አየህ አንዳንዴ ቁስል ሲደርቅ፤ ጠባሳም አብሮ ይጠፋል። ያኔ ነው የመዘንጋት አባዜ የሚሳፈር። መዘንጋት ደግሞ ‹‹pure›› በሽታ ነው። ህመምህ ሳይድን ሰንበርህ እንኳን ቢጠፋ፤ ማን እንደለጠለጠህ ካላወክ የገራፊህ ወዳጅ ሆነህ፤ ለክፍል ሁለቱ አርጩሜ ጀርባህን እያደነደንክ ትጠብቃለህ።
እመነኝ ወዳጄ የወጋ ቢረሳ የተወጋ አይረሳም ቢሆንም ቅሉ፤ አባባሉ! ትዝታ ላይ ድር ሲያደራ ያኔ… አንዳንዴ! አንዳንድ ጊዜ ብቻ…የተወጋም ይረሳል። አዳም በስንብት ቀለማት እንዲህ ይላል… ለእያንዳንዱ ሰው የት እንዳለ የሚያሳየው፤ ካርታ እየተሰራ ካልተሰጠው፤ አፉን ሚጥሚጣ ባሞቀው ቁጥር አዋቂ ሊሆንብን ነው…እናማ ወዳጄ የቆምክበትን ካርታ ጎንበስ ብለህ አስተውል። ምናልባት የመዘንጋት አባዜ ተጠናውቶህስ ቢሆን? ግን እኮ መዘንጋት ባይሆንም ሱስም ሊሆን ይችላል። የመቀጥቀጥ፣ የመሰደብ፣ የመሰደድ… አባዜ።
እናም አንዳንዴ የወጋ ብቻ ሳይሆን የተወጋም ይረሳል። ‹‹መቼ መቼ?›› ካልክ መልሱ ይሄውልህ…. ጠባሳህ ጠፍቶ ትውስታህ በጭጋግ ሲጋረድ፤ የታሪክ ሚዛኑ ተዛብቶ የቆመበት መሬት ሲክድህ…ማስተዋል እርቆህ ከጠላትህ ጋር ትጣባለህ። ቁስልህ ሽሮ ያልተነካህ ቢመስልህ፤ ያን ጊዜ ነው…የተወጋ የሚረሳ።
‹‹ፍትህ ትወዳለህ ፍትህ እንደጎደለ እያወክ ግን ዝም ትላለህ። አየህ ይሄ አንድ ሰው ሲከፋፈል ነው›› ይልሃል አዳም፤ ጎጥ የሸበበው ሽል ውስጥ ተሸሽገህ መላ ቅጡ ጠፍቶህ ሲያይህ። ቆሜለታለው የምትለው ቀድሞ ሲሞትልህ፤ ፍሬው ሳይደርስ ተስገብግበህ አጨድከው። እናም የቆምክበትን ካርታ ተመልከተው፤ በሳር ውስጥ ካለ እባብ ጋር ወዳጅ መስሎህ ለምደህ ይሆን?
ምን መሰለህ ወንድም ዓለም ምላስም እኮ ያዳልጣል። አንዳንዴ ህሊናም ከራስ ይሸሻል። ታዲያ ሰንበርህ ከውስጥ ተሸፍኖ የጠፋ መስሎ ቢያስትህ፤ ከምኔው ከጠላቶችህ ተወዳጅተህ አዛኞችህን መንከስህ። ሙሾ አውራጅ እንዲህ ትላለች፤ የደረቀውን የእንባ ቀረጢቷን በአይበሉባዋ እያሸች…‹‹ወይ እኛና ዶሮ፤ አሞራና ሞት ሲመጣ መንጫጫት፤ ሲሄድም መርሳት››…ዛዲያማ ወንድሜ ከገባህበት ማቅ ለመውጣት የህሊናህን ድር ጠራርጋት። የማስተዋልህን በር ክፈታት…
‹‹አህያውን ፈርቶ ዳውላውን›› እንዲሉ… በከሰረ፣ በተንሸዋረረ የጥላቻ ‹‹ቦጠሊቃ›› አውቀህ ያስተኛህው ህሊናህ አንተን ብቻ ሳይሆን ያመነህንም ገደል ሊከት ነው። ‹‹በእንኪያ ሰላምታ›› እውነትህን አርቀህ ቀብረህ ‹‹ስተህ ለማሳት›› ልብህን ምን አበረታው?
አየህ የተወጋ ሲረሳ… ለተዛባ ፍትህ ቆሜያለሁ ብሎ፤ ንጋትን ለማጨለም ይጣደፋል። ያመነበት ሲሳካ፤ ጉም የዘገነ ይመስለዋል። ትናንቱ እንደ ገደል ማሚቱ ጮሆ ይጠራዋል። ሳይጠጣ እንደሰከረ፣ አሁንም አሁንም እንደሚወላገድ፤ የቆመበት መሬት ስምጥ ገደል እንደሆነ ይታየዋል። ታሪክን ያጨልማል፤ በጭካኔ ተሞልቶ ምስኪን ገበሬን ይከሳል። የእርሱ ያልሆነን ያማትራል…ከአራጁ እየዋለ የበቀለ…በትን መሬት ይክዳል። ለካ የተወጋም ይረሳል….።ከገዳዩ ጋራ አብሮ መሬት ይምሳል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 9/2012
ዳግም ከበደ
የተወጋም ይረሳል!