ደን ለሰው ልጆችም ሆነ ለእንስሳት የመኖር ህልውና እጅግ ወሳኝ ነው። የአፈር መከላት፤ የበረሃማነት መስፋፋት፤ የብዝሐ ሕይወት መመናመንን ለመግታት፤ ምርትና ምርታማነትን ለማስቀጠል፤ የቱሪዝም መስህብ በመሆን ደን ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋል። ደን ዓለም አቀፍ ሀብት ነው። ደንን በማልማት የከርሰ ምድር ውሃን በአስተማማኝ ደረጃ ለማግኘት፤ የአካባቢውን ሥነ ምህዳር በመጠበቅ ምርታማነትን ለማሳደግና ወደ አካባቢ አየር የሚለቀቀውን የካርቦንዳይኦክሳይድ መጠን በመቀነስ ንፁህ አየር ለማግኘት እንዲሁም ድርቅና የተለያዩ በሽታዎችን ለመከላከል ይረዳል። ደኖች ከሚሰጡት እጅግ ሰፊ ጥቅም የተነሳ ለአገር እድገት ወሳኝ ናቸው። በዚህ ዙሪያ የኢትዮጵያ የአካባቢና የደን ምርምር ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር አጌና አንጅሎ ጋር ቆይታ አድርገናል።
ዶክተር አጌና አንጅሎ እንደሚገልጹት፤ ደን ማለት በግማሽ ሄክታር መሬት ላይ የሚገኝ ዛፎች ያሉበት፣ ቢያንስ የቦታው 20 በመቶ በዛፍ የተሸፈነ እንዲሁም የዛፎቹ ቁመት ሁለት ሜትር የሆነ ነው። በአገራችን አሁኑ ወቅት ያለው የደን ሽፋን 15.5 በመቶ የሚገመት ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ በርካታዎቹ የቆላ ደኖች ናቸው። ደረቅና እርጥብ የሚባሉ ደኖች፤ አፍሮ ማውንቴንና ቤተክርስቲያን አካባቢ ያሉ ተፈጥሮ ደኖች በደቡብ ምዕራብ በባሌና በግሼን አካባቢ የሚገኙትን የሚያካትት ነው።
በተከላ የተሸፈኑት ደኖች ከ30 ዓመት በፊት በ1ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ የተተከሉ ናቸው። እነዚህም አሁን ላይ በብዙ ቦታዎች ለጣውላ አገልግሎት እየዋሉ ይገኛሉ። ቀደም ሲልም ጀምሮ የደን ተከላዎች እየተካሄዱ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በየቦታው ደን ይተከላል። ነገር ግን ደን ተብሎ በሰፊው የተከለለ እውቅና ያለው ወይም አንድ የማኔጀመንት ዩኒት ደን የማልማት ሥራ ብዙም እየተሰራ አይደለም። የአፈር መከላትና የተፈጥሮ መጎሳቆልን ለመከላከል የሚተከሉ ዛፎች መኖራቸው ሥነምህዳር ላይ የሚከተለውን ጉዳት ከመከላከል አንጻር ጥቅም እንዳላቸው ነው ዶክተር አጌና የሚናገሩት።
በየዓመቱ የችግኝ ተከላ በመጀመሪያውና በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ሲከናወን መቆየቱን የሚናገሩት ዶክተሩ፤ ይሁን እንጂ ከአደረጃጀት ጋር ተያይዞ ኃላፊነቱ የተሰጠው ለክልሎች ነው። በመሆኑ ክልሎች በሕገ መንግሥቱ የተሰጣቸውን ሥልጣን በመጠቀም የራሳቸውን ደን የማልማት፤ ያላቸውን መሬት በመጠበቅ በመንከባከብ የአካባቢ የደን ሽፋኑን ለመጨመር፤ ከተፈጥሮ መዛባት ለመጠበቅ፤ በየዓመቱ ችግኖች እያፈሉ እንደሚተክሉ ይገልጻሉ።
በርካቶቹ ችግኞች አርሶ አደሩ የሚተክላቸው በግብርና አካባቢዎች ላይ ነው የሚያርፉት፤ አነስተኛ የሚባሉት አርሶ አደሩ በአነስተኛ መሬት ላይ ለማገዶ፤ ለቤት መስሪያ፤ ለገበያ ምርት የሚተክላቸው በርካታ ተከላዎች በመኖራቸው የዚህ ሁሉ ገበሬ በአንድ ላይ ሲስላ ብዙ ሄክታር እንደሚሆን ይጠቁማሉ። ከዚህ ሌላም በወል መሬት ላይ የሚተከሉ አሉ። በእነዚህ የወል መሬቶች በሀገር ደረጃ በጣም የተጎዱ መሬቶች ላይ ነው የሚያርፉት ምክንያቱም የወል መሬቶች ብዙ ጥበቃ አይደረግላቸውም፤ ተንከባካቢ የላቸውም፤ ብዙ ጊዜም የተጎሳቆሉ ናቸው። ከብት ይለቀቅባቸዋል፤ የተጋጋጡ ናቸው፤ አፈራቸው አይጠበቅም። የአፈር ውሃ ጥበቃ ቢሰራላቸውም ተከታታይ የሆነ እንክብካቤ የማይደረግላቸው በመሆኑ እነዚህ ቦታዎች ላይ የተተከሉ ዛፎች ብዙ ጊዜ ጽድቀታቸው ከእንክብካቤ አንጻር ዝግ የሚል መሆኑን ያስረዳሉ።
ዶክተር አጌና አንጅሎ እንደሚገልጹት፤ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከ2011 ክረምት ጀምሮ እየመሩት ባለው የአረንጓዴ ልማት ሌጋሲ የተተከሉ ደኖች የተለዩ ደኖች እንዲኖር አስተዋፅኦ ሊያበረክት ይሆናል። ኅብረተሰቡ የበለጠ ተበረታቶ በደን ዙሪያ ያለውን ግንዛቤ ከፍ አድርጎ ቢተክል ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው። ክልሎች የደን መሬት ብለው ለይተው፤ ለሌላ ነገር እንዳይውል አድርገው፤ ስም ያለው ደን በማልማት ለምሳሌ እንደ የመናገሻ ሱባ፤ የጭልሞ፤ በርካታ ደኖች፤ በደቡብ ምዕራብ አካባቢ ያሉ ደኖችን ማፍራት የሚቻል መሆኑን ይጠቅሳሉ። የተከላ ደኖችም እንዲሁ ስም ያለው ደን ፈጥረው ዘንድሮ የተተከለው ዛፍ የዛሬ አስራ አምስት ዓመት ገደማ ለሀገሪቱ ከፍተኛ የሆነ የእንጨት ምርት ያቀርባል። ይሄ በጣም በብዙ ሚሊዮን ዶላር ከውጭ የምናስገባውን የእንጨት ውጤቶች ሊያስቀር የሚችል ነው።
ደን በአጭር ጊዜ የማይደርስ፤ ብዙ ዓመታትን የሚፈጅ በመሆኑ በአግባቡ መጠበቅና መንከባከብ ከተከላ በላይ ይጠቅማል የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ ደን የሚተከለው ካለው የተፈጥሮ ዕድገት ሁኔታ በተለያየ ሥነምህዳር፤ ደረቅ፤ ድንጋያማ እንክብካቤ በሌለበት መሬት ላይ በመሆኑም ብዙ ዓመት ፈጅቶ ነው ደን የሚሆነው። በሌሎች ሀገሮች ጥሩ መሬት ላይ በምርትነት የሚተከል ደን ልክ እንደ ሰብል በጥልቅ አፈርና እርጥበት ሊይዝ የሚችል መሬት ላይ የሚተከል በመሆኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ምርታማ ደን ሊደርስ ይችላል። ደኑ ልክ እንደማንኛውም ሰብል ተመርቶ፤ ታጭዶ እንደሚወሰድ በተወሰነ ዓመት እየታጨደ፤ በዚያ ቦታ ላይ ምትክ ደግሞሌላ እየተተከለ የሚሄድበት አግባብ መኖሩን ገልጸው፤ ይህንንም የአማራ ደን ኢንተርፕራይዝና የኦሮሚያ ደንና ዱር እንስሳት ኢንተርፕራይዝ በሰፊው እየሰሩት መሆኑን ያብራራሉ።
ከዚሁ ጋር ተይይዞ ኢንስትቲዩቱ፤ በየክልሎች ባሉት የምርምር ማዕከላት በኩል ከዘር አቅርቦት ጀምሮ አስፈላጊውን ዓይነት የቴክኒክ ድጋፍ ከማድረግ አንጸር እየሰራ ነው የሚሉት ዶክተሩ፤ በምርምሮች በሀገር ውስጥ ያሉትን የተለያዩ የዛፍ ዝርያዎች በምን መልኩ፤ የት ቦታ ላይ ቢተከሉ ቶሎ ይደርሳሉ ተብለው እየተሞከሩ ነው። በአገራችን በርካታ ዓይነት ዛፎች ያሉ ሲሆን እነዚህኑ ከደቡብ ምዕራብ አካባቢ ወደ ሌሎች አካባቢዎች የማስፋፋት ሥራ እየተሰራ መሆኑን ይገልጻሉ። ‹ጥሩ፣ ምርታማና ውጤታማ የሆኑ ዛፎች አሉ፤ በእነዚህም በቀጣይ ረጅም ዓመታት የሚሰሩባቸው ነው የሚሆነው›። አዳዲስ ዝርያዎችን ከውጭ በማምጣት የማለማመድ፤ ከደኖች ላይ የሚገኝ የተለያዩ የደን ውጤቶችን የተሻለ አጠቃቀም እንዲኖራቸው በማድረግ፤ ኅብረተሰቡ የሚጠቀምባቸውን እንጨት የሆኑና ያልሆኑ ተብለው ተለይተው የሚሰሩ የምርምር ሥራዎች መኖራቸውን ይጠቁማሉ። የእነዚህን ውጤቶችም እንደ ጣውላ፤ቺፕውድ፤ ዓይነቶች ከምን ጋር ተሰባጥረው ቢዘጋጁ ውጤታማ ይሆናሉ በሚል የምርምር ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
ስለ ደን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንደ ዶክተሩ ማብራሪያ፤ ደን ከሌለ የእርሻ ምርታማነት ምን ያህል እንደሚጎዳ የተሰሩ ጥናቶች ያመላክታሉ። ደን የሌለበት አካባቢ ላይ ውሃ የለም፤ደን የመስኖ ውሃ እንዲመጣም አስተዋዕኦ አለው። ሥነምህዳሩን ያቀዘቅዛል። ካደገ በኋላ ውስጡ ለከብቶች የግጦሽ ቦታ ይሆናል በማለት ብዙ የሥነምህዳር አገልግሎቶች እንዳሉት ይጠቅሳሉ። ለኅብረተሰቡ ከሚሰጠው የመስብህነት አገልግሎት በተጨማሪ አሁን ላይ አርሶ አደሩ የእርሻ መሬቱን፤ ምርትና ምርታማነቱ ዝቅ ስላለ የደን ዛፍ ቢተክልበት በየዓመቱ ከእርሻ ከሚገኘው በሦስትና አራት ዓመት ጠብቄ ደኑ ከደረሰልኝ አንዴ ቆርጩ የማገኘው ጥቅም ይበልጣል ብሎ ሂሳብ መስራት ጀምሯል ይላሉ።
ለፈጣን አገልግሎት የሚውሉ የቀርከሃ ዝርያዎች አሉ። በእኛ ሀገር ፈጣን ዛፍ የሚባለው የፈረንጅ ጥድ ነው። ሀገር በቀል ከሆኑ ዛፎቻችን ውስጥ ፈጣን ለጣውላ ቶሎ የሚደርስ ዋንዛ ሲሆን በአርሶ አደሩ መሬት ላይ በስፋት ይገኛል። ብዙዎች ለሀገር ውስጥ ገበያ የሚመረተውን የጣውላ ምርት የሚያዘጋጁት ከዋንዛ ነው። ዶክተር አጌና እንደሚሉት ባህር ዛፍ ለጣውልነት እንዲውል ለማስተማር ዝግጅት ላይ ይገኛሉ። ከዚህ የተሻለ ባህሪ ያላቸው የግራንድስ ባህርዛፍ ሀገራችን ውስጥ የሚገኝ በጣም ረጅም ቁመት ያለው፤ ከ30 -40 ሜትር ቁመት ስላለው አንዱ በርካታ ጣውላዎችን ማውጣት ይቻላል። ሳሊና የሚባል ዝርያ ከውጭ በማስገባት ለረጅም ጊዜ ያላመድነው የጣውላ ባህር ዛፍ በመሆኑ ባህሪያቸውን በማጥናት ከውጭ ከማስገባት ይልቅ በእነዚህ በመጠቀም ውጤታማ የሆነ ሥራ መስራት ያስችላል። ከዚህ አንጻር አርሶ አደሩ ተክሎ ተጠቃሚ እንዲሆን የሚያስችል ቴክኖሎጂ እየተሰራ መሆኑንም ይናገራሉ።
ደኖች ከእርሻው ባልተናነስ መልኩ ጠቀሜታቸው እጅግ ከፍተኛ ነው የሚሉት ዶክተሩ፤ ባህርዛፍ በማምረት አርሶ አደሩ መጠቀምና ሌሎችንም ዛፎች አምርቶ ለገበያ ቢያቀርብ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ መሆን ያስችላል። በተለይ የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ትልቅ ትርጉም ያለው ዛፍ ነው። በሌሎች ሀገራት ዛፍን ተክለው ከ40 እስከ 60 ዓመታት ይጠብቃሉ፤ ዛፍንም የሚተክሉት ለልጅ ልጅ እንዲተላለፍ አድርገው ነው። ለዚህም ማሳያ የሚሆነው ወደ ሀገራችን ከውጭ የምናስገባው ጣውላ 40 እና 50 ዓመት የቆየ ዛፍ መሆኑን ይጠቁማሉ።
እንደ ዶክተር አጌና አንጅሎ ገለጻ፤ እኛ ሀገር ትኩረት ተሰጥቶት ከተሰራ፤ ከሃያ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ሁሉንም የእንጨት ዓይነቶች ማግኘት እንችላለን። በዚህም በቅርብ ጊዜ ውስጥ ሀገራችን ከደኑ ዘርፍ ከየትኛውም ዘርፍ ከምታገኘው ገቢ ያላነሰ ማግኘት የምትችል መሆኑንም ይጠቁማሉ። የኢህአዴግ መንግሥት ከመጣ በኋላ እንኳን የተተከለ ሰፊ ደን ቢኖር፤ አሁን ላይ በጣም ብዙ ገቢ እናገኝበት ነበር፤ ነገር ግን ይህ አልሆነም። አሁንም በየቦታ በየክልሉ ስም ያለው ደን ሊኖረን ይገባል። ሰፊ መሬት ቢኖረንም ትልቁ ችግር ለደን ብሎ ማስቀመጡ እንደሆነ ይናገራሉ።
የደን ሥርዓት በእቅድ የሚመራ መሆን አለበት። ደን ይታቀዳል፤ በጀት ይያዝለታል፤ በባለሙያ ዝግጅት ይደረጋል፤ ይተከላል፤ እንክብካቤ፤ ይደረግለታል፤ ይመረታል የሚሉት ዶክተር አጌና፤ የደን ሳይንስ እውቀት ባለው ባለሙያ ሊመራ የሚገባ ዘርፍም ነው። ይህ ማለት በአንድ ጊዜ ሰፊ ቦታ ለመሸፈን የሚያደርግ ርብርብና የሰው ኃይል ያስፈልገዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደመሩት ዓይነት ትልቅ ትርጉም ያለው ንቅናቄም እጅግ አስፈላጊ ነው። ክልሎች ከመሬታቸው የደን መሬት ብለው ቢለዩ፤ ለነገ ምርታማ የሚሆን፤- አፈርና ውሃ ሊጠብቅ የሚችል፣ የደን እርሻ ስብጥር ወይንም አግሮ ፎረስት የምንለው ለዚያ የሚሆን የፍራፍሬ ዛፍን፤ የመኖ ዛፍ ያካተተ በተለይም በአርሶ አደሩ ማሳ ላይ በተለያዩ መንገዶች ቢተከሉ ውጤታማ መሆን የሚችሉና የሚበረታቱ መሆኑን ይገልጻሉ።
‹ኢትዮጵያ የማስባት የደን ሀገር እንደትሆነው ነው› የሚሉት ዶክተሩ፤ ሰፊ ለደን የሚሆን መሬት፤ ብዙ ያልተነኩ ያልተሰሩ ተራራዎችም አሉ። እነዚህ ተራሮች ተጋግጠዋል። በተለይ ሰሜንና ሰሜን ምሥራቅ አካባቢ ምዕራብ ኢትዮጵያን ጨምሮ የሐረርጌ፤ ከፍተኛ ቦታዎች ሁሉ በርካታ ቦታዎች ደን ላይ መሰራት እንዳለበት ይጠቁማሉ። ልክ እርሻ መካናይዝድ የሆነ ማሽን እንደሚፈልገው ሁሉ ደንም ተራሮቹ በአግባቡ ለደን ተከላ የሚያመቹ ሆነው እንዲዘጋጁ እርጥበት እንዲይዙ የአፈር ውሃ ጥበቃ በማሽነሪ ቢሰራ ብዙ ተራሮቻችን ሰው ደርሶ ሊተክልባቸው ስለማይችል ማሽነሪ የሚያስፈልገው መሆኑ ይጠቁማሉ። ሰው ሁሉም ተራሮች ላይ ሊደርስ እንዲችል በማድረግ የደን ልማቱ ቢካሄድ መንከባከብ ቢቻል ሥነምህዳር ለውጡ ግድቦቻችን ላይ የሚሄደውን የአፈር ክምችት ከማስወገድ አንጻር ከፍተኛ ጠቀሜታ ሊሰጥ የሚችል መሆኑን ተናግረዋል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ የቀርከሃ ምርት በሀገራችን ትልቅ አቅም እንዳለው የሚናገሩት ዶክተሩ፤ በወንዞች ዳርቻ በቆላ አካባቢዎችና በደጋማ አካባቢዎች ቀርከሃ በመትከል በሰፊው ወደፊት ማምጣት ያስፈልጋል። በተለይ የተቦረቦሩ መሬቶች ላይ ቀርከሃን መትከል የተጎዱ ውሃ ዳርቻዎች ላይ ውሃን በደንብ ይዞ አፈር እንዳይከላ የማድረግና የመከላከል አቅም አላቸው። በአፍሪካ አገራት ብዙ ቦታዎች ላይ ይህ ልምድ ተግባራዊ ይደረጋል። ቀርከሃ አንዴ ከተተከለ ራሱ እየተስፋፋ የሚሄድ ነው፤ ሰፊ ቦታዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ይሸፍናል። ከዚህ አንጻር እነዚህ ላይ ትኩረት ተደርጎ ቢሰራ ተጠቃሚ እንሆናለን። የደኑ ዘርፍ ከየትኛው ዘርፍ ያላነሰ ለሀገር እድገት ቀጣይነት ያለው ወደፊት ወደ ኋላ በማይል መልኩ ውጤታማ የሆነ ገቢ ያስገኛል› ብለዋል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 24/2012
ወርቅነሽ ደምሰው