ተወልደው ያደጉት እዚሁ አዲስ አበባ ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በፍሬሕይወት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በአዲስ ከተማ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል። በመቀጠልም በምኒልክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ በሚገኘው የሥነጥበብ ትምህርት ቤት በመግባት በስዕልና ቅብ (ድሮዊንግና ፔይንቲንግ) ዘርፍ ትምህርታቸውን ተከታትለው በዲፕሎማ ተመርቀዋል። የተማሩት የሥነ ጥበብ ትምህርት ገፋፍቷቸው ወደ ማስታወቂያ ሥራ በመግባት ላለፉት ሃያ ዓመታት በማስታወቂያ ሥራ ቆይተዋል – የኤርሚያስ አድቨርታይዚንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ባለቤት አቶ ኤርሚያስ መንግስቱ።
አቶ ኤርሚያስ ከሥነ-ጥበብ ትምህርት ቤት ተመርቀው እንደወጡ ብሔራዊ በተሰኘ የማስታወቂያ ድርጅት ውስጥ ተቀጥረው ለአራት ዓመታት አገልግለዋል። በወቅቱ የዲጂታል ማስታወቂያ ሥራ ያልተጀመረ በመሆኑ የማስታወቂያ ሥራን የጀመሩት የሥነ-ጥበብ እውቀታቸውን ተጠቅመው ትልልቅ ማስታወቂያዎችን በላሜራዎች ላይ በመሳልና ጽሑፎችን በመፃፍ ነበር። በአራት ዓመት የማስታወቂያ ሥራ ቆይታቸው በቂ ልምድ በመቅሰማቸው እና የማስታወቂያ ቢዘነስን ጠንቅቀው በመረዳታቸው ከደመወዝ የሚያገኟትን ትርፍ ገንዘብ እናታቸው ዘንድ እንዲቀመጥ በማድረግ እና በማጠራቀም አስር ሺህ ብር በሚጠጋ መነሻ ካፒታል የራሳቸውን የማስታወቂያ ድርጅት ከፍተዋል። ለዚህም የእናታቸውና የጓደኛቸው ድጋፍ ትልቅ አስተዋፅኦ አድርጎላቸዋል።
በዚሁ መነሻ ካፒታል ከሥራ አጋራቸው ጋር በመሆን ሦስት በሦስት የምትሆን አነስተኛ ቤት በመከራየት እና አንድ ግራይነደርና አንድ ድሪል በመግዛት፤ ያላቸውን ብቸኛ የማስታወቂያ እውቀትና ፍላጎት በመያዝ የማስታወቂያ ሥራቸውን ‹‹ሀ›› ብለው ጀምረዋል። በጊዜውም የተለያዩ የህትመት ሥራዎችን በተለይ የቲ- ሸርት ህትመት ሥራዎችን ሰርተዋል። ቀጥለውም የቁልፍ ማንጠልጠያዎችን፣ ላይት ቦክሶችንና የካፍቴሪያ ጽሑፎችን አክለዋል። ወደዚህ የማስታወቂያ ሥራ ለመግባት እና የራሳቸውን የማስታወቂያ ድርጅት ለመከፈት ታዲያ እርሳቸው ዘንድ ያለው እውቀት እና ማስታወቂያ ለመስራት ያላቸው ፍላጎት ትልቁን አስተዋፅኦ አበርክቷል። በጊዜው የነበሩ ሞኖ፣ ብሔራዊ፣ ቢቲ እና ኒዮን አዲስ የተሰኙ የማስታወቂያ ድርጅቶችም ወደ ማስታወቂያ ሥራው እንዲገቡ አነሳስተዋቸዋል።
‹‹በማስታወቂያ ሥራ እንደአገር ስኬታማ ነኝ›› የሚሉት አቶ ኤርሚያስ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስኬታማ ለመሆን በርካታ ሥራዎችን መስራት እንደሚጠበቅባቸው ይናገራሉ። ለስኬት ያበቃቸው ምስጢርም ጠንክሮ መስራታቸው፣ ፍላጎቱ እና እውቀቱ ባላቸው ሙያ ላይ ተሰማርተው በፍቅር መስራታቸው መሆኑንም ያስረዳሉ።
በከተማዋ በተደጋጋሚ የሚሰሩ የህትመትና የጽሑፍ ማስታወቂያ ሥራዎች አሁንም ብዙ የሚቀራቸውና ከዚህም በላይ ሊሰሩ እንደሚችሉ የተረዱት አቶ ኤርሚያስ፣ ከዚህ በበለጠ የማስታወቂያ ሥራዎችን በመስራት ሌሎችን መብለጥ እንደሚቻል ከራሳቸው ጋር በመነጋገርና ይህንኑ ኢላማ አድርገው በመስራታቸው ዛሬ ላይ ህልማቸውን ማሳካት ችለዋል። የማስታወቂያ ሥራዎችን በተሻለ እና በተለየ መልኩ፣ በጥራት እና በእልህ በመስራታቸው የተሻለ ደረጃ ላይ ደርሰዋል። የተሻለ ሥራ የመስራት እና በልጦ የመገኘት ፍላጎትም ሲያደርጉ የነበረውን ጥረት ለፍሬ አብቅተውታል።
በዚያች ሦስት በሦስት ክፍል ውስጥ ፍራሽ አንጥፈው እዚያው እያደሩና ሃያ አራት ሰዓታት እየሰሩ የዘለቁት አቶ ኤርሚያስ፣ የወጣትነት ዕድሜያቸውን በአብዛኛው በሥራ አሳልፈዋል። ትዳርም የያዙት በጊዜ ነው። ይህም ዛሬ ላይ ለደረሱበት ስኬት የራሱን አስተዋፅኦ አበርክቷል። እናታቸው ሁሌም ካጠገባቸው መሆናቸው እና ሥራቸውን ጠንክረው እንዲሰሩ ያበረታቷቸው የነበረ በመሆኑ በሥራቸው ይበልጥ እንዲበረቱ አድርጓቸዋል። በአንድ ወቅትም በብሔራዊ የማስታወቂያ ድርጅት ውስጥ ተቀጥረው እየሰሩ በሥራቸው ተማረው ለመተው ሲሞክሩ ከሥራቸው ተሰናክለው እንዳይቀሩ፤ ይልቁንም በርትተው እንዲሰሩ የእናታቸው ምክር እና ተግሳፅ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክቷል። ሥራቸውን ተግተው እንዲሰሩ እና ጠንካራ የሥራ ባህልን እንዲያዳብሩም በእጅጉ ረድቷቸዋል።
በአስር ሺህ ብር በሚጠጋ ካፒታል ሥራውን የጀመረው ኤርሚያስ፣ አድቨርታይዚንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ በአሁኑ ወቅት ካፒታሉ 40 ሚሊዮን ብር ደርሷል። በተለያዩ ዘርፎች ላይ የሚሰሩ አንድ መቶ የሚሆኑ ሠራተኞችን በስሩ ቀጥሮም ያሰራል። በስሩ ቀጥሮ በሚያሰራቸው ሠራተኞች እና በሚሰራቸው የማስታወቂያ ሥራዎች ብዛትም በአገር ውስጥ ካሉ ትልልቅ የማስታወቂያ ድርጅቶች ውስጥ አንዱ ለመሆን በቅቷል። ከሃያ በላይ የሚሆኑ ልዩ ልዩ የማስታወቂያ ህትመት ማሽኖችንም ከውጭ አገራት በማስገባት እየሰራ ይገኛል።
ከላይ እስከታች በሚገባ የተደራጀ የማኔጅመንት መዋቅር ያለው ኩባንያው፣ ዓለም አቀፍ የማስታወቂያ ድርጅት የመሆንን ዓላማ በማንገብ እና በጎረቤት አገራት የመስራት ፍላጎትን በመሰነቅ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። በዓለም አቀፍ ደረጃም ተመዝግቦ ዓለም አቀፍ ጨረታዎችን መጫረት የሚችልበትን አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎችን አሟልቷል።
ኩባንያው፣ የቤት ውስጥ እና ከቤት ውጪ ያሉ የማስታወቂያ ሥራዎችን እየሰራ የሚገኝ ሲሆን፣ የማስተዋወቂያ ማቴሪያሎችን፣ የቲ-ሸርትና የኮፍያ፣ የካፍቴሪያ ጽሑፎች፣ ባንዲራዎች እና ሌሎችንም የማስታወቂያ ሥራዎችን ይሰራል። በተጨማሪም መኪናዎች ላይ የብራንድ ሥራ፣ ቢልቦርድ እና ላይት ቦክስ ሥራዎችንና ጉዳዮችን በአጠቃላይ በማስታወቂያው ዘርፍ ላይ ያሉ ሥራዎችንም እንደደንበኞቹ ፍላጎት ያከናውናል።
ይሁንና በመንግሥት በኩል በመመሪያ ደረጃ ሊስተካከሉ የሚገቡ እና አሁንም ኩባንያውን ይበልጥ እንዳይሰራ ማነቆ የሆኑ ችግሮች እንዳሉ አቶ ኤርሚያስ ያመለክታሉ። በተለይ በአገሪቷ ያለው የማስታወቂያ መመሪያ ስታንዳርዶች እስኪወጡ ድረስ ትልልቅ ቢል ቦርዶችንና ዘመናዊ ስክሪኖችን ለመስራት የሚከለክል በመሆኑ ማስታወቂያው እንዳያድግ ትልቅ ማነቆ መሆኑንም ይጠቁማሉ። ኩባንያውም የተሻለ ገንዘብ በማውጣት በከተማዋ ትልልቅ ማስታወቂያዎችን እንዳይሰራ እንቅፋት እንደሆነበትም ይገልፃሉ። ከዚህ በተቃራኒ ግን አሁንም ስታንዳርዳቸውን ያልጠበቁ ትላልቅ ቢልቦርዶች በከተማዋ አንዳንድ ቦታዎች ላይ እንደሚሰቀሉ እና ይህም መመሪያው ክፍተት ያለበት መሆኑን እንዲሁም ሁሉም ሰው በተለያየ መንገድ የማስታወቂያ ሥራዎችን የመስራት ልምድ እንዳጎለበተ ጠቋሚ መሆኑንም ያስረዳሉ።
‹‹አንድ ማስታወቂያ ድርጅት እያደገ በሄደ ቁጥር አዳዲስ ነገሮችን መስራት ያለበት ቢሆንም፤ በአሁኑ ወቅት ያሉት የማስታወቂያ ሕጎችና መመሪያዎች ይህን ለማድረግ ስለማይፈቅዱ ኩባንያው በሚፈለገው ስታንዳርድ ልክ በከተማዋ ማስታወቂያ ሥራ መስራት አልቻለም፤ እድገቱም ቆሟል›› የሚሉት አቶ ኤርሚያስ፣ ‹‹በዚህ ረገድ ያሉ ክፍተቶችን መንግሥት ማስተካከል የሚችል ከሆነ በከተማዋ ጥራት ያላቸው እና ትልልቅ ሥራዎችን መስራት የሚቻልበት ዕድል ይፈጠራል›› ይላሉ። ከዚህ ውጪ ግን የማስታወቂያ ኩባንያው ከዓለም አቀፍ የማስታወቂያ ድርጅቶች ጋር የሚወዳደር እና አስፈላጊ የሆኑ ማሽነሪዎችን ሁሉ በማሟላት ማምረት የሚችለውን ያህል ባለማምረቱ አብዛኛዎቹ ማሽነሪዎች ያለሥራ መቆማቸውንም ያስረዳሉ።
‹‹በዓለም አቀፍ ደረጃ የማስታወቂያው ዘርፍ ትልቅ ቢዝነስ መሆኑ የሚታወቅ ቢሆንም፤ የኢትዮጵያ የማስታወቂያ ኢንዱስትሪ ገና አላደገም›› የሚሉት አቶ ኤርሚያስ፣ በዘርፉ ላይ የሚደረገው ኢንቨስትመንትም ዝቀተኛ መሆኑንና ገና ብዙ የሚቀረው፤ መንግሥትም የዘነጋው ዘርፍ መሆኑን ይጠቁማሉ። ዘርፉ የተማረውን ኅብረተሰብ ብቻ ሳይሆን ትምህርታቸውን ገና ያላጠናቀቁ ወጣቶችን እና የቴክኒክና ሙያ እውቀት ያላቸውን ሰዎችን በማሳተፍ የሚካሄድ ነው። ይሁንና ዘርፉ በርካታ ወጣቶችን እንደመያዙና በርካታ ግብር ለመንግሥት የሚያስገባ የመሆኑን ያህል መንግሥት ትኩረት እንዳልሰጠው አቶ ኤርሚያስ ይናገራሉ።
በየቦታው የሚለጠፉና ፍቃድ እንዳላቸው የማይታወቁ ማስታወቂያዎችም የዘርፉን ደረጃ ዝቅ እንዲል እንዳደረጉት እና ሰዎችም የማስታወቂያውን ሥነምግባር በተከተለ መልኩ እየሰሩ እንዳልሆነም ጠቅሰው፤ የማስታወቂያው ዘርፍ ገና ብዙ መሰራት ያለበትና በትክክል ቢያዝና በስታንዳርድ ቢመራ ደግሞ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ የሚያበረክተው አስተዋፅኦ የዚያኑ ያህል ከፍ ያለ እንደሚሆንና ለበርካታ ዜጎችም የሥራ ዕድል መፍጠር እንደሚችል ያብራራሉ።
እርሳቸው እንደሚሉት ከሆነ፤ የማስታወቂያው ዘርፍ እንዲያድግ ከተፈለገ በዋናነት በማስታወቂያው ዘርፍ ላይ ያሉ ሰዎችና መንግሥት በቅርበት በመነጋገር ሊሰሩ ይገባል። ዘርፉ ባለቤት እንዳለውም ስለማይታወቅ ባለቤት ያስፈልገዋል። በደንብ ትኩረት ተሰጥቶትና ግልፅና ሊያሰራ የሚችል መመሪያ በአገሪቱ መውጣትም ይኖርበታል። ይህም የከተማዋን ፕላን በጠበቀ መልኩ ትልልቅ ማስታወቂያዎችን ለመስራት ያስችላል። መንግሥትም በውጪዎቹ የማስታወቂያ ኩባንዎች ላይ ከማተኮር ይልቅ በአገር ውስጥ ላሉ ትኩረት በመስጠት አቅማቸውን በመገንባት ሥራዎችን እንዲሰሩ ማበረታታት ይገባዋል። በዚህ ዘርፍ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ሰዎችም በጋራ በመሆን በማህበራቸው አማካኝነት ዘርፉን ለማሳደግ ሊንቀሳቀሱ ይገባል።
እንደ አንድ የማስታወቂያ ድርጅትም በቀጣይ በርካታ ሥራዎችን ለመስራት እቅድ ይዟል። ኩባንያው በዋናነት ቅርንጫፎቹን የማስፋት እቅድ ያለው ሲሆን፣ በቀጣይም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ ትልልቅ ከተሞች ቅርንጫፎችን የመክፈት ሃሳብ አለው። በአሁኑ ወቅትም በሰበታ እና በዓለም ገና ከተሞች ቅርንጫፉን እንደከፈተና በባህርዳር ከተማ ደግሞ ሦስተኛ ቅርንጫፉን ለመክፈት ዝግጅት እያደረገ ይገኛል። በሌላ በኩልም ዓለም አቀፍ የማስታወቂያ ጨረታዎችን በመወዳደር ከጎረቤት አገራት በዘለለ ዓለም አቀፍ የማስታወቂያ ሥራዎችን የመስራት ውጥንም ይዟል።
ለአገር ውስጥ የማስታወቂያ ኩባንያዎች በተለይ መንግሥት ድጋፍ የሚያደርግና የሚያበረታታ ከሆነ ኩባንያው በምሥራቅ አፍሪካ ላይ በሚገኙ አገራት በስፋት የመስራት ፍላጎት ያለው ሲሆን፣ የማስታወቂያ ሥራን በሚመለከት በመንግሥት በኩል ያሉ አንዳንድ መመሪያዎች የሚሻሻሉ ከሆነ በርካታ የማስታወቂያ ሥራዎችን የሚሰራበት ዕድል ይኖራል። ለዚህም ኩባንያው በስፋት ሊሰራበት የሚያስችለውን 2 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ አለምገና አካባቢ በመግዛት እና ወርክሾፕ በማዘጋጀት የማስታወቂያ ሥራውን ለማሳደግ እየሰራ ይገኛል።
የማስታወቂያው ኢንዱስትሪ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለኢኮኖሚው የሚያበረክተው አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑ እሙን ነው። ለዚህም አገራት ከፍተኛ ገንዘብ ለዘርፉ በማውጣት በየዓመቱ ዳጎስ ያለ ገቢ ያገኛሉ። በኢትዮጵያም የማስታወቂያው ኢንዱስትሪ እምብዛም ያደገ ባይሆንም፤ ለዘርፉ ማደግ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴዎች በኤርሚያስ አድቨርታይዚንግና መሰል የማስታወቂያ ድርጅቶች አሁን አሁን መታየት ጀምሯል። የኩባንያው ባለቤት እንዳሉትም፤ መንግሥት ለማስታወቂያው ኢንዱስትሪ ተገቢውን ድጋፍ በማድረግ ዘርፉ በሚገባው ደረጃ እንዲያድግ የድርሻውን መወጣት ከቻለ ፋይዳው ከፍ ያለ ነው።
አዲስ ዘመን ግንቦት 4/2012
አስናቀ ፀጋዬ