ብዙ ጊዜያቸውን በሥራ ነውና የሚያሳልፉት ፋታ የላቸውም ከሚባሉ ባለሙያዎች መካከል ይመደባሉ። የተረጋጋ ባህሪያ ያላቸው ሲሆን፤ አነጋገራቸው ደግሞ ቁጥብ ነው። በሙያቸው ያገኙትን ልምድ ለሌሎች ማካፈል እንደሚወዱ ደግሞ የሚያውቋቸው ይመሰክራሉ። ባለታሪካችን በወጣትነት እድሜያቸው ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች የሥራ እድልን መፍጠር የቻሉ የሕክምና ባለሙያ ናቸው። እንግዳችን ዶክተር አሚር ነጌሶ ይባላሉ።
ዶክተር አሚር የተወለዱት በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ አርሲ ዞን ከሻሸመኔ ከተማ አቅራቢያ በምትገኘው ነገሌ ሚጠማ የተባለች አካባቢ ነው። ለቤተሰባቸው ሁለተኛ ልጅ ናቸው። አባታቸው አቶ ነጌሴ ሴንጢ በመምህርነት ሙያ የተሰማሩ በመሆናቸው ከቦታ ቦታ በተመደቡበት አካባቢ ሲዘዋወሩ ቤተሰባቸውን ይዘው ነበር የሚጓዙት። እናም ሄረሮ ወደተባለች የገጠር መንደር ሲዘዋወሩ የሶስት ዓመት ህጻን የነበሩት የአሁኑ ዶክተር አሚር አብረው ወደ ሄረሮ ተጓዙ።
በከተማዋም የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን መከታተል የጀመሩት ዶክተር አሚር በወቅቱ አባታቸው ከትምህርት መልስ ያለውን ሰዓት በጥናት ብቻ እንዲያሳልፉ ስለሚፈልጉ አብዛኛውን ጊዜ በንባብ ያሳልፉ እንደነበር ያስታውሳሉ። በወቅቱ ለሒሳብ ትምህርት ልዩ ፍላጎት ስለነበራቸው እንደአባታቸው መምህር በመሆን ሂሳብ ስለማስተማር ያልሙ እንደነበር አይዘነጉትም። በሄረሮ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እስከ አራተኛ ክፍል ከተማሩ በኋላ ደግሞ አሁንም አባታቸው ወደዶዶላ በወዛወራቸው አብረው ተጓዙ።
በዶዶላም ከአምስተኛ ክፍል እስከ 10ኛ ክፍል ድረስ ከተማሩ በኋላ ጊዜው የትምህርት ፖሊሲው ከ10ኛ ክፍል የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ማጠናቀቂያ ፈተና የሚሰጡበት ነበርና ፈተናውን በብቃት አለፉ። እናም ዶክተር አሚርም ወደመሰናዶ ትምህርት ገብተው የተፈጥሮ ሳይንስ ዘርፍን ምርጫቸው አደረጉ።
በልጅነት የነበራቸው የሒሳብ ትምህርት ፍቅር እና የመምህርነት ሙያ ራዕይ ሲያድጉ ወደባይሎጂ እና ኬሚስትሪ ትምህርቶች በመቀየሩ ወደጤናው ሳይንስ ለመግባት ፍላጎት እንዳሳደረባቸው አይዘነጉትም።
በዶዶላም የተፈጥሮ ሳይንስ መሰናዶ ትምህርት አጠናቀው የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተናውን በጥሩ ውጤት አጠናቀቁ። እናም የከፍተኛ ትምህርት ምርጫቸው ጤና ሳይንስ ዩኒቨርሲቲው ደግሞ አዲስ አበባ ምርጫቸው አድርገው ፎርም ሞሉ። በወቅቱ ውጤታቸው ደግሞ ከፍተኛ በመሆኑ በቀጥታ ምርጫቸውን መሰረት ተደርጎ የጤና ሳይንስ ትምህርቱን እንዲከታተሉ እድሉን አገኙ።
እናም የጤና ሳይንስን ለመማር አዲስ አበባ በ1996 ዓ.ም ሲገቡ በመጀመሪያ የተመደቡት በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ነበር። በወቅቱ ገና በመጀመሪያዎቹ የወጣትነት እደሜያቸው ማለትም በ17 ዓመታቸው ከቤተሰብ ተለይተው መኖሩ የግድ ነበርና ለእርሳቸው ጥቂት አስቸግሯቸው ነበር። ይሁንና አይለመድ የለ የቤተሰብ ናፍቆቱንም ሆነ ከዘመድ ርቆ መማሩን እየለመዱት በመምጣታቸው ትምህርታቸው ላይ ብቻ ማተኮሩን ተያያዙት። ለዚህ ጥንካሬያቸው ደግሞ የአባታቸው የሞራል ድጋፍ ቁልፍ ሚና እንደነበረው ዶክተር አሚር ያስታውሳሉ።
ጥቀር አንበሳ እየተማሩ ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የተማሪዎች ማደሪያ ነበርና እየተመላለሱ ዕውቀት መሸመቱን ቀጠሉበት። የህክምና ሳይንስ ትምህርቱን እየተከታተሉ ደግሞ አንዳንዱ ወደራዲዮሎጂ ሌላው ወደህጻናት ህክምና ሲገባ እርሳቸው ደግሞ የጥርስ ህክምናን ምርጫቸው አደረጉ።
በወቅቱ ኢትዮጵያ ውስጥ የነበሩ የጥርስ ሐኪሞች 50 ብቻ በመሆናቸው እና የህክምናው ዘርፍ ብዙም ያልተሰራበት መሆኑን ታዝበዋል። በተጨማሪም ሰዎችን ሲያማክሩ የጥርስ ህክምና ተመራጭ ቢያደርጉ ውጤታማ እንደሚሆኑ እና በርካቶችንም ማገልገል እንደሚችሉ ስለገለጹላቸው በሙያው ለማገልገል የነበራቸውን ፍላጎት አናረው። እናም ትዝብታቸውን እና የሰዎችን ምክር ምክንያት አድርገው የጥርስ ህክምናን መምረጣቸው በፍላጎት የተከወነ ጉዳይ እንደነበር የኋሊት በትዝታ ተጉዘው ያስታውሱታል።
እናም የመረጡትን የህክምና ሙያ ለመማር የካቲት 12 ሆስፒታል ጀርባ የሚገኘው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጥርስ ህክምና ትምህርት ቤት ገቡ። በወቅቱ በጥርስ ህክምና ትምህርት ቤቱ የመጀመሪያ ተማሪዎች መካከል ስለነበሩ ትምህርታቸውን እንኳን ሳይጨርሱ የግል ጥርስ ህክምና ክሊኖኮች ዘንድ በትርፍ ሰዓታቸው መስራት ጀምረው ነበር።
አስፈላጊውን የጥርስ ህክምና ትምህርት በጥሩ ውጤት አጠናቀው በ1998 ዓ.ም ሲመረቁ ደግሞ በተማሩበት ዩኒቨርሲቲ ግቢ አስተማሪ እንዲሆኑ ተመረጡ። በወቅቱ ለመጀመሪያ የመንግሥት ቅጥር ሥራቸው የሚከፈላቸው የወር ደመወዝ ደግሞ 980 ብር እንደነበር በፈገግታ ታጅበው ያስታውሱታል። ይሁንና በተለያዩ ክሊኒኮች ዘንድ ጎራ በማለት ከመንግሥት ሥራ ሰዓት ውጪ መስራቱን ደግሞ አላቋረጡም ነበር።
በዚህ ሁኔታ ላይ እያሉ ታዲያ ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝ ሆስፒታል ውስጥ ትምህርታቸውን ከፍ የሚያደርጉበትን እድል አገኙ። በጥርስ ህክምናው ሙያ ትምህርታቸውን በመግፋት ደግሞ በ2003 ዓ.ም ዶክትሬታቸውን አግኝተዋል። ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ የማስተማር ሥራቸውም እንደቀጠለ ነው።
የእያንዷንዷ ቀን ሥራ ትምህርት የሚገኝባት መሆኗን የተገነዘቡት ዶክተር አሚር፤ ወደክሊኒኮች ጎራ ብለው ህክምና በሚሰጡበት ወቅት የተለያዩ ክፍተቶችን መመልከታቸው አልቀረም። አንዱ ጋር በቂ መሳሪያ ሳይኖር ሌላው ጋር ደግሞ የባለሙያ እጥረት መኖሩን ይታዘባሉ። እናም ህብረተሰቡ በርካታ የጥርስ ህክምና ክሊኒኮች እና የተደራጁ ማዕከላት እንደሚያስፈልጉ በማመናቸው የእራሳቸውን ህክምና መስጫ ለመክፈት ልባቸው ፈልጓል።
የህክምና ማዕከል ውጥናቸውን ይዘውም አዲስ አበባ ፒያሳ አትክልት ተራ አካባቢ የሚገኘው ከሊፋ ህንጻ ጎራ አሉ። ለጥርስ ህክምና የሚሆን አንድ ሙሉ ወለል ለመከራየት እንደሚፈልጉም ሃሳባቸውን ገለጹ። ይሁንና የህንጻው አከራዮች ከፍተኛ አቅም ላላቸው ተቋማት ወለሉን ለማከራየት በማቀዳቸው ለዶክተር አሚር ጥያቄ ብዙም ቦታ አልሰጡትም ነበር።
ዶክተር አሚር ለግል ሥራቸው በመረጡት ቦታ ኪራይ ባለማግኘታቸው ጉዳዩን ጋብ አድርገው መደበኛ ሥራቸው ላይ አተኩረዋል። አንድ ቀን ግን የእጅ ስልካቸው አቃጨለች። የከሊፋ ህንጻ ላይ የጠየቁትን ወለል መከራየት ስለሚችሉ መምጣት ይችላሉ የሚል ድንገቴ ብስራት ከወዲያኛው የስልኩ ጫፍ ደረሳቸው። ሄደውም 17 ሺ ብር የወር ኪራይ ለመክፈል ስምምነት አደረጉ።
ሁኔታው ያላሰቡት አጋጣሚ ቢሆንም ግን ዶክተር አሚር አስፈላጊውን መስፈርት እና መጠነኛ መሳሪያዎችን አሟልተው ሥራው ተጀመረ። ዶክተር አሚር ማስታወቂያም በሚገባ አሰሩ። በተጨማሪም ቀድሞ የሚያውቋቸው ሰዎች መካከለኛ ክሊኒክ መክፈታቸውን ሲያውቁ ወደእርሳቸው በመምጣታቸው የግል ክሊኒክ ሥራ በጀመሩባቸው ጊዜያት በደንበኛ ዕጦትም ሆነ በገቢ ደረጃ አልተቸገሩም ነበር።
ቀስ በቀስም የባለሙያ ቁጥርም ሆነ መሳሪያዎችን እያሳደጉ ህክምናውን ቀጠሉበት። የግል ጥርስ ህክምና ከከፈቱ ከሁለት ዓመታት በኋላ ደግሞ ከውጭ ሀገራት የጥርስ ህክምና ማሽኖችን በማስመጣት ጭምር ሥራቸውን እያደራጁ እና ተጨማሪ ባለሙያዎችንም እየቀጠሩ ክሊኒካቸውንም አጠናከሩ። አንድ የነበረውን የህክምና ክፍል ወደሶስት በማድረስም በአንድ ጊዜ ለበርካቶች አገልግሎት ወደመስጠቱም ተሸጋገሩ። በዚህ ወቅት ክሊኒካቸው ወደስፔሻሊስት ህክምና ተቋምነት ለማደግ ማንም አልከለከለውም።
በዚህ ሁሉ መሃል ደግሞ ለሥራ ጉዳይ ወደአዳማ ከተማ ማቅናታቸውንና በወቅቱ በርካታ ሰዎች የጥርስ ህክምና ሲፈልጉ ማየታቸውን ይናገራሉ። በተለይ በስምጥ ሸለቆ የኢትዮጵያ ክፍል የሚገኙ ዜጎች ጥርሳቸው በፍሎራይድ ውሃ የተጠቃ በመሆኑ ህክምና የሚፈልጉ ዜጎች በስፋት መኖራቸውን ታዝበዋል። እናም አዳማ ከተማ ላይ የጥርስ ክሊኒክ ከፍተው በአቅማቸው የበኩላቸውን ሚና መወጣት እንዳለባቸው ወሰኑ።
ወስነውም አልቀረ አዳማ ከተማ የድሮው መናኸሪያ አጠገብ በተከራዩት ህንጻ ላይ የተደራጀ የጥርስ ህክምን ክሊኒክ ከፍተው ባለሙያዎችንም ቀጠሩ። በፍሎራይድ የተጠቁ እና የተለያየ የጥርስ ችግር ያለባቸውን ሰዎች በማከም አሁንም በማገልገል ላይ ናቸው።
ዶክተር አሚር በክልል ከተሞች ከከፈቱት የመጀመሪያ ቅርንጫፍ በዘለለ በአዲስ አበባም ተጨማሪ ክሊኒክ ወደመክፈቱም ተሸጋገሩ። በአዲስ አበባ 22 አካባቢ ሌክስ ፕላዛ ህንጻ ላይ ከሶስት ዓመት በፊት በተከራዩት ቦታ ዘመናዊ የጥርስ ህክምና አገልግሎቶችን መስጠት ጀምረው ነበር። ይሁንና ከማስተማር ሥራቸው እና ከግል ክሊኒኮቻቸው ቁጥጥር ሥራ ጋር በተያያዘ የሌክስ ፕላዛውን ቅርንጫፍ በአግባቡ ለማስተዳደር መቸገራቸው አልቀረም።
አካባቢው ከጥቂት ዓመታት በፊት ለባቡር መንገድ በሚል በመቆፋፈሩ ምክንያት ወደክሊኒኩ ሲያቀኑ ይቸገሩ እንደነበር ያስታውሳሉ። በተጨማሪ ከሥራ ቦታዎቻቸው እና ከመኖሪያቸው የራቀ ቦታ በመሆኑ ክሊኒኩን ወደሌላ ቦታ ማዘዋወር እንዳለባቸው ተረድተዋል። በዚህ መሰረት የሌክስ ፕላዛውን ክሊኒክ በኦዲተር ሒሳቡን አዘግተው ወደቤተል አካባቢ እንዲዛወር አደረጉ።
ቤተል አደባባዩ አጠገብ በተከራዩት ቢሮ የጥርስ ህክምና በመስጠት ላይ ናቸው። መኖሪያ ቤታቸው ደግሞ ቤተል አካባቢ በመሆኑ ለማስተዳደሩም ሆነ ቁጥጥር ለማድረጉ ይበልጥ ተመቻቸላቸው።
ከአንድ የተነሳው የዶክተር አሚር የጥርስ ህክምና ክሊኒክ አሁን ላይ አራተኛ ቅርንጫፍ ላይ ደርሷል። ከአንድ ዓመት በፊት አዳማ ከተማ መብራት ኃይል በተባለው አካባቢ በዘመናዊ መሳሪያዎች የተደራጀ ተጨማሪ ክሊኒክ በመክፈት በዘርፉ ያላቸውን ተሳትፎ ከፍ አድርገዋል። በጥርስ ህክምና መስጫዎቻቸው አሁን ላይ ከብሬስ ሥራ ጀምሮ እስከ መንጋጋ ስብራት እንዲሁም ጥርስ መትከልና ቀዶ ጥገና የደረሱ ህክምናዎችን በመስጠት ላይ ናቸው። አጠቃላይ የጥርስ እና የአፍ ውስጥ ህክምናዎችን በተለያዩ ባለሙያዎች እየሰጡ ይገኛል።
ለሥራቸው የሚሆኑ እንደ ኤክስሬይ እና የጥርስ ህክምና ላብራቶሪዎችን እና በርካታ የጥርስ ህክምና ወንበሮችንም/ ዴንታል ቼይር/ ይዘው አገልግሎት በመስጠት ላይ ናቸው። የተወላገደ ጥርስ በብሬስ ለማከም ከአንድ ዓመት ተኩል እስከ ሶስት ዓመት ሊወስድ እንደሚችል የሚናገሩት ዶክተር አሚር ለዚህ ሥራ ደግሞ ከስድስት ሺህ ብር እስከ 12 ሺህ ብር በአማካይ ያስከፍላሉ።
አሁን ላይ በአጠቃላይ በዶክተር አሚር ሥር በሚገኙ በጥርስ ህክምና መስጫዎች ለ36 ሰራተኞች የሥራ እድል መፍጠር ችለዋል። ከዚህ ውስጥ ደግሞ ገሚሶቹ የጥርስ ሐኪሞች እና ነርሶች ናቸው።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የማስተማሩንም ሥራ ሆነ የግል ህክምና ሙያውን ጎን ለጎን እያስኬዱ የሚገኙት የአርሲው የህክምና ባለሙያ የነገ እቅዳቸው ሰፊ ነው። በተለይ በኢትዮጵያ የጥርስ ህክምና ሆስፒታል ገንብተው በእራሳቸው ህንጻ ላይ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት እያደረጉ ነው። ከዚህ ባለፈ ግን በዘርፉ ብቁ ባለሙያዎችን ለማፍራት የሚያስችል የትምህርት ማዕከልም የመክፈት ውጥን አላቸው።
<<እኔ በወጣትነት እድሜዬም ቢሆን ጊዜዬን በሚገባ ስለምጠቀምበት የተሻለ ደረጃ ለመድረስ አልተቸገርኩም>> የሚሉት ዶክተር አሚር፤ እያንዳንዱ ወጣት የጊዜ አጠቃቀሙን ውጤታማ ማድረግ ከቻለ ስኬታማ የማይሆንበት ምክንያት የለም ይላሉ።
እንደ እርሳቸው፤ ወጣትነት ለሁሉም የሚበቃ ጊዜ አለው፤ ለመዝናናቱም ሆነ ለመስራቱም ቢሆን የወጣትነት እድሜ ምቹ ነው፤ ነገር ግን አብዛኛውን ጊዜ በሥራ በማሳለፍ ለቀጣዩ ህይወት ስንቅ መያዝ ሊረሳ የማይገባው ጉዳይ ነው። ለነገ የሚባል የሥራ ቀጠሮን መጠቀም ተገቢ አይደለም ፤ ወሳኙን ሥራ ዛሬ ላይ አከናውኖ በማለፍ አላማን ማሳካት ይገባል የሚለው ደግሞ ምክራቸው ነው። ቸር እንሰንብት!!
አዲስ ዘመን ግንቦት 29/2012
ጌትነት ተስፋማርያም