«ለእናቶች ተብሎ በተዘጋጀ ልዩ የደም ልገሳ ላይ ተገኝቼ ደም ስለግስ የመጀመሪያዬ ነው፡፡ ከወሊድ ጋር በተያያዘ በደም መፍሰስ ምክንያት እናቶች እንደሚሞቱ ስሰማ ልቤ በጣም ስለተነካ እኔም የበኩሌን ለማድረግ ተነሳሳሁ፡፡
«በእኔ ደም ህይወት ማትረፍ ከቻልኩ ከዚህ በኋላም ደም መለገሴን አላቋርጥም፡፡እናት ደግሞ ከምንም በላይ ስለሆነች ደሜን እሰጣለሁ» ይላሉ በአዲስ አበባ የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ጌታቸው አስማማው፡፡
አቶ ጌታቸው በዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል የተገኙት ለግል ጉዳያቸው ነበር፡፡ ከጥር አንድ ቀን ጀምሮ ወሩን በሙሉ በተለያየ ዝግጅት በመከበር ላይ ያለውን ጤናማ የእናትነት ወር አስመልክቶ በሆስፒታሉ የደም ልገሳ እየተካሄደ ነው፡፡ በመርሃግብሩ ላይ እናቶች ህይወት እየሰጡ ነገር ግን በደም መፍሰስ የሚሞቱት ቁጥር ከፍተኛ መሆኑ ሲነገር ይሰማሉ፡፡
ደማቸውን ለመለገስ አላንገራገሩም፡፡ የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማንን ጨምሮ በጤናው ዘርፍ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ነበር አቶ ጌታቸው ደም የለገሱት፡፡ በተለያየ ጊዜ ደም የመለገስ ልምድ ቢኖራቸውም ከዚህ በኋላ እንደማያቋርጡ ይናገራሉ፡፡
የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማን የዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል ወሩን ሙሉ ለእናቶች ምቹ ሁኔታ በመፍጠር የበለጠ አገልግሎት እንዲሰጥ የሆስፒታሉን ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ዘላለም ጨምቤሳን ቃል አስገብተዋቸዋል፡፡
ዶክተር ዘላለም በገቡት ቃል መሰረት በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ በመውለድ ላይ ያሉትን ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ሴቶች ተገቢውን አገልግሎት አጠናክረው እንደሚሰጡ ተናግረዋል፡፡ዶክተር ዘላለም እንዳሉት የሆስፒታሉ ሰራተኞች ህፃናት ልጆቻቸውን የሚያቆዩበት የማቆያ ስፍራ የለውም፡፡ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ግን ማቆያ ለመሥራት ተዘጋጅተዋል፡፡ በሆስፒታሉ በወር እስከ ስድስት መቶ፣ በዓመት ደግሞ ከ3,600 በላይ እናቶች የቅድመና ድህረ ወሊድ አገልግሎት ያገኛሉ፡፡
እንደ ዶክተር ዘላለም ገለፃ እናቶች እንዳይንገላቱና ከወሊድ ጋር በተያያዘ የሚፈጠረውን ሞት ለማስቀረት ሆስፒታሉ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከአጎራባች ጤና ጣቢያዎች ጋር በቅንጅት በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡ ውስብስብ የጤና ችግር የሌለባቸው በጤና ጣቢያ እንዲወልዱ በማድረግ፣ ከፍተኛ ክትትል የሚያስፈልጋቸውን ደግሞ በሆስፒታሉ አገልግሎት በመስጠት ክፍተቶች እንዳይፈጠሩ ጥረት በማድረግ ላይ ነው፡፡ በአሰራር የሚያጋጥሙ ችግሮችን በሂደት በመፍታት የእናቶችን ጤና ለማሻሻል አስፈላጊውን ሁሉ ያደርጋል፡፡
ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማን በበኩላቸው እንደተናገሩት በወሊድ ወቅት የሚያጋጥም ሞት ከደም መፍሰስ ጋር የተያያዘ ሲሆን፤ይህን መከላከል ሁሉም ሰው ደም ለመለገስ ፈቃደኛ መሆን ይኖርበታል፡፡በተለይ ወንዶች ደም በመለገስ አጋርነታቸውን ማሳየት ይኖርባቸዋል፡፡
ሚኒስትሩ አርአያ ለመሆን የደም ልገሳውን ከራሳቸው የጀመሩ ሲሆን፤ እናቶች ቅድመና ድህረ ወሊድ የህክምና ክትትል እንዲያደርጉና በጤና ተቋማት እንዲወልዱ ተገቢውን ግንዛቤ መስጠት ከጤና ባለሙያውም እንደሚጠበቅ፣ በቂ የሆነ የህክምና ግብአት ለማሟላትም ትኩረት እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡
መረጃዎች የሚያሳዩት በየዓመቱ በሚካሄደው ጥናት62 በመቶ፤ በየአምስት ዓመቱ በሚደረገው ጥናት ደግሞ 70 በመቶ የሚሆኑት በቤት ውስጥ የወልዳሉ፡፡ በከተማም ሆነ በገጠርም የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራምን በማጠናከር እናቶች በጤና ተቋማት የማይወልዱበትን ምክንያት በዝርዝር በጥናት መመለስ እንደሚያስፈልግ የጠቆሙት ሚኒስትሩ፤ በጤናማ እናትነት ወር ብቻ ሳይሆን ሁሌም ለሴቶች ክብር በመስጠት እንዲሁም ከወሊድ ጋር በተያያዘ ለእናቶች ሞት ምክንያት ሊሆኑ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት እንዲሰጥ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በልዩ የደም ልገሳው ላይ ያገኘናቸው በአዲስ አበባ ከተማ ጦር ኃይሎች አካባቢ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ትዕግስት ተስፋው ዝግጅቱ ለእናቶች የተሰጠውን ትኩረት እንደሚያሳይና በዝግጅቱ ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ወይዘሮ ትዕግስት የሁለት ልጆች እናት ሲሆኑ፤በአሁኑ ወቅት የስድስት ወር ነፍሰጡር ናቸው፡፡ቅድመና ድህረ ወሊድ ክትትል እንደሚያደርጉና በህክምና ታግዞ መውለድ እራስንም ልጅንም ከአደጋ ለመታደግ እንደሚቻል፤ በሀኪም የሚሰጣቸውን ትዕዛዝም እንደሚፈፅሙና ቀደም ሲል ጀምሮ በህክምና ክትትል በመውለዳቸው ችግር እንዳላጋጠማቸው ይገልጻሉ፡፡
ጤናማ የእናትነት ወር ‹‹በደም መፍሰስ ምክንያት የሚከሰተውን የእናቶች ሞት በጋራ እንከላከል›› በሚል መሪ ቃል እየተከበረ ይገኛል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 10/2011
በለምለም መንግሥቱ