ዓለም አቀፉ ወረርሽኝ ኮሮና ቫይረስ ዓለምን ግራ አጋብቶ አሁንም ድረስ እያስጨነቀ ይገኛል። ኃያላን ነን ባዮችን መንግሥታት ሁሉ አሽመድምዶ እያራዳቸውም ነው። የሰው ልጅ የቱንም ያህል በቴክኖሎጂ ቢረቅና ቢመጥቅ በአንድ ጀምበር ሁሉም እንዳልነበረ ሆኖ እንደሚወድቅ ኮሮና ለዓለም በተጨባጭ አሳይቷል። ኮሮና የምድሪቱ ሆነ የሰማዩ ብቸኛው አድራጊ ፈጣሪ ሰውና መንግሥታት ሳይሆኑ እግዚአብሔር እንደሆነ በማሳየቱም የሚማርና ልበ ብሩህ ካለ ሊያስተውል ይገባል። ኮሮና የኃያላኑን ሀገራት በርከት ያሉ ዜጎች በየዕለቱ በሞት እየነጠቀ የሞት መላዕክት ሆኖ እርምጃውን ጨምሯል። ድሀ ሀገራትንም እያተራመሰ ይገኛል።
የዓለማችን ሳይንቲስቶች መድኃኒት ፍለጋ ሲባጁ ውለው ቢያድሩም እስከአሁን የተገኘ ፈዋሽ መድኃኒት አሊያም ክትባት የለም። ሲነገር ከነበረው ውጪ የቫይረሱ መተላለፊያ መንገዶች ተለዋዋጭ ባህርይ እንዳላቸው የሚወጡት ዓለም አቀፍ መረጃዎች ያሳያሉ። በአሁኑ ሰዓት ይህ ወረርሽኝ በአሜሪካ የከፋ ብትሩን ሲያሳርፍ ብዙ ሰው እጅግም ጉዳዬ አላለውም ነበር። ዛሬ አሜሪካ በኮሮና ቫይረስ 80 ሺህ 423 ዜጎቿን በሞት ተነጥቃለች። እንግሊዝ፣ ጣሊያን፣ ፈረንሳይ፣ ስፔን፣ ቻይና እና ሌሎችም ብዙ ሀገራት ብዙ ሺህ ዜጎቻቸው በቫይረሱ ሞተዋል። የዓለም ሀገራት ኢኮኖሚውም ሆነ የግብይት ልውውጡ ደቋል። በዓለማችን በአጠቃላይ ወደ አራት ሚሊዮን ሕዝብ በኮሮና ቫይረስ የተያዘ መሆኑን እውን ሆኗል።
በዚሁ ወረርሽኝ ሳቢያ ፖላንድ በግንቦት 10 ቀን 2012 ዓ.ም ልታደርግ የነበረውን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ አስተላልፋለች። በፓኪስታን በቫይረሱ 18 ሺህ ሰዎች ሲያዙ 550 ሰው ሞቷል። በሕንድ ወደ ሁለት ሺህ ሰው ሞቷል። ቫይረሱ በመላው ዓለም ተሰራጭቶ እየፈነጨ ነው። በየዕለቱ በቫይረሱ የሚያዙትና የሚሞቱት ቁጥር እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ አልሄደም።
እስከአሁን ቫይረሱን ለመከላከልና ስርጭቱን ለመቀነስ ያለው ብቸኛ አማራጭ መንግሥትና የጤና ተቋማት የሚሰጡትን ምክርና መመሪያ በአግባቡ መቀበልና ሥራ ላይ ማዋል ብቻ ነው። ‹ቤታችሁ ቆዩ አትውጡ፤ እጃችሁን በሳሙና በሚገባ ታጠቡ፤ ርቀታችሁን ጠብቁ፤ ሰዎች ከበዙበት ቦታ ራቁ፤ የመከላከያ ማስክ አድርጉ›
የሚለውን ተቀብሎ ተግባራዊ ማድረግ ግድ ይላል።
ወደ እኛው ሀገር ስንመለስ መንግሥት በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ ከተከሰተ ጀምሮ ሕዝቡ ለከፋ አደጋ እንዳይጋለጥ ይበል የሚያሰኙ የተለያዩ እርምጃዎችን ወስዷል። የማስተማርና የማሳወቅ ሥራዎች በሰፊው ተሰርቷል። በተቻለ ሁሉ ሰዎች ሊሰሟቸው ይችላሉ ተብለው በሚታሰቡ ሰዎች ሁሉ መልዕክት ቢተላለፍም ተግባራዊ የሚያደርገው ብዙው የኅብረተሰብ ክፍል አይደለም።
ሰው ያለው በየአደባባዩና በየጎዳናው ነው። ሲጋፋና ሲተራመስ ይውላል። ኮሮና እኛን አይነካንም ይላል። እንዲህ ዓይነት ጭፍንና ኋላቀር አመለካከት ያላቸው ብዙ ናቸው። ገበያተኛው እየተጋፋ ትንፋሽ ለትንፋሽ ሲማማግ ይውላል። ውሃና መብራት ከፈላው ትርምስ ነው። የቀበሌ ሸማቾች ሱቅ በገዢው ሰልፈኛ ብዛት ተፋፍጎ ትንፋሹ ይጋረፋል።
መንግሥት የኮሮና ቫይረስን ስርጭት ለመግታት አዋጅ አወጣ። ሕዝቡ ትንሽ ቀን አከበረውና እንደ ልማዱ ጥሶት አደባባይ ወጣ። መዝናኛ ቤቶችና መናፈሻዎች ከጠዋት እስከ ማታ በሕዝብ እንደተሞሉ ነው። በኢትዮጵያ ምድር የዓለምን ሕዝብ በአራቱ ማዕዘናት በሞት እየቀጠፈና እያራገፈ በየዕለቱ ወደ ጅምላ መቃብር እያወረደ ያለው ዘር፣ ጾታ፣ ዕድሜ፣ ቀለም፣ ሀብት፣ የትምህርት ደረጃና ሃይማኖት የማይለየው ሁሉን ኮሮና ቫይረስ ጭርሱንም የገባ ሰውም የሰማ አይመስልም። ‹ሰውረነ ከመአቱ› የሚባለው በእንዲህ ዓይነቱ ክፉ ጊዜ ነው።
ዓለም በኮሮና ቫይረስ ምጣድ ተጥዳ እየተቆላች እየነፈረች ትገኛለች። ነጮቹ እኛ ያልቻልነውን ድሀና ታዳጊ ሀገራት አይመክቱትም፤ በቂ የጤና አገልግሎት የላቸውም፤ ስለዚህ እነሱ ዘንድ ኮሮና ቫይረስ ከገባ በተለይ አፍሪካ፣ ደቡብ እስያ ሀገራትና ላቲን አሜሪካን ጨምሮ በብዙ መቶ ሺህ ሕዝብ ያልቃል ይሉት የነበረው ዛሬ በገሀድ ለመታየት እየተንደረደረ ነው። ኮሮና ‹ውቃው ደብልቀው› ሊል ቀናት የቀሩት ይመስላል። ሰው መትረፊያውን ስትነግረው መጥፊያውን የሚፈልግ ሆነ። መንግሥትም ቃተተ።
የእኛን ለየት የሚያደርገው በዚህ ጅምላ ጨራሽ ስውር መሣሪያ ኮሮና ቫይረስ ዜጎች በየዕለቱ እየተያዙ እየሞቱ ባሉበት፤ ሀገራዊ ኢኮኖሚያችን ቁልቁል እየተምዘገዘገ በሚገኝበት፤ እንደልብ ወጥቶ ሰርቶ መግባት ባልተቻለበት፤ ሠርግም ሆነ ለቅሶ በቅጡ ማድረግ በቀረበት፤ ቤተሰብ ከቤተሰብ፣ ዘመድ ከዘመድ መገናኘት አስፈሪ በሆነበት ሰዓት ስለፖለቲካና ምርጫ የሚያወሩ ሰዎችን ማየትና መስማት እጅግ አድርጎ ይዘገንናል፤ ይሰቀጥጣልም።
ምን ያህል ከሰውኛ ባህርይና ከሰብአዊነት የተፋቱ ለሕዝብ ደንታ የሌላቸው መሆኑን አሳይቶናል። እሪ ያሰኛል። የምርጫ ውድድሩ፤ የሥልጣን ፉክክሩ፤ ሰላም ሲሆን ይደረስበታል። መጀመሪያ እስቲ ከዚህ መቅሰፍት በሽታ ሕዝብና ሀገር ይውጡ። በፍርሀት ቆፈን ተቀፍድዶ ‹እንተርፍ ይሆን ወይንስ እናልቃለን› በሚል ጭንቀት ውስጥ የሚገኝን ሕዝብ ያውም ደግሞ ተጠንቀቅ ቢባልም የዕለት ኑሮውና ጉርሱ አስገድዶት በየቦታው ሲባትል፣ ሲጋፋና ሲተራመስ የሚውለውን ከከተማ እስከ ገጠር ያለ ሕዝብ ከሞት ጋር ተፋጦ ትግል በገጠመበት ሰዓት ስለምርጫ ማውራት ያሳፍራል። በገዛ እጃቸው ከሕዝቡ ጋር እንደተቆራረጡ ይረዱት።
ይሄ ክፉ ቀን ይለፍ፤ ሕዝብም ከሞት ይትረፍ፤ ምርጫውም ሆነ ፖለቲካው ሕዝብና ሀገር ሰላም ሲሆን ነው። ሀገር ያለ ሕዝብ ባዶ መሬት ነች። የሀገር ውበትና ድምቀቷ ሕዝብ ነው። ሕዝብን አፍጥጦ ከመጣው ቀሳፊ ሞት ለማትረፍ ነው ርብርብ መደረግ ያለበት። አሁንም ማስተማሩ ማሳወቁ ይቀጥል።
ኮርኖ ቫይረስን ከፖለቲካ ጋር ለማያያዝ የሚክለፈለፉ ወሰላቶችም አሉ። የፖለቲካ ቁማር መጫወቱ ይብቃ። ‹አቦ ተዉና!› አለ የሐረር ልጅ። ሕዝቡን ይተውት። ከጀርባው ይውረዱ።ሕዝብ የሀገሩን ሰላም ፈላጊና አክባሪ ነው። ሌላው ኮሮና ሆነው እልቂት ለመፍጠር ከመክለፍለፍ የሚሻላቸው አደብ መግዛቱ ነው። የሞት ነጋዴዎች ከመሆን ይታቀቡ። ሕዝቡን ከበሽታው እንዲጠነቀቅ በስፋት ማስተማሩ ይቀጥል።ግፊያና የአደባባይ ትርምሱ ይቁም።
ቢያንስ ስርጭቱን ለመግታት እንድንችል የመንግሥትንና የባለሙያዎችን ምክር እንስማ። ተግባራዊ እናድርግ። አደጋውን እንቀንስ። በበሽታው መንስኤነት ተያይዞ መጠፋፋቱ፣ መተላለቁ ለማንም አይበጅም። ሰው ከሌለ መሬትም ሆነ ቤት ባዶ አውድማ ነው። ከገንዘብ፣ ከሀብት፣ ከሥልጣንም በላይ የሰው ልጅ ሕይወት ክቡር ነው። ምከረው ምከረው እምቢ ካለ መከራ ይምከረው የሚባለው የአባቶች አባባል እንዳይደገም እንጠንቀቅ!!!
አዲስ ዘመን ግንቦት 4/2012
ወንድወሰን መኮንን