ብዙ ጥበባዊ ሥራዎች መነሻቸው ሃይማኖት ነው። የኪነ ህንጻ፣ የዘመን አቆጣጠር፣ የተለያዩ ዜማዎች… ወዘተ። በተለይም በዓለም አቀፍ ደረጃ በቅርስነት የተመዘገቡ ኪነ ህንጻዎች መነሻቸው ሃይማኖታዊ ነው። በኢትዮጵያ ያሉ ታሪካዊ ቅርሶችንም ካየን በሃይማኖታዊ እሳብ /ጥበብ/ የተሰሩ ናቸው። የእስልምና ሃይማኖት እንዲሁ ለተለያዩ የዓለም አገራት የኪነ ህንጻ ጥበብ መሰረት ሆኗል። የመካከለኛው ምሥራቅ ዓለም ቅርሶች ዛሬም ለዚሁ እውነታ ም ሥክር ናቸው።
ለእስልምና እምነት ተከታዮች ‹‹ሮመዳን ከሪም›› እያልን፤ የተለያዩ የታሪክ ድርሳናትን፣ ጥናታዊ ጽሑፎችንና ድረ ገጾችን በመቃኘት የእስልምና ሃይማኖት በኪነ ህንጻና በዜማ ያበረከታቸውን የጥበብ ሥራዎች እንዳስሳለን።
ዶክተር ሀሰን ሰዒድ የተባሉ አጥኚ ባቀረቡት አንድ ጥናት ላይ እንደገለጹት፤ ነብዩ መሀመድ ለኢትዮጵያ ነገስታት የተለያዩ ሥጦታዎችን ልከዋል። እነዚህም ጥበባዊ ሥጦታዎች ጥቁር ሙሉ ልብስ፣ የወርቅ ቀለበት፣ የአበሻ ፈርጥ ያለበት ሦስት አንካሴዎች፣ ሽቶ፣ የአበሻ በቅሎዎች እና ሌሎችም ይገኛሉ። የእስልምና ሃይማኖት በኢትዮጵያ ያበረከታቸው መንፈሳዊም ሆኑ ቁሳዊ ቅርሶች አያሌ ናቸው። በሶማሌ፣ በአፋር፣ በሐረሪ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ በአርጎባ እና በሌሎችም አካባቢዎች የእስልምና ሃይማኖት ታሪካዊ ቅርሶችን እናገኛለን።
ወደ ሐረርና አካባቢዋ ስንሄድ የሐረሪዎችን እስላማዊ ቅርስ እናገኛለን። የአያሌ መስኪዶች ደብር የሆነችው ሐረር እስልምናን ከተቀበለች ከአንድ ሺ ዓመታት በላይ አስቆጥራለች። ሼህ አባድር እና ተከታዮቻቸው የሐረርን ምድር ከረገጡባት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን ባለው ጊዜ አያሌ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ቅርሶች ተፈጥረዋል።
ለምሳሌ ‹‹አሹራ›› ተብሎ የሚታወቀው እስላማዊ በዓል በሐረር ውስጥ በተለየ መልኩ ይከበራል። ይህም ጅቦችን ገንፎ በማብላትና ከጅቦች ጋር ሠላማዊ ኑሮ ከመመስረት ጋር የተገናኘ ልዩ የአካባቢያዊ ስርዓቶች አሉት። ይሄ ኢትዮጵያዊ የሆነ የሙስሊሞች ባህላዊ ቅርስ ነው።
የእስልምና ጉዳዮች ተመራማሪ እና የታሪክ አጥኚ የሆኑት ተሾመ ብርሃኑ ከማል በተለያዩ ጥናቶቻቸው እና የጋዜጣ ጽሑፎቻቸው (ሪፖርተር ጋዜጣ) ስለመንዙማ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል። የእርሳቸውን ጥናቶች ዋቢ አድርገን በሮመዳን በዓል ስለመንዙማ እናውራችሁ።
‹‹መንዙማ›› የዓረብኛ ቃል ሲሆን የተገኘውም ነዞመ፣ ከተሰኘው ሥርወ ቃል ነው። ትርጉሙም አዘጋጀ፣ አደረጀ፣ ትክክለኛ ቦታ ላይ አስቀመጠ፣ አስተካከለ፣ ተስተካከለ ማለት ነው። ‹‹አልሺዕር›› የሚል ቃል ሲጨመርበት ደግሞ ነዞም አልሺዕር ግጥም መደርደር፣ መግጠም፣ ቃላትን ሐረጎችን፣ ስንኞችን በትክክለኛ ቦታቸው ማስቀመጥ መደርደር ይሆናል። ኢንተዞመ፣ ተነዞመ፣ ተናዞመ፣ ሲሆን ደግሞ አዘገጃጀት፣ አደረጃጀት፣ አደራደር የሚል ስሜት ይሰጣል። ተንዚሙል ሺዕር ሲሆን ግጥምና ቅኔ የግጥምን ሥነ ጽሑፋዊ ውበት በተከተለ ሥልት፣ ሥርዓት፣ አካሄድ በቅደም ተከተል ማስቀመጥ፣ መደርደር፣ ለወጣለት ዜማ ወይም ለሚወጣለት ዜማ እንዲሆን አድርጎ መድረስ የሚል አንድምታ አለው። መንዙማ ከሌላው ግጥም የሚለየው ከእስልምና እምነት ጋር የተያያዘ መንፈሳዊ ግጥም በመሆኑ ነው። እስካሁን ሲነገር የነበረው የመንዙማ ትርጉም በዚህ የሚተካ ከሆነ ዜማውንና ግጥሙን፣ እንዲሁም ውዝዋዜውንና የምት መሣሪያውን የሚያጠቃልል ገላጭ ስም ማውጣት አስፈላጊ ይሆናል።
ከመንዙማ ጋር ግጥምና ዜማ አብረው የሚኖሩ ሲሆን ገጣሚዎቹና ዜማ አውጭዎቹም በሚያውቁት፣ በታያቸው፣ በበራላቸው፣ በተረዳቸው መንገድ ሐሳብ የሚያመነጩና የሚያዜሙ ሲሆኑ የግጥምና የዜማ ደራሲዎቹም ዘመን አይሽሬ ሥራ ሊያበረክቱ እንደሚችሉት ሁሉ ለጊዜው አንጎራጉረው የሚተውት ሊሆን ይችላል።
ከመንዙማ ግጥምና ዜማ ጋር የሚነሳው ዋናው ቁም ነገር ደራሲዎቹ እነማን ናቸው? ከየት ናቸው ? በኅብረተሰቡ የነበራቸው ወይም ያላቸው የላቀ ደረጃ እስከ ምን ድረስ ነው? ከዚህም በተጨማሪ በግልጽም ሆነ በረቀቀና በጠለቀ ሚስጥራዊ መንገድ የሚያስተላልፉት መልዕክት ምንድ ነው? ጥልቀቱና ምጥቀቱ ምን ያህል ነው? ቅርፁ ምን ያህል ማራኪ በሆነ ውበት ይዘቱን ገልጾታል? ብሎ መመርመር ያስፈልጋል። መንዙማውን ሰምተን ምን አገኘን ? ደረጃችንን ከፍ አደረግን ወይስ የጨመርነው ነገር የለም? ከዚህም በላይ የመንዙማ ግጥሞቹ በእንጉርጉሮም ሆነ በሌላ መንፈስ ቀስቃሽና ስሜት ኮርኳሪ ዜማ ተቀናብረው ሲቀርቡ ምን ያህል ቀና ናቸው? ምንስ ያህል የሰውን ልቦና ይማርካሉ? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው።
መንዙማ ጥንታዊ የፈጣሪ ማመስገኛ፣ የነብዩ ሙሐመድ (ሱዓወ) ማወደሻ፣ የፈጣሪ አሀድነትን ማስተማሪያ ሲሆን፤ በዚህ ረገድ በሰሜን ኢትዮጵያና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ የንጉሥ (ወሎ) ሙጃሂዱ በግንባር ቀደምነት እንደሚጠቀሱ፣ ቀጥሎም የአና ሸኾች እንደሚመጡ፣ ከአናም ወደ ዳና፣ ከዳና ወደ ጫሌና ወደ ሌሎች እንደ ተዛመተ አስረድቶኛል። በራያ (አና) እነ ጀማሉዲን አንይ፣ ሼክ ኢብራሂም ሪሓና፣ ሼክ አዋሎዎ፣ ሼክ ዓብዱሶመድ፣ ሼክ ዓብዱራሕማን፣ ሼክ መሐመድ ዓረቡ ሲራጅ፣ ሼክ ዓብዱረዑፍ፣ ሼክ ቡሰይሪል አንይ፣ ሼክ ሚስባህ አንይ፣ አባታቸው ሼክ አወል ይጠቀሳሉ። በዚህ ዓይነት የዳናውን፣ የጫሌውን፣ የሾንኴን፣ የዳባቱን፣ የጎንደሩን፣ የጎጃሙን፣ የቀጥባሬውን፣ የአልከሶውንና የአብሬቱን መግለጽ ይቻላል።
መንዙማ ከዘመኑ ጋር የሚያድግ፣ አገሪቱ ከሌሎች አገሮች ጋር በሚኖራት ግንኙነት የሚጎለምስ ስለሆነ ግጥም በወዲያኛዎቹ አያቶቻችን ዘመን፣ ግጥም በአባቶቻችን ዘመንና ግጥም በእኛ ዘመን ብሎ መተንተን ሊያስፈልግ ይችላል። ለምሳሌ የዛሬ 70 ዓመት ገደማ ሐጂ ባደረገበት ጊዜ መካንና መዲናን ዓይቶ የድንጋይና የአሸዋው ክምር፣ ስለአነስተኛዎቹ የመኖሪያ ቤቶች፣ ፅዳት ስለጎደላቸው ምግብ ቤቶች፣ ስለዓረብ ምጽዋት ፈላጊዎች፣ ስለተላላፊ በሽታዎች ቢቃኝ፣ በዚህ ዘመን የሚቃኘው ደግሞ ስለፎቆቹና መንገዶቹ ውበት፣ ስለመብራቱና በመብራት ስለተሠሩት ውብ ጌጦች፣ ስለመኪኖችና ስለሌሎች አስገራሚ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ሊጽፍ ይችላል።
‹‹በአሁኑ ጊዜ በወጣቶች የሚቀርበው መንዙማ በዓረብ አገሮች ከሚቀርበው ነሺዳ የተቀዳ ወይም የተዳቀለ፣ አንዳንዱም ከዓለማዊው ዘፈን የተወሰደ መሆኑን ስናጤን መንዙማንና ዘመንን አብሮ የማየት አስፈላጊነት እንገነዘባለን›› ይላሉ ተመራማሪው። እንዲህም ያብራሩታል።
‹‹ምክነር ቢ ትራዊንክ›› የተባለ ጸሐፊ፣ ‹‹ወርልድ ሊትሬቸር›› በሚል ርዕስ በ1953 ዓ.ም ባሳተመው መጽሐፉ እንደገለጸው፣ የዓረብ ሥነ ጽሑፍ ከሰባተኛው ክፍለ ዘመን በፊት እምብዛም አይታወቅም ነበር። ከዚያ በፊት በነበረው ታሪክ ሲጠናም ዓረቦች ከብቶቻቸውን ይዘው እስከ ግብፅና ሜሶፖታሚያ ድረስ የሚንቀሳቀሱ ዘላኖች ነበሩ። ከዚህም በተጨማሪ፣ እርስ በርሳቸው በጦርነት ይቆራቆሱ ስለነበር ህብረት አልነበራቸውም። ይሁንና ከ622 እስከ 630 በነበረው ጊዜ የተወለዱት ነብዩ ሙሐመድ (ሱዓወ) ይዘውት በተነሱት የኢስላም እምነትና በነበራቸው ኃይል ጠንካራዋን የዓረቢያ መንግሥት መሠረቱ። በዚህም መሠረት ፋርስን፣ ታናሿ እስያን፣ ሰሜን አፍሪካን፣ ስፔንና ከፊል የህንድ ግዛት፣ አፍጋኒስታንና ፓኪስታንን ለመያዝ በቁ። ከ650 እስከ 1300 ባለው ጊዜም በእነዚህ አገሮች መካከል ከፍተኛ የባህል፣ የዕውቀትና የማህበራዊ ሕይወት ውህደት ተፈጠረ።
የዓረብኛ ሥነ ጽሑፍ በተለይም ከሃይማኖትና ከፍልስፍና እንዲሁም ከሳይንስ ጋር ቁርኝት ያለው ሥነ ጽሑፍም በዚህ አጋጣሚ ለማስፋፋት ዕድል አገኘ። በዚህም ምክንያት ልዩ ልዩ የግጥም ዓይነቶች በብዛት ተገጥመዋል። ታሪኮች፣ ሐተታዎችና አፈ ታሪኮች ተጽፈዋል። የዓረብኛ መንዙማዎች መዲህ ነባዊ (ነብዩ ሙሐመድንና ቤተሰቦቻቸውን የሚያሞግሱ)፣ መቃም (ሰዎች በአንድ ላይ ሆነው የሚያቀርቡት)፣ ማዕሉፍ (በሰሜን አፍሪካ)፣ ድር (በግብፅ)፣ ሙወሸሽ (በሶሪያና በኢራቅ)፣ እና መቃም አል ኢራቂ ተብለው የሚታወቁ መንዙማዎች አሉ። በቱርክ ‹‹ነዓት››፣ በኅብረት የሚቀርብ የመውላዊ ዚክር፣ ሰምዓ በተባለው የአጦለሌ ውዝዋዜ የሚቀርብ ዓዩን የተባለ መንዙማና ሌሎች ስሞች ያሉዋቸው የመንዙማ ዓይነቶች ሲኖሯቸው፣ ዓረቦች የመንዙማ ወይም የዜማ መጽሐፍ (ኪታቡ አቃኒም) አላቸው። የሆነ ሆኖ መንዙማ አጥኝዎች በቃሲዳ (በዓረብኛ አጠቃላይ ሥነ ጽሑፍ ላይ) የበለጠ ትኩረት እንደሚያደርጉ መረጃዎች ያመለክታሉ።
የዓረብ የግጥም ቅርጾች በርካታ ቢሆኑም ዋና ዋናዎቹ መዲህ (አሞጋሽ፣ አሞካሽ፣ አግናኝ)፣ ሒጃ (አጥላይ፣ ተሳዳቢ፣ አሽሟጣጭ፣ ሸርዳጅ)፣ ቐዛል (የፈጣሪ፣ የነብይ፣ የሰው ፍቅር የሚገለጽበት)፣ ቂጣህ (በተራ አጋጣሚ የሚገጠም)፣ ማስናዊ (ድርብ ትርጉም ያለው)፣ ወስፍ (ገላጭ)፣ ሪጣ (እንጉርጉሮ፣ ወዮ እኔ፣ ዓይኔ)፣ ኺምሪያ (ወይን ወይም በወይን የሚመሰል አስካሪ፣ መንፈስን የሚለውጥ ምሳሌ የሚያሰክር ፍቅር)፣ ተርዲያህ (የአደን ግጥም)፣ ፈኽር (የፉከራ ግጥም)፣ ሙወሸሻ (ስለአገር ፍቅር)፣ ሐመስ (የጦርነት ግጥም) ናቸው።
በዓረብ ሥነ ጽሑፍ ውስጥ በደንብ ዳብሯል የሚባለው ስል መቐማህ የተባለው አሽሙር ነክ ዝርው ጽሑፍ ሲሆን፣ የዚህም ሥነ ጽሑፍ ሰው ሥራ ከ969 እስከ 1008 የነበረው አል ሐማድሐኒ የተባለ ደራሲ ነው። ምንም እንኳን መቃማህ አጻጻፍ ዘዴ በአል ሐማድሐኒ ይፈጠር እንጂ ሥልቱን አንድ ዕርምጃ ወደፊት እንዲገፋ አድርጎታል የሚባለው ግን ከ1054 እስከ 1122 የኖረው፣ ኢራቃዊው መሐመድ አልቃሲም ኢብ ዓሊ አልሐሪሪ ነው። ይኸው አንባቢውን በማዝናናት ሳይወሰን ምጥቀትና ጥልቀት ባላቸው ቃላት ይጠቀም የነበረው ጸሐፊ የቃላት ጎተራ እንደነበረ በሥራዎቹ አስመስክሯል። መልሀት አልሂራብ ፊአናዋህዋ በሚል ርዕስ የደረሰው የሰዋስው መጽሐፉ የዓረቡን ሥነ ጽሑፍ በማዳበር ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል።
በመንዙማ ዜማ ከሚነገሩ ግጥሞች ጥቂቶችን እናካፍላችሁ።
አንዳንድ ጊዜ ታሳያለህ ውብ መልክህን፣
ዳሩ ግን የተሸፈነ ነው፣ ፍፁም የሚታይ ሳይሆን።
ስለሆነም ሁለ መናህን እንድናይህ፣
በሚያቃጥል ስሜት ታነሳሳናለህ፣
እሳታችንንም እንዲጨምር አድርገህ።
የተገለጠውን ተፈቃሪ ስመለከት፣
ከእርሱ ጋር በፍቅር የወደቅሁለት።
እንዲህም ይሆንና በመንገድ ላይ ግራ የተጋባሁ ይመስለኛል፣
የተፈቃሪው ብርሃን በልቤ ውስጥ እሳት ያቀጣጥላል፣
እንደ ጨረር ሆኖ ተፈነጣጥቆ ይወጣል።
ለዚህም ነው ተቃጥየ ያገኘኸኝ፣
በውቅያኖስ ውስጥ ሰምጬ ያየኸኝ።
አዲስ ዘመን ግንቦት15/2012
ዋለልኝ አየለ