
ዓለምአቀፉ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በዓለም ላይ እያስከተለ ያለው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውስ ከፍተኛ ነው። የበሽታው ስርጭት ከጀመረበትና ዓለምአቀፍ ወረርሽኝ መሆኑ በዓለም የጤና ድርጅት ከታወጀበት ጊዜ አንስቶ ያስከተለው ሰብአዊና ቁሳዊ ቀውስ ከፍተኛ ከመሆኑም ባሻገር አሁንም ሁነኛ መፍትሄ ሳይገኝለት የሰው ልጆች ስጋት እንደሆነ ቀጥሏል።
በሽታው እስካሁን በዓለም ላይ ከ7 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ዜጎችን ያጠቃ ሲሆን ከ416 ሺህ በላይ ዜጎችን ለህልፈት ዳርጓል። በርካቶችንም ከስራ እንዲፈናቀሉ በማድረግ የስራ አጥነትን እያባባሰ ይገኛል። የአለምን የኢኮኖሚ እድገት በመግታት እድገትን ለአስር ዓመታት ወደ ኋላ ሊመልስ እንደሚችል ባለሙያዎች እየተነበዩ ይገኛሉ።
በሽታው በፖለቲካውም ረገድ ቢሆን ተጽዕኖ ማሳረፉ አልቀረም። በዓለም ላይ 58 አገራት የዘንድሮውን ምርጫ ለሌላ ጊዜ እንዲያራዝሙ አስገድዷል። አሜሪካ፣ ብራዚል፣ ሜክሲኮ፣ አርጀንቲና፣ ፈረንሳይ፣ እንግሊዝ፣ጀርመን፣ ጣልያን፣ ሩስያ፣ ወዘተ በዚህ ምክንያት ምርጫን ካራዘሙ አገራት ተጠቃሾች ናቸው።
እነዚህ አገራት በቴክኖሎጂ እድገትም፣ ሆነ በኢኮኖሚ አቅም ከአገራችን ጋር የሚወዳደሩ አይደሉም። በብዙ መልኩ የኢኮኖሚ አቅማቸው የፈረጠመና የቴክኖሎጂ አቅማቸውም ያደገ ነው። ነገር ግን በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ምርጫን ማካሄድ የሚያስከትለውን ቀውስ በመረዳትና ለጊዜው ወረርሽኙን መከላከል ላይ ማተኮር እንደሚገባ በመገንዘብ ምርጫውን አራዝመዋል። እነዚህ አገራት ይህንን ሲያደርጉ ታዲያ የቀረበባቸው ክስም ሆነ ወቀሳ የለም። የፖለቲካ ተቀናቃኞቻቸውም እምቧ ከረዩ አላሉም።
አገራችንም ይህንን ዓለምአቀፍ ፈተና እየተጋፈጠች ትገኛለች። በተለይ የበሽታው ስርጭት ቀስ በቀስ እየሰፋ ከመምጣቱም ባሻገር በየእለቱም የሚቀጥፈው ህይወት እየጨመረ በመጣበት በዚህ ወቅት ስጋቱም በዚያው ልክ ጨምሯል። ችግሩ በቀጣይ ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይና ሊያስከትል የሚችለው አደጋም ስለማይታወቅ መንግስት ሙሉ ትኩረቱን በዚህ ላይ አድርጎ መስራት ካልቻለ የሚከሰተው አደጋ አገራዊ ቀውስን የሚፈጥር እንደሆነ መገመት አይከብድም።
በዚህም መሰረት መንግስት ቀጣዩን ምርጫ ለማካሄድ የሚችልበት እድል ባለመኖሩ አማራጮችን በመፈተሽ ህገመንግስታዊ በሆነ አግባብ ምርጫውን አራዝሟል። ይህ ደግሞ በአንድ በኩል መንግስት ሙሉ ትኩረቱን በሽታውን በመከላከል ላይ አድርጎ ህዝቡን ከሚመጣው አደጋ ለመጠበቅ የሚያግዝ ሲሆን በሌላም በኩል በቀጣይ በተረጋጋ መንፈስ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማካሄድና በአገሪቱ አስተማማኝ የዴሞክራሲ ስርዓትን ለማስፈን ያስችላል።
ከዚህም ባሻገር ዜጎች በኮሮና ቫይረስ እንዳይጠቁ ለማድረግ ትልቅ አቅም የሚፈጥር ውሳኔ ሲሆን የተጀመሩ የልማት ስራዎች ሳይቋረጡ እንዲካሄዱም ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል።
ያም ሆኖ ግን ይህ አካሄድ የማይመቻቸው እና በአቋራጭ ስልጣን ለመያዝ የሚጥሩ ኃይሎች ይህንን አካሄድ ሲቃወሙና በገሃድና በተዘዋዋሪ በአገሪቷ ቀውስ እንዲፈጠር ሲቀሰቅሱ ይስተዋላል። ነገር ግን መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ከምንም በላይ ሰላምና መረጋጋትን የሚፈልግ በመሆኑ ለዚህ ጥሪ ምላሽ አልሰጠም።
በቀጣይም መላው ህብረተሰብ ከሰላም ጎን በመሆን በመላ አገሪቱ ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም እንዲኖርና የተጀመረው ኮሮናን የመከላከል ስራ ተጠናክሮ በሽታው የከፋ ጉዳት ሳያስከትል በቁጥጥር ስር እንዲውል ለማድረግ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከት ይጠበቅበታል።
በሌላም በኩል አሁንም ከፊታችን የሚታዩ በርካታ ስራዎች አሉ። ከነዚህም ውስጥ አንዱ በዚህ የክረምት ወቅት የሚካሄደው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ነው። ይህ ተግባር ለታላቁ ህዳሴ ግድብ አስተማማኝ የውሃ ፍሰት እንዲፈጠር በማድረግ ለዘላቂ ልማታችን አቅም የሚፈጥር ሲሆን ምቹ የአየር ንብረት እንዲኖርና ለግብርናው ዘርፍ ዕድገትም ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር የሚያደርግ ነው።
በመሆኑም እነዚህን ስራዎች ስናከናውን በህክምና ባለሙያዎች የሚሰጡ ምክሮችና ክልከላዎችን በአግባቡ ተግባራዊ ማድረግ ከእያንዳንዳችን ይጠበቃል። ስለዚህ ከቤት ውጪ ማስክ መጠቀም፣ እጅን በየጊዜው በሳሙናና በውሃ መታጠብ፣ ቫይረሱን ሊያሰራጩ ከሚችሉ ንኪኪዎች ራስን መጠበቅ፣ አካላዊ ርቀትን መጠበቅና የመሳሰሉ ጥንቃቄዎችን በአግባቡ በመተግበር ራሳችንን፣ ቤተሰባችንንና መላውን ህዝብ ከበሽታው እየተከላከልን ልማታችንን ማፋጠን ለነገ ይደር የምንለው ሥራ አይሆንም።
አዲስ ዘመን ሰኔ 5/2012