የራስ ምታት በየትኛውም የጭንቅላት /የራስ ክፍል/አካባቢ የሚከሰት የህመም አይነት ሲሆን ህመሙ የሚሰማዎት ጭንቅላትዎን ከፍሎ በአንዱ በኩል አሊያም በሁለቱም በኩል ሊኖር ይችላል። በተወሰነ ቦታ ብቻ ተለይቶ ሊታይ የሚችል ሲሆን ከአንዱ የጭንቅላትዎ ክፍል ወደ ሌለኛው ሊዛመት/ሊሰራጭ የሚችልበትም እድል አለ። ህመሙ የመውጋት፣ የመምታት ወይም ለመግለፅ የሚያስቸግር አይነት ስሜት ሊኖረው ይችላል። የራስምታት ቀስበቀስ ወይም በድንገት ሊመጣ የሚችል ሲሆን ህመሙ ከጀመረ በኋላ ለሰዓታት ወይም ለቀናት ሊቀጥል ይችላል።
የራስ ምታት ምክንያቶች
የራስ ምታትዎ ምልክቶች የህክምና ባለሙያዎን የህመሙን መንስኤ ለማወቅና ተገቢውን ህክምና ለመወሰን ሊረዳቸው ይችላል። የራስ ምታት በአብዛኛው ጊዜ የሚከሰተው ቀላል በሆኑ ምክንያቶች ሲሆን አንዳንድ ጊዜ ግን ለህይወት አስጊ በሆኑ ምክንያቶች ሊመጣ ይችላል። የራስ ምታት በአጠቃላይ ሲታይ የራስ ምታቱን በሚያመጡ ምክንያቶች ሊከፈል
ይችላል። እነርሱም:-
ፕራይመሪ የራስ ምታት (ሌላ ምክንያት የሌለው የራስምታት አይነት)
ይህ የራስምታት አይነት የሚከሰተው በጭንቅላትዎ ውስጥ ያሉና ህመም እንዲሰማዎ የሚያደርጉ ክፍሎች ችግር ሲከሰትባቸው ወይም ከመጠን ያለፈ ስሜት በሚፈጠርበት ወቅት ነው። ይህ የራስ ምታት አይነት የመሰረታዊ ህመም ምክንያት አይደለም። ይልቁንም በጭንቅላታችን ውስጥ ባሉ ኬሚካሎች እንቅስቃሴ፣ በጭንቅላታችን ውስጥ (ውጪ) ባሉ የደምና የነርቭ ስሮች፣ የአንገትና ጭንቅላት ጡንቻዎች ወይም የእነዚህ ድብልቅ ምክንያቶች ችግር ሲከሰት ነው። አንዳንድ ሰዎች ለዚህ አይነት የራስምታት ችግር ሊያጋልጣቸው የሚችል በዘር የሚወረስ ነገር ሊኖራቸው ይችላል። በጣም ከሚታወቁትና ከዚህ የራስምታት አይነት ውስጥ የሚመደቡ የራስ ምታት አይነቶች
- ክላስተር ሄድኤክ
- ማይግሬይን ሄድኤክ
- ቴንሽን ሄድአክና የመሳሰሉት ናቸው።
እነዚህ የራስ ምታት አይነቶች የተወሰኑ የአኗኗር ዘይቤ ምክንቶች ሊያስነሱትና ሊያባብሱት ይችላሉ። እነሱም
- መጠጥ/አልኮሆል፡- በተለይ ቀይ ወይን
- የተወሰኑ የምግብ አይነቶች፡- ለምሳሌ የተቀነባበሩ እና ናይትሬትስ ያላቸው ምግቦች( ስጋ)
- የእንቅልፍ መለዋወጥ/ የእንቅልፍ ማጣት
- ትክክል ያልሆነ የሰውነት ቅርፅ
- የምግብ መርሃግብርዎን መዝለል
- ጭንቀትና የመሳሰሉት ካለዎ የህመሙ መነሻ ሊሆኑ ይችላሉ።
ሰከንደሪ ራስምታት (ምክንያት ያለው)
ይህ የራስምታት አይነት ሌላ ህመሙን ሊያመጡ ለሚችሉ የመሰረታዊ ህመም ምልክት ነው። በጣም ብዙ ምክንያቶች ለዚህ አይነት የራስምታት መከሰት ምክንት ሲሆኑ ከነዚህም ውስጥ
- ድንገተኛ የሳይነስ ኢንፌክሽን
- በጭንቅላት ውስጥ በደም መልስ ውስጥ ደም መርጋት
- በጭንቅላት ውስጥ የደም ቧንቧ መወጠር፤ መስፋት መከሰት
- የጭንቅላት ውስጥ ዕጢ
- በካርቦንሞኖኦክሳይድ መመረዝ፡- ለምሳሌ የከሰል ጭስ
- የፈሳሽ ዕጥረት(ዲሃይድሬሽን)
- የጥርስ ችግር
- የጆሮ ኢንፌክሽን
- ወዘተ…. ሊጠቀሱ ይችላሉ።
የህክምና ባለሙያ ማማከር የሚገባዎ መቼ ነው?
የራስ ምታት እንደ ስትሮክና የማጅራት ገትር ለመሳሰሉ በጣም አደገኛ/ከፍተኛ የሆነ የጤና ችግር ሊያመጡ ለሚችሉ ህመሞች ምልክት ሊሆን ይችላል። ስለሆነም በህይወትዎ አይተውት የማያውቁት የራስ ምታት ስሜት፣ በድንገት የመጣና ከፍተኛ የራስምታት አይነት ካለዎና የሚከተሉት ምልክቶች ከራስምታቱ ጋር ተያይዞ ካለዎ አቅራቢያዎ ወደሚገኝ ድንገተኛ የህክምና መስጫ ተቋም ባአስቸኳይ መሄድ ይገባዎታል። እነዚህም ምልክቶች፡-
- እራስን መሳት
- የመቀበጣጠር ወይም የሰዎችን ንግግር መረዳት ያለመቻል ካለዎ
- ከፍተኛ ትኩሳት ካለዎ፡- ከ39° ሴ. ግሬድ በላይ ከሆነ
- ባንድ በኩል ያለው የሰውነት ክፍልዎ የመደንዘዝ፣ የመስነፍ ወይም ሽባ የሆነ ከሆነ
- የአንገት ያለመታጠፍ ችግር ካለዎ
- የዕይታ ችግር ከገጠመዎ
- የመናገር ችግር ከገጠመዎ
- የመራመድ ችግር ከገጠመዎ
- ማቅለሽለሽና ትውከት የመሳሰሉት ናቸው።
ለራስ ምታት ሊሰጡ የሚችሉ ህክምናዎች ለማይግሬይን አይነት የራስ ምታት ህመሙን/ ስቃይን ሊያስታግሱ የሚችሉ መድሃኒቶች
- ጥሩ ውጤት እንዲያመጣ ከተፈለገ የህመም ማስተጋሻ መድሃኒቶችን ህመሙ እንደጀመረዎ ወዲያው መውሰድ ይገባል። ህመሙ ባለበት ወቅት መድሃኒትዎን ወስደሁ ዕረፍት ቢያደርጉ ወይም ጨለማ ክፍል ውስጥ እንቅልፍ ቢተኙ ሊረዳዎት ይችላል።
- የህመም ማስታገሻ፡- አስፒሪን፣አይቡፕሮፌንና አሴታሚኖፌን የመሳሰሉት መለስተኛ የማይግሬይን ህመሞችን ሊያስታግሱ ይችላሉ።
- እንደ ትሪፕታነስ፣ኢርጎትስ፣ኦፕዮይድስ፣የትውከት ማስታገሻ እንክብሎችና ጉሉኮኮርቲኮይድስ የመሳሰሉት መድሃኒቶችም ለህክምናው አገልግሎት ይውላሉ።
የማይግሬይን ራስምታትን ለመከላከል የሚሰጡ ህክምናዎች
እነዚህ መድሃኒቶች የሚታዘዝልዎ የስቃይ ማስታገሻ መድኃኒቶች ህመሙን መስታገስ ካልቻሉ፥ ከፍተኛ የሆነ ህመም በወር አራቴና ከዚያ በላይ ካለዎ፥ የህመሙ ስቃይ ከ12 ሰዓታት በላይ የሚቆይ ከሆነ እና የራስ ምታቱ ተያያዥ የሆነ እንደ መደንዘዝ፣የጡንቻዎች መስነፍና የራስምታቱ ሊመጣ ሲል የሚሰሙት፣የሚያዩት ወይም የሚሸትዎ ነገሮች ካሉ። እነዚህ መድሃኒቶች የራስምታቱ የሚመጣበትን ፍጥነት፣ ደረጃና የሚቆይበትን ርዝማኔ የሚቀንሱ ሲሆን በተጨማሪም የህመም ማስታገሻ መድሃኒቶቹን የመስራት አቅም ይጨምራሉ። መድሃኒቶቹ በየቀኑ ሊወሰዱ ይችላሉ፤ አለበለዚያም ህመሙን ሊቀሰቅሱ የሚችሉ ነገሮች በሚቃረቡበት ወቅት (የወር አበባ ሊመጣ ሲል) ሊወሰዱ ይችላሉ። ከእነዚህ መድሃኒቶች ውስጥ የሚከተሉት ይጠቀሳሉ።
- ካርዲዮቫስኩላር ድረግስ፡- ሮፕራኖሎል፣ ሜቶፕሮል
- አንታይዲፕሬሳንት፡- አሚትሪፕትሊን
- ለሚጥል ህመም ሊሰጡ ከሚችሉ መድሃኒቶች እንደ ቫልፑሬት ሶዲያም ያሉት ይገኛሉ።
የአኗኗር ዘይቤ ለውጥና የቤት ውስጥ ህክምና
ለራስዎ የሚያደርጉት እንክብካቤ የራስ ምታትን የህመም ስሜትዎን ሊቀንስ ይችላል።
- የጡንቻ ማፍታታት እንቅስቃሴ ማድረግ፡- ይህን ማድረግዎ ህመምዎን ሊቀንስልዎ ይችላል። ይህም ዮጋና ሜድቴሽን የመሳሰሉት ናቸው።
- በቂ እንቅልፍ ማግኘት፡- በእያንዳንዱ ሌሊት በቂ እንቅልፍ ለማግኘት መቻል ነው እንጂ ከመጠን ያለፈ እንቅልፍ መተኛት የለብዎትም። ሁሌም ቢሆን ወደ አልጋ ለእንቅልፍ የሚሄዱበትና ሲነጋ የሚነሱበት ሰዓት ተመሳሳይ ቢሆን ይመረጣል።
- እረፍት ማድረግና ዘና ማለት፡- ያለዎት ራስምታት ማይግሬይን ከሆነ ከተቻለ ፀጥ ያለና ጨለማ ክፍል ቢያርፉ ይመረጣል። በረዶ በጨርቅ አድርገው በማጅራትዎ ስር ያድርጉና በመጠኑ ህመም በሚሰማዎ የጭንቅላትዎ አካባቢ ጫን ጫን ያድርጉ::
- ሁሌ የራስምታት ደያሪ መያዝ/መመዝገብ፡- ይህን አዘውትሮ ማድረግ የራስምታት ህመምዎን ምን እንደሚያስነሳብዎና የትኛው ህክምና እንደሚያሽልዎ ለማወቅ ይረዳል።
ምንጭ፡- ማህደረ ጤና
አዲስ ዘመን ግንቦት 22 /2012 ዓ.ም