«መተንፈስ አልቻልኩም» አሊያም በአገሬው ቋንቋ “I can’t breathe” ሰሞኑን በማህበራዊ ድረገፆች በስፋት ሲስተጋባ የነበረና አሁንም በተደጋጋሚ በመስተጋባት ላይ ያለ የሰቆቃ ድምጽ ሆኗል። በዚህም አላበቃም በዓለም አራቱም ማዕዘናት የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና እና ሰው መሆኑ ብቻ በቂ ነው ብለው ሰብዓዊነትን ከፍ አድርገው ከጣሪያው ላይ የሰቀሉ ሁሉ ቁጣቸውን በሚችሉት አጋጣሚና አቅም ሁሉ እየገለፁ ነው።
«መተንፈስ አልቻልኩም፤ እባክህን እግርህን አንሳልኝ። እባክህ እንዳትገድለኝ፣ እባክህን ውሃ ስጠኝ ትንፋሽ እያጠረኝ ነው ልቤ ደክሞታል፣ ሳንባዬ መተንፈስ እየተሳነው ነው» የሚሉና ሌሎች የተማፅኖ ድምፆች ከሞት አፋፍ ላይ ሆኖ ያሰማል። ይህ የሲቃ ድምጽ አሜሪካውያንን ጨምሮ የበርካቶችን ልብ ሰብሯል። የጭካኔ ጥግና ለሰብዓዊነት ቅንጣት ስፍራ በሌላቸውና የክፋት ጥግ ሥራዬ ብለው በተካኑ ፖሊስ መኮንኖች መደረጉ ደግሞ የበለጠ አነጋጋሪና አሳዛኝ አድርጎታል።
ይህን የተማፅኖ ድምፅ ሲያሰማ የነበረው ጥቁር አሜሪካዊው «ጆርጅ ፍሎይድ» ሲሆን የ44 ዓመቱ ዴሬክ ቻውቪን ኔልት የተባለውና እብሪት ናላውን የወጠረው አንድ የአሜሪካ ነጭ ፖሊስ እና ሌሎች ግብረአበሮቹ ከመሬት ላይ አስተኝተውት የሚያደርሱበትን ሰቆቃና እንግልት መቋቋም አቅቶት ሲንፈራፈር የሚያሰማው የሲቃ ድምጽ ነው።
የ44 ዓመቱ ዴሬክ ቻውቪን ኔልት (Derek Chauvin knelt) የጆርጅ ፍሎይድ አንገት ላይ በጉልበቱ ለሰባት ደቂቃ ቆሞ ነብስ የማጥፋቱ አሳዛኝና አፀያፊ ተግባር በተንቀሳቃሽ የእጅ ስልክ ተቀርፆ በየሶሻል ሚዲያው ከመሰራጨቱ በፊት ላለፉት አስራ ዘጠኝ ዓመታት በሜኒሶታ ፖሊስ ዲፓርትመንት ውስጥ አገልግሏል።
በተንቀሳቃሽ ምስሉ ላይ አብሮት የሚታየው የሥራ ባልደረባው ቱ ታዎ (Tou Thao ) ደግሞ ወደ ፖሊስ ማሰልጠኛ የመጣው በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2009፤ የሙሉ ጊዜ ተቀጣሪ ሆኖ ሥራ የጀመረው በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ 2012 ነው። በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2017 እንደዚሁ ከአቅም በላይ ኃይል በመጠቀሙ 25ሺ የአሜሪካን ዶላር ካሳ ተላልፎበት ነበር።
አፍሪካ አሜሪካዊ ጆርጅ ፍሎይድ አሰቃቂ ግድያ በተንቀሳቃሽ ምስል በመላው ዓለም ከተዳረሰ በኋላ ጉዳዩ ወደ አመፅ አምርቷል። ቁጣቸውን መቆጣጠር ባቃታቸው አሜሪካውያን በርካታ ንብረቶችም የዶግ አመድ ሆነዋል። በግዛቲቱም ከፍተኛ ውጥረት የነገሰ ሲሆን የፖሊስ ተቋማት የጥቃቱ ዋና ዒላማ ሆነዋል። በጆርጅ ፍሎይድ ግድያ ላይ በምስሉ ላይ ቁልጭ ብለው የሚታዩት የፖሊስ መኮንኖች ሁለት ቢሆኑም በጉዳዩ የተሳተፉት አራት መሆናቸውን የሜኒሶታ ፖሊስ ዲፓርትመንት አስታውቋል። በግድያው ማግስት በፈረንጆቹ አቆጣጠር ግንቦት 27 ቀን 2020 የተለዩት ቶማስ እና አሌክሳንደር (homas Lane and J. Alexander Kueng) ግድያው ከተፈፀመ በኋላ ወደ ሕዝቡ ሲተኩሱ ነበር።
በሴኪዩሪቲ ጋርድነት ሞያ የሚተዳደረውና በሜኒሶታ ሴንት ሉዊስ ፓርክ ይኖር የነበረው የ46 ዓመቱ አፍሪካ አሜሪካዊ ጆርጅ ፍሎይድ ትውልዱ እና አመጣጡ ከወደ ሂውስተን ቴክሳስ ነበር።
የሜኒሶታ ፖሊስ ዲፓርትመንት በጀመረው ምርመራም ሟች ጆርጅ ፍሎይድ (George Floyd) በፈረንጆቹ አቆጣጠር ግንቦት25 ቀን 2020 ከቀኑ በ 8:00 በአሜሪካ፣ ሜኒሶታ፣ በሚኒያፖሊስ አካባቢ በ 44.934306°N (ዲግሪ ሰሜን) እና 93.262417°W (ዲግሪ ምዕራብ) አቅጣጫ (ቦታ) መሞቱን አረጋግጬ መዝግቤያለሁ ካለ በኋላ አጋጣሚው ግን በጣም ይገርማል በማለት ቀጥሏል። የጆርጅ ፍሎይድ አማሟት በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2014 ከተከሰተው ኤሪክ ጋርነር (Eric Garner)ሞት ጋር እጅግ በጣም ተመሣሣይ ነው።
ነብሱን ይማርና ኤሪክም ሕይወቱ ከማለፉ በፊት የፖሊስ መኮንኑ እጅ አንገቱ ላይ እንደ ተጠመጠመ በታፈነና በሚያጣጥር የተቆራረጠ ድምፅ በተደጋጋሚ “መተንፈስ አልቻልኩም” “I can’t breathe” ይል እንደነበር በወቅቱ በተንቀሳቃሽ የእጅ ስልክ ተቀርፀው ሶሻል ሚዲያ ላይ የተለቀቁት ተንቀሳቃሽ ምስሎች ያሳያሉ።
ሕዝቡም ልክ እንደአሁኑ “Ican’t breathes” የሚል መፈክር ይዞ ለተቃውሞ አደባባይ ወጥቶ ነበር። የጆርጅን ሞት ለመቃወም የወጡት ሰልፈኞች ከያዙት መፈክሮች መካከል «መተንፈስ አልቻልንም» ወይንም “we can’t breathe” የሚለውን በርካቶች እየተቀባበሉት ነው።
የዴሞክራሲና ሁሉም ነገር ቁንጮ ናት የምትባለው አሜሪካ ዛሬም በጥቁሮች ጥላቻ የታወሩ በርካታ ዜጎች ስለመኖራቸው አያሌ መዝገቦችን ማገላበጥ ይቻላል። የጥቁርና የነጮችን እኩልነትን ለማንገስ የአገራቸውን መሪ ጨምሮ በርካቶችን ለጥይት ገብረዋል። አሜሪካውያን ግን ከአድሎና ከዚህ ኋላቀር አስተሳሰብ ሙሉ ለሙሉ ነፃ መውጣት አልቻሉም። የዴሞክራሲ አናት ላይ ነን ቢሉም ከዴሞክራሲ በፍፁም በተቃራኒው ሆነው አሁንም ዓለምን እያሳዘኑ ስለመሆኑ በርካታ መገለጫዎች ይስተዋላሉ።
የሰሞኑ ጆርጅ ፍሎይድ (George Floyd) ሞት ማህበራዊ ድረገፁ ይቆጣጠረው እንጂ በዚሁ ሳምንት ሌላ ልብ ሠባሪ ድርጊት በዚህችው አገር መስተዋሉን ህብር ራዲዮ አስድምጧል። ነጭ አሜሪካዊቷ ኤሚ ኩፐር በማዕከላዊ የኒውዮርኩ ፓርክ ውስጥ ውሻዋን ባለፈው ሰኞ ጠዋት በማዝናናት ላይ ሳለች በስፍራው አዕዋፋትን ከሚያደንቀው ከ57 ዓመቱ ጥቁር አሜሪካዊው ክርስቲያን ኩፐር ጋር በድንገት ይገናኛሉ።
ክርስቲያንም በፓርኩ ውስጥ ውሾች ያለ ሰንሰለት መንቀሳቀስ እንደማይቻል የሚደነግገውን ሕግን አጣቅሶ ሲነግራት ኤሚ ብዙም መስማት አልፈለገችም። ውሻዋን ማዝናናት እንደምትፈልግ በመግለጽ እምቢተኝነቷን ታሳውቃለች። የግለሰቧ ሁናቴ ያላማረው ክርስቲያንም ሁኔታውን በተንቀሳቃሽ ስልኩ ይቀርጽ ጀመር። መቀረጿን ያልፈለገችው ኤሚም ወዲያውኑ ተንቀሳቃሽ ስልኳን አንስታ በመቅረጽ «ፖሊስ ልጠራብህ ነው» ስትል ክርስቲያንን ታስፈራራዋለች።
እርሱም የፈለገችውን መጥራት እና ማድረግ እንደምትችል እና በአቋሙ መጽናቱን ስትረዳ የአደጋ ጊዜ ጥሪ መቀበያውን 911 በመደወል «አንድ ጥቁር አሜሪካዊ እኔን እየቀረፀኝ፣ ከውሻዬ ጋር እያስፈራራን ነው በነፍስ ድረሱልኝ» ትላለች። በቪዲዮ ላይ አንድም የማስፈራራት ቃል ባይሰነዘርባትም ግለሰቧ «አፍሪካዊ አሜሪካ» የሚለውን ቃል በጥሪዋ ውስጥ ደጋግማ ስትናገር በዩቲዩብ ላይ የተለቀቁ ምስሎች ያስረዳሉ።
ታዲያ ጥሪዋን ችላ ያላለውና በሥፍራው የደረሰው የኒውዮርክ ፖሊስ በጊዜው ከቃላት አተካሮ ውጪ ምንም አካላዊ አደጋ አለመከሰቱን በመረዳት ሁለቱንም ግለሰቦችን ቢያሰናብትም ነጯ፣ ባለውሻዋ ኤሚን የቀጠራት የኢንቨስትመንት ኩባንያ ካደረገው ማጣራት በኋላ «ዘረኝነትን በምንም መልኩ አናስተናግድም» በማለት ወዲያውኑ ከሥራዋ አሰናብቷታል። ለቃላት ጦርነቱ መንስኤ የሆነችው ውሻም ወደመጣችበት የእንስሳት መጠለያ ካምፕ በፈቃደኝነት እንድትመለስ ተደርጋለች።
የኒውዮርክ ከተማ ከንቲባ የሆኑት ቢል ዲብላሲዮ በትዊተር ገጻቸው ላይ «ይህቺ ሴት ሕጉን የጣሰች እርሷ መሆኑ እየታወቀ፣ ክርስቲያን ጥቁር በመሆኑ ብቻ ፖሊስ ልትጠራ ተንደረደረች። ይህ ዓይን ያወጣ ዘረኝነት ሲሆን ለዘረኝነት ደግሞ ፍፁም ቦታ የለንም» በማለት የግለሰቧን ድርጊቱን አውግዘዋል።
ስለ ነበረው ያልተጠበቀ ሁኔታ በማስመልከት ኩፐር የቀረፀው እና በማህበራዊ ድረ ገጽ (ፌስ ቡኩ) ላይ የለጠፈው ቪዲዮ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ተከታትለውታል፣ ከ130ሺ ሰዎች በላይ በትዊተር ገጻቸው ላይ «አዕዋፋትን ለማድነቅ የወጣው ጥቁርነቱ መነጋገሪያ አርስት የሆነበት›› በማለት ድርጊቱን ክፉኛ ኮንነዋል። ምንም እንኳን ኤሚ ወደ ሲኤን ኤን ቴሌቪዥን ጣቢያ ቀርባ ለተፈጸመው ድርጊት ይቅርታ ብትጠይቅም ብዙዎች ‹‹ቀድሞ ነበር እንጂ…›› በማለት ሥራዋን የዘረኝነት አድራጎት በማለት ተቃውመውታል።
እርሱም ለሲ ኤንኤን በሰጠው አስተያየት ‹‹አሁን የምንኖርበት ዓለም ጥቁሮች በቀለማቸው ብቻ ዒላማ የሚሆኑበት ወቅት በመሆኑ ቪዲዮ መቅረፄ ጠቀመኝ እንጂ፣ ይህቺ ግለሰብ አጋጣሚውን ተጠቅማ ልታጠቃኝ ነበር›› ሲል ጠንቃቃነቱን ገልጿል።
ክርስቲያን ከሲኤን ኤን አንድ ቁልፍ ጥያቄ ቀርቦለት ነበር፣ እርሱም ይቅርታ ታደርግላታለህ? የሚል ነበር። ምላሹም ‹‹ጥያቄዋ ከልብ እና ከቅንነት የመነጨ ከሆነ ወደፊት ውሻዋን በሰንሰለቱ ከያዘች፣ሕጉን ከተከተለች ለከፋ የሚሰጥ ፀብ የለንም» ሲል ነበር ምላሽ የሰጠው።
አዲስ ዘመን ግንቦት 22 /2012 ዓ.ም ክፍለዮሐንስ አንበርብር