ኢትዮጵያ ምቹ የሆነ ምድራዊ አቀማመጥ፣ የአየር ንብረትና ለቁጥር የሚያታክት የብዝሃ ሕይወት ስብጥር ካላቸው ሀገራት አንዱዋ ናት:: ይሁን እንጂ ለረጅም ጊዜ ከተፈጥሮ ሀብቶቿ በኢኮኖሚያዊ ፤ በማህበራዊ ፤ በተፈጥሯዊ አገልግሎቶች ተጠቃሚ ሳትሆን ቆይታለች:: ለዚህም በመንስኤነት ከሚጠቀሱት እያደገ የመጣው ሕዝብ ቁጥር ተከትሎ የእርሻ መሬት ማስፋፋትና ለመኖሪያነት መዋል ፤ የደን ምንጣሮና መመናመን ናቸው:: የተፈጥሮ ሀብቶች መኖር የአየር ንብረት ለውጥ እያሳደረ ያለውን ተዕፅኖ ለመቋቋም ፤ የከርሰ ምድርና የገጽ ምድር ውሃ እንዲጨምር በማድረግ፤ የቱሪዝም መስህብ በመሆን፤ የአየር ንብረትን ጠብቆ ለማቆየትና ኢኮኖሚ ለማሳደግ የጎላ ሚና ያላቸው ናቸው::
በኢትዮጵያም የኢኮኖሚ ዕድገትን በዘላቂነት ለማስቀጠል በሁለተኛው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች አንዱ ዘላቂ ልማትን ከአካባቢ ደህንነት ጋር እንዲጣጣም ማድረግ ላይ ነው። የአረንጓዴ ልማት ኢኮኖሚ ግንባታ ስትራቴጂ መሠረታዊ መነሻው የአካባቢ ሙቀት ሳቢ ጋዞች ልቀትን በመቀነስ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ነው። በመሆኑም አካባቢ ጥበቃ የህልውና ጉዳይ እንጂ ለነገ ሊባል የሚችል አይደለም:: የሁሉንም ህብረተሰብ ክፍል ርብርብ የሚጠይቅ ስለሆነም በሀገር ደረጃ የተያዙ በርካታ እቅዶች ምን ያህል ወደ መሬት ወርደው ተግባራዊ እየተደረጉ እንደሚገኙ መመልከት ተገቢ ነው::
አሁን ላይ ባለው ነባራዊ ሁኔታ በየክልሉ እየተካሄዱ የሚገኙ የአካባቢና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራዎች ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኙ መዳሰሱ ጠቃሚ ይሆናል:: ከዚህም ጋር በተያያዘ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት አካባቢ ጥበቃ ላይ ምን እየተሰራ እንደሆነ ከክልሉ የአካባቢ ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር በላይነህ አየለ ጋር ቆይታ አድርገናል::
ዶክተር በላይነህ አየለ እንደሚገልጹት ፤ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከሚሰራቸው ስራዎች መካከል የአካባቢ ጥበቃ፣ የተፈጥሮ ደኖችን የመጠበቅና የመንከባከብ ፤ የደን ሀብት ውጤቶችን መቆጣጠርና ፈቃድ መስጠት እና ፓርኮችንና ጥብቅ ደኖችን ማስተዳደርና መምራት ይገኙበታል::
በክልሉ የአካባቢ ጥበቃ ትኩረት የሚያደርገው በልማት ፕሮጀክቶች ላይ መሆኑን የሚገልጹት ዳይሬክተሩ፤ ፕሮጀክቶቹ በሚለሙበት አካባቢ በማህበረሰብ ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ ፤ አካባቢ ጋር የተጣጣሙ መሆናቸው ፤ ብክለት የሚፈጠር ከሆነ ማስቀረት ካልሆነ ለመቀነስ የሚቻልበት ሁኔታ ላይ እየተሰራ ይገኛሉ:: ፕሮጀክቶቹ በሚለሙበት አካባቢ ላይ ተጽፅኖ የሚደርስባቸውና ልዩ ፍላጎት ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ሃሳባቸው ስለመደመጡ ክትትል መደረጉን ፤ እንዲሁም በፕሮጀክቱ ምክንያት የሚፈናቀሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ካሉ በምን መልኩ ምላሽ አግኝተዋል የሚለውን በመጠየቅ፤ መስማማታቸው ሲረጋገጥ የአካባቢ ይሁንታ ፈቃድ ወይም ሰርተፊኬት የሚሰጥ መሆኑን ይገልጻሉ:: በዚህ ዓመት ከ2ሺህ በላይ ለሚሆኑ ፕሮጀክቶች በክልል፤ በዞንና በወረዳ ፍቃድ ተሰጥቷል::
የፍቃድ አሰጣጡ እንደፕሮጀክቱ ውስብስብነትና ባህሪይ በክልል፤ በዞን፤ በወረዳ የሚሰጥ ነው:: የአካባቢ ተጽፅኖ ፈቃድ (ኢንቫይሮመንታል ሰርተፊኬት) ያገኙ ፕሮጀክቶች አፈጻጸማቸው ምን ይመስላል ተብሎ ኦዲት የሚደረጉ መሆኑን ይጠቁማሉ:: የደረቅና የፈሳሽ ቆሻሻ አያያዛቸው፤ የሰራተኛ አያያዛቸው፤ ብክለትን ለመቆጣጠር እያከናወኑ ያለው ተግባር ፈቃድ ሲወስዱ የገቡት ግዴታ መፈጸማቸውንና አለመፈጸማቸውን ማረጋገጥ ስራ እየተሰራ መሆኑን ይገልጻሉ:: ከዚህ ጋር ተያይዞ በህብረተሰቡ በኩል የሚቀርቡ ብክለት ይወገድልን ጥቆማዎች በመቀበል፤ ጥቆማ የቀረበበትን አካባቢ በመቆጣጠር ኦዲት በማድረግ፤ የሚቆሙ ፕሮጀክቶች በማስቆም፤ በገንዘብ የሚቀጡ በመቅጣት ተገቢውን የእርምት እርምጃዎች የመውሰድ ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል::
በሀገር አቀፍ ደረጃ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ከፌዴራል የአካባቢ፤ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ጋር የሚፈራረሙ ደረጃውቸን ጠብቀው ፕሮጀክቶች አሉ የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ ከእነዚህም ውስጥ ሬድ ፕላስና ሬድ ኢንቪስትመንት ፕሮግራም( አርአይቲ) ፤ የኖርዌ ጃል ፎሮስት ጉርፕ እና ፤ ኬፍ ደብልዩ የመሳሳሉትን መጥቀስ ይቻላል:: በአጠቃላይ በክልሉ ከ55 ወረዳዎች በላይ በርካታ መዋለ ነዋይ እየፈሰሰባቸው የሚገኙ የአካባቢ ጥበቃና የደን ፕሮጀክቶች መኖራቸውን የሚናገሩት ዳይሬክተሩ፤ ፕሮጀክቶቹ የሚሰሩት ሦስት ዋናዋና ስራዎች አሉ:: እነዚህም የደን ልማት፣ የተጋጋጡ መሬቶችን በመዝጋት እንዲያገግሙ ማድረግና በአሳታፊ የደን አስተዳደር የአካባቢውን አርሶ አደሮች በማቀፍ ሲሆን፤ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በበላይ የመመራትና የማስተዳደር ስራን እንደሚሰራ ያስረዳሉ::
አካባቢ ጥበቃ ዙሪያ ከሚሰሩ ስራዎች ዋነኛው የህብረተሰብ ግንዛቤ መፍጠር ነው የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ የአካባቢ ጥበቃ ስራ የብዙ የህብረተሰብ ክፍል ርብርብ ይፈልጋል:: ‹እያንዳንዱ ሰው አካባቢውን ቢያጸዳ፤ ፋብሪካውን ንጹህ ቢያደርግ ሀገር ይጸዳል ይላሉ:: የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም፤ ወቅታዊ የሆኑ አጀንዳዎች በመምረጥ ፤ በሬዲዮ፣ በቴሌቪዥንና በበራሪ ወረቀቶች እንዲሁም የተለያዩ አጋጣሚዎች በመጠቀም ለህብረተሰቡ የግንዛቤ ትምህርት እየተሰጠ መሆኑን ይገልጻሉ::
ከአካባቢ ጥበቃ ጋር በተያያዘ ለየት ያሉ ክስተቶች ሲፈጠሩ የአካባቢ ጉስቁልና ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ለማወቅ ጥናት የሚደረግ መሆኑን የሚናገሩት ኃላፊው፤ ከጥናቱ በኋላ ወደ ፓርክ ወይም ጥብቅ ስፍራነት የሚካተት ደን ካለ ማህበረሰቡን በማወያየት የማካተት ስራ የሚሰራ መሆኑን ይገልጻሉ:: ከተለያዩ ፕሮጀክቶች ጋር በመሆን በጣም የተጎዱ አካባቢዎች ተከልለው እንዲጠበቁና የመሬት ገጽታውን እንዲቀይሩ እየተደረገ እንደሆነ ያብራራሉ::
በክልል ውስጥ ያሉ የተፈጥሮ ደኖችን ማስጠበቅና የአካባቢ ሥርዓት ምህዳር እንዲያገግም ትልቅ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ለማድረግ እየተሰራ ነው የሚሉት ዳይሬክተሩ:: ለአብነትም በክልሉ ከሚገኙ ትልልቅ ደኖች በወፍ ዋሻ ፤ በአለም ሳጋ ፤ በአራ ገዳም ፤ በጉባ ላፍቶ ወረዳ ፤ በደቡብ ወሎ፤ በአዊ ዞን በመሳሰሉት ላሉ በርካታ ትልልቅ የተፈጥሮ ደኖች ተገቢው በጀት በመመደብ እንዲጠበቁ ተደርጓል:: እነዚህ የተፈጥሮ ደኖች በአብዛኛው የአካባቢ የአየር ንብረት ለውጥ በመጠበቅ ፤ ሥርዓተ ምህዳሩ የተስተካከለ እንዲሆን ለማድረግ ይጠቅማሉ::
በክልሉ በቁጥር 30 የሚሆኑ በ90ሺህ ሄክታር ላይ የሚገኙ የተለያዩ ጥብቅ ደኖች አሉ:: ደኖቹ የሚጠበቁት ለብዝሃ ሕይወት ጥበቃ፤ የአካባቢውን ሥነ ምህዳር፤ ከደኖች አካባቢ ከፍተኛ የሆነ እርጥበት አዘል ወንዞች እንዲወርዱ፤ ምንጮች እንዲፈልቁ ነው ፤ እነዚህ ካልተጠበቁ በአካባቢው ላይ ጉስቁልና ሊከስት እንደሚችል ነው ዳይሬክተሩ የሚናገሩት::
በክልሉ የሰው ሰራሽ ደን መጠን እየጨመረ ነው የመጣው ለምሳሌ አዊ ዞን ብንመለከት ከአጠቃላይ የመሬት ሽፋኑ 70 በመቶ በላይ ደን መሆኑን ይጠቁማሉ:: ይህ የሚያሳየን ህዝቡ የሚተዳደር ደን መር ኢኮኖሚ ውጤታማ መሆኑን ነው:: ደን ከሚመረትበት ጊዜ ጀምሮና ተመርቶም ለተለያየ አገልግሎት በመዋል በአገሪቱ በተለያዩ ክልሎች ተዘዋወሮ እንዲሸጥ ይደረጋል:: ባለስልጣኑ ደኑ ከመቆረጡ በፊት፤ በአካባቢ ላይ የሚያደርሰው ጉዳት መኖሩን በመቆጣጠር በባለሙያዎች ታይቶ ፈቃድ እንደሚሰጥና ፤ ከተቆረጠ በኋላ ምርቱ በአግባቡ ከየት ወዴት እንደሚደርስ በመቆጣጠር የይለፍ ፈቃድ የሚሰጥ መሆኑን ይናገራሉ::
እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ፤ ባለስልጣኑ የደን ውጤቱን የሚገዛው ነጋዴ የሮያሊት ወይም የልማት ክፍያ እንዲከፍል ያደርጋል:: በዚህም መሰረት ከክልሉ በ2011 በጀት ዓመት ብቻ ከሮያሊት ክፍያ ወደ አንድ መቶ ሚሊዮን ብር ተሰብሰቧል:: የዘንድሮውም ከአምናው እንደማይተናነስ ይጠበቃል:: ክፍያውም ከአጣናና ከከሰል ሽያጭ ከመሳሰሉት የተሰበሰበ ሲሆን ለአካባቢው ልማት እንዲውል በማድረግ የአካባቢው ማህበረሰብ ደን በመልማቱ እንዲጠቀም ይደረጋል ብለዋል::
በክልሉ የሚገኙ ጥብቅ ስፍራዎች በአጠቃላይ የክልሉን 3 ፐርሰንት ይሸፍናሉ የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ በዚህም በሁለተኛ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ 2.8 ፐርሰንት የክልሉ የቆዳ ስፋት በጥብቅ ስፍራዎችና በፓርኮች ይሸፋናል በሚል የተያዘው እቅድ ከወዲሁ ግቡን መቷል ብለዋል::
በአማራ ክልል 11 የሚደርሱ ፓርኮችና ጥብቅ ደኖች አሉ:: ምሳሌ ቦረና ሳይንት ወረ ይመኑ ፓርክ፤ የወለቃ አባይ በቶ ብሔራዊ ፓርክ፤ ጎደቤ ብሔራዊ ፓርክ፤ የባኩሳ ብሔራዊ ፓርክ፤ አባይ ወንዝ ብሔራዊ ፓርክ ፤ የአቡነ ዮሴፍ ጥብቅ ስፍራ፤ የመንዝ ጓሳ ጥብቅ ስፍራ ፤ የጉና ጥብቅ ስፍራ ፤ የማህበረ ስላሴ ጥብቅ ስፍራ ዋና ዋናዎቹ ናቸው እነዚህን ማስተዳደርና መጠበቅ ስራ እየተሰራ መሆኑን የሚገልጹት ኃላፊው፤ የዱር እንስሳቶች እንዲረቡና እንዳይገደሉ በመጠበቅ፤ ህገወጥ የዱር እንስሳት ዝውውር ለመቆጣጠር ፤ ጥብቅ ስፍራዎች የበለጠ በደንብ ተጠብቀው ለአካባቢው ህብረተሰብ ሁለንተናዊ አገልግሎቶች እንዲሰጡ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል::
ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ በበላይነት የሚያስተባብረው አካባቢ ጥበቃ ነው የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ እያንዳንዱ ተቋም በተለይ ሙቀት አማቂ ጋዞችን የሚለቁ ተቋማት እንደ የግብርና ቢሮ፤ የእንስሳት ጥበቃና ልማት ባለስልጣን ፤ የኢንዱስትሪና አንቨስትመንት ቢሮ፤ የከተማ ልማት ቢሮ በሚሰሩት ማንኛውም አይነት ስራ የአየር ንብረት ተጋላጭነት በሚቀንስ መልኩ እንዲሰሩ የማሰልጠን፤ የመደገፍና የመከታተል ስራ እየተሰራ ይገኛል::
የኢንዱስትሪዎችና ፕሮጀክቶች ባለቤቶች የሚጠበቅባቸውን ግዴታዎች አለመወጣት፤ ጥብቅ ስፍራዎችና ፓርኮች አካባቢ ህገወጥ እንቅስቃሴ መኖር ፤ በተለይ ለውጡን ተከትሎ እየተከሰተ ያለው የመሬት ወረራ መስፋፋት ፤ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂን የሚተግበሩ ተቋማት በሚጠበቅባቸው መጠን ያለመስራት በዘርፉ በዋናነት የሚጠቀሱ ችግሮች ናቸው::
በአጠቃላይ ስለአካባቢ ጥበቃ ማህበረሰቡ ያለው ግንዛቤ አነስተኛ በመሆኑ ከፍተኛ ብክለት ይከሰታል የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ ህብረተሰቡ ዘንድ ቆሻሻ በአግባቡ አለማስወገድ፤ የተጠቀሙበትን ቁሳቁሶች የመወርወርና የፕላስቲክ ብክለት በየቦታው መኖሩንም ይገልጻሉ:: ለዘርፉ የሚሰጠው ትኩረት አነስተኛ መሆን፤ በመንግስት ቅድሚያ ጉዳይ ተደርጎ መሰራት ሲገባው የተሰጠው ትኩረት ላይ ክፍተቶች መኖራቸውና እንዲሁም የመዋቅር ችግር በመኖሩ ፤ የክልል አደረጃጀቱ ከዞንና ከወረዳ ጋር የተናበበ አለመሆኑም ተጨማሪ ተግዳሮቶች መሆናቸውን ይገልጻሉ::
የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ላለፉት 8 ዓመታት የጣና ሀይቅ የእምቦጭ አረምን በተመለከተ በርካታ ስራዎችን ሲሰራና ሲያስተባብር ቆይቷል:: ከዘንድሮ ጀምሮ ግን እራሱን የቻለ መስሪያ ቤት ተቋቋሟል:: የጣና ሐይቅን ለመጠበቅ በሚደረገው እንቅስቃሴ ህብረተሰቡ አስተዋጽኦ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን የሚገልጹት ዳይሬክተሩ፤ የጣና ሐይቅን መጠበቅ ብዙ ኃላፊነትን የሚጠይቅ ስራ ነው:: በፋይናንስ፣ በማቴሪያልና በእውቀት መደገፍ የሚጠይቅ በመሆኑ ህዝብ ከላይ እስከ ታች ከጎናችን መሆን አለበት ብለዋል::
ከኮቪድ 19 ቫይረስ ጋር በተያያዘ የዱር እንስሳቶችን ከሰው ጋር ንክኪ እንዳይኖራቸው በሁሉም ፓርኮችና ጥብቅ ስፍራዎች ቡድን በማሰማራት ልዩ እቅድ ታቅዶ እየተሰራ ነው የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ ሌላው ልዩ ትኩረት የተሰጠው ቫይረሱን ለመከላከል ለንጽህ መጠበቂያ አገልግሎት የዋሉ ቁሳቁሶች በአግባቡ ማስወገድ ነው:: የእጅ ጓንቶች፤ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭንብሎችና ሌሎች ቁሳቁሶች እንደማንኛውም ቆሻሻ ሳይሆን በጥንቃቄ መወገድ እንደሚገባቸውም ይጠቁማሉ:: ለዚህም በዳይሬክቶሬት የሚመራ የኮቪድ መከላከል አስተባባሪ በማቋቋም ወረዳ ላይ ባለሙያዎች እንዲቆጣጠሩ ተደርጓል:: በሚዲያዎች፤ በማህበራዊ ሚዲያና በመስክ በመገኘት በማስተማርና በመደገፍ ላይ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል::
የአካባቢ ጥበቃ ጉዳይ የህልውና ጉዳይ ነው የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ከፍተኛ የሆነ የአካባቢ ጎስቁልና እየተከሰተ ፤ አግባብ ባልሆነ መንገድ ቆሻሻ ያለቦታው የማስወገድ ጉዳይ እየተስተዋለ መሆኑንና ህገወጥ የፓርኮች ወረራ መኖራቸው ይጠቅሳሉ:: “የአካባቢ ጥበቃ ሀገርን አረንጓዴ የማድረግ የህልውና ጉዳይ መሆኑን ህዝቡ ተረድቶ የሚጠበቅበትን አስተዋፅኦ ማበርከት አለበት:: እያንዳንዱ ሰው አካባቢውን ቢያለማ፤ እያንዳንዱ አርሶ አደሩ አካባቢውን ከጉስቁልና ቢጠብቅ ሀገራችን ኢትዮጵያ ትበለጽጋለች፤ ስለሆነም ትልቁን ሚና መጫወት ያለበት ማህበረሰቡ ነው:: ማህበረሰቡ ከተንቀሳቀሰ ለአካባቢ ጥበቃ ንቁ ፤ተቆርቆሪና ጠባቂ መሆን ይችላል” ሲሉ ሃሳባቸውን ቋጭተዋል::
አዲስ ዘመን ሰኔ 1/2012
ወርቅነሽ ደምሰው