ከሌሊቱ 10 ሰዓት ጀምረው ወደ ስራ ይሰማራሉ። ብዙም እረፍት በሌለው የንግድ ህይወታቸው የጊዜን ጥቅም በተግባር ያሳዩ መሆናቸውን የሚያውቁዋቸው ይመሰክራሉ። እርሳቸው ብቻ ሳይሆኑ የእጅ ስልካቸውም ብዙ እረፍት የለውም።
በየደቂቃው በሚደወሉ የደንበኞች ጥሪ ድምጿን ታሰማለች። አንዱን እቃ ወደ ደንበኛቸው ልከው ስልኩን ሲዘጉ በሌላኛው መስመር የሚገኝ ሸማች ደግሞ ይህንን እቃ ላክልኝ የሚል ጥሪ ያሰማቸዋል። እናም ቤተሰባቸውን ባህር ዳር ከተማ ላይ አድርገው በየቀኑ ለነገ ጥሪት የሚሆናቸውን ንግድ በመከወን ላይ ናቸው።
የዛሬ ባለታሪካችን አቶ ተፈራ መንግስቴ ይባላሉ። የተወለዱት በ1964 ዓ.ም በአማራ ክልል ምስራቅ ጎጃም ዞን ብቸና ከተማ ነው። ለወላጆቻቸው አምስተኛ ልጅ ናቸው። ቤተሰባቸው በግብርና ስራ የሚተዳደር በመሆኑ ገና በልጅነት እድሜያቸው ነው ወደ እርሻውም ሆነ ወደ እረኝነቱ ስራ ጎራ ማለት የጀመሩት።
ወላጆቻቸው ጠንካራ አራሽ ገበሬዎች በመሆናቸው ጥሩ ገቢ እንዳላቸው አቶ ተፈራ ያስታውሳሉ። ልጃቸው ከእረኝነቱ ባለፈ የቀለም ትምህርት እንዲቀስም እድሉን ከፍተዋል። እናም አቶ ተፈራ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ አራጆ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት አስገቧቸው። ከትምህርት መልስ በሚያገኟት ጊዜ ቤተሰባቸውን በተለያዩ ስራዎች ማገዝ የሚወዱት አቶ ተፈራ ታዲያ ከብቶቹንም መመገብም ሆነ በእርሻ ስራው ተሳትፏቸውን ቀጥለዋል።
ወደ ሰባተኛ ክፍል ሲሸጋገሩ ደግሞ ቢቸና ከተማ በሚገኘው ራስ ኃይሉ ዮሴዴቅ ትምህርት ቤት ገቡ። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ ቢቸና ከተማ በሚገኘው በላይ ዘለቀ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸው ሊጠናቀቅ ሲቃረብ ግን ያልታሰበው ተከሰተ።
በ1983 ዓ.ም ላይ ምስራቅ ጎጃም የደረሰው እና የደርግ እና የኢህአዴግ ጦርነት ለአካባቢው ሰላም ባለመስጠቱ ለሁለተኛ ደረጃ ማጠናቀቂያ ፈተና ጥቂት ቀናት የቀረው ትምህርትም ከናካቴውም እንዲዘጋ ምክንያት ሆነ። አቶ ተፈራም ለአንድ ዓመት ትምህርትቸው ተቋርጦ ከዓመት በኋላ የማጠቃለያ ፈተናውን ወሰዱ። የፈተኛው ውጤት ሲመጣም የዲፕሎማ ትምህርት መከታተል የሚችሉበት እድል እንዳላቸው አወቁ።
ይሁንና በወቅቱ የፖለቲካ ፓርቲ ተሳትፎ ውስጥ በመግባታቸው ፓርቲያቸው በፖሊስነት ሙያ እየሰሩ እንዲያገለግሉ መደባቸው። ግዴታውን እምቢ ማለት ያልቻሉት አቶ ተፈራ በአማራ ክልል በሚገኝ የፖሊስ ማሰልጠኛ ገብተው ለሶስት ወራት ስለጠና ከወሰዱ በኋላ ቢቸና ከተማ ላይ የትራፊክ ፖሊስ ሆነው ተመደቡ። በወቅቱ የወር ደመወዛቸው 220 ብር ብቻ እንደነበረም በትዝታ ወደ ኋላ ተጉዘው ያስታውሱታል።
በትራፊክ ፖሊስ ሙያ ለሶስት ዓመታት የተወለዱበት ከተማ ላይ ከሰሩ በኋላ ተጨማሪ ስልጠናዎችን በመውሰድ ወደ ምስራቅ ጎጃም ዞን ትራፊክ ፖሊስ ጽህፈት ቤት ተዘዋወሩ። በዚያም እስከ ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች አገልግለዋል። በቀጣይም በሰንዳፋ ፖሊስ ማሰልጠኛ ተልከው የአመራርነት ስልጠናዎችን ወሰዱ።
ለሁለት ዓመታት ከሰሩበት የደብረማርቆስ ስራ ቦታ ተዘዋውረውም ባህርዳር ከተማ ላይ በአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ውስጥ እንዲሰሩ ተመደቡ። በባህር ዳርም በተለያዩ ቦታዎች ተመድበው ሰርተዋል። በተለያዩ ቦታዎች ተመድበው በሰሩበት ወቅት ግን ጥቂት ጥቂት እያሉ በቆጠቧት ገንዘብ ቢቸና ላይ በአቅማቸው ቤት ሰሩ።
በባህር ዳር ከተማ ጥቂት ዓመታትን እንደሰሩ ግን የተሻለ የገቢ ምንጭ ማግኘው እንዳለባቸው ማሰብ ጀመሩ። ለዚህም የከተማው እንቅስቃሴ ሰፊነት እርሳቸውንም ተጨማሪ ስራ መስራት እንዳለባቸው እንዳነሳሳቸው ይናገራሉ። እናም ቤታቸውን መያዣ አድርገው <<5ኤል>> የተሰኘችውን ሚኒባስ ለመግዛት ለባንክ ጥያቄ አቀረቡ።
ጥቄያቸው ተቀባይነት አግኝቶ በ280 ሺ ብር ተሽከርካሪውን በ2002 ዓ.ም ገዝተው የትራንስፖርት ዘርፉንም ተቀላቀሉ። በወቅቱ የፖሊስ ስራቸውን ሳይለቁ ሾፌር ቀጥረው ያሰሩ ነበር። በትርፍ ሰዓታቸው ደግሞ ተሽከርካሪያቸው ወደየትኛው የጉዞ መስመር እንደተሰማራ በመቆጣጠር ገቢያቸውን አሰፉ።የተሽከርካሪያቸው ገቢ ከፍ እያለ ሲሄድም ቀስ በቀስ ብድራቸው ወደ መክፈሉ ተሸጋገሩ።
የመጀመሪያዋን ተሽከርካሪ ከገዙ ከሶስት ዓመታት በኋላ ደግሞ የፖሊስነት ስራቸውን ትተው ሙሉ በሙሉ የግል ስራቸው ላይ ማተኮር እንዳለባቸው ለራሳቸው ቃል ገቡ። የስራ መልቀቂያቸውን አስገቡ። በጊዜው የዋና ሳጅንነት ደረጃ የደረሱ በመሆኑ አራት ሺህ ብር ደመወዝ ይከፈላቸው እንደነበረ ያስታውሳሉ። ይሁንና በግላቸው ተንቀሳቅሰው የተሻለ ገቢ ማግኘት እንደሚችሉ በመገነዘባቸው ለስራ የወሰዷቸውን ንብረቶች ለመስሪያ ቤታቸው አስረክበው በህጋዊ መንገድ ተሰናበቱ። ትምህርታቸውንም ቀጥለው የህግ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ያዙ።
ከመንግስት ስራቸው እንደለቀቁ ደግሞ ሚኒባስ ተሽከርካሪያቸውን ብድር ከፍለው ጨረሰው ነበርና ተጨማሪ ብድር ከባንክ ጠየቁ። ከብድር ገቢው በተጨማሪም ተሽከርካሪዋን ሸጠው የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ገዙበት።የህዝብ ማመላለሻውንም እራሳቸው በመሾፈር ከባህር ዳር ወደ ተለያዩ ከተሞች የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት ጀመሩ።
የአገር አቋራጭ ትራንስፖርት ስራቸውን እያከናወኑ በተወለዱባት ቢቸና ከተማ ከሚገኙ ጓደኞቻቸው ጋር እቁብ ይጥሉ ነበር። የሚያገኙትንም ገንዘብም በአልባሌ ጉዳዮች ከማጥፋት ይልቅ የቁጠባ ልምድ በማዳበር ለወደፊት ህይወታቸው የሚሆን ስንቅ መያዙንም አውቀውበት ነበር።
ተሽከርካሪያቸው በሚበላሽበት ወቅትም እራሳቸውም ጭምር የቴክኒክ ስራውን በመከወን ጥሩ ገቢ ይሰበስቡ እንደነበር አቶ ተፈራ ያስታውሳሉ። ለአራት ዓመታት ያክል በሾፌርነት የእራሳቸውን አገር አቋራጭ መኪና ካሽከረከሩ በኋላ ከፍ ወዳለ የገቢ ማስገኛ ስራ መሸጋገር እንዳለባቸው ማሰብ ጀመሩ።
በልባቸው ያለው ደግሞ የተሽከርካሪዎች መለዋወጫ ንግድ ዘርፉን መቀላቀል ነው። ለዚህም አሁንም ከባንክ ብድር መጠየቃቸው ግድ ሆነ። የባንክ ሰዎችም አቶ ተፈራ ሰርተው መክፈሉን የሚችሉበት ጠንካራ ሰራተኛ መሆናቸው በተደጋጋሚ በማየታቸው ብድሩን ፈቀዱላቸው።
አቶ ተፈራም ባህር ዳር ከተማ ልዩ ስሙ ቀበሌ 12 በተባለው አካባቢ ላይ ለንግድ የሚሆናቸውን የቦታ መረጣ ጥናት አደረጉ። በአካባቢው የሚገኝ ባለአንድ ወለል ህንጻ የታችኛውን ክፍል በስምንት ሺ ብር ተከራይተው የከባድ ተሽከርካሪዎች መለዋወጫ ንግዱን <<ሀ>> ብለው ተቀላቀሉ።
በወቅቱ ቤታቸውን አስይዘው ካገኙት የባንክ ብድር እና ከቢቸናው የእቁብ ገቢያቸው ጋር በማጣመር አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር ወጪ አድርገው ሱቃቸውን ሙሉ እንዳደረጉት ይናገራሉ። ከአዲስ አበባ የመለዋወጫ አስመጪዎች ዘንድ እቃዎችን በመግዛት ወደ ባህር ዳር ወስደው መሸጡንም በአጭር ጊዜ ለመዱት።
በወቅቱ ሱቃቸውን ሲከፍቱ የገበያ ችግር እንዳልገጠማቸው የሚያስታውሱት አቶ ተፈራ፣ ለዚህ ደግሞ በአሽከርካሪነት ስራ ላይ በነበሩነት ወቅት በጓደኝነት እና በስራ ባልደረባነት የሚያውቋቸው ሰዎች እቃ ሲፈልጉ ከእርሳቸው ስለሚወስዱ የገበያ ችግር እንዳላጋጠማቸው ይናገራሉ።
ከአራት ዓመት በፊት መለዋወጫ ሱቁን ሲከፍቱ እርሳቸውን ጨምሮ ሶስት ሰራተኞች ቀጥረው ያሰሩ ነበር። በዚህም ገቢያቸው እያደገ ሲመጣ ባህር ዳር ላይ ዘመናዊ የመኖሪያ ቤት ገነቡ።
በቤታቸው አካባቢም ከመሬት በላይ ባለሁለት ወለል ህንጻ ገንብተው የተለያዩ ክፍሎችን እያከራዩ ይገኛል። ይህም ከንግድ ስራቸው በዘለለ ተጨማሪ የገቢ ምንጫቸው ሆኗል። በንግድ ሱቃቸው አማካኝነትም አንደ የቤት መኪና ገዝተዋል።
የአቶ ተፈራ መለዋወጫ ሱቅ አሁን ላይ ከ110 ሺ ብር ጀምሮ የሚሸጡ የሞተር እቃዎች እና የተለያዩ የከባድ ተሽከርካሪ መለዋወጫዎችን ይዟል። ካምቢዮ፣ ዲፈረንሻል እና የተለያየ አገልግሎት ያላቸው እና በልዩ ስማቸው <<አይሱዙ>> እና <<ኤፍ ኤስ አር>> የተባሉ የከባድ ተሽከርካሪ መለዋወጫዎችም በሱቃቸው ይሸጣሉ። እርሳቸውን ጨምሮም አምስት ሰራተኞች በአሁኑ ወቅት በመለዋወጫ ሱቃቸው በስራ ላይ ናቸው።
በቀጣይ የንግድ እቅዳቸው ደግሞ የመለዋወጫ እቃዎች አስመጪነት ለመሸጋገር ወጥነዋል። ለአስመጪነቱ የሚሆን አቅምም ማደራጀታቸውን የሚናገሩት አቶ ተፈራ፤የኮሮና ቫይረስ ከኢትዮጵያም ሆነ ከአለም ላይ ተወግዶ የሰላም ቀን ሲመጣ ለተጨማሪ ሰራተኞች የስራ እድል መፍጠር የሚያስችላቸው ዝግጅት አድርገዋል።
ከዱባይ እና ከተለያዩ ሀገራት የተሽከርካሪ መለዋወጫዎችን በማስመጣት ወደ ከፍተኛ የንግድ ስራ እንደሚሸጋገሩ እምነታቸው ነው። ባለትዳር እና የሁለት ልጆች አባት የሆኑት የቢቸናው ነጋዴ ከስራቸው በተጨማሪ ደግሞ መልካም አባት መሆናቸውን አስመስክረዋል።
አንደኛው ልጃቸው ከሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ በኮምፒዩውተር ሳይንስ ትምህርት ዘንድሮ ለመመረቅ ዝግጅት እያደረገ ይገኛል። ሌላኛው ልጃቸውን ደግሞ 11ኛ ክፍል ተማሪ ነው። አምሽተው ወደ ቤታቸው ሲገቡ የቤተሰብ ጨዋታ እና ውይይቱ የሚናፍቁት ጉዳይ ነው።
ሌሊት ላይ ግን 10 ሰዓት ተነስተው ወደ ሰራ ይሰማራሉ።ተሽከርካሪያቸው ወደሚሰማራበት መናኸሪያ በማምራት ስራቸውን ከጨረሱ በኋላ ወደንግድ ሱቃቸው ያመራሉ። በዚያም በስልክም ሆነ በአካል የሚመጡ ግብይቶችን በማቀላጠፍ ጉዳያቸውን ይፈጽማሉ።
ከስራቸው በተጨማሪ ደግሞ የማህበረሰብ አገልግሎት ላይም ተሳታፊ ናቸው።በተለይ በንግድ አካባቢያቸው የሚገኙ ወጣቶች ተደራጅተው የመኪና ማቆሚያ አገልግሎት እንዲሰጡ ድጋፍ ያደርጋሉ።ወጣቶች ህይወታቸውን ለቁም ነገር ለማብቃት ሀገርን በሚጠቅም ስራ ማሳለፍ አለባቸው ለዚህ ደግሞ መንገዱን ማሳየት ያስፈልጋል ይላሉ።
ማንኛውም ወጣት የወደፊት ህይወቱ በተረጋጋ እና በቀና መንገድ ላይ እንዲጓዝ ችሎታውን መሰረት ያደረገ ስራ ላይ መሰማራት ቢችል ለሀገርም ለወገንም የሚበጅ ውጤት ያገኛል የሚለው ደግሞ ምክራቸው ነው።
አዲስ ዘመን ግንቦት 22 /2012 ዓ.ም
ጌትነት ተስፋማርያም