
በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ የኢትዮጵያ ሕልውና ከሁለት ውሃ አካሎች ጋር የተያያዘ ነው። ከዓባይ እና ከቀይ ባሕር ጋር። እነዚህ የውሃ አካላት ለኢትዮጵያ ውሃ ብቻ አይደሉም። የመኖሯ ምስጢር፤ የታሪኳ አካል፤ የማንነቷ መገለጫዎች በአጠቃላይ የሕልውናዋ መሠረቶች ናቸው።
ዓባይ የሚለው የአማርኛ ቃል አባት ማለትም የወንዞች ሁሉ አባት ከሚለው የመጣ መሆኑን የተለያዩ መዝገበ ቃላት ያትታሉ። አለፍ ሲል በመፅሐፍ ቅዱስ ኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ 2፤ ቁጥር 13 ላይ ወንዙ ፈለገ-ጊዮን በሚልም ይጠራል። ይህ የሚያመላክተው ወንዙ ያለውን ግዝፈት እና ኢትዮጵያ በተነሳች ቁጥር አብሮ የሚነሳ ታላቅ ወንዝ መሆኑን ነው።
ኢትዮጵያ የዓባይ ንዑስ ተፋሰስ የሆነው ጥቁር ዓባይ ምንጭ ነች። እስከ 86 በመቶ የሚደርሰውም የናይል ወንዝ ውሃ የሚመነጨውም ከእዚችው ሀገር ነው። ሆኖም በተዛቡ እሳቤዎች እና በተለይም የቅኝ ግዛት ውሎችን መሠረት ተደርጎ በተፈጠሩ ኢፍትሃዊ አካሄዶች ኢትዮጵያ 86 በመቶ ድርሻ ካላት ዓባይ ውሃ እንዳትጠቀም ማዕቀብ ተደርጎባት ዘመናትን የበይ ተመልካች ሆኖ ኖራለች።
ሆኖም መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም ይህንን የቅኝ ግዛት አስተሳሰብ የሚያፈርስ ታሪካዊ ድል በኢትዮጵያ ምድር ተከወነ። የዓባይ ግድብ መሠረት ተጣለ። የዓባይ ግድብ ለኢትዮጵያውያን የአይበገሬነት ዓርማ ነው። የዓድዋ ድልን ያህል ክብር የሚሰጠው ነው። የሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ በዘመኗ ከሠራቻቸው ግዙፍ ፕሮጀክቶች አቻ አይገኝለትም። በአፍሪካ አንደኛ በዓለም ሰባተኛ የሆነው ይህ ግዙፍ ግድብ ያለማንም የፋይናንስ ድጋፍ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በነፍስ ወከፍ ባዋጣው ገንዘብ የተሠራ ነው። ግድቡ ሲጠናቀቅ የሚይዘው የውሃ መጠን 74 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ሲሆን ከግድቡ ኋላ የሚተኛው የውሃ መጠን 256 ከሎ ሜትር ይሆናል።
ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ በዓመት በአማካይ 15 ሺህ 759 ጊጋ ዋት ሰዓት ኢነርጂ በማመንጨት ለሀገር አቀፍ የኤሌክትሪክ ትስስር ሥርዓት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል፤ ኤሌክትሪክ ያልተዳረሰባቸው የገጠር መንደሮችና ከተሞች የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግና አቅርቦቱን አሁን ካለበት 44 በመቶ ወደ 90 በመቶ ከፍ ለማድረግ የተያዘውን ግብ ለማሳካት የዚህ ፕሮጀክት ድርሻ ከፍተኛ ነው።
የዓባይ ግድብ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ሲታይ በባሕር ትራንስፖርትና በዓሳ ሀብት ልማት ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል። 74 ቢሊዮን ሜትር ኪዩቢክ ውሃ የመያዝ አቅም ያለው ሰው ሠራሽ ሐይቅ ስለሚፈጠር በአካባቢው በታንኳ እና በጀልባ የትራንስፖርት አገልግሎት፣ እንዲሁም በዓለማችንም ተጠቃሽ የቱሪስት መዳረሻም የመሆን አቅም አለው። በተለይም በግድቡ ዙሪያ የተፈጠረው ሰው ሠራሽ ኃይቅ እየሰፋ ሲሄድና ግንባታው ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅም ከ78 በላይ ደሴቶች የሚፈጠሩ በመሆናቸው ይህም ዋነኛ የቱሪስት ማዕከል እንዲሆን ያስችለዋል። ከፍተኛ የዓሳ ሀብትም ይኖረዋል።
ይህ ዘርፍ ብዙ ጠቀሜታዎች ያሉት ግዙፍ ግድብ እዚህ የደረሰው በርካታ ውጣ ውረዶችን አልፎ ነው። የግድቡ የመሠረት ድንጋይ ከተጣለበት ጊዜ አንስቶ እዚህ እስኪደርስ ድረስ የኢትዮጵያን መልማት የማይፈልጉ ሀገራት በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያም ሆነች ግድቡ በጥርጣሬ እንዲታዩና አልፎ ተርፎም ጦርነት እንዲከፈትባቸው የሚያነሳሱ ሰፋፊ ዘመቻዎች ተካሂዶባቸዋል። ሆኖም የኢትዮጵያውያን የፖለቲካ ቁርጠኝነት፣ ብርቱ የዲፕሎማሲ ጥረትና የማኅበረሰብ ተሳትፎ ተደምረው ጫናዎችን በማለፍ ግድቡ አሁን የደረሰበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ አስችለዋል።
ኢትዮጵያ በታሪኳ ያሳለፈቻቸው መነሳትም ሆነ መውደቅ በቀጥታ ከባሕር ጋር ይያያዛል። በቀይ ባሕር ላይ በነገሠችባቸው ዘመናት ከአራት በላይ ሰፋፊ ወደቦች ነበሯት። የባሕር በሯና ወደቦቿ ባጎናጸፏት ዕድልም ከአክሱም ጊዜ ጀምሮ በኃያልነቷ የዓለምን ስልጣኔ መቆጣጠር የቻለች ሀገር ነበረች። ኢትዮጵያ ለሺህ ዓመታት የቀይ ባሕር ንጉሥ ሆና የኖረች ሀገር ነበረች።
በአንጻሩ ኢፍትሃዊ በሆነ መንገድ ወደብ አልባ ስትሆን ደግሞ ከስልጣኔዋ አሽቆልቁላ፤ ብትናገር የማትደመጥ፤ አቅሟ የደበዘዘ፤ ኢኮኖሚዋ የተዳከመ፤ ሰላም የራቃት ሀገር ለመሆን በቅታለች። በተለይም በኢዛናና በካሌብ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ በነበራት ከወርቅ ከብርና ከነሃስ በተሠሩ መገበያያ ገንዘቦች በቀይ ባሕር ላይ በምታንቀሳቅሳቸውና በምታዛቸው ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የጦርና የንግድ መርከቦች በመታገዝ ከደቡብ አረብ ሀገራት እስከ ሕንድ ውቅያኖስና የአሁኗ ቻይና ድረስ በሰፊው የተዘረጋ የኢኮኖሚ የንግድ የዲፕሎማሲና የመንግሥታት ግንኙነት በተጠናከረ መልኩ ታካሂድ እንደነበረ ከጥንት ስልጣኔዋ የከፍታ ልኬት አንጻር የተሰነዱ ነባራዊ የታሪክ ድርሳናት አስረጂዎች ናቸው።
ኢትዮጵያ ለአያሌ ዓመታት ታስተዳድረው በነበረው የቀይ ባሕርና የባሕር በሮቿ የዝሆን ጥርስ የቅመማ ቅመም ምርቶችን የሙጫ ተክሎችን እንዲሁም ሌሎች ወጪና ገቢ ሸቀጦችን አልባሳት ሽቶና ጌጣጌጦችን በመላክና ወደሀገር ውስጥ በማስገባት የተቀላጠፈ የንግድ እንቅስቃሴ ታካሂድ እንደነበርም ታሪክ ይነግረናል።
ከቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት በኋላ የዓለም ነባራዊ ሁኔታ መቀየር በራሷ በሀገሪቱም የመሪዎች መለዋወጥ ምክንያት ሀገሪቱን ካለወደብ በሚያስቀር ውል ኤርትራ ከኢትዮጵያ እንድትገነጠል ሆነ። ይህ መሆኑ ደግሞ የሀገሪቱን ፖለቲካዊ ወታደራዊና ዲፕሎማሲያዊ ኩነቶች በመቀያየር ሀገሪቱን ወደብ አልባ ከማድረጉም ባሻገር ከቀይ ባሕርና ከኤደን ባሕረሰላጤ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነቷ ውጪ እንድትሆን አስገድዷታል።
በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ ወደብ አልባ ሀገር በመሆኗ በወጪ ገቢ ምርቷ ላይ የሌላ ሀገር ጥገኛ እንድትሆን አስገድዷታል። ይህም ለራሷ ታውለው የነበረውን የውጭ ምንዛሪ ገቢ በማቀጨጭ በኢኮኖሚዋ ላይ እድገት እንዳይመዘገብ የፊጥኝ አስሯታል። ከቀይ ባሕር በ60 ኪሎ ሜትርና ከሕንድ ውቅያኖስ በ2 መቶ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ቢሆንም ላለፉት 34 ዓመታት ከማንኛውም እንቅስቃሴ ታግታ ኖራለች።
ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ላይ ነግሳ በቆየችባቸው ወቅቶች የበርካታ ወደቦች ባለቤት ነበረች። ከእነዚህ ውስጥ በዋነኝነት አዶሊስ፤ ምጽዋ፤ አሰብ፤ ዘይላ ተጠቃሾች ናቸው። ዘይላ ሶማሊያ እንደ ሀገር ከመፈጠሯ በፊት ኢትዮጵያ የምትጠቀምበት የባሕር በር የነበረና ከዛግዌ መንግሥት ጀምሮ ኢትዮጵያ በወደቡ ስትጠቀም ኖራለች።
አሰብ፤ ምጽዋ እና አዶሊስ የኢትዮጵያ በብቸኝነት ስትጠቀምባቸው የነበሩና ኤርትራ ስትገነጠል አብረው የሄዱ ናቸው። በተለይም አሰብ ኢትዮጵያዊ አፋሮችን ጨምሮ ከነወደቡ ኢፍትሃዊ ባልሆነ መልኩ ተላልፈው የተሰጡ ኢትዮጵያ ሀብቶች ናቸው። ይህ ኢፍትሃዊ ውሳኔም ባለብዙ ወደቦች ባለቤት የነበረችውን ሀገር ከነጭራሹ ወደብ አልባ አድርጎ አስቀርቷታል።
የባሕር በር ወይም ወደብ ለአንድ ሀገር ኢኮኖሚ ወሳኝ ከመሆኑ ባሻገር ፖለቲካዊ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ባለሙያዎች ይናገራሉ። በአሁኑ ወቅት ጅቡቲ ከአራት በላይ ወደቦች አሏት። ይህች ትንሽ ሀገር ተፈላጊነቷም ከአውሮፓ እስከ አሜሪካ እንዲሁም ከአሜሪካ እስከ እስያ ድረስ ደርሷል። የተወሰኑ ሀገሮች ቻይናን ጨምሮ በአሁኑ ወቅት በዚች ትንሽ ሀገር ወታደራዊ ቤዝ ገንብተዋል። እነዚህ ሀገሮች ወደእዚች ትንሽ ሀገር መጥተው ወታደራዊ ቤዝ እንዲኖራቸው ካስፈለጓቸው ምክንያቶች መካከል የአካባቢው ተፈላጊነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱ እንደሆነም ባለሙያዎች ያብራራሉ።
ኢትዮጵያ ወደብ አልባ ከሆነች ጀምሮም በየቀኑ ለወደብ ኪራይ ከ3 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንደምታወጣ መረጃዎች ያሳያሉ። ይህንኑ ሀቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለወደብ ኪራይ የሚወጣው ወጪ በርካታ የሕዳሴ ግድቦችን ለመገንባት ያስችለን ነበር ሲሉ በቁጭት መናገራቸው የሚታወስ ነው።
ሌላኛው የወደብ አልባነት ጉዳት ደግሞ ከዲፕሎማሲ ጋር የሚያያዝ ነው። ወደብ ያላቸውና የሌላቸው ሀገራት እኩል ተደማጭነት አይኖራቸውም። ኢትዮጵያም ከቀይ ባሕር ከተወገደች ጀምሮ በዓለም ላይ ያላት ተሰማኒት እየተቀዛቀዘ እንደመጣና በምትኩ ጅቡቲን የመሳሰሉ ትንንሽ ሀገሮች የበለጠ ተሰሚነትን እያገኙ መጥተዋል፡፡
ሶስተኛው ችግር ደግሞ ወደብ አልባ ሀገራት የሚገጥማቸው የሉዓላዊነት ፈተና ነው። ወደብ አልባ ሀገራት ራሳቸውን ከጠላት ለመከላከል ይቸገራሉ። በአጠቃላይ እንደ ሀገር መቆም ይከብዳቸዋል።
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር መቀጠል የምትችለው ዓባይና እና ቀይ ባሕር እስካሉ ድረስ ነው። እነዚህ ሁለት አካላት ከእጇ በወጡ ቁጥር ጥንታዊ ታሪኳ መነሻ አይኖረውም፤ ሉዓላዊነቷን ለማስከበር ያደረገቻችቸው ተጋድሎዎች ጎዶሎ ይሆናሉ፤ የወደፊት ጉዞዋም በውጣ ውረድ የተሞላ ይሆናል። ስለዚህም ኢትዮጵያ እንደ ሀገር እንድትቆም በዓባይና በቀይ ባሕር ላይ ያሏት መብቶቿ ሊረጋገጡላት ይገባል።
ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው።በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።
እስማኤል አረቦ
አዲስ ዘመን ዓርብ ሐምሌ 11 ቀን 2017 ዓ.ም