በተለይ አዋጭ የንግድ ስራ ይዘው ገንዘብ ካጠራቸው ባለብሩዕ እዕምሮ ባለቤት ወጣቶች ጋር በጋራ የመስራት ትልቅ ፍላጎት አላቸው። በዚህ የተነሳ በርካታ ወጣቶችን በየዕለቱ ያማክራሉ። በሌላ በኩል ደግሞ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማትን እና የማስታወቂያ ድርጅቶችን አቋቁመው በርካታ ሰራተኞችን መቅጠር ችለዋል። ባለታሪካችን አቶ አዲስ ዓለማየሁ ይባላሉ።
አቶ አዲስ የተወደሉት አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ነው። የልጅነት ጊዜያቸውን ያሳለፉት በአያታቸው ቤት ነው፣ ሰፊ ቤተሰብ ውስጥ ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በቅዱስ ዮሴፍ ትምህርት ቤት ነው የተማሩት። በወቅቱ ከትምህርቱ ይልቅ ለንግድ ስራ ያላቸው ፍላጎት ከፍተኛ እንደነበር አይዘነጉትም። በተለይ ላምበረት አካባቢ በሚገኝ የአያታቸው ጠጅ ቤት ውስጥ በአስተናባሪነት ለተቀጠረ ሰው ረዳት በመሆን በቀን 25 ሳንቲም ይቀበሉ እንደነበር ፈገግታ በተሞላበት ሁናቴ ያስታወሱታል። ይሁንና አያታቸው ይህን የድብቅ ስራቸውን በማወቃቸው ክልከላ ተጣለባቸው። ጠጅ ቤትም ድርሽ ሳይሉ ወደ ትምህርታቸው እንዲያተኩሩ ተነገራቸው።
አያታቸው ጠንካራ ሰራተኛ በመሆናቸው የልጅ ልጃቸውንም ሲያድግ ተቀጥሮ ሳይሆን የእራሱ ድርጅት አቋቁሞ እንዲሰራ ገና በለጋ እድሜው ያበረታቱ እንደነበር አቶ አዲስ ያስታውሳሉ። አራተኛ ክፍልን ሲያጠናቅቁ ግን ከአያታቸው ተለይተው ከአባታቸው ጋር ወደኬንያ የሚሄዱበት አጋጣሚ ተፈጠረ። የአንበጣ መከላከል ድርጅት ውስጥ በአውሮፕላን መካኒክነት ሙያ የተሰማሩት አባታቸው በየሀገሩ ተዟዙረው ይሰሩ ነበርና ወደኬንያ ሲመደቡ ልጆቻቸውንም ይዘው ወደዚያው አቀኑ ። እናታቸው ደግሞ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰራተኛ ነበሩና በየጊዜው እየሄዱ ይጎበኟቸው ነበር።
ኑሮ በኬንያ የመጀመሪያዎቹ አመታት ከነ ቤተሰባቸው ከበድ ብሎ ነበር። አዲስ ባህል፤ ቋንቋ እና ከዘመድ አዝማድ መራቁ ፈታኝ ነበር። ይሁንና አባታቸው በጥንካሬ የሀገር ባህልንም ሆነ ቋንቋን እንዲሁም የውጭውንም ባህል እና ቋንቋ በሚገባ ልጆቻቸውን ማስተማር መቻላቸውን አቶ አዲስ ይናገራሉ። በኬንያም ከ5ኛ ከፍል ጀምረው አስኳላውን ቀጠሉበት። በወቅቱ በኬንያ ትምህት ቤቶች በየሶስት ወሩ እረፍት ስለነበራቸው አዲስ አበባ እየመጡ ቤተሰባቸውን ይጠይቁ ነበር። ለዚህ ደግሞ የእናታቸው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰራተኝነት ነጻ የትኬት አገልግሎት በእጅጉ ረድቷቸዋል።
በኬንያም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲደርሱ ደግሞ ከአስኳላው ጎን ለጎን አሁንም ገንዘብ የማግኛ መንገዶችን ይፈልጉ እንደነበር ያስታውሳሉ። በተለይ አባታቸው ረዘም ላለ ጊዜ ለስራ በሚለዩበት ወቅት የቤት መኪናቸውን በመያዝ ለጓደኞቻቸው የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ጥቂት ገቢ ይሰበስቡ ነበር። በናይሮቢ ቤታቸው በነበረ አነስተኛ የጓሮ ቦታ ላይ ደግሞ ከወንድማቸው ጋር አትክልት ተክለው ለእናታቸው በክፍያ ያቀርቡ እንደነበረም በፈገግታ ያስታውሱታል።
በኬንያ እስከ 11ኛ ክፍል እንደተማሩ ግን ቤተሰቡም ወደአሜሪካ በማቅናቱ 12ኛ ክፍልን እዚያው አጠናቀቁ። ከአሜሪካ በኋላ ደግሞ አሁንም ቤተሰቡ ወደካናዳ አመራ። በካናዳም ብርዱ፣ የአኗኗር ባህሉ እና ማህበራዊ ህይወቱን ለመልመድ ተቸግረው ነበር። በዚህም ምክንያት ምን ጊዜም ልባቸው ሀገራቸው ላይ ነበር። ይሁንና ጊዜያቸውን በሁለት እና ሶስት ስራ ማሳለፋቸው ደግሞ አልቀረም። በተለይ በካናዳ ቤቶችን እየገዙ ወደማከራየት ስራ በመሳባቸው በ21 ዓመታቸው የሶስት ቤቶች ባለቤት እንደነበሩ ይናገራሉ። ጥንካሬያቸውም ከእድሜያቸው ጋር እያደገ ቢመጣም የካናዳ ኑሮ ግን ከውጭ ለመጣ በተለይ ለአንድ ጥቁር አፍሪካዊ ብዙ የሚያሳድግ ሁኔታ እንደሌለው መረዳት ይጀምራሉ።
በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያሉ እናታቸው በጠና ታመው ለመጠየቅ አዲስ አበባ መጡ፤ ከሶስት ወራት በኋላ ደግሞ እናታቸው በማረፋቸው ለሀዘን ስርዓቱ አዲስ አበባ ተመልሰው ሲመጡ የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት የሚካሄድበት ወቅት ነበርና ብዙም ለመቆየት ተመራጭ አልሆነላቸውም። ከሁለት ዓመታት በኋላ ወደአዲስ አበባ ሲመለሱ ግን በመጠኑ የተረጋጋ ሁኔታ ነበር። ከዚህ ባለፈ ግን በየሄዱበት ሁሉ ልክ እንደካናዳው ህይወታቸው <<ከየት ነህ>> የሚል የባይተዋርነት ስሜት የሚፈጥር ጥያቄ የሚጠይቃቸው ሰው አለመኖሩን ታዘቡ። ይህም በሀገር ቤት ለመኖር እጅጉን አነሳሳቸው።
ነጻነታቸው እና ክብራቸው ያለው በሀገራቸው መሆኑን በእጅጉ የተሰማቸው ጊዜ ነበርና ለአባታቸው ደውለው <<በቃ ከዚህ በኋላ ወደካናዳ አልመለስም አዲስ አበባ ነው መኖር የምፈልገው የሚል መልዕክት አስተላለፉ>>። በወቅቱ አባታቸው ለስራ የሚሆን በቂ ገንዘብ እንደሌላቸው እና የሚያወቁትም የቅርብ ሰው አለመኖሩን በመንገር እንዲመለሱ ቢጠይቁም እርሳቸው ግን <<እስቲ እንደሚሆንልኝ ልየው>> የሚል ምክንያት በማቅረባቸው አዲስ አበባ የመቆየታቸው ጉዳይ እውን ሆነ። በወቅቱም የሚረዳቸው ሁነኛ ዘመድ ባይኖርም ምክር ሲፈልጉ ግን የአባታቸው ጓደኞቸ የሆኑት የኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ ኩባንያ መሥራች አቶ ብዙአየሁ ታደለ እና የአልሜታ ሻይ ባለቤት አቶ መስፍን ተሾመ በመሄድ ለስራቸው የሚሆኑ ጠቃሚ ሃሳቦችን ያገኙ እንደነበር አይዘነጉትም።
በአዲስ አበባ ቆይታቸው አንድ ከሳተላይት ጋር የተያያዘ ስራ ለሚከውን ድርጅት የምስራቅ አፍሪካ ማናጀር ሆነው የሚሰሩበት እድል አገኙ። በተለያዩ የምስራቅ አፍሪካ አገራት እየተዘዋወሩም ጥቂት ጊዜያትን ሰሩ። ከዚህ በኋላ የእራሳቸው የግል ስራቸውን መስራት እንዳለባቸው በመወሰን አንድ የኬንያ ባለሃብትን ሲያማክሩ ሬዲዮ ጣቢያ ቢከፍቱ አዋጭ እንደሆነ ይነግራቸዋል። ኢትዮጵያ ላይ ሲመለከቱ ደግሞ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ እና የብዙ ኤምሳሲዎች መገኛ በሆነችው አዲስ አበባ እንኳን አንድም የእንግሊዘኛ ሬዲዮ ጣቢያ አለመኖሩን ያጤናሉ። እናም የእንግሊዘኛ ሬዲዮ ጣቢያ ፈቃድ ለማውጣት ወደ ኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ጎራ አሉ።
ይሁንና በወቅቱ የተደራጀ አሰራር እና ፖሊሲ እንኳን ባለመኖሩ ለሰራተኞቹ የኬንያ የሬዲዮ ጣቢያ ፖሊሲዎችን እና መመሪያዎችን ጭምር ከኢንተርኔት እያወረዱ ይሰጡ እንደነበር ይናገራሉ። በመጨረሻም ፍቃድ የሚሰጠው በጨረታ ነው በመባሉ እርሳቸው በተሳተፉበት ወቅተ 14 ተቋማት ፍቃድ ለማውጣት ተወዳደሩ። በጊዜው ግን ለሌሎች ሁለት ሬዲዮ ጣቢያዎች ፍቃድ በመሰጠቱ የአቶ አዲስ የእንግሊዘኛ ሬዲዮ ጣቢያ ከነፕሮፖዛሉ ለተጨማሪ ወራት መቀመጡ ግድ ሆነ።
ከዚህ በኋላ ከአንድ መንግስታዊ ካልሆነ ድርጅት ጋር ወደአሜሪካ በሚላኩ የጨርቃጨርቅ ምርቶች ማበረታቻ /አጎዋ/ እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያግዝ ፕሮጀክት መምራት ጀመሩ። በዚህ ስራ ላይ እያሉ ግን በርካታ ሰዎችን መተዋወቃቸውን እና በኢትዮጵያ ያለውን የስራ አካሄድ በሰፊው ለመረዳት እድል እንዳገኙ ይናገራሉ። እናም ከብዙ ጥረት እና ትግል በኋላ የሬዲዮ ጣቢያውን ለመክፈት ካሰቡ ከስምንት ዓመት በኋላ ፍቃዱን አግኝተው አፍሮ ኤፍ ኤም የተሰኘውን የእንግሊዘኛ ቋንቋ ማሰራጫ ከአጋሮቻቸው ጋር ለመከፈት ቻሉ።
በወቅቱም ከኬንያ እና ከተለያዩ ቦታዎች ታዋቂ የእንግሊዘኛ ፐሮግራም አዘጋጆችን ጭምር በመያዝ ኤድናሞል ህንጻ ላይ ቢሮ ተከራይተው መስራት ጀመሩ። የሬዲዮ ቴክኖሎጂው ተገጥሞ የመጀመሪያው የሙከራ ስርጭት ሲደረግ በከተማዋ እየተዘዋወሩ ባዳመጡበት ወቅት የተሰማቸው ደስታ ልዩ እንደነበር አይዘነጉትም። በሬዲዮ ጣቢያውም ለተለያዩ ዜጎች በኢትዮጵያ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ እና አስፈላጊ መረጃዎችም እንዲሁም መዝናኛዎችን በማስተላለፍ በአጭር ጊዜ ተቀባይነት መገኘቱን ያስታውሳሉ። አንድ ነገር ካሳኩ በኋላ ወደሌላ ለሌላ ስራ ማቀድን የሚመረጡት አቶ አዲስ ከሬዲዮው ምስረታ በኋላ የቴሌቪዥን ጣቢያ ማቋቋም እንዳለባቸው ወሰኑ።
ስለጣቢያው የሚያትት የቢዝነስ እቅድ በማዘጋጀት ዱባይ የሚገኙ ማሰራጫዎችን በማነጋገር ዋጋውን አወጡ። ያሰቡት ጣቢያ ደግሞ ሙዚቃ ብቻ የሚተላለፍበት ደቡብ አፍሪካ የሚገኘውን ኤምቲቪ የተሰኘውን ታዋቂ የመዝናኛ ጣቢያ ኃላፊዎችን አነጋገሩ። ይሁንና አብረው ለመስራት ዋጋው እንደሚወደድባቸው በመንገር በእራሳቸው ጣቢያ የሚሰራጩ ፕሮግራሞችን ይዘው ቢሰሩ መልካም እንደሚሆን ኤምቲቪዎች መከሯቸው። ይህንን ሃሳብ እንደያዙ ግን 251 ኮሚዩኒኬሽን የተሰኘውን የማስታወቂያ ድርጅት አቋቋሙ።
በማስታወቂያ ተቋሙ ስር የሎጎ፤ ብራንድ እና የኢንተርኔት ማስታወቂያዎችን ጨምሮ ለተለያዩ ዓለም አቀፍ እና የሀገር ውስጥ ተቋማት በርካታ ማስታወቂያዎችን ማዘጋጀት ችለዋል። ከዚህ በኋላ እቅዱ ወደተዘጋጀው የቴሌቪዥን ስራ ተመልሰው አረብ ሀገራት ላይ ስለሚቀረቡ ፕሮግራሞች ምልከታ አደረጉ። እናም በአውሮፓም ሆነ በአረቡ ዓለም ላይ ፊልሞችን በአገሬው ቋንቋ ተርጉመው የሚያቀርቡባቸው ጣቢያዎች በመኖራቸው በኢትዮጵያም ተግባራዊ ለማድረግ ወሰኑ።
ከንግድ አጋሮቻቸው ጋር በመሆንም ፍቃድ አውጥተው ቃና የተሰኘውን በዋናነት የትርጉም ፊልሞችን በአማርኛ ቋንቋ የሚያቀርብ ጣቢያ ከፈቱ። ይሁንና ጣቢያው ገና ስራ ሳይጀምር ቴያትር እና ፊልም ቤቶች ላይ ኪሳራ ያደርሳል የሚል ቅሬታ በተለያዩ ሰዎች መቅረብ ጀመረበት። በዚህ የተነሳ ጣቢያው ገና ስራ ሳይጀምር ነጻ ማስታወቂያ እንደተሰራለት አቶ አዲስ ይናገራሉ። እናም ቃና ስርጭቱን ሲጨምር ከመላ ኢትዮጵያ አልፎ እስከ ኤርትራ ድረስ ሰፊ ተከታታይ ማግኘት የቻለ ጣቢያ ሆነ። አቶ አዲስ እንደሚሉት ከሆነ፤ ቃና ከመዝናኛው ዘርፍ ባሻገር ኤርትራ የሚገኙ ህጻናት አማርኛ ቋንቋን እንዲለምዱ ያደረገ ጣቢያ መሆኑ አስገራሚው ነገር ነው።
አቶ አዲስ በአንድ ዘርፍ ብቻ መወሰን አይፈልጉምና ከጣቢያው ስራ ጎን ለጎን ከሶስት ዓመት በፊት ደቡብ አፍሪካ ላይ አፍሪካ ኮሚዩኒኬሽን ግሩፕ የተሰኘ ህዝብ ግንኙነት ስራ የሚከውን ተቋም በዘርፉ ታዋቂ ከሆነች ኢትዮጵያዊት ጋር በጋራ አቋቁመዋል። በጆሃንስበርግም 13 ሰራተኞችን ይዘው ለትላልቅ የኢትዮጵያ እና የውጭ ሀገራት ተቋማት ከመገናኛ ብዙሃን እና የህዝብ ግንኙነት ጋር የተያያዙ ስራዎችን ላይ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛል።
ከዚህ ባለፈ በተለያዩ ዘርፎች ላይ አጋር ሆነው መስራት የሚወዱት የንግድ ሰው የማስታወቂያ ህትመት ድርጅቶች፣ ስራና ሰራተኛን ከሚያገናኝ የቴክኖሎጂ ፈጠራ እንዲሁም ከተለያዩ ወጣቶች ጋር በጋራ የሚሰሩባቸው ድርጅቶችንም አቋቁመዋል። ስራ እና ሰራተኛን የሚያገናኘው ድርጅት በወጣቶች የተዋቀረና የእራሱ የሞባይል መተገበሪያ ያለው ሲሆን በጂፒኤስ ተገናኝቶ በሚፈለግበት አካባቢ ብቻ የስራ ማስታወቂያዎች ይተላለፍበታል። በቴክኖሎጂ የታገዘ የወጣቶች ኢንጂነሪንግ ስራ ላይም ኢንቨስት ያደርጋሉ። አቶ አዲስ ከካናዳ ሲመጡ የነበራቸውን ችግር በማስታወሳቸው ሃሳብ ይዘው የኢንቨስትመንት መነሻ ከቸገራቸው ወጣቶች ጋር መስራትን ምርጫቸው አድርገዋል። በየቀኑም በርካታ ወጣቶችን በኢትዮጵያ ስላለው የስራ አማራጮች በማማከር ላይ ናቸው።
በአጠቃላይ በአቶ አዲስ ስር በሚገኙ ተቋማት ከ400 በላይ ሰዎቸ ተቀጥረዋል። በቀጣይም ሰፊ የስራ እድል የሚፈጥሩ እቅዶች አሏቸው። በዚህ ረገድ ባህር ዳር ከሚገኝ ስራ ፈጣሪ ወጣት ጋር የካልሲ ማምረቻ ፋብሪካ ለመክፈት ዝግጅት እያደረጉ ይገኛል። በወጣቶች ሃሳብ ላይ ኢንቨስት ለማድረግም የአዲስ ኤንጅል ኔትወርክ የሚል የተለያዩ ባለሙያዎች ስብስብ አባል በመሆን ሃሳብ ኖሯቸው ገንዘብ ያጠራቸውን ወጣቶች ለማገዝ ይሰራሉ። ማንኛውም አዋጭ የንግድ ስራ ሃሳብ ያለው ወጣት ቢያማክራቸው አዋጭነቱን አይተው አብረውት ሊሰሩ እንደሚችሉ አቶ አዲስ ይናገራሉ።
<<መንግስት ለሁሉም ስራ መፈጠር አይችልምና ወጣቱ ነጋዴ ለሚለው ቃል ጥሩ አመለካከት ኖሮት ሀገርን እና እራሱን የሚጠቅም ስራ ላይ መሰማራት አለበት>> ይላሉ። መውደቅና መነሳት ይኖራል፤ ዋናው ግን በችግር ውስጥም ቢሆን ተምሮ ማደጉ ነውና ማንኛውንም ጊዜ በስራ ማሳለፍ ይገባል የሚለው ደግሞ ምክራቸው ነው። ቸር እንሰንብት!!
አዲስ ዘመን ግንቦት15/2012
ጌትነት ተስፋማርያም