የተማሪና መምህራንን የፊት ለፊት ግንኙነት የሚጠይቀው የመማር ማስተማር ሂደት ዛሬ ላይ በኮሮና ቫይረስ ወረርሺን ምክንያት ሊቋረጥ እና ተማሪዎችም ሆኑ መምህራን በቤታቸው ሊውሉ ግድ ብሏል:: ይህ ሂደት ደግሞ በተማሪዎች የትምህርት ሂደት ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩ እውን ቢሆንም፤ ይህ ተጽዕኖ ጉልቶ እንዳይታይ የሚያደርጉ በርካታ እርምጃዎች እየተወሰዱ ይገኛል:: ከዚህ አንጻር ባለፉት እትሞቻችን በፌዴራል መንግስት፣ በኦሮሚያ ክልል እና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን ማቅረባችን ይታወሳል:: በዛሬው እትማችንም በአማራ ክልል እየተወሰዱ ስላሉ እርምጃዎች የዳሰስን ሲሆን፤ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሙላው አበበ ያደረሱንን መረጃ እንደሚከተለው ለንባብ በሚያመች መልኩ አቅርበነዋል::
የኮቪድ 19 ወረርሺኝ መከሰትን ተከትሎ አጠቃላይ የመማር ማስተማር ሂደቱ እንደተቋረጠ የሚታወቅ ነው:: ይሄን ተከትሎም የትምህርት በሬዲዮ ስርጭት ላይ የነበሩ መርሃ ግብሮችም አብረው ነበር የተቋረጡት:: በመሆኑም በወረርሺኙ ምክንያት የተቋረጠው ትምህርት እንደሚቆይና ትምህርት ቤቶች በአጭር ጊዜ እንደማይከፈቱ በመገንዘብ ምን ማድረግ ይገባል? በሚል እንደ ክልል ኮማንድ ፖስት ውይይት አድርጓል:: በዚህም በትምህርት ሚኒስቴር የሚተላለፈው የፕላዝማ ትምህርት በክልሉ ተደራሽ እንዲሆንና ሶፍት ኮፒውን ጭምር ለተማሪዎች በማድረስ በየላፕቶፖቻቸው በመጫን እንዲከታተሉ በማስቻል ተጠናክሮ እንዲቀጥል የማድረጉ ስራ እንደተጠበቀ ሆኖ የክልሉ ኮማንድ ፖስትም በክልሉ መከናወን ስላለባቸው ተግባራት አቅጣጫ አስቀምጧል:: ከእነዚህ መካከል አንዱና የመጀመሪያ እርምጃ የተቋረጠው ትምህርት በሬዲዮ ማሰራጫዎች መደበኛ ስራቸውን እንዲቀጥሉ ማድረግ ነው::
በዚህም መሰረት እንደ ክልል የትምህርት በሬዲዮ ማሰራጫዎች አራት የነበሩ ቢሆንም፤ በስራ ላይ ያሉት ሁለት ናቸው:: ከዚህ ቀደምም ትምህርት በሬዲዮ ስርጭቱ በማይደርስባቸው አካባቢዎች በፍላሽ ነበር ትምህርት ቤቶችጋ ተደራሽ የምንደርገው:: አሁን ላይ ግን ተማሪዎችና ትምህርት ቤቶች ስለማይገናኙ ለዚህም መፍትሄ መስጠት እንደሚገባ ታሳቢ በማድረግ የመፍትሄ እርምጃ ተወስዷል:: የመጀመሪያው የጎንደር እና የደብረ ማርቆስ የትምህርት ማሰራጫዎች ተደራሽ በሚሆኑባቸው አካባቢዎች በስራቸው እንዲቀጥሉ ሲደረግ፤ ሁለተኛው ደግሞ እነዚህ ተደራሽ በማይሆኑባቸው አካባቢዎች መድረስ እንዲቻል ከአማራ ብዙሃን መገናኛ የራዲዮ ዘርፉ ጋር በመወያየት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ለየት ባለ መልኩ ለሌላ ተይዞ የነበረውን የአየር ሰዓት በክፍያ ማግኘት ተችሏል::
በዚህ መሰረት የወሎ ኤፍ.ኤም፣ የሸዋ ኤፍ.ኤም እና የባህር ዳር ኤፍ.ኤምን ተጠቅሞ ትምህርት በሬዲዮ እንዲሰራጭ እየተደረገ ይገኛል:: በእነዚህ የኤፍ.ኤም ሬዲዮ ጣቢያዎች የሚተላለፈውን የትምህርት በሬዲዮ ስርጭት አየር ሰዓት ክፍያም ዩኒሴፍ ድጋፍ ያደረገው ሲሆን፤ ይሄም የተቋረጠው ስርጭት ወዲያው እንዲጀምር አስችሏል:: መደበኛው የራዲዮ ትምህርት ስርጭት በዚህ መልኩ ወደ ስራ ከገባ በኋላም ወዲያውኑ የብሔረሰቦች ትምህርት የማስጀመር ተግባር የተከናወነ ሲሆን፤ በዚህም ከዚህ በፊት የነበሩትና ተቀርፀው የተቀመጡ አዊኛና ኦሮምኛ የመሳሰሉ የብሔረሰብ ቋንቋ ትምህርት ስርጭቶች ራሱን በቻለ የአየር ሰዓት እንዲተላለፍ ተደርጓል::
ከዚህ በተጨማሪ የሰባተኛ እና የስምንተኛ ክፍል ከዚህ በፊት ትምህርት በሬዲዮ ተሰጥቶ አያውቅም:: ስለዚህ የሰባተኛ እና የስምንተና ክፍል ትምህርት በሬዲዮ ስርጭት መርሀ ግብር እንደ አዲስ ተቀርጾ እንዲሰራጭ የተደረገ ሲሆን፤ በተለይ የፊዚክስ፣ ኬሚስትሪ እና ባዮሎጂ አይነት ትምህርቶችን የይዘት መረጣ ተከናውኖ የትምህርት በሬዲዮ እንዲቀርጽላቸው እና ካለፈው ሳምንት ጀምሮ አየር ላይ እንዲውል ተደርጓል:: ከዚህ በተጓዳኝም ከአንድኛ እስከ አራተኛ ክፍል ላሉ ተማሪዎች በተለይም የአማርኛ አፍ መፍቻ ቋንቋ ትምህርት በሬዲዮ አይሰራጭም ነበር:: ይሄንንም ከሬዴዮ ፕሮጀክት ጋር በመሆን በጀት መድበውለት ቀረጻ ተጀምሯል::
በሌላ በኩል የ10ኛ እና 12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ወሳጅ የነበሩ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ራሳቸውን ከትምህርት ብቻ ሳይሆን ከፈተናም እንዳያርቁ የማድረግ ተግባር እየተከናወነ ነው:: በዚህም ዞን አቀፍ የሞዴል ፈተና ተዘጋጅቶ በወረዳዎች በኩል ለእያንዳንዱ ትምህርት ቤትና ተማሪ እንዲደርሰው ለማድረግ እየተሰራ ሲሆን፤ ይሄም ተማሪዎች ትምህርት ቤት መገኘት ሳይጠበቅባቸው በየቀበሌያቸው እንዲደርሳቸው ማስቻልን ታላሚ ያደረገ ነው:: ከዚህ ባለፈ የግል ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ በከተማ አካባቢ ላሉ ተማሪዎች የተለያዩ ዎርክሾፖች እንዲደርሱ የማድረግ ተግባር ቴሌግራምን ጨምሮ በተለያዩ የመገናኛ አውታሮች እየተከናወነ ነው::
ትልቁ ጉዳይ እነዚህ ሁሉ ተግባራት ተከናውነውም ሆነ እየተከናወኑ እያሉ ሁሉንም ተማሪዎች ተደራሽ ማድረግ ተችሏል ወይ የሚለው ሲሆን፤ በዚህ ረገድ በሚፈለገው ልክ ሁሉንም ተማሪዎች በተለይም ሩቅና ገጠራማ አካባቢ ያሉ ተማሪዎችን በሚፈለገው ልክ ተደራሽ ማድረግ አለመቻሉ ተለይቷል:: ይሄን በመገንዘብም የራዲዮ ስርጭቶች ከሌላ ጣቢያ ጋር ጭምር እንዲገናኙ (ሊንክ) በማድረግ ወደነዚህ አካባቢዎች እንዲደርስ የማስቻል ጥረት እየተደረገ ሲሆን፤ ይሄም ሆኖ የተወሰኑ ቀበሌዎች ላይ እየደረሰ አለመሆኑን መገንዘብ ተችሏል:: ከዚህ በተጓዳኝም በአንዳንድ አካባቢዎች ተማሪዎች በራሳቸው እንዲሁም ወላጆች ትምህርት ልጆች ስርጭቱን እንዲከታተሉ ሳይሆን ስራ ላይ እንዲያተኩሩ የማድረግ አዝማሚያዎች መኖራቸውም ታውቋል:: ይሄን ችግር ለመፍታትም በየወረዳውም ሆነ በየቀበሌው አመራሩ ጭምር ድጋፍ አድርጎ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ጥረት እየተደረገ ነው::
በዚህ ሂደት መምህራን ከተማሪዎች ጋር የሚያደርጓቸው የቀጥታ ግንኙነቶች ባይኖሩም በዚህ ወቅት መምህራን መልካም ተግባር እያከናወኑ መሆኑም ታውቋል:: በተለይ በተለያዩ አካባቢዎች ግንዛቤ የማስጨበጥ ተግባር እያከናወኑ ሲሆን፤ ለተማሪዎች የሚያስፈልጉ የትምህርትም ሆነ የፈተና ዝግጅቶች ላይ ሰፊ ተሳትፎ በማድረግም አበርክቷቸው የጎላ ነው:: በዚህም ሁሉም ናቸው ባይባልም የተወሰኑ መምህራንም ቢሆኑ የተለያዩ ፈተናዎችን በማውጣትና ለዞኖች በመስጠት ዞኖች እያበዙ ለየወረዳዎች፣ ወረዳዎችም ለየትምህርት ቤቶችና ቀበሌዎች በማድረስ ተማሪዎቹ እንዲደርሳቸው በማድረግ ረገድ የድርሻቸውን እየተወጡ ይገኛል:: ትምህርት ቤቶች ላይ ሊከናወኑ የሚገባቸው ተግባራት ሲኖሩም ተሳትፏቸውን ያላቋረጡ መምህራን መኖራቸውንም መገንዘብ ተችሏል::
እንደ አጠቃላይ ግን ከወረርሺኙ ራስን ከመጠበቅ ጎን ለጎን ከቢሮው የሚወርዱ ስራዎች ይኖራሉ:: በዚህም ከክልል እስከ ትምህርት ቤት ምን መስራት እንዳለባቸው የሚያመላክት የወረደ ሰነድ አለ:: በመሆኑም ትምህርት ቤቶች ትምህርት ሲጀመር እንዴት አድርገው መቀበል እንደሚገባቸው ማሰብ አለባቸው:: የቅበላ ሂደቱም የሚሆነው ከዚህ በፊት እንደነበረው ሳይሆን ለየት ባለ መልኩ ከባድ ስራ እንደሚጠበቅባቸው አውቀው ሊሆን ይገባል:: ለምሳሌ፣ ቅበላው በሚቀጥለው ዓመት የሚሆን ከሆነ ከባድ ስራ ነው የሚጠብቀው::
ምክንያቱም አሁን የቀረው ትምህርት በመኖሩ እሱን የመሸፈን ተግባር ይከናወናል፤ ፈተና የመፈተንና ውጤት የማጠናቀር ብሎም ተማሪዎችን ወደሚቀጥለው ክፍል የማዘዋወር እንዲሁም ወደ ሚቀጥለው ክፍል የተሸጋገሩ ተማሪዎችን ለማስተማር እቅድ ማውጣትን የመሳሰሉ ተደራራቢና ከባድ ስራዎች አሉ:: እንደ ቢሮም ይሄን በመገንዘብ እየሰራ ሲሆን፤ በተጓዳኝ ተማሪዎች በጥያቄና መልስ መልኩ ተሳትፏቸውን የሚያሳድጉበት አቅጣጫ ተነድፎ የሚተገበርበት ሂደት ላይ እየተሰራ ነው:: በመሆኑም ወላጆች ልጆቻቸው እነዚህን የትምህርት መርሃ ግብሮች እንዲከታተሉ ጊዜ ሊሰጧቸው፤ ተማሪዎችም ትምህርት የለም ብሎ መዘናጋት ሳይሆን በእጃቸው ካሉ መጽሐፍት ጋር በማገናኘት ትምህርቱን ትኩረት ሰጥተው ሊሳተፉም፣ ሊያጠኑም ይገባል::
አዲስ ዘመን ግንቦት 21/2012
ወንድወሰን ሽመልስ