ለልጆች አርአያ መሆን
‹‹ህፃናት የሚያዩትን እና የሚሰሙትን ነገር ለመተግበር ይሞክራሉ፡፡ በተፈጥሯቸው ፈጣን ከመሆናቸውም በላይ ጥሩም ይሁን መጥፎ ያዩትን ነገር ይነካካሉ፡፡ ወላጆችም ልጆቻቸው አንዳንድ ነገር እንዳያደርጉ ከመከልከል ይልቅ መጥፎ እና ጥሩ መሆኑን በምክንያት ማስረዳት ይጠበቅባቸዋል›› ይላሉ የልጆች አስተዳደግ ጥበብ መፅሐፍ ደራሲ አቶ ሽመልስ ፋንታሁነኝ።
ልጆች የወላጆቻቸው ክትትል በስፋት ያስፈልጋቸዋል። ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኙ ጋር በተያያዘ እያንዳንዱ ቤተሰብ መጨነቅን ማስወገድ አለበት፡፡ ወላጆች የሚጨነቁ ከሆነ ልጆችም ይጨነቃሉ፡፡ ከመጨነቅ ይልቅ ለልጆች ለኮቪድ-19 ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ መከላከል እንደሚቻል በመንገር ማረጋጋት ያስፈልጋል፡፡ ይህ ደግሞ ለልጆች ብርታት ነው፡፡ ልጆችን መከታተልና በቂ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ማድረግ ይገባል፡፡
አቶ ሽመልስ እንደሚሉት ወላጆች ለሀገር የሚጠቅሙ፣ በመልካም ባህሪ የታነፁ ልጆችን ለማሳደግ አስቀድመው ስለልጆች አስተዳደግ ሊያስቡበት እና ለነገሮች ሁሉ ምክንያታዊ ሊሆኑ ይገባል፡፡እንዲሁም ወላጆች መልካም ነገሮችን በመስራት አርአያ መሆን አለባቸው፡፡
ወላጆች ሰዎችን በመርዳት፣ ችግሮችን በውይይት እና በመነጋገር የሚፈቱ ከሆነ ጥሩ ስነምግባር ያለው ልጅ ለማሳደግ ይችላሉ፡፡ ወላጆች ለልጆቻቸው ጊዜ ከመስጠት በላይ በቅርበት ሆነው ፍላጎታቸውን በጥልቀት በመረዳት የሚፈልጉትን ነገር ማሟላት አለባቸው ይላል፡፡
የአብዛኞቻችን ኢትዮጵያዊያን አስተዳደግ ከሳይንሱ በተቃራኒው መሆኑን አቶ ሽመልስ ይናገራሉ። ወላጆች ከልማዳዊ የአኗኗር ልምድ ‹‹ልጆች በእድላቸው ያድጋሉ›› ከሚለው በመውጣት የቤተሰብ አስተዳደግ መርህን ተከትለው ማሳደግ አለባቸው፡፡ ይህም በስነ ልቦና ጠንካራ የሆነ ልጅ ለማሳደግ ይጠቅማል ሲሉ ይመክራሉ፡፡
‹‹ በዚህ ወቅት ልጆች ከቤት ስለማይወጡ በቤት ውስጥ የሚሰሩትን ነገር መከታተል ወላጆች ሊዘነጉት አይገባም›› ያሉት ደራሲ ሽመልስ እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ልጆች እያንዳንዱን ቀን በፕሮግራም በመከፋፈል መቼ ማንበብ፣ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ማድረግ እና ማጥናት እንዳለባቸው ማገዝ እና መከታተል አለባቸው፡፡
በስነልቦና ጫና ውስጥ ያደጉ ልጆች ከማህበረሰቡ ጋር አይግባቡም፣ ራሳቸውን ያገላሉ፣ በጥቅሉ ተወዳዳሪ እና ብቁ አይሆኑም፡፡ በሰፈርም ሆነ በትምርት ቤት ከልጆች ጋር አይጫወቱም፡፡በዚህ ሁኔታ የሚያድጉ ልጆች ማህበራዊ ህይወታቸው የተገለለ እና ውስንነት ያለው ይሆናል፡፡ ከዚህ በተቃራኒው የተስተካከለ የእድገት ደረጃን ይዘው እንዲያድጉ ወላጆች ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው ሲል ያስረዳል፡፡
ሞገስ ፀጋዬ
ትምህርት በቴሌቪዥን መከታተልና ጥያቄ መመለስ ያሸልማል
ልጆች! ትምህርት በቤት ውስጥ ተጀምሯል አይደል? እናንተም ይሄንን የቴሌቪዥን ትምህርት እየተከታተላችሁ እንደሚሆን እገምታለሁ። ባሳለፍነው ሳምንት የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር በቴሌቪዥን ትምህርታቸውን ተከታትለው በፍጥነት፣ በትክክልና በብዛት መልስ ለመለሱ ሰላሳ ተማሪዎች ከቴሌቪዥን እስከ ላፕቶፖች ማበረታቻ ሽልማት ሰጥቷቸዋል፡፡ ከተሸለሙ ተማሪዎች መካከል በቤቷ ቴሌቪዥን ሳይኖር ጎረቤት በመሄድ ተከታትላ መልስ በመመለስ የተሌቪዥን ተሸላሚ የሆነች ተማሪም ነበረች። ሌሎች ተማሪዎች ሽልማቱ ሲበረከትላቸው ደስታቸው እጥፍ ድርብ መሆኑን ተናግረዋል፡፡እናንተም በቀጣይ ተሸላሚ ለመሆን በቤት ውስጥ ትምህርቱን በደንብ መከታተልና መማር አለባችሁ፡፡ እንዲሁም ጥያቄ መመለሳችሁንና፣ መሳተፋችሁን ቀጥሉ፡፡ በመጀመሪያው ዙር በርካታ ተማሪዎች መሳተፍ ችለዋል፡፡ ነገር ግን መሸለም የቻሉት ጥቂት ተማሪዎች ብቻ ናቸው፡፡ ከተሸለሙት ተማሪዎች ውጪ ወደ አምስት መቶ ሺ ለሚጠጉ ተማሪዎች የማበረታቻ መልዕክትና ለሰላሳ ሺ ተማሪዎች ደግሞ እንዲበረታቱ ስልክ ተደውሎ ጎበዞች ተብለዋል፡፡እናንተስ?
ልጆች! ከሁሉም ተማሪዎች አሸናፊ ሆኖ ለመሸለም ሦስት ቅድመ ሁኔታዎችን ማሟላት እንዳለባችሁ እንዳትዘነጉ፡፡ የመጀመሪያው መልስ መመለስ ብቻ ሳይሆን የምትማሩበትን ትምህርት ቤትና የክፍል ደረጃችሁን በትክክል መግለፅ አለባችሁ፡፡ ለምሳሌ የአስረኛ ክፍል ተማሪ ሆናችሁ የዘጠነኛ ወይም የስምንተኛ ክፍል ጥያቄዎችን መመለስ ብትችሉ አያሸልምም ማለት ነው፡፡ ለመሸለም አሁን ለምትማሩበት የክፍል ደረጃ የሚዘጋጁ ጥያቄዎችን መመለስ ይጠበቅባችኋል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ጥያቄ በምትመልሱበት ወቅት በፍጥነት ትክክለኛውን መልስ መመለስ ያስፈልጋል፤ ይህም አሸናፊ እንድትሆኑ ያደርጋል፡፡ ለመሸለም ጥያቄ መመለስ ብቻ ሳይሆን በፍጥነት መመለስ ትልቅ ዋጋ አለው፡፡ ሦስተኛውና የመጨረሻው በርካታ ጥያቄዎችን በተደጋጋሚ መመለስ ነው ተሸላሚ የሚያደርገው።
ከላይ በተጠቀሱት ሶስት መስፈርቶች መሰረት የመጀመሪያ ዙር ተሸላሚዎች ተለይተው ተሸልመዋል፡፡ ለቀጣይ 8455 ላይ ‹‹answer›› የሚለውን በማስቀደምና የምትማሩበትን የክፍል ደረጃ በመጥቀስ እንዲሁም የምትመልሱትን የትምህርት አይነት የመጀመሪያ ፊደል በማስገባት መልሶቻችሁን ብትልኩ በቀላሉ ተሸላሚ መሆን ትችላላችሁ፡፡ ትክክለኛ መልስም በፍጥነት መመለስ ሁሌም ያሸልማል፡፡
ልጆች! በቤት ውስጥ ሆናችሁ በቴሌቪዥን ትምህርት መከታተልና ለምትጠየቁት ጥያቄ በፍጥነት መልስ መመለስ አለባችሁ፡፡ በመጀመሪያው ዙር ያልተሸለማችሁ ተማሪዎች ለቀጣይ ዙር ለመሸለም የቻላችሁትን ሁሉ ማድረግ አለባችሁ፡፡ የተሸለማችሁ ተማሪዎችም ድጋሚ ለመሸለም ይበልጥ መበርታት ይኖርባችኋል፡፡ መልካም ቀን!
ሞገስ ፀጋዬ