ኢ ትዮጵያ የመንግስታቱ ማህበር / ሊግ ኦፍ ኔሽን /አባል የሆነችው መስከረም 17 1916 ዓም ነው:: የፊታችን መስቀል፣ መስከረም 17 ቀን 2013 ዓ.ም አንድ ክፍለ ዘመን፣ 100 አመት ሊሞላት ሶስት አመት ብቻ ይቀራታል:: አባል በሆነች 12ኛው አመት እኤአ በሰኔ 30 ፣ 1936 ዓ.ም፤ ጥላ ከለላ ይሆነኛል ባለችው ሊግ ኦፍ ኔሽን በአደባባይ ክህደት ተፈፅሞባታል::ለፋሺስት ጣሊያን በሀጢያት ተሸካሚነት ተላልፋ ተሰጥታለች:: ንጉሠ ነገሥታት ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ከዚህ ታሪካዊና አሳፋሪ ክህደት በፊት ፤ ሊግ ኦፍ ኔሽን ለአባል ሀገር ኢትዮጵያ የሚገባውን ጥበቃ ፣ ከለላና እገዛ እንዲያደርግ፤ በመንግስታቱ ማህበር 16ኛው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ተገኝተው ያደረጉትን ታሪካዊና ትንቢታዊ ንግግር ፤ ጋዜጠኛ ፣ አምባሳደርና ደራሲ ዘውዴ ረታ ፣ ” የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግስት ” በሚለው ድንቅ መፅሐፋቸው እንዲህ ከትበው አቆይተውልናል ፤ “…የአለምን ሰላምና የአገሮችን ነጻነት ለማስከበር ከፍተኛ የቃል ኪዳን አደራ የተጣለበት የመንግስታት ማህበር ፤ የአንድ አባል አገር መሪ የሆነ ንጉሠ ነገሥት ሌላው አባል መንግስት በጦር ኃይል ተደራጅቶ በሕዝቡ ላይ ስለአደረሰበት አሰቃቂ የሆነ እልቂት፤ በሊግ ኦፍ ኔሽን ሸንጎ ላይ ተገኝቶ አቤቱታውን የሚያቀርበው ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን የሚስተው ይኖራል ብዬ አላስብም::
ከብዙ ሺህ አመታት ጀምሮ ነጻነቱን ጠብቆ የኖረውን የአገሬን የኢትዮጵያ ሕዝብ ፤ በአሁኑ ሰዓት የጣሊያን መንግስት ቅኝ አድርጎ ለመግዛት በጦር ኃይልና በመርዝ ጋዝ የሚፈጽምበትን ግፍና ጭካኔ ፤ ከዚህ ቀደም በሰለጠነው አለም ውስጥ ደርሶ ያልታየና ተወዳዳሪ የማይገኝለት መሆኑን የምገልጽላችሁ እጅግ በመረረ የኃዘን ስሜት ነው::የጣሊያን መንግስት ካለፈው አንድ አመት ተኩል ጀምሮ በአገሬ በኢትዮጵያና በሕዝቤ ላይ ሲወስድ የቆየው ሕገ ወጥ እርምጃ ፤ ምን ያህል አሳሳቢና ምን ያህል አደገኛ እንደሆነ ፤ በየጊዜው ለመንግስታቱ ማህበር ያመለከትኩባቸው ሰነዶች ፤ በጽህፈት ቤቱ ተመዝግበው የሚገኙ መሆናቸውን ማስታወስ እፈልጋለሁ:: ሆኖም በዛሬው እለት የ52 መንግስታት እንደራሴዎች የኢትዮጵያን አቤቱታ ሰምታችሁ ፍርዳችሁን ለመስጠት ስለተሰበሰባችሁ ፤ የወልወል ግጭት ከተፈጠረበት ጊዜ አንስቶ እስከዛሬ ድረስ ፤ የጣሊያን መንግስት በአገሬና በሕዝቤ ላይ የፈጸማቸውን ግፍና በደል ዋና ዋናዎቹን ልገልጽላችሁ ከፊታችሁ ቀርቤያለሁ::
“ግርማዊነታቸው በዚህ ታሪካዊ ንግግራቸው የጣሊያን ፋሽስት በኢትዮጵያ ላይ የፈጸመውን ግፍና ወረራ ከወልወል ግጭት አንስቶ ፤ የመንግስታቱ ማህበር በወራሪው ላይ የጣለው የይምሰል ኢኮኖሚያዊ ማዕቀብ ነዳጅ ፣ ዘይት ፣ ከሰልና ብረታብረትን ያካተተ ስላልነበር ግቡን ሊመታ ባለመቻሉ የጣሊያን ወራሪ ግፍና ጭካኔ እየተባባሰ መምጣቱን በሶስት ዋና ዋና ነጥቦች አትተው ካቀረቡ በኋላ በንግግራቸው ማጠቃለያ ላይ ይህን ትንቢታዊ መልዕክት አስተላልፈዋል ፤ “… ዛሬ ባለንበት ሰዓት ከሁሉ ይበልጥ የአለምን ሕዝብ እጅግ ሊያስጨንቀውና ሊያሳስበው የሚችለው ፤ የአለም መንግስታት ተስማምተው ለሰላም የሚያወጧቸውን ሕጎች ፤ በጉልበትና በማን አለብኝነት መንፈስ እየተነሱ የሚደመስሱ መሪዎች መፈጠራቸው ነው::በዚህም አኳኋን የፋሽስት መንግስት ዛሬ በኢትዮጵያ ላይ የሚፈጽመውን የግፍ ስራ ነገ በሌሎች ሀገሮች ላይ ለማድረግ ምን ያግደዋል ? ተብሎ የሚቀርበው ጥያቄ ነው::ለዚህም አስጨናቂ ጥያቄ ዛሬ መልስ ካልተገኘለትና አጥቂዎችን ለመቋቋም ተገቢው እርምጃ ካልተወሰደ ፤ አደጋው በድሀ አገሮች ላይ ተወስኖ የሚቀር ሳይሆን ፤ ታላላቆቹ መንግስታት እንደሚደርስባቸው ሊያስቡበት ይገባል::…” (ይህ የግርማዊነታቸው ትንቢት ከአመታት በኋላ ተፈፅሞ ከታሪክ ድርሳናት አንብበናል::የናዚ ጀርመኑ አዶልፍ ሒትለር የአርያም ዘሮች ነን በሚልና አውሮፓን ብሎም አለምን ለመቆጣጠር በነበረው እብሪት ጎረቤቶችን በኋላም እነ ፈረንሳይን በመውረሩ የ2ኛው የአለም ጦርነት ተቀስቅሶ ሚሊዮኖቹ ሞቱ፤ ቆሰሉ:: ስድስት ሚሊዮን አይሁዶችም በግፍ ተጨፈጨፉ::የአለም ኢኮኖሚም እምሽክ ድቅቅ አለ። የሰው ልጅ ስልጣኔ ወድሞ ለጥቂት አመታት ቢሆንም አለማችን በድንቁርና፣ በወረርሽኝና በችጋር ተመታች::የንጉሠ ነገሥቱ ታሪካዊ ንግግር ዛሬ ድረስ በትንቢትነት የሚወሰደው ለዚህ ነው::) የግርማዊነታቸው የሊግ ኦፍ ኔሽን ንግግር እንዲህ ካቆመበት ቀጥሏል:: “…
ከሥነ ፍጥረት ሕግና ከሰብአዊ መንፈስ ውጪ ፤ ያ ሁሉ አሰቃቂ ዕልቂት ቢደርስበትም ፤ ሰላማዊና ሃይማኖተኛ የሆነው ያገሬ የኢትዮጵያ ሕዝብ ፤ ለነጻነት የሚያደርገው ተጋድሎ እስከ ዕለተ ሞቱ የጠነከረ ስለሆነ ፤ በየጫካው በዱር በገደሉና በየበረሀው እየተዘዋወረ በመዋጋት ፤ ጠላቱን ማስጨነቅ አላቋረጠም::እኔም በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ ጠላት ለመያዝ ሞክሮ ባቃተው በአንድ ልዩ ቦታ፤ አዲስ አበባ ያለውን መንግስቴን ካዛወርኩ በኋላ ወደ ዤኔቭ የመጣሁት ፤ እውነትን ብቻ ተመርኩዤ አቤቱታዬን ለእናንተ ለማመልከትና የመንግስታት ማህበርን እርዳታ አግኝቼ ፤ የነጻነት ትግሌን ወደምቀጥልበት ቦታ ለመሄድ መሆኑን እንድታውቁልኝ እፈልጋለሁ:: ስለዚህ በንግግሬ መደምደሚያ ላይ የምጠይቃችሁ ፤ ለሕዝቤ ምን ይዤለት እንደምመለስ መልሳችሁን እንድትሰጡኝ ነው፡፡”
ግርማዊነታቸው ከመንግስታቱ ማህበር ለሕዝባቸው ይዘውት እንዲሄዱ የተወሰነላቸው እንደ አባል ሀገር የምስራች ሳይሆን ቅስም ሰባሪ መርዶ እንደነበር በዚሁ መፅሐፍ እንዲህ ተመዝግቦ ይገኛል ፤ “… የ16ኛው የመንግስታቱ ማህበር ጉባኤ ሊቀ መንበር ቫን ዚላንድ በኢትዮጵያ ግዛት አሁን ያለው የፋሽስት ይዞታ በይፋ እንዲወገዝና ለወደፊትም ምንም አይነት እውቅና እንዳይሰጠው የሚጠይቀውን የሀገራችንን የመጀመሪያ ረቂቅ ውሳኔ ለጉባኤው አላቀርብም ብሎ ከለከለ::…” ይህ አልበቃ ብሎ ፣ “… የፋሽስት መንግስት በሊግ ኦፍ ኔሽን ተፈርዶበት የነበረው የኢኮኖሚ ጭቆና / ማዕቀብ እንዲነሳ ተወሰነለት::የጣሊያን ፋሽስት በወረራ የያዘው ይዞታ እውቅና እንዳያገኝ ኢትዮጵያ ያቀረበችው ጥያቄ በጉባኤው ውድቅ ተደረገ::የመንግስታቱ ማህበር ሕግ በሚፈቅደው መሰረት ሀገራችን የጠየቀችው ብድር ተከለከለ::…”
ይህ ፍርደ ገምድልነት አሀዱ ብሎ የጀመረው በወጉ ለአንድ ሀገር መሪ የሚደረገውን የፕሮቶኮል አቀባበል ለንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለስላሴ በመንፈግ እና ለጉባኤው ንግግር ለማድረግ ከመቀመጫቸው ሲነሱ በስብሰባው አዳራሽ ፎቅ ግራና ቀኝ ባሉት ጋላሪዎች ተሰግስገው የሚጠባበቁት የፋሽስት ደጋፊዎች ከፍ ባለ የብልግና ስድብ ፣ ጩኸትና ፉጨት አዳራሹን በማደባለቅ እንደነበር፤ ጸሐፊው ያትታሉ::
ታሪክ ራሱን ይደግማል አይደግምም የሚለው ሙግት ጉንጭ እንዳለፋ መልስ ሳያገኝ ዛሬ ድረስ የቀጠለ ቢሆንም፤ ለካርል ማርክስ ግን ታሪክ ራሱን የመድገም ጉዳይ አጠያያቂ አይደለም::ለዚህ ይመስላል ፣ ” ታሪክ ራሱን ሲደግም መጀመሪያ በአሳዛኝ ሁኔታ በማስከተል በአስቂኝ ሁኔታ ” ያለው::ከ80 አመት በኋላ በከፊል ታሪክ ራሱን ሊደግም ወደ ኋላ ማጠንጠን የጀመረ ይመስላል:: ታሪክ ራሱን የሚደግመው እኤአ 1936 ዓ.ም በአሳዛኝ ሁኔታ ወይም በአስቂኝ ሁኔታ ይሁን አይሁን ወደፊት የምናየው ሆኖ ፤ የዛን ጊዜ ሀገራችን ወራሪውንና አረመኔውን የጣሊያን ፋሽስት ከሳ ሸንጎ ፊት ” አቁማው ” ነበር ፤ ዛሬ ደግሞ ግብፅ በመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ሀገራችንን ፤ ” ኢትዮጵያ በመጠናቀቅ ላይ ስላለው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረው ድርድር አቋርጣ መውጣቷ ስጋት እንደፈጠረባት እና ድርድሩን ሆን ብላ እያጓተተችና ጊዜ እየገዛች ነው::”
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ባለፈው ሳምንት በቃል አቀባያቸው በኩል ባስተላለፉት መልዕክት ፤ (ከግብፅ የጸጥታው ምክር ቤት ክስ ወዲህ መሆኑ ነው ፤) አንቶኒዮ ጉቴሬስ ፣ ኢትዮጵያ ፣ ሱዳንና ግብፅ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ላይ ያላቸውን ልዩነት በውይይት እንዲፈቱ አበረታትተዋል:: ዋና ጸሐፊው ሀገራቱ በትብብር ላይ የቆመውንና በአለማቀፍ ሕጎች ላይ የተመሰረተውን ፤ መግባባትን ፣ መተማመንና የጋራ ተጠቃሚነትን ወደሚያረጋግጠው የ2007 ዓ.ም የመርሆዎች መግለጫ (Declaration of Principles) እንዲመለሱም አሳስበዋል::በሀገራቱ ሚኒስትሮችና ባለሙያዎች መካከል የሚደረገው ድርድር መግባባት ላይ የማይደረስ ከሆነ ድርድሩ በሀገራቱ መሪዎች ደረጃ እንዲከናወን ዋና ጸሐፊው አመላክተዋል::ይህ የዋና ፀሐፊው መልዕክት የኢትዮጵያን አቋም የሚያጸና ሲሆን በተቃራኒው ደግሞ በግብፅ የጸጥታው ምክር ቤት ክስና በአሜሪካው ድርድር ላይ ቀዝቃዛ ውሃ የቸለሰ ሆኖ ይሰማኛል::
ለኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ጉልበት የሚሆን ሌላው ሰሞነኛ ክስተት የአውሮፓ ኮሚሽንና ምክር ቤት ፤ የአባይ ወንዝና የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለሀገሪቱ ያለውን ስትራቴጂካዊ ጥቅም እንረዳለን ሲሉ ለኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በጻፉት ደብዳቤ አረጋግጠዋል:: እንዲሁም ሱዳንና ኢትዮጵያ በከፍተኛ ባለሥልጣኖቻቸው አማካኝነት ከግንቦት 9 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ለሁለት ቀናት በአዲስ አበባ ከመከሩ በኋላ ከድንበር ጉዳዮች በተጨማሪ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብና በሌሎች የሁለትዮሽ ጉዳዮች ለመተባበር ስምምነት ከመድረሳቸውም ባሻገር የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ፣ ” የሁለቱ አገሮች ግንኙነት በአስቸጋሪ ጊዜም ቢሆን ተጠናክሮ ይቀጥላል::” ብለዋል::እነዚህን ሶስት ታላላቅ ዲፕሎማሲያዊ ድሎች ተከትሎ ነው እንግዲህ ግብፅ ረግጣው ወጥታ ወደ ነበረው የሶስትዮሹ ድርድር እንደምትመለስ ከሰሞኑ ይፋ ያደረገችው::የጸጥታው ምክር ቤት ነገር ከመንግስታቱ ድርጅት እና ከአውሮፓ ኮሚሽንና ምክር ቤት ሰሞነኛ መግለጫ በኋላ ያከተመ ይመስላል፡፡
እንደ መውጫ
በሱዳንም ሆነ በግብፅ ወደ ሶስትዮሽ ድርድሩ መምጣት መዘናጋትም ሆነ መኩራራት አይገባም::ይልቅ የዲፕሎማሲ ጥረቱን ማፋፋም ፣ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ከአሁኑ በላይ ማፋጠን ፣ ከስምንቱ የራስጌ ተፋሰስ ሀገራት ጋር ስለ ድርድሩ መመካከር ፣ መንግስት ድርድሩን የአፍሪካ ፣ የተፋሰሱ ሀገራት ጉዳይ ማድረግ፤ በ2002 ዓም የተፈረመውን የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት (Cooperation Frame Work Agreement) እና በ2007 ዓም በግብፅ፣ በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል የተፈረመውን የመርሆዎች መግለጫ (Declaration of Principles) መልሶ የመደራደሪያ ሰነዶች አካል ማድረግ ያሻል፡፡
ከዚህ ጎን ለጎን መከላከያን ፣ የደህንነትና የስለላ ተቋማትን በሁለንተናዊ ማዕቀፍ ማዘጋጀት ፣ ለሕዝብ ትኩስ ትኩስ መረጃዎችን በማድረስ ሊመጣ ላለው ድልም ሆነ አደጋ በስነ ልቦናም ሆነ በአካል ማሰናዳት፣ ብረትን መቀጥቀጥ እንደጋለ ነው እንዲሉ ፤ የመንግስታቱንም ሆነ የሕብረቱን መግለጫ ተከትሎ በጸጥታው ምክር ቤት በተለይ በአምስቱ ቋሚ አባላት እና በምዕራባውያንና በአለማቀፍ ተቋማት የዲፕሎማሲ ስራዎችን አጠናክሮ ቀን ከሌት መስራት ይጠበቃል::በመላው አለም የሚገኝ ዳያስፓራ የዲፕሎማሲው ጠንካራ ክንድ እንዲሆን መስራት ይገባል:: በአገራቱ ወደ ድርድር መመለስ መዘናጋት አያስፈልግም::በተለይ ግብፅ የተመለሰችው ጊዜ ለመግዛት ወይም ምን አልባት በቀጣይ ልትወስደው ስላሰበችው ወታደራዊ ጥቃት ድርድሩን እንደ ምክንያት / ኤክስኪውዝ / ልትጠቀምበት አስባ ሊሆን ስለሚችል በንቃት ቆፍጠን ማለት ወሳኝ ነው::የኔልሰን ማንዴላ ቀመር በሚል የሚታወቅ የድርድር ስነ ዘዴ አለ። ተደራዳሪው ሀገር ወደ ድርድር ከመግባቱ በፊት ድክመቱንና ጥንካሬውን ለይቶ መስራት ይጠበቅበታል። ለድርድሩ ጉልበት / ሌቬሬጅ / የሚሆኑ ነጥቦችን በመለየት ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 21/2012
በቁምላቸው አበበ ይማም ( ሞሼ ዳያን )