የተወለዱት በአዲስ አበባ ከተማ ፒያሳ አካባቢ ነው። ከወላጆቻቸው ስምንት ልጆች መካከል ሰባተኛ ልጅ ሲሆኑ ባደጉበት ሰፊ ቤተሰብ ውስጥ ከወንድምና እህቶቻቸው ጋር ተቀራርቦ የመኖርን ልምድ አዳብረዋል። ሲያድጉ ተቀጥረው ሳይሆን የእራሳቸውን ሥራ የሚመሩ ሰው እንደሚሆኑ ያልሙ እንደነበር ያስታውሳሉ። የዛሬው የሲራራ እንግዳችንና ትምህርት፣ ጤናን፥ ምግብ ዘርፎች ላይ ተሰማርተው የሚገኙት ከሀገር ውስጥ ባለፈ በወጪ ንግድ ላይም ተሳትፎ ያደርጋሉ። አቶ ዳዊት ኃይሉ።
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉት ቤተልሔም የተሰኘው ትምህርት ቤት ነው። የሁለተኛ ደረጃን ደግሞ ጥቁር አንበሳ ትምህርትም ቤት ነው ያሳለፉት። በወቅቱ ግን የአባታቸው የመድኃኒት መደብር ጎራ እያሉ በትርፍ ሰዓታቸው ያግዙ እንደነበር አይዘነጉትም። ከትምህርቱ ጎን ለጎን በጊዮን ሆቴል በአስተኛጋጅነት ተቀጥረው ይሰሩ እንደነበር ያስታውሳሉ።
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸው ሲጠናቀቅ ደግሞ ለከፍተኛ ትምህርት የተመደቡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ንግድ ሥራ ኮሌጅ ግቢ ነው። በዚያም የአካውንቲንግ ትምህርት ክፍል ተቀላቅለው መማር ጀመሩ። በወቅቱ ደግሞ በማታው የትምህርት ጊዜ ተጨማሪ የትምህርት ዕድል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በማግኘታቸው የሶሺዎሎጂ ክፍልን ተቀላቀሉ። እናም ቀን ቀን አካውንቲንግ ሲማሩ ማታ ላይ ደግሞ ሶሺዎሎጂ ትምህርት መከታተሉን ተያያዙት።
በሚያገኟት የተጣበበች ጊዜ ደግሞ የሂሳብ ሥራዎችን በመሥራት እራሳቸውን በገቢ ያጠናክሩ ነበር። የአካውንቲንግ ትምህርታቸውን አጠናቀው ከተመረቁ በኋላም የተለያዩ የሂሳብ ሥራዎችን መከወኑን አላስተጓጎሉም። የሶሲዎሎጂው የማታ ትምህርታቸው ሳይጠናቀቅ ደግሞ ትዳር ወደመያዙ ተሸጋገሩ። በዚህ ወቅት ታዲያ እስከመቼ የተለያዩ ሥራዎች እየሰራሁ እቆያለሁ የሚል እሳቤ ወደአዕምሯቸው ይመላለስ ነበርና፤ የእራሳቸውን ሥራ መጀመር እንዳለባቸው ይወስናሉ።
የሰርግ ድግስ እየተሰናዳ ባለበት ወቅት ጥቂት ወራት ብቻ ለጋብቻ ቀናቸው ሲቀር የሃገር ባህል ልብስ ቤት ለመክፈት ሱቅ ማፈላለጉን ተያያዙት። ሠርጋቸውን ከከወኑ በኋላ ደግሞ ከባለቤታቸው ጋር በመሆን አሮጌው ፖስታ ቤት አካባቢ በተከራዩት ሱቅ ውስጥ በ1996 ዓ.ም 10 ሺህ ብር በማይሞላ ገንዘብ የሀገር ባህል አልባሳትን መንገድ ጀመሩ።
በባለቤታቸው ስም «ውዳሴ» ብለው በሰየሙት ሱቅ ውስጥ አቶ ዳዊት እና አንድ ሠራተኛ ተቀጥሮ የተለያዩ የጥበብ ውጤቶችን ለገበያ ማቅረብ ተያያዙት። ይሁንና በሱቁ ውስጥ ያሉት ጥቂት አልባሳት የንግድ ቦታውን ባዶ ስላስመሰሉት አቶ ዳዊት አንድ መላ ዘየዱ። የተለያዩ ጥበብ አምራቾች በሱቁ ውስጥ አልባሳትን በማስቀመጥ ሲሸጥ ብቻ እንዲከፈላቸው የሚያደርግ አሠራር በመዘርጋት ሱቃቸውን በተለያዩ የባህል አልባሳት አደመቁት።
በዚህም ብቻ አላበቁ ሥራቸውን በቴክኖሎጂ የተደረገለማድረስ ድረ-ገጽ አስከፍተው ማስተዋወቅ ጀመሩ። በኦንላይን ለሚያገበያዩ የተለያዩ ተቋማት ድረ-ገጾች ላይ ምርቶቻቸውን በማስተዋወቅ በጥቂት ቀናት ሰፊ ገበያን ማግኘት ቻሉ። በዚህ ወቅት ታዲያ የተሻለ ገቢ በማግኘታቸው አቶ ዳዊት ከሱቃቸው አጠገብ ተጨማሪ ቅርንጫፍን ከፈቱ።
የሀገር ባህል አልባሳት ንግዱንም ከሃገር ውስጥ አልፈው ወደውጭ አገራት ጭምር ወደማቅረብም አሸጋገሩት። በተለይ እሥራኤል እና የተለያዩ አውሮፓ አገራት አልባሳትን ልከዋል። ንግዳቸው እየተስፋፋ ሲሄድም ሦስተኛ ሱቅ ከፍተው የተደራጀ ንግድ ባለቤት ሆኑ። የአልባሳት ትዕዛዝ በርከት በሚልበት ወቅት ደግሞ ሸማ አምራቾችን ጭምር በመቅጠር ወደማምረት ሥራውም ገብተው እንደነበር ያስታውሳሉ። በተለይ ሥራ በሚኖርበት ወቅት ከ50 በላይ አምራቾችን ቀጥረው የተለያዩ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ የጥበብ ውጤቶችን ያመርቱ ነበር።
የአልባሳት ንግዱ ላይ እያሉ ግን ወደሌላም ሙያ መሰማራት አለብኝ ብለው ይወስናሉ። እናም
አሮጌው ፖስታ ቤት አካባቢም አንድ ግቢ ውስጥ ውዳሴ ዲያግኖስቲክ የተሰኘ የህክምና ተቋም ከፈቱ። በአንድ መሣሪያ ብቻ የጀመሩት ሥራም ቀስ በቀስ እየተደራጀ ኤክስሬይ መመረመሪያ ማሽን እና ሲቲ እስካን ማሽኖችን በመጨመር ሰፊ የጤና ምርመራ የሚካሄድበት ማዕከል ለመሆን በቃ። በውዳሴ ዲያግኖስቲክ ማዕከል በአሁኑ ወቅተ 150 ሠራተኞች እና የተለያዩ ምርመራ የሚከናወንባቸው የህክምና መሣሪያዎች ይገኛሉ። የአንቡላንስ አገልግሎት የሚሰጡ እና ለተቋሙ ሥራ የሚያገለግሉ ተሽከርካሪዎችም በሥራ ላይ ናቸው።
አቶ ዳዊት ከጤና ተቋሙ ሥራ ጎን ለጎን ያስኬዱት የነበረውን የአልባሳት ምርት ንግድ በተለያዩ ምክንያቶች በማቋረጥ ወደህጻናት ጡጦ ምርት አስመጪነት ተሸጋግረው ነበር። በአልባሳት ሱቆች ውስጥም ከውጭ የሚመጡ የህጻናት መመገቢያ እቃዎችን ለዓመታት አቅርበዋል። ይሁንና አሁን ላይ በሀገር ውስጥ በሚዘጋጁ ምርቶች ገበያውን ለመቀላቀል ዝግጅት ላይ ናቸው።
በዘርፈ ብዙ ንግዶች ላይ መሰማራት የሚወዱት ዳዊት ከአንድ ዓመት በፊት ደግሞ አኮ ቡና የተሰኘ ድርጅት ከፍተዋል። ለዚህ መነሻ የሆናቸው ደግሞ የእናታቸው ታሪክ ነው። እናታቸው አኮ ይባላሉ። አኮ ማለት ደግሞ በኦሮምኛ ቋንቋ አያቴ ማለት ነው። እናታቸው ደግሞ 24 የልጅ ልጆች ያላቸው እና ቤተሰባቸውን መንከባከብ የሚወዱ ኢትዮጵያዊ ናቸው።
እናም እናታቸው ቤት ሲሄዱ መጀመሪያ የሚያገኙት አንድ መሶብ አለ፤ ሁልጊዜም ሙሉ የሆነ መሶብ። ማንኛውም ቤት የገባ ሰው ያንን መሶብ ከፍቶ
ጣዕም እና ጥራት ያለውን የተለያየ ምግብ ማጣጣም ደግሞ ይችላል። ይህን ታሪክ መነሾ አድርገው አቶ ዳዊት በጣዕሙ የተለየ እና ጥራቱን የጠበቀ የቡና እና የምግብ ምርቶችን ማዘጋጃት አላማው ያደረገ ተቋም ከፈቱ።
አቶ ዳዊትም «አኮ ቡና» የተሰኘውን ድርጅት ከጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ጀርባ በሚገኝ ቦታ ላይ መስርተው እየሰሩ ይገኛል። በአኮ ቡና ስር የታሸጉ የቡና ምርቶች እና የተለያዩ ምግቦች ተዘጋጅተው ይቀርባሉ። ለቡናው ምርት ደግሞ አቶ ዳዊት በምዕራብ ወለጋ አካባቢ ጊዳሜ በተባለ ቦታ ላይ የቡና እርሻ አላቸው። በቡና እርሻው ላይ ሰፊ ሥራ በሚኖርበት ወቅት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞችም ተቀጥረው የሚያመረቱበት ወቅት አለ።
ከእርሻው የሚመረተውን የአረቢካ ቡና አይነት ደግሞ ወደአዲስ አበባ አስመጥተው ለተጨማሪ አገልግሎት ያውሉታል። አቶ ዳዊት ለዚህ ሥራ ቡናን ቆልቶ እና አሽጎ የሚያቀርብ ፋብሪካ ሽሮሜዳ አካባቢ ገንብተዋል። ከግብርና ሥራ እስከ የፋብሪካ ሂዳት ያለፈውን የታሸገ ቡና ደግሞ ለገበያ ከማቅረብ ባለፈ በአኮ ቡና ስር ተፈልቶ ለገበያ ይቀርባል። በተጨማሪም የታሸጉ የአረቢካ ቡና ምርቶቹን ወደውጭ አገራት ለመላክ ዝግጅት በማድረግ ላይ ናቸው። ከዚህ ባለፈም የተለያዩ ጣዕም ያላቸው ምግቦች በአኮ ቡና መመገቢያ ውስጥ ለደንበኞች ያደርሳሉ። ለተለያዩ ድግሶች እና መርሃግብሮችም አገልግል ከሚሰኘው የምግብ አዘገጃጀት ጀምሮ እስከ ተለያዩ የምግብ አይነቶች እያቀረቡ ይገኛል። የካፌ እና ምግብ አገልግሎት የሚሰጠው የአኮ ቡና የጥቁር አንበሳ ጀርባ የንግድ ቦታ ሳምንቱን ሙሉ ለ24 ሰዓታት መስተንግዱ ይቀርብበታል።
አቶ ዳዊት አሁን ላይ የአኮ ቡናን የምግብ እና ቡና መስተንግዶ መስጫ ቅርንጫፎችን በተለያዩ አካባቢዎች ለመክፈት የቦታ መረጣ በማድረግ ላይ ናቸው። በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ በመሃል ፒያሳ አካባቢ ሁለተኛውን ቅርንጫፍ ለመክፈት ዝግጅት ጨርሰዋል። በተመሳሳይ መልኩ ደግሞ በክልል ከተሞች ላይ ድርጅቱን ለማስፋፋት ውስጥ ይዘው እየሰሩ እንደሚገኝ ይናገራሉ። በአሁኑ ወቅት ስድስት ተሽከርካሪዎችን ጥቅም ላይ እያዋለ በሚገኘው የአኮ ቡና ድርጅት ውስጥ ከእርሻ ሠራተኞች ውጭ ሰላሳ ሠራተኞች ተቀጥረው በመስራት ላይ ናቸው።
ሌላኛው የአቶ ዳዊት የሥራ ዘርፍ የተመሰረተው ደግሞ በትምህርት መስክ ነው። በኦሮሚያ ክልል ቢሾፍቱ ከተማ ላይ በመንግሥት ፍቃድ የተሰጠው ትምህርት ቤት ከፍተው እየሰሩ ይገኛል። ጆርጎ አካዳሚ ተብሎ በተሰየመው ተቋም ውስጥ ደግሞ ከቤተመጽሐፍት ጀምሮ ለመማር ማስተማር የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን አሟልተው እስከ ስምንተኛ ክፍል ድረስ ትምህርት ይሰጡበታል። በአካዳሚ ውስጥ በአሁኑ ወቅት ምንም እንኳን በኮሮና ምክንያት ትምህርት ቢቋረጥም ስምንት መቶ ተማሪዎች በየዕለቱ ይስተናገዱ እንደነበር አቶ ዳዊት ያስታውሳሉ። በአጠቃላይም በቢሾፍቱው አካዳሚ ስር መምህራንን ጨምሮ አንድ መቶ ሠራተኞች ይገኛሉ።
በተለያዩ የጤና፣ ትምህርት እና ምግብ ዘርፎች ላይ በተመሰረተው የአቶ ዳዊት የንግድ ድርጅቶች ስር በአጠቃላይ ሦስት መቶ ሠራተኞች ተቀጥረው እየሰሩ ይገኛል። የአምስት ልጆች አባት የሆኑት የ43 ዓመቱ አቶ ዳዊት በቀጣይ ደግሞ የኮሮና በሽታ በቁጥጥር ስር ሲውል እና የቡና ምርታቸው ወጪ ንግድ ስራዎች ሲጠናከር ለተጨማሪ ሰዎች የሥራ ዕድል በመፍጠር ድርጅታቸውን ለማስፋፋት ውጥን ይዘዋል።
ሥራ በጥራት እና በዕውነተኛ ማንነት ላይ የተመሰረተ ከሆነ ውጤታማ ያደርጋል የሚል እምነት ያላቸው አቶ ዳዊት፤ ማንኛውም ወጣት በሚችለው ሙያ ተሰማርቶ ጥራት እና ጥንካሬን ካከለበት ውጤታማ የማይሆንበት ምክንያት እንደሌለ ይናገራሉ። ስንፍናን አብዝቶ ምክንያት እየቆጠሩ መቀመጥ ግን እራስንም ብቻ ሳይሆን አገርንም መግደል ነውና ወጣቱ ትውልድ ነገውን ብሩህ ለማድረግ ከአሁኑ ለሥራ ሊነሳ ይገባል፡፡ የሚለው ደግሞ ምክራቸው ነው።
አዲስ ዘመን ግንቦት 1/2012
ጌትነት ተስፋማርያም
ዘርፈ ብዙው የንግድ ሰው