ለወትሮው ተማሪዎች ከቤት ከዋሉ አንድም የእረፍት ቀናቸው ነው፤ ካልሆነም የትምህርት ዓመት መንፈቅ አጋማሽ ወይም ከክፍል ክፍል መሸጋገሪያ የክረምት ጊዜ ላይ ናቸው። ዛሬ ግን እነዚህ የተለመዱ ሁነቶች በሌሉበት ተማሪዎች ከቤታቸው ውለዋል። ለምን ቢባል ጊዜው በቤት ሆኖ ቀንን ማሳለፍን የሚጠይቅ ክፉ ወረርሺኝ ኮቪድ 19 የነገሰበት ስለሆነ ነው። ኢትዮጵያም የዚህ ችግር ገፈት ቀማሽ ሆና በመገኘቷ ከእርምጃዎቿ ሁሉ ቀድማ ካከናወነቻቸው ክልከላዎች መካከል የነገ አገር ተረካቢ የሆኑ ተማሪዎች ከዚህ አደጋ እንዲጠበቁ በሚል ትምህርት ቤቶች ሁሉ ተዘግተው ተማሪዎች በቤታቸው እንዲቀመጡ ማድረግን ነበር።
ይህ ከሆነ በኋላ ግን ከወረርሺኙ የሚጠበቁበት እድል ቢፈጠርም፤ ከወረርሺኙ መወገድ ማግስት ወደ ትምህርት ገበታቸው መመለሳቸው አይቀርምና ተማሪዎች ያለ ትምህርት በቤት ውስጥ መቀመጣቸው ከትምህርት ዓለም ሊያርቃቸው እንደሚችል በማሰብ የተለያዩ አማራጮች ታስበው መተግበር ጀመሩ። በዚህም እንደ አገር ተማሪዎች በእጃቸው ካለ የትምህርት ቁሳቁስ ጀምሮ ሊደርሱበት በሚችሉት የመገናኛ አውታር ሁሉ ትምህርት ሊማሩ የሚችሉበት እድል ተመቻቸ። ክልሎችም ይሄን ተቀብለው እንደየአከባቢያቸው ነባራዊና ተጨባጭ ሁኔታ ስራቸውን ጀመሩ። እኛም ለዛሬው እትማችን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በዚህ ረገድ እያከናወነ ያለውን ተግባር የአስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አበበ ቸርነት ያደረሱንን መረጃ ዋቢ በማድረግ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
አጠቃላይ ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተገናኘ ተማሪዎች በቤት እንዲቆዩ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል። በተለያዩ መንገዶችም ትምህርት እንዲያገኙ እያደረገ ነው። አንደኛው ትምህርት በቤቴ በሚል በሬዲዮና ቴሌቪዥን ቻናሎች ማሰራጨት ሲሆን፤ የተለያዩ የቢሮውን ማህበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀምም ለተማሪዎቹ የማድረስ ተግባር እየተከናወነ ነው። በትምህርት በቤቴ የሬዲዮና ቴሌቪዥን ከሰባተኛ እስከ 12ኛ ክፍል ላሉ ተማሪዎች ባዮሎጂ፣ ኬሚስትሪና ፊዚክስን የመሳሰሉ ትምህርቶች በተመረጡ መምህራን እየተሰጡ ሲሆን፤ በቢሮ መረጃ መስጫ ቻናሎችም የተለያዩ ትምህርታዊ ጉዳዮችና ይዘቶች እየቀረቡላቸው ይገኛል።
በተለይ በቢሮው የመረጃ መስጫ ቻናሎች የተለያዩ ትምህርታዊ ይዘት ያላቸው መጽሀፍትና ተያያዥ ቁሳቁሶስ እየቀረቡባቸው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ተማሪዎች በእነዚህ ቻናሎች የሚቀርቡላቸውን አጋዥ የትምህርት ቁሳቁሶች በአግባቡ እየተጠቀሙባቸውና ትምህርታቸውንም እየተከታተሉ ይገኛል። ይህ ሲባልም ተማሪዎቹ በአግባቡ እየተከታተሉ ስለመሆኑ ማረጋገጥ የሚያስችሉ የተለያዩ መንገዶችን በመከተል የተረጋገጠ ሲሆን፤ በተለይ የቢሮው መረጃ መስጫ ቻናሎች የትምህርት ይዘቶችን ማድረሻ ብቻ ሳይሆኑ ተማሪዎች ትምህርቱን ስለመከታተል አለመከታተላቸው የመፈተሻ መንገዶችም ሆነው እያገለገሉ ይገኛል።
ምክንያቱም እነዚህን ቻናሎች ከተማሪ ግብረ መልስ መቀበያ ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ። ለምሳሌ የቢሮው ቴሌግራም አድርሻ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ተማሪዎች የሚከታተሉትም የሚሳተፉበትም ነው። ይህ ተሳትፎና ግብረ መልስም በሬዲዮም፣ በቴሌቪዥንም ሆነ በማህበራዊ ቻናሎቹ የሚተላ ለፉ ትምህርቶች ላይ ያላቸውን ምልከታም የሚያስቀምጡበትና ለቢሮው የሚያደርሱበት ነው። ከዚህ በሻገር የተማሪዎቹን ትምህርት መከታተል አለመከታተል ለማረጋገጥም ሆነ ተሳትፏቸውን ለማሳደግ በቴሌቪዥንም ሆነ በሌሎች ቻናሎች በሚሰራጩ ትምህርቶች የተሳትፎ ጥያቄዎች ይቀርባሉ።
እነዚህ ጥያቄዎች ደግሞ በማህበራዊ ሚዲያ ቻናሎች አማካኝነት የሚመለሱ ሲሆን፤ በዚህ መልኩ የሚደረግ ጥያቄ የመመለስ ተሳትፎ አኳያም በተመሳሳይ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ተማሪዎች ይሳተፋሉ። በአጭር የጽሑፍ መልእክትም በተመሳሳይ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ተማሪዎች ጥያቄዎችን ይመልሳሉ። በመሆኑም እነዚህ የተማሪዎች ተሳትፎዎችና ግብረ መልሶች ትምህርት በቤት የሚለውን መርሃ ግብር ተማሪዎች እየተከታተሉት ስለመሆኑ ማሳያዎች ሲሆኑ፤ የሚቀርቡ ጥያቄዎችም ተማሪዎች ምን ያህል ተከታትለዋል ብቻ ሳይሆን ምን ያክል ተገንዝበዋል የሚለውንም አመላካቾች ናቸው። ይሄንኑ የተማሪዎች ተሳትፎ ለማጎትበትና ለማበረታታት ሲባልም በቅርቡ በጥያቄዎቹ ከፍተኛ ውጤት ያመጡ ወይም በርካታ ጥያቄ የመለሱ ተማሪዎች የሚሸለሙበት መርሃ ግብር ይኖራል።
ይህ የትምህርት በቤቴ በሚል የሚከናወነው መርሃ ግብር ደግሞ ለግልም ሆነ ለመንግስት ተማሪዎች የሚተላለፍ እንጂ ለመንግስት ትምህርት ቤት ተማሪዎች ብቻ ለይቶ እንዲደርስ የሚደረግ አይደለም። የግል የመንግስት የሚባል ትምህርት ባለመኖሩም ሁሉም በዚሁ አግባብ እንዲደርሳቸው እና እንዲከታተሉ ነው እየተደረገ ያለው። በሚቀርቡ ጥያቄዎችም መልስ በመስጠት የሚሳተፉትም ሆኑ ግብረ መልስና አስተያየት የሚሰጡ ተማሪዎችም የግልም የመንግስትም ተማሪዎች ናቸው። ሆኖም ቢሮው ከሚሰጠው በተጨማሪ የግል ትምህርት ቤቶችም የራሳቸውን ቴሌግራም ቻናል ፈጥረው ተማሪዎች ቤታቸው ቁጭ ብለው እንዲከታተሉ የማድረግ ተግባር እያከናወኑ ናቸው።
ከግል ትምህርት ቤቶች ክፍያ ጋር በተያያዘ የሚነሱ ጉዳዮችን በተመለከተም ከኮቪድ 19 ጋር በተያያዘ የትምህርት ሚኒስቴር ያወጣው መመሪያ አለ። እንደ ከተማ አስተዳደርም ይሄው መመሪያ እንዲተገበር ነው ቢሮው እየሰራ ያለው። ይሄን በአግባቡ የማይተገብሩ ተቋማት ወይም ትምህርት ቤቶች ላይ ለህዝብ ሲገለጽ እንደነበረውም እርምጃ እየተወሰደ ሲሆን፤ በዚህም ችግራቸውን አርመው ያስተካከሉም አሉ። በመሆኑም ከክፍያ ጋር ተያይዞ ያለው ችግር በዚህ አግባብ እየታረመና ባልተስተካከሉት ላይም እርምጃ እየተወሰደ ነው ያለው።
በሌላ በኩል ይህ ወቅት እንደ ተማሪዎች ሁሉ መምህራንም በአብዛኛው በቤታቸው ያሉ ሲሆን፤ የተመረጡ አስተማሪዎች በተለያየ መልኩ የሚቀርቡ ይዘቶችን ይዘው እያስተማሩ ይገኛል። ገሚሱም በትምህርት ቤት እየተገኙም ሆነ በቤታቸው ሆነው በየማህበራዊ ሚዲያው ለሚሰራጩ ትምህርቶች ይዘቶችን ያዘጋጃሉ፤ በኦንላይንም ትምህርቱን እንዲሰራጭ እያደረጉም ናቸው። ይህ ደግሞ መምህራን የትም ቦታ ሆነው ስራ ላይ መኖራቸውን የሚያሳይ ሲሆን፤ በቤታቸው ባሉበት ወቅትም ለቀጣይ ዝግጅት እያደረጉ ይገኛል። በመሆኑም መምህራን አንድም በተለያየ መልኩ ለተማሪዎች ትምህርት እንዲደርስ በማድረግ ተማሪዎችን እያገዙ ሲሆን፤ በሌላ በኩል በቤታቸው ሆነው ለቀጣይ ዝግጅት በማድረግ ላይ ናቸው።
እንደ አጠቃላይ ሲታይ በዚህ መልኩ ከመምህራንና የዘርፉ ባለሙያዎች ጋር በመቀናጀት ቢሮው ወቅቱን የዋጁ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል። በመሆኑም ተማሪዎች ወላጆችና ሌሎች የተማሪ የቅርብ ቤተሰቦች በቢሮው ተዘጋጅተው የሚቀርቡ ትምህርቶች በአግባቡ ተማሪዎች ጋር እንዲደርሱ የድርሻቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል። በዚህም ተማሪዎች የሚቀርበውን ትምህርት እየተ ከታተሉ ስለመሆናቸው ወላጆች እርግጠኛ መሆን ይኖርባቸዋል። ተማሪዎችም የሚቀርበውን ትምህርት መከታተል፣ ማንበብና መዘጋጀት አለባ ቸው። መምህራንም አሁንም ተማሪዎችን በተለያየ አግባብ እያገኙና እየረዱ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ይሄንኑ አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል፤ ለቀጣይ ስራቸውም ዝግጅት ማድረግ ይኖርባቸዋል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 14/2012
ወንድወሰን ሽመልስ