ህይወት ቁጥር ስፍር በሌላቸው ፈተናዎችና ከባድ ጥያቄዎች የተሞላች ትምህርት ቤት መሆኗን ማንም ይረዳዋል። ህይወት በፈተና የተሞላች ነች። ፈተናውን የሚያልፍ ይኖርባታል። የህይወትን ፈተና ለማለፍ ፅናትን፣ ብርታትንና ትዕግስትን ይጠይቃል።
የአካል ጉዳት ባለባቸው ሰዎች ደግሞ የህይወት ፈተና ይበረታል። ይሁን እንጂ በዚያም ሆነ በዚህ ብሎ ብርታቱን ላሳየ አሸናፊ መሆኑ የማይቀር ነው። ለዚህም ብዙዎች የአካል ጉዳት እያለባቸው ከህይወት ጋር ታግለው ያሸነፉ ሰዎች ምስክሮች ናቸው። የአካል ጉድለት ያለባቸው ጉድለታቸውን ለመሸፈንና ራሱን ለማሸነፍ ተግቶ ከተነሳ ያሰበው ላይ እንደሚደርስ በብርታታቸው ያሳያሉና። ከእነዚህ መካከል ደግሞ የዛሬው የህይወት እንዲህ ናት እንግዳችን አቶ ሲሳይ መላኩ አንዱ ናቸው።
የእርሳቸው የአካል ጉዳተኝነት ጠንካራነትን፤ የሥራ ወዳድነትን ማስተማሪያ ነው። ምክንያቱም በአንድ እጃቸው እየሠሩ ዓለምን እንዳስደመሙ ለመሆን ይጥራሉ። በእርሳቸው ብዙዎች እንዲማሩ ሳይቦዝኑ ይሠራሉ። በተፈጥሮ የተሰጣቸውን አምነው በመቀበል የህይወት ውጣውረዱን ለማሸነፍ ይተጋሉ። ብዙዎች በተለይ በአገሪቱ ሙሉ አካል ኖሯቸው መንገድ ዳር ተቀምጠው ይለምናሉ፤ አካል ጉዳታቸውን ሰበብ አድርገውም ላለመሥራት የሚጥሩ አሉ፤ ከዚያ አልፈውም የማጭበርበሪያ መሳሪያዎችን አካላቸው ላይ እየተጠቀሙ የአካል ጉዳተኛን የሚያስደምሙ አይጠፉም።
አቶ ሲሳይ ግን ከዚህ ሁሉ የተለዩ ናቸው። በአካለ ጉዳት ሰበብ የማይሠራን አይወዱም፤ በተለይም ተቀምጦ የሰው አጅ የሚጠብቀውን ወጣት አጥብቀው ይጠሉታል፤ «አካል ጉዳተኝነት ከመሥራት አያግድም። የሚያሳፍረው የሰው ፊት ማየትና መስረቅ ነው» የሚል እምነት አላቸው። አይዞህ ባይ ባይኖራቸውም መቃብር እየቆፈሩ ቤታቸውን የሚያስተዳድሩ ጥሩ አባወራ ለመሆናቸው ምክንያቱ ሥራ ወዳድነታቸው እንደሆነ ይናገራሉ። ቤተሰባቸውን ለማስተዳደርና ራሳቸውን ለማኖር መቃብር ይቆፍራሉ፣ ሀውልት ይሠራሉ፣ የቤተክርስቲያኑን መጸዳጃ ቤት ያጸዳሉ፤ የመቃብር ስፍራውንም እንዲሁ ሲያስተካክሉና ሲያጸዱ ይውላሉ። ከዚያም አለፍ ሲል የግለሰቦችን የሕንፃ ጉድጓዶችንና ውኃልኮችን ይሠራሉ። ይህ ደግሞ አንድ እጅ መሆናቸው ከሥራ እንዳልገደባቸው ማሳያ ነው። እናም ከዚህ ጥንካሬያቸው ትምህርትን ትቀስሙ ዘንድ የህይወት እንዲህ ናት እንግዳችን አደረግናቸው።
ልጅነት
ተፈጥሮ ገና ሲወለዱ ነው ግራ እጃቸውን የነጠቀቻቸው። በዚህም በማህበረሰቡ ዘንድ ከንፈር እየተመ ጠጠላቸው፣ ቤተሰብም ሁል ጊዜ «የት ይደርስ ይሆን?፣ ምን ሠርቶ ይበላ ይሆን?፣ ማንስ ይቀጥረዋል?» እያለ ሲጨነቅላቸው፣ አንዳንዶችም አይዞህ በርታ እያላቸው ነው ያደጉት። ግን እርሳቸው በሁሉም አይከፉም ነበር። ምክንያቱም «ሥራ በራሱ ጊዜ ማንነትንና አካል ጉዳተኝነትን ይቀይራል»ያምናሉ። ለሥራቸው ስንቅ የሆናቸውን የአሠራር ጥበብንም ከልጅነታቸው ጀምሮ ተለማምደዋል።
«አንድ እጅ እያለኝ ምንም አልሆንም፤ ሠርቼ ራሴን መመገብ አያቅተኝም» የሚል ወኔን አንግበው ዛሬ ድረስ እየሠሩና በሥራቸው እየተደሰቱ የኖሩትም በልጅነት ዕድሜያቸው ባካበቱት የመሥራት ልምድ እንደነበር ይናገራሉ። ልጅ እያሉ በተለይ ቤተሰቦቻቸውን ከእርሳቸው አቅም በላይ በሆኑ ሥራዎች ሁሉ ያግዟቸው እንደነበርም ያስታውሳሉ። በእርግጥ ቤተሰቡ የአካል ጉዳተኛ ከመሆናቸው አንጻር ሥራዎችን እንዳይሠሩ ይገድቧቸው ነበር። እርሳቸው ግን አሻፈረኝ እያሉ «ከእናንተ ስለይ ምን እሆናለሁ?» በማለት አሳምነው በግዳጅም ቢሆን እንዲሠሩ እንዲፈቅዱላቸው ያደርጉ እንደነበር አጫውተውኛል። ይህ ደግሞ ለዛሬ ጥንካሪያቸው መሰረት እንደሆናቸው ይናገራሉ።
አቶ ሲሳይ ተወልደው ያደጉት ሰሜን ወሎ ዋድላ ደላንታ ኮን ነው፤ ከመጨረሻው ልጅ አንድ ቀደም ብለው በ1964ዓ.ም ነው የተወለዱት። ይሁንና የመጨረሻው ልጅ በህይወት ባለመቆየቱ የተነሳ እንደ መጨረሻ ልጅ ተደርገው በእንክብካቤ ነው ያደጉት። ቤተሰቦቻቸው በግብርና የሚተዳደሩ በመሆናቸው ደግሞ የግብርና ሥራ ላይ ጠንካራ ሠራተኛ እንደነበሩ ይናገራሉ።
ስለ ከተማ ኑሮ በየጊዜው ከአዲስ አበባ የሚመጡ ዘመዶቻቸው አጋነው መንገራቸው ሌላ አቅጣጫን እንዲከተሉ አድርጓቸዋል። በዚህ ዕድሜ ላይ ነጭ ወረቀት ላይ የተቀመጠ ፊደል ይመስል ንግግሮች ይያዛሉና ለልጆች ከመንገር ብዙዎች መቆጠብ አለባቸው ይላሉ። ምክንያታቸውም የእርሳቸው ዘመዶች ለዛሬ ውጥንቅጥ ህይወት የእነርሱ እጅ አለበትና ነው። ንግግራቸው አዲስ አበባን ገነት አድርጓታል፤ «በአዲስ አበባ ከተማ መልበስ፣ መዘነጥና ማማር ብቻ ነው ያለው። መራብ፣ መራቆትና መፈተን በፍጹም የማይታሰቡ ናቸው» የሚል አስተሳሰብ አዳብረዋል። እናም ይህንን የያዘው የሕፃንነት አዕምሮ ሁልጊዜ በአዲስ አበባ መኖርን ያስባል። ግን ቤተሰብ በወቅቱ ትልቅ ትምህርት ቤት ነው ብሎ ወዳሰበው የቄስ ትምህርት ቤት አስገብቷቸው ነበርና ሃሳቡን ባይተውትም የተሰጣቸውን ዕድል መጠቀም ጀመሩ። በቤተ ክህነት ትምህርት ራሳቸውን ማሳደግ ላይ አተኩረው እስከ ድቁና ተምረዋል።
አካል ጉዳተኛ በመሆናቸው ከሌሎች ልጆቻቸው በተለየ መልኩ ቤተሰቦቻቸው እንክብካቤ ያደርጉላቸው ነበር። ልጅነታቸውን በሚገባ ከቤተሰቦቻቸው አጋር አጣጣሙት። የአካባቢው ሰውም እንዲሁ በጣም ያዝንላቸውና ይወዳቸው ስለነበር ከጓደኞቻቸው ጋር የፈለጋቸውን ያደርጉ እንደነበር ይናገራሉ። ይሁንና ያ የተዘራ የከተሜነት መንፈስ ከህሊናቸው ሊወጣ አልቻለምና ከቤተሰብ ኮብልለው አዲስ አበባ ገቡ።
ኑሮ በሸገር
አዲስ አበባን ዘመዶቻቸው እንደነገሯቸው አላገኟትም። ይልቁንም ስቃያቸውን አበዛችባቸው። የማያውቁት ምድር ላይ እንዳረፉ እንዲሰማቸውም አደረገቻቸው። ይህ የሆነው በ1990ዓ.ም ነበር። ሲመጡ ማንንም አላማከሩም፤ ለማንም አልተናገሩም። በዚህም ማን ጋር ፣ የት መሄድ እንዳለባቸው እንኳን አያውቁም። ስለዚህም አይዞህ ባይ ባጡባት ከተማ መንከራተቱን ተያያዙት። በመጨረሻ ግን «ሳይደግስ አይጣላም» እንዲሉ የጥበቃ ሥራ ፈረንሳይ ለጋዮን አካባቢ በሚገኘው በገነተኢየሱስ ቤተክርስቲያን አገኙ።
ለዓመታት ባገለገሉበት ቤተክርስቲያኑና በእርሳቸው መካከል አለመስማማት በመፈጠሩ አቶ ሲሳይ ከጥበቃ ሥራቸው እንዲለቁ ተደረገ። ይህ ደግሞ ባለታሪኩን ለሌላ እንግልትና የህይወት ፈተና ውስጥ ዳረጋቸው። ይሁን እንጅ ለፈተና እጅ መስጠት አለመዱምና መንገድ ዳር ወድቀው መለመንን አልመረጡም። ይልቁንም ቦሌ አካባቢ ሌላ ሥራ እንዲጀምሩ ዕድል ፈጠረላቸው።
ለመቀጠር እጃቸው ነበር መሰናክል የሚሆናቸው። ነገር ግን እርሳቸው ሳትከፍሉ እዩኝና ሥራዬ ከተመቻችሁ ክፍያ ትፈጽሙልኛላችሁ ብለው አሳመኗቸው። አሠሪዎቹም በእሽታ ተቀበሏቸውና ሥራ ሰጧቸው። በዚህም በአንድ እጃቸው ይሠሩበታል፤ ይደግፉበታል፤ ጉዳተኛ ነኝ ብሎ እንዳያስብ ያንቀሳቅሱታል። አለፍ ብለውም ጥበባቸውን ያሳዩበታል። በዚህ የተደመሙ የሥራ አጋሮቻቸውም ያበረቷቸው ጀመር። አሠሪዎቹም ሥራ እስኪያገኙ በቀን እየከፈሏቸው ያሠሯቸው ነበር። የተጎዳው የአካል ክፍላቸው ግራ እጃቸው በመሆኑ በቀኝ እጃቸው ደግፈው ጉልበት እንዲያገኝ ያደርጉታል። በዚህም ጥበባቸው ሙሉ አካል ካለው እኩል ይናገርላቸዋል።
«እግዜር አንዱን ነገር ሲያጎል ጥንካሬን እንደሚሰጥ ማመን ይገባል» የሚሉት አቶ ሲሳይ፤ በአዲስ አበባ ቆይታቸው ስቃያቸው እንዳይበረታ ያደረጋቸው ከልጅነታቸው ጀምሮ ቤተሰቦቻቸው ጠንካራ እንደሆኑ እየነገሩ ስላሳደጓቸው ነበር። በዚያ ላይ አካል ጉዳተኛ ቢሆኑም የአካል ጉዳታቸው ሳይሰማቸው የሠሩት ጥንካሬን ባላበሳቸው ቤተሰባቸው አማካኝነት ነው። «ቤቴ ሙሉ ባይሆንም እጄን በማጣቴ የመጣብኝ ነገር የለም። ጤነኛ ነኝ፤ እስከአሁን በምንም ህመም አልተሰቃየሁም። በዚህም አምላኬን አላማርርም። ስለዚህም የአዲስ አበባን ችግር በሥራ እየተቋቋምኩት እገኛለሁ» ይላሉ።
በአንድ እጅ መቃብር ቁፈራ
ብዙዎች የመቃብር ቁፋሮውን ሲጀምሩ «እንዴት ለቀብር ያደርሰዋል። በዚያ ላይ ምን ያህል ይችላል ብላችሁ አስቀመጣችሁት?» ይሏቸው ነበር። ግን ቆየት ብለው ሲመለከቱ ሃሳባቸውን ይቀይራሉ። በእርግጥ እኔም ብሆን ይህ ነገር ተአምር ነበር የመሰለኝ። ልጎበኛቸው ወደ ጫካው በገባንበት ወቅት አካባቢው በጣም ያስፈራ ነበር። ለመረማመድ እንኳን ይቸግራል። መቃብሮቹ ባሉበት ዙሪያ ሀረጉ እየጠለፈ ይጥላል። በይበልጥ ደግሞ እሾሁ ብዙ ነው። እጅና እግሬ ሳይቀር እየተጫጫረና ሳማ እየለበለበኝ ነበር ሥራቸውን ላለማስፈታት ወደፈለጉበት ቦታ ተከትያቸው የተጓዝኩት።
በወቅቱ ከእርሳቸው ጋር ቃለ መጠየቅ ለማድረግ ተሳነኝ። የተጫጫረውንና በሳማ የተለበለበውን እግርና እጄን መደባበስ ጀመርኩ። ለእርሳቸው ግን ይህ የዘወትር ተግባር መሆኑን ሳስብ ህመሜ ሁሉ ብንብሎ ጠፋ። እንግዲህ ልብ በሉ በዚህ ሁሉ ውስጥ እያለፉ ነው የዘወትር ተግባራቸውን የሚያከናውኑት። አካባቢውን እያጸዱ እንደነበረና አሁን ደግሞ የመቃብር ቁፋሮ እንደሚጀምሩ ከገለጹልኝ በኋላ እያወራን መሥራት እንደሚችሉም ነገሩኝ። ለቁፋሮው የሚያገለግላቸውን መሳሪያም በአንድ እጃቸው በማንሳት ተሸክመው ሌላ መንገድ ጀመርን። ቦታው ላይ ስንደርስም የቀብር ጉድጓዱን ለመጀመር ራሳቸውን አዘጋጁ።
ዶማውን ሲያነሱ አላመንኩም ነበር። በጣም ፈጣን ቆፋሪ ናቸው። ግራ እጃቸው ስለነበር የተጎዳው ደገፍ እያደረጉ በቀኛቸው አፈሩን እያወጡ ነው የሚቆፍሩት። «ይህ ጉድጓድ ለስድስት ሰዓት የሚደርስ ነው» አሉኝ ቀና ብለው ዝምታችንን ለመገርሰስ ያህል። ገና መጀመራቸው ነበርና እንዴት አድርጎ ይደርሳል? አልኩ በውስጤ። አላስችል አለኝናም «ታዲያ በስንት ሰዓት ይጨርሱታል? አልኳቸው ሰዓቴን ተመልክቼ» እርሳቸው ግን ኮራ ብለው «ከዚህ ሳትሄጂ እጨርሰዋለሁ። ምክንያቱም ልምዴ ነው። ሥራ ቶሎ ሲያልቅ ያስደስተኛል። ገና ነው የሚል ነገር አይመቸኝም። በመሆኑም በደቂቃዎች ውስጥ እጨርሳለሁ» አሉኝ። አላመንኳቸውም ወጋችን ግን ቀጥሏል።
በደቂቃዎች ውስጥ ጉድጓዱን ቆፍረዋል። አሁን ወደ ማመኑ ተቃረብኩ። «ሁሌም ብቻዎትን ነው የሚቆፍሩት?» በማለት ጠየቅኳቸው። ጓደኛቸውን አመላከቱኝ። እርሱም እንደእርሳቸው በሌላ ሥራ ተጠምዶ ነበር። ግን እርሱ ሙሉ አካል ስላለው ቢፈጥንም አያስገርምም። እርሳቸው ግን በጣም ያስገርማል። ምነው ሁሉም እንደርሳቸው ቢሆንም ያሰኛል። ለነገሩ «ላያስችል አይሰጥ» አይደል የሚባለው። የእርሳቸውም ጥንካሬና መቻል ካለባቸው ጫና አንጻር የመጣ ይሆናል።
አሁንም ሥራ ላይ ናቸው። የመቃብሩ ቁፋሮ ቢያልቅም ክዳኑን አምጥቶ ማስቀመጥ ይጠበቅባቸዋል። ስለዚህም ክዳኑን ለማምጣት እያወራን ተጓዝን። በቦታው ስንደርስም ብዙ ተጠርበው የቤተክርስቲያኑን ቅጥር ግንብ ተደግፈው የተቀመጡ ድንጋዮች ተመለከትሁ። እያንዳንዳቸው የየራሳቸው ክብደትም ሆነ ርዝማኔ አላቸው። ያው እንደሞተው ሰው ስፋትና ቁመት ይለያያሉ። እናም ክብደቱ በግምት ከ60 ኪሎ በላይ የሚሆን ድንጋይ መርጠው በአንድ እጃቸው ደግፈው አነሱና በትከሻቸው ላይ ተሸከሙት።
በወቅቱ እንዳላሸክማቸው ከእኔ ክብደት በላይ ነው፤ ግራ ተጋብቼ ቆሜ በአድናቆት ተመለከትኳቸው። ትንሽ ከተጓዙም በኋላ «ምነው ነይ እንጂ» ሲሉኝ ከነበርኩበት ሰመመን ነቃሁና ተከተልኳቸው። ክብደቱ ምንም አልመሰላቸውም። የመጣንበትን ዳገት በፍጥነት እየተራመዱ ይወጡታል። በዚያ ላይ ጢሻው አላስቸገራቸውም። እኔም ልብሴን እየያዘ ወደኋላ ቢጎትተኝም በግድ እያስለቀቅሁ ተከተልኳቸውና የነበርንበት ቦታ ላይ ደረስን።
የተሸከሙትን ድንጋይ እንደልማዳቸው በፍጥነት ከአወጡት አፈር ራቅ አድርገው አስቀመጡና የሚመጣውን አስከሬን ይጠባበቁ ጀመር። አሁን አረፍ አልን። ጥያቄዎቼን ማንሳቴን ቀጠልኩ። እርሳቸውም ምላሹን አከታተሉልኝ። አቶ ሲሳይ ቅጥራቸው በቋሚነት የሚሠራበት አይደለም። በቀን ሠራተኛ መልክ ነው እንዲሠሩ የተቀጠሩት። በቀን 100 ብር ይከፈላቸዋል። የሚያወጡት ጉልበት ግን ከዚያ በላይ እንደሚያስከፍላቸው የሚቆፍሩትና የሚሸከሙትን ድንጋይ ያየ ይፈርደዋል። ሳይበሉ የሚሠሩበት ቀን ብዙ ነው። ከሰንበት ውጪ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ ምንም ምግብ በአፋቸው ሳይገባ ይውላሉ። ሥራ ከሌለና ጾም ካልሆነ ብቻ ነው ትንሽ ምግብ የሚቀምሱት።
በባዶ ሆዳቸው ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ጉድጓድ ሲቆፍሩ ይውላሉ። በተለይ ሁለትና ሦስት ሰው ከሞተ የሚኖርባቸው ድካም ቀላል እንዳልሆነ ይናገራሉ። ግን እንጀራቸው አይደለ ምን ማድረግ ይችላሉ? ባይሠሩ ቤተሰባቸው ጦሙን ያድራል፤ መጠለያ አይኖራቸውም። የአምስት ሰው መቀበሪያ ጉድጓድ ቆፈሩም የአንድ ሰው ቆፈሩ የሚከፈላቸው ያው በቀን 100ብር ብቻ ነው። ብዙ ጉልበት ያፈሳሉ ግን የሚመጣው መቶ ብር ብቻ ስለሆነ ለቤት ኪራይና ለቤተሰባቸው ነው።
በአንድ እጃቸው ለክዳን የሚያነሱት ድንጋይ በሁለት እጅ ለማንሳት ያስፈራል። ያንን በትከሻ ላይ አኑሮ በጢሻ ውስጥ እየተደናቀፉ መሄድ ደግሞ ከዚያ ይብሳል። ሁሌ ለተመለከታቸው ቢወድቅስ እያለ በስጋት ያልቃል። ምክንያቱም ድንጋዩ በጣም ከመተለቁ የተነሳ ከወደቀ በደቂቃ ውስጥ ጸጥ ሊያደርግ ይችላል።
መቃብር ለመቆፈርና የዕለት ሥራቸውን ለማከናወን ከቤታቸው 11 ሰዓት የሚነሱት አቶ ሲሳይ፤ በየጊዜው የመቃብሩን ድንጋይ ከሚያስቆፍሩት አካላት የሚሰነዘርባቸው ንግግር ያሳምማቸዋል። ደግነቱ በቀጠሯቸው የቤተክርስቲያኑ አገልጋዮች ዘንድ ሥራቸው ስለሚታወቅ መፍትሔ ያገኛል እንጂ። በዚያው ልክ ግን ብዙዎች የእጃቸውን ጥበብ ከተመለከቱ በኋላ በእጅጉ ይጸጸታሉ፤ አድናቆታቸውንም ይቸሯቸዋል። በጣም የተደሰተ ካለም በርታ በማለት «ቲፕ» ይሰጣቸዋል። እናም እንዲህ እንዲህ እያሉ ነው የመቃብር ቆፋሪነታቸውን ህይወት የሚኖሩት።
ቤተሰብ
ትውውቃቸው በትውልድ ቀያቸው የጀመረ ነው። አብረው ጭቃ አቡክተውና አፈር ፈጭተው ነው ያደጉት። ግን እርሷ ውብ በመሆኗ የተሻለ አማራጭ የነበራትና ሌላ እንደምታገባ ያምናሉ። ለእርሳቸው ብትሆን ግን ፍላጎታቸው ነው። ስለዚህም በተደጋጋሚ የእርሳቸው ትሆን ዘንድ ጥያቄ አቅርበውላታል። የእርሷም ፍላጎት ከእርሳቸው ጋር መኖር ነበርና በጊዜው ተግደርድራ መጨረሻ በእሽታ አሰረችው። ወደአዲስ አበባ መጥተው በአንድ ክፍል ቤት ተከራይተው ኑሯቸውን መምራት ጀመሩ።
እርሷ ሰው ቤት እንጀራ እየጋገረች፣ ልብስ እያጠበች ቤቱን ስትደጉም እርሳቸው ደግሞ በጥበቃ በሚያገኟት ገንዘብ ጎጇቸውን አቆሙ። እንዲህ እንዲህ እያሉም የመጀመሪያ ልጃቸውን ወለዱ። ግን አምላክ ሳይፈቅድ ቀረና ሞት ነጠቃቸው። አሁን አንዲት ሴት ልጅ ሰጥቷቸው ቤታቸው ሞቋል። አንድ ክፍልም ብትሆን በወር ስድስት መቶ ብር እየከፈሉ በደስታ ይኖሩባታል። ይህ የሆነውም በሰዎቹ አዛኝነትና ችግራቸውን ስለተረዷቸው እንደሆነ ይናገራሉ።
መልዕክት
አካል ጉዳተኛም ሆነ ሙሉ አካል ያለው ሰው በህይወቱ መከበር ካለበት በሥራውና በሥራው ብቻ መሆን እንዳለበት የሚናገሩት አቶ ሲሳይ፤ በተለይም በልመና ሥራ ላይ የሚሰማራው ሰው ከዚህ ስህተቱ መንቃት ያለበት እኛን በማየት ነው ይላሉ። ምክንያቱም ሥራ ጥንካሬን፣ ጤንነትን፣ ብርታትን ያላብሳል። በተለይ ደግሞ ከሰዎች ዕርዳታ ነፃ መሆንን የሚነግረው ሥራ እንደሆነ ያስረዳሉ። ልመና ሁል ጊዜ የሰው ፊት የሚገርፍበት፣ የሚያሸማቅቅበትና ህሊና ንጹህ እንዳይሆን የሚያደርግ ነው። ለወጣቱ ደግሞ ይህ ነገር በጣም አሳፋሪ ነው። ምክንያቱም በዚህ ሳቢያ ሳያረጅ ያስረጃል። ሰዎች ላይ ጥገኛ መሆንን ያላምደዋል። በመሆኑም በሥራ መለወጥን የምንጊዜም ተግባር ማድረግ ይገባል። ዛሬ ብዙ ዕድል አለ። ሥራ ፈጠራ በተለይ ለወጣቱ ምንም አይሳነውም። ስለዚህም ከኪስ ማውለቅ ወደ አዕምሮ መጠቀም መዛወር ላይ ቢያተኩሩ ይበጃቸዋል በማለት ይመክራሉ።
መንግሥት ይህንን አደረገብን፣ ይህንን ካላደረገልን መሥራት አንችልም የሚለውም መቆም አለበት። እያንዳንዱ ወጣት መንግሥቱ መሆን ያለበት ሥራው ነው። በዕድሜ እየገፋሁ ብሄድም ዛሬም ጠንካራ ነኝ፤ አንድ እጅ ብሆንም ዛሬም አስከሬን አንስቼ መቃብር ውስጥ እከታለሁ። የሞተውን ሰው ቁመት ለክቼም ለሁሉም እንደሚቀበርበት ርቀት ጉድጓዶችን ቆፍሬ አዘጋጃለሁ። ሀውልት በሚፈለገው ዲዛይን ዓይነት እያወጣሁ መሥራት እችላለሁ። ይህ የሆነው ደግሞ በሥራ ወዳድነቴና ደከመኝ ሳልል በመሥራቴ ነውና ሰዎች ከእኔ ይህንን ይማሩ መልዕክታቸው ነው።
«መቼም ቢሆን ቁጭ ብዬ ልብላ፣ ሰው እጁን ይዘርጋልኝ ማለት አልፈልግም። ምክንያቱም የሰው እጅ ያማል፣ የሰው ላብም ይከረፋል። ስለዚህም የአካል ጉዳቴን ዓይተው ለእኔ የሚመች ሥራ ቢሰጡኝ ጥበቤን በእጅጉ ተጠቅሜ ላሳያቸውና ላስደስታቸው እችላለሁ» ይላሉ የዕርዳታ ጥሪያቸውን ሲያቀርቡ። አንድ እጅ ብሆንም ሙሉ አካል ካለው እኩል እሠራለሁ። ለጉልበቴም አልሰስትም። ብቻዬን በቀን ከዘጠኝ የመቃብር ጉድጓድ በላይ ቆፍሬ አውቃለሁ። ይህ ደግሞ መሥራት እንደምችል አሳይቶኛል። እናም በሀውልት ሥራና በመቃብር ጉድጓድ ቁፈራ ብቻ ህይወቴን ከማሳልፍ ጉልበቴም ከሚደክም የአንድ እጅ ጥበቤ የላቀ ነውና ቢያሠሩኝና ብጠቀም እነርሱም ሥራቸው ቢጠራላቸው እመኛለሁ።
ማንኛውንም ሥራ አልንቅም። ግን ገና አይተውኝ እንዴት ሊሠራ ነው? ስለሚሉ እኔን ለማሠራት ፈቃደኛ የሚሆን አካል እስከአሁን አልመጣልኝም። መቀመጥ ካለ ስንፍና ይመጣል። በዚያው ልክም የጉልበት መድከም ይበረታልና እለፋለሁ። ውጤቱ ግን ከእጅ ወደአፍ ነው። የቤት ኪራይ እንኳን አይሸፍንም። የዘጠኝ ወር ልጄንና ባለቤቴንም ለማስተዳደር እየተቸገርኩበት ነው። ስለዚህም እኔም በአንድ እጄ እናንተም በገንዘባችሁ እንጠቃቀም ይላሉ።
አዲስ አበባ ሲኖር ቤት መሰረት ነው። ቆሎ በልቶ ማደር ይቻላል፤ ጎዳና ግን በጣም ያማል። ስለዚህም የቤት ኪራይ መክፈል እንድችል አግዙኝ ይላሉ። እኛም ማገዝ የሚፈልጉና እርሳቸውን ለማሠራት ፈቃደኛ የሆኑ ድርጅቶች ካሉ 011264326ስልክ ቁጥር በመደወል የምናገናኝዎ መሆኑን በመጠቆም የእንግዳችንን ታሪክ በዚህ እንቋጭ። ሰላም!
አዲስ ዘመን ጥር 5/2011
ጽጌረዳ ጫንያለው