አዲስ አበባ፡- በአገር አቀፍ ደረጃ ወጥነት ያለው የአፈፃፀም መለኪያ እና የፍትህ ሥርዓት ለመዘርጋት የማሻሻያ እና ማጠናከሪያ የሆኑ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የፌዴራል የፍትህና የህግ ምርምርና ስልጠና ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡
ፍትህ አካላት የአፈፃፀም መለኪያ አመላካቾች በሚል መሪ ርዕስ ፍርድ ቤቶች፣ አቃቤ ህግ፣ ፖሊስና የማረሚያ ቤቶች ላይ በማተኮር ተቋማቱ ሊተገብሩት በሚገቡ አሠራሮች ላይ የሚመክር ውይይት ትናንት በኢንተር ኮንኔታል ሆቴል በተካሄደበት ወቅት በሚኒስትር ማዕረግ የፌዴራል የፍትህና የህግ ምርምር እና ስልጠና ኢንቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ደግፌ ቡላ እንደተናገሩት፤ የፍትህ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ፣ የህብረተ ሰቡን ፍላጎት ለማሳካት ብሎም በአገሪቱ ያለውን የፍትህ ሥርዓት ለማዘመን ትኩረት ተደርጎ በመሰራት ላይ ነው፡፡
አቶ ደግፌ እንዳሉት፤ የፍትህ ተቋማት የአፈፃፀም ምዘና ሥርዓት ለመዘርጋትና ለመተግበር ከፍተኛ ጥረት ያደረጉ ቢሆንም በአፈፃፀም አመልካቾች አዘገጃጀትም ሆነ አተገባበሩ ላይ ክፍተቶች እንዳሉ በጥናትና ከህብረተሰቡ በሚመነጩ ቅሬታዎች መረጋገጡን ገልፀዋል፡፡ በመሆኑም የፍትህ አካላት ያወጡትን እቅድ ከተቀመጠው ዓላማና ግብ አኳያ ምን ያክል እየተገበሩት እንደሆነ አፈፃፀ ማቸውን የሚለኩበት ሥርዓት መዘርጋት ይኖርባቸዋል፡፡ በተለይም ደግሞ የሥራ ደረጃዎቻቸው ያሉበትን ደረጃ መገንዘብ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ የአፈፃፀም አመልካቾችም የስትራቴጂካዊ ግቦችን ስኬት በማረጋገጥ፣ ኃላፊዎችና ፈፃሚዎች ውጤት በሚያመጡ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ማድረግ የግድ እንደሚላቸው አስረድተዋል፡፡
የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩ ላቸው፤ በአገር አቀፍ ደረጃ የተጀመ ረውን ለውጥ ለማስቀጠል በሁሉም ዘርፎች ሪፎርም እንደሚስፈልግ በመጠቆም፤ ፍትህ ሥርዓቱም እንዲ ዘመንና አዳዲስ አሰራርና ሥርዓት መዘርጋቱ ተገቢ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡ ሆኖም የፍትህ ሥርዓቱ ሁሌም መዘመን እንዳለበት በመጠቆም በቀጣይ የዜጎች ከዓለም አቀፍ ነባራዊ ሁኔታዎች ጋር የተጣጣመ፣ በሠው ኃይልና ቴክኖሎጂ የተደገፈ ብሎም ስትራቴጂካዊ ስልቶችን ከግምት ውስጥ ያስገባ አሠራር መተግበር እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
ክፍለዮሐንስ አንበርብር