው! ኧረ ገደልከኝ» እያለ እስከሞት የተድፈጠፈጠበት ጎዳና እኔ በተለይ በመጨረሻዎቹ የሚኒያፖሊስ ዓመታቴ እኖርበት በነበረው ሰፈር አቅራቢያ ነው የሚገኘው። ቀጥሎም የተቀጣጠለው ዓመፅ አካባቢውን አጥለቅልቆታል።
ጆርጅ አንድ ሰው አይደለም። የጆርጅ ሞት የአያሌ ጥቁሮችን፣ የአያሌ ገፀ ብዙ ግፉአንን ይወክላል። በአሜሪካ የጥቁሮች ደም ደመ ከልብ ነው። በጥቁሮችና አሜሪካን ሕንዶች እንዲሁም በተለያዩ ስደተኞች የተገነባችው አሜሪካ፤ ስደተኝነታቸውን በረሱና ሚሊዮኖችን ባፈናቀሉ፣ በባርነት በቀጠቀጡ የነጭ ሥርዓት ፈጣሪዎች ፀፀትን የመደበቅና የስግብግቡን የካፒታሊዝም ሥርዓት የመጠበቅ አባዜ ሃጢያቷን በፍትህ ከማጠብ ይልቅ በበለጠ ደም እያጨማለቀች መጓዝን መርጣለች። ደሞ የነፃነት ስብከቷ ይባስ።
እናም በጆርጅ ላይ የተፈፀመው ግድያ አስደንጋጭ ቢሆንም፣ ድንገት ደራሽ አይደለም። ሥርዓታዊ ነው። የነጩ ፖሊስ ዘግናኝ ኢፍትሃዊነትም የሱና የግብረ አበሮቹ ብቻ አይደለም። ሥርዓታዊ ነው። ችግሩም መልሱም ውስብስብ ነው ማለት ነው። መፍትሄውም የሁሉ ነገር መፍቻ እኔ ነኝ ከሚለው የሊበራል ምርጫ (ኢሌክሽን) እና ነፃ ገበያ ተብዬ (ሶ ኮልድ ፍሪ ማርኬት) ባሻገር ሥርዓታዊና ተቋማዊ ብሎም ዕለታዊ ፍትህን ማስፈንን ይጠይቃል።
ጥቁር ነኝና ይሄ ዕጣ ፈንታ የኔም እንደሆነ አምናለሁ። ለዚያም ነው በሚኔሶታ የሚኒያፖሊስ ኑሮዬ ዘወትር በሰቀቀን እኖር የነበረው። ነጭ ፖሊስ የጥቁር ሰውነቴን፣ የጥቁር ሕይወቴን እንዳይነጥቀኝ በስጋት ነበር የምኖረው። ስጋት የየዕለት የመንገድ ላይ አረማመድን ይቀይዳል። ወይም የተለየ ያደርገዋል። ዓይኔን ከሚያልፉ ፖሊሶች ዓይን ለመነጠል አደርግ የነበረው ጥረት፣ ጆሮዬን አለሁላችሁ በሚል ስም አለሁባችሁ እያለ መንፈስን ከሚበጠብጠው የፖሊስ መኪና ጩኸት እከልልበት የነበረው ጭንቅ፣ ፖሊሶች በአንድ በኩል ሲመጡ በዚያኛው መንገድ ተሻግሬ አሳብሬ እሄድ የነበረበት መጥፎ ትዝታው አሁንም በሰውነቴ ውስጥ ተቀብሮ አለ።
እንደዚያም ሆኜ አልቀረልኝም። በወቅቱ የንጥቂያ ወንጀል ተሞክሮበት ነበር በተባለበት አካባቢ አለመኖሬ እየታወቀ የዩኒቨርሲቲ ኦፍ ሚኔሶታ ፖሊስ ከ«ወንጀል ሙከራው ክስተት» በኋላ የዚያን ዕለት ምሽት ወደ ዛንዚባር (ለወርክሾፕ) ጉዞ የሚያስፈልገኝን መድኃኒት ከዩኒቨርሲቲው ክሊኒክ ለመውሰድ ስሄድ በካሜራ የተነሳውን ምስሌን ‘ተጠርጣሪው’ ብሎ ስልሳ ሺህ ለሚሆኑት የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ በተነው። በዚያ የተነሳ ከጉዞዬ ተመለስኩ። ያን ባላደርግ ዓለም አቀፍ ተሳዳጅ (ፉጂቲቭ) ነበር የምሆነው።
የዩኒቨርሲቲው ፖሊስ ከሚኒያፖሊስ ፖሊስ ጋር በጥብቅ የሚሰራ ነበርና ከኤርፖርት ስመለስ የት ሄጄ ልደር? ስንቀሳቀስ የሚኒያፖሊስ ፖሊስ ቢይዘኝስ? እንዴት ነው የምሆነው? እጄን ምኑ ጋር ነው የማደርግላቸው? ዝም ብለው ቢተኩሱብኝስ? ቢያስሩኝስ? እስከፈለጉት ዘመን ዘብጥያቸው ቢወረውሩኝስ? በሚል መባተት ውስጥ ነበርሁ።
ያ ስጋት እጥፍ ድርብ ሆኖ የመጣው ምስሌ ከዩኒቨርሲቲው አልፎ በበነጋው በፎክስ ቴሌቪዥን አማካይነት ለመላው ሚኔሶታ ሲሰራጭ ነው። ብዙ ታሪክ አለፈና እኔም በወዳጅ ዘመዶቼ፥ በጥቂት ቀናኢ መምህራኔ ያንን ክፉ አጋጣሚም፣ ዘመንም አለፍኩ። መጥፎ ትዝታውና የዛሬው ዓለም አቀፋዊ የዘረኝነት ስጋት አልፎ ባያልፍም።
ሆኖም የኔ ጥቁርነት የራሱ ዳራም አለው። የጥቁር አሜሪካኖቹም የተለየ ነው። ጥቁር አሜሪካዊ መሆን ዘለዓለም እንዲህ ባለ ስጋት ውስጥ መኖር ብቻ ሳይሆን፣ እነሱም ነጮቹም በሚጋሩት ከባሪያው ሥርዓት እስከአሁኑ ኒዮሊበራል ኦርደር ድረስ በዘለቀው የማይፈታ ቅራኔ ምክንያት ሰውነታቸው በነጭ ፖሊስ የትም የሚቀጠቀጥ፣ የሚገደልና የሚጣል እንደሆነ አለ።
ጥቁር አሜሪካውያን ለዘመናት እንደተጨቆኑ፣ ለዘመናት እንደታገሉ አሉ። የነሱ ትግል ለብዙዎች ትሩፋትን ሰጥቷል። ለኢትዮጵያውያን ጭምር። ጥቁሮች ስል የቆዳ ቀለማቸውን በመያዝ ብቻ ሳይሆን በቆዳ ቀለማቸው ምክንያት ለነጭ ጥቅም ከፍትህ ዓለም የተገለሉትን ቡኒና ቢጫ የሚባሉትንም ሕዝቦች ሁሉ እንደማስብ ልብ በሉልኝ። እነዚህ ሕዝቦች በተናጠልም በቅንጅትም እየታገሉ አሉ። ነገር ግን አገዛዙ ረቂቅ ነውና እራሱን ራቅ እያደረገ በተበዳዮቹ መካከል መርዝ እየረጨ እነሱን እያናጨ ህልውናውን ያስቀጥላል።
በሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ልዩ ልዩ ዓይነት ናቸውና ሁሉንም በአንድ ከረጢት ውስጥ መክተት ተገቢ አይደለም። እናም ገና ከ 1920ዎቹና 30ዎቹ አንስቶ ከተደረገው ፀረ ቅኝ አገዛዝና ፀረ ፋሽስት ትግል አንስቶ ኢትዮጵያውያንና ጥቁር አሜሪካውያን በትብብር ሰርተዋል። ጥቁር አሜሪካውያን ለኢትዮጵያ ለመዝመት ሰልፍ ይዘው ተመዝግበዋል፣ የሕክምና እና ሌሎች ለጦርነቱ አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶችን ከመላ ሰሜን አሜሪካ ጥቁሮች አሰባስበው ለግሰዋል፣ ጥቂት ተዋጊዎችንም ልከዋል። ከዚያም በብላክ ፓንተር የነፃነት ንቅናቄና የሲቪል መብት ንቅናቄ ወቅት ኢትዮጵያውያን ከጥቁር አሜሪካውያን ጋር ሰርተዋል። አሁንም በተለይ ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን በማንነት ምስረታቸውም የተነሳ ከጥቁር አሜሪካውያን ጋር እንደ ኢትዮጵያዊ ጥቁር አሜሪካውያን አብረው ለነፃነት እየታገሉ ያሉ ብዙዎች ናቸው።
ሆኖም ግን ብዙዎች ኢትዮጵያውያን በተለያዩ ምክንያቶች ውስብስብ የሆነውን የሀገሬው አሜሪካ ሕንዳውያን፣ ጥቁር አሜሪካውያንና ሂስፓኒክ ሕዝቦችን የታሪክና የኑሮ ሁኔታ (ጥቁሮችን እርስ በራሳቸው ለመከፋፈልና ለማባላት ሆን ተብሎ የሚሸረበውን ሴራ) ባለመረዳት ወደ መፍረድና ወደመናቅ መሄድ ይስተዋልባቸዋል። ከዚህም ባሻገር ሙሉ የአሜሪካ ዜግነት ተቀብለው ሕይወታቸውን በአሜሪካ ለመኖር የወሰኑ ኢትዮጵያውያን የእነሱንም ሆነ የልጆቻቸውን ሕይወት ሲያስጨንቅና ሲቀጥፍ ሊኖር ስለሚችለው ዘረኝነት በአደባባይ ሲናገሩ አለመታየታቸው ነገሩን ፍርጃም ባይሆን ውይይት ሊቀሰቅስ የሚገባው ጉዳይ ያደርገዋል።»
የሆነው ሆኖ ጆርጅ ፍሎይድ ላይመለስ እስከወዲያኛው ሄዷል። በመንግሥተ ሰማያት ከውድ እናቱ ጋርም ተቀላቅሏል። ሞቱ ግን ዓለምን አንድ ትልቅ ትምህርት አስተምሮ ያለፈ ይመስላል።
ቸር ያቆየን!
አዲስ ዘመን ሰኔ 5/2012
በሐሚልተን አብዱልአዚዝ