አሻም አዲስ ዘመኖች
አሻም የአዲስ ዘመን ቤተሰቦች? ባላችሁበት ሰላምና ጤና አይለያችሁ።
ዛሬ የሁላችን ጉዳይ ስለሆነው ስለ ዓባይ ላወራችሁ ነው አመጣጤ። መልካም ንባብ!
የዓለማችን ረጅሙ ወንዝ የሆነው ዓባያችን ለዘመናት በታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት በሆኑት ኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳን መካከል ያመረቀዘው ቁርሾ ዋነኛ ማጠንጠኛ ሆኖ ሰንብቷል። እነዚህ የዓባይ ሀገራት ይህንኑ ቀውስ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለመፍታት በየጊዜው የሚያካሄዱት ድርድር አንዴ ሞቅ ሌላ ጊዜ ደግሞ ጋብ እያለ ዛሬ ላይ ደርሷል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በልዕለ ኃያሏ አሜሪካ “አሸማጋይነት” የተጀመረው ድርድር ገና ከጅምሩ ተንገራግጮ ሳለ እንኳ የዚህ ወንዝ ጉዳይ የቀጠናውን ፖለቲካ ማጨቅየቱን አላቆመም።
ይኸው የምድራችን አንጋፋ ወንዝ የሶስቱ ሀገራት ዘርፈብዙ ግጭት ዋና መነሻ የመሆኑን ያክል እርስ በርሳቸው እንዲጋጩም ጭምር ሲያደርግ ቆይቷል። ከፍ ሲል ለማንሳት እንደተሞከረው ከወራት በፊት በዋሽንግተን “አደራዳሪነት” የተጀመረው መድረክ ተቋርጦ ሳለም ለአፍታ እንኳ ቆሞ የማያውቀው የሶስቱም ሀገራት የእለት ተእለት ህልውና የተመሰረተው በዚሁ የወንዞች ሁሉ ንጉሥ በሆነው ዓባያችን ላይ ነው።
ጉዳዩን ካባባሱት ነገሮች ዋነኛው ሶስቱም ሀገራት ዘንዳ የሚስተዋለው “የውኃው ትልቁ ድርሻ የኔ ነው” የሚለው ስር የሰደደው እምነት እና ትርክት ነው። ግብፅ በበኩሏ በናይል ላይ ታሪካዊ የባለቤትነት መብት እንዳላት እና ትልቁ ድርሻ እንደሚገባት ስትገልጽ ኢትዮጵያ ደግሞ የናይል ገባር ወንዞች መፍለቂያ እንዲሁ የራሱ የግዮንም ምንጭ እና ሰማንያ አምስት በመቶ የሚሆነውን ዉኃ የማመነጨው እኔ ስለሆንኩ የወንዙ ተፈጥሯዊ ባለቤት ነኝ ባይ ናት። በሌላ በኩል ሱዳን ደግሞ በእኔስ ከማን አንሼነት በሁለቱ ተፎካካሪ የአባይ ልጆች መካከል ባላት ስትራቴጂካዊ አቀማመጥ የውኃው እኩል ባለቤትነት መብት እንዳላት ትከራከራለች።
በእነዚህ የታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊ እና ጂኦ-ስትራተጂካዊ መከራከሪያ ሃሳቦች የጦዘው የሶስቱ ጎረቤት ሀገራትን ግንኙነት ይባሱኑ በቅኝ አገዛዝ ዘመናት የተደረጉ አድሎአዊ ስምምነቶች ደግሞ ቀውሱን ይበልጥ አባብሰውታል። እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር በ1929 ዓ.ም በወቅቱ ቅኝ ገዢዋ ብሪታንያ እና በግብፅ መካከል የተደረገው ስምምነት ግብፅን የናይል ወንዝ ፍፁም ሉዓላዊ የባለቤትነት ስልጣን የሰጠ እና የዉኃውን የፍሰት መጠን የሚነካ በማንኛውም የላይኛው ተፋሰስ ሀገራት የሚከናወን የውሃ ላይ የግንባታ ፕሮጀክት የመቆጣጠር ስልጣንም ጭምር ያጎናፀፋት ነበር። ከሠላሳ ዓመታት በኋላ በ1959 ዓ.ም ደግሞ ሌላ የስምምነት ውል የተፈረመ ሲሆን በዚህኛው ጊዜ ደግሞ በሱዳንና በግብፅ መካከል ብቻ የተደረገ እና ከአጠቃላይ የውኃው ፍሰት ሶስት አራተኛ የሚሆነውን ድርሻ ለግብፅ ቀሪውን አንድ አራተኛ ደግሞ ለሱዳን የሰጠ ስምምነት ነበር። ይህም ግብፅ ለኤሌክትሪክ ፍጆታዋ እና ለመስኖ ልማት አገልግሎቷ እንዲውል በናይል ወንዝ ላይ የአስዋን ግድብን እንድትገነባ ያስቻላት ክስተት ነበር። ነገር ግን በኢትዮጵያ የሚመራው የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት ይህን ስምምነት ያወገዙና ሀገራቱ ከቅኝ አገዛዝ ስር በወደቁበት ወቅት ተገደው የፈረሙት በመሆኑ የግል ጥቅማቸውን እና መብቶቻቸውን ወደ መድረክ ለማምጣት ቅቡልነቱንም እድሉንም የነፈጋቸው መሆኑን በመከራከሪያነት ያነሳሉ።
ፕሬዚዳንት ትራምፕ የኢትዮ-ግብፅን ውዝግብ ይፈቱ ይሆን? እኔንጃ! ቀድሞውኑ ለአንድ ወገን በቻ በማዳላት የቆመው የትራምፕ አስተዳደር ሁለቱን አፍሪካውያን የአባይ ልጆችን ጥም የሚያረካ ፖለቲካዊ እልባት መስጠት እንደማይችል አለምአቀፍ የዲፕሎማሲ ምሁራን ይመሰክራሉ።
እ.ኤ.አ. በየካቲት ወር መጀመሪያ ላይ ከግብጽ ፣ ከኢትዮጵያ እና ከሱዳን የተውጣጡ ባለስልጣናት በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የኢትዮጵያ መንግስት በአባይ ወንዝ ላይ እየገነባው የሚገኘውን ታላቁ የህዳሴ ግድብን አሞላልና አሰራር በተመለከተ መንገዱን እንዳጸዱ እና መግባባት ላይ መደረሳቸውን በጋራ አስታውቀዋል። የአሜሪካ መራሹን ድርድር ተከትሎ ከወራት በኋላ የመጣው ይህ የጋራ መግለጫ ሦስቱ የሰሜን ምስራቅ አፍሪቃ አገራት በስተመጨረሻም በዚህ ባለብዙ ቢሊዮን
ዶላር ፕሮጀክት ላይ ስምምነት ላይ መድረስ እንደሚችሉ ብዙዎችን እንዲያምኑ ማድረግ የቻለ ክስተት ነበር ማለት ይቻላል።
ይሁንና ይህ እንደ መልካም ጅማሮ የታየው ክስተት ብዙም ሳይቆይ እዚህ ሀገር ቤት ላለን ኢትዮጵያውን ዘንድ ግን መጠነ ሰፊ ጥርጣሬ እና እልህን የቀሰቀሰ ክስተት ከመሆኑም አልፎ በተለይም የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ልዑካን ቡድን የአገሪቱን ጥቅም የሚጻረር ስምምነት እንዲፈርም በአሜሪካ መንግስት ግፊት እየተደረገበት የመሆኑን ዜና ስንሰማ ከፍተኛ ስጋት አሳድሮብናል። በዚህ የተነሳም የካቲት 18 ቀን 2012 ዓም የኢትዮጵያ መንግስት የሚቀጥለውን ዙር የዋሽንግተን ስብሰባ ላይ ልዑካኑ እንደማይገኝ አስታውቋል።
ምንም እንኳን ኢትዮጵያ ከድርድሩ ያገለለች መሆኗን ያሳወቀች ቢሆንም አደራዳሪዋ አሜሪካ ግን እኔ ያልኩት ለምን ይቀራል በሚያሰኝ መልኩ ከሱዳን እና ከግብፅ ልዑካን ጋር ውይይቱ እንዲቀጥል በማድረግ ሦስቱም ሀገራት እንዲፈርሙ የሚያስችል ረቂቅ ስምምነት ኢትዮጵያ በሌለችበት አቀረበች። ይባስ ብሎም በድርድሩ ላይ የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዋና ሰው ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩት የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስትር እስቲቨን ማኑቺን በሶስት ጉዳዮች ላይ የኢትዮጵያን እጅ ለመጠምዘዝ የሚያስችለውን መግለጫ ይፋ ያደረገ ሲሆን እነዚህ ሶስቱ እጅ መጠምዘዣ ቅርቃሮችም “ኢትዮጵያ ወደ ድርድሩ ከተመለሰች በኋላ ረቂቁ ስምምነቱን መፈረም፣ ስምምነቱን ከመፈረሟ በፊት ደግሞ ምንም አይነት የግድቡ የሙሊትም ሆነ የሙከራ እንቅስቃሴ እንደማታደርግ እና ስምምነቱን ከመፈረምዋ በፊት ግድቡን “መሙላት ከመጀመሯ በፊት በዓለም አቀፍ ደረጃዎች መሠረት ሁሉንም አስፈላጊ የደህንነት መስፈርቶች የመተግበር” አስፈላጊነት እውቅና የምትሰጥ መሆኑን የሚያስገድዱ ናቸው። በምላሹም ኢትዮጵያ የአሜሪካ አካሄድ “ኢ-ዲፕሎማሲያዊ” ነው በማለት የከሰሰች ሲሆን የግድቡም ባለቤት እንደመሆኗ መጠን “ፍትሃዊ እና ምክንያታዊ አጠቃቀም መርሆዎች እና ትልቅ ጉዳት የማያስከትሉ ጉዳዮችን” ታሳቢ ባደረገ አሰራር መሰረት ግድቡን የመሙላት ስራ ባስቀመጠችው የጊዜ ገደብ እንደምታስጀምር ይፋ አድርጋለች።
ሁሉም አካላት አሁንም ድርድሩን ለማስቀጠል
ፈቃደኞች እንደሆኑ ቢናገሩም፣ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ተብሎ የሚጠራው የዚህ የአስር ዓመት ፕሮጀክት ዕጣ ፈንታ ገና ያልተወሰነ ይመስላል ።
የግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት እ.ኤ.አ. ከ2011 ዓም አንስቶ ግዙፉን የግድቡን የውሃ ማጠራቀሚያ ሃይቅ እጅግ ባጠረ ጊዜ መሙላት የአባይ ወንዝን ፍሰት ሊቀንስ እና የግብፅ የውሃ አቅርቦት ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል በሚል ግብጻውያን ዘንድ የተቀሰቀሰው ፍርሃት አዲስ አበባ እና ካይሮ በአይነ ቁራኛ እንዲተያዩ አድርጓል። ግብፅ በግድቡ ላይ ወታደራዊ እርምጃ እስከመውሰድ እንደምትሄድ ዛቻ እና ማስፈራሪያ ባሳየችባቸው ዓመታት ሁሉ ሂደቱ ላይ ብጥብጥ ለመቀሰቀስ ሙከራዎችን ብታደርግም ኢትዮጵያ ይህንን ሰፊ የልማት ሥራ ለመተው ፈቃደኛ ባለመሆኗ ለዓመታት ተገዳ ወደ ድርድር ለመምጣት ችላለች።
ነገር ግን ይህ የኢትዮጵያ አቋምና ወሳኝነት በ2010 ዓም የግብፅ ፕሬዚዳንት አብደል ፋታህ ኤል-ሲሲ ለዓጋራቸው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የድረሱልኝ ጥያቄ በሀገሪቱ የገንዘብ ሚኒስቴር አማካኝነት ካቀረቡ በኋላ ተቀየረ። አሜሪካም የሃይል አሰላለፏን በመሰረታዊነት ቀየረች። ይኸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ውዝግቡን ለመፍታት ባደረገው ጥረት ገለልተኛ እና ሐቀኛ አደራዳሪ ከመሆን ይልቅ ኢትዮጵያን ወደ ጎን በመተው የካይሮ ጥቅም ተወካይ ሆኖ ለመገኘት መረጠ። በእርግጥ ይህን መሰሉ አቋም የፕሬዚዳንት ትራምፕ አስተዳደር በመካከለኛው ምስራቅ የሚከተላቸውን ፖሊሲዎች እና የሚፈጥራቸውን አጋርነቶች በትኩረት ለሚከታተል ለማንኛውም ሰው እምብዛም የሚገርም አይደለም።
ከአሜሪካ እና ከእስራኤል ጋር ጥብቅ ስትራቴጂካዊ ወዳጅነት የመሰረተችው ግብፅ ዛሬ በመካከለኛው ምስራቅ በሳዑዲ የሚመራው የፀረ-ኢራን ቡድን ዋና አባል ናት። ምንም እንኳን ኢትዮጵያም የዩናይትድ ስቴትስ አጋር ብትሆንም ለዋሽንግተን ግን የግብፅን ያህል ሚዛን አታነሳም። ፕሬዚዳንት ትራምፕ ስልጣን ከተረከበበት ጊዜ አንስቶ የራሱን ጥቅም ለማስቀጠል ሲል አንደኛውን አጋር ከሌላኛው አጋር ጭምር በማበላለጥ እና አንዳንዴም በማጋጨት ያለውን ፍላጎት በግልጽ ደጋግሞ ሲያሳይ ነበር። ለምሳሌ ያክል የዛሬ ሶስት ዓመታት ገደማ በተፈጠረው የገልፍ ሀገራት ውዝግብ ወቅት ለሳኡዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ወግነው ኳታርን ደግሞ በመፃረር ምንም እንኳ ዶሃም የረጅም ጊዜ የአሜሪካን አጋር እንዲሁም በባህረሰላጤው ትልቁን የዩኤስ የጦር ሰፈር የምታስተናግድ ሀገር ብትሆንም በሚስተር ትራምፕ የውጭ ፖሊሲ አጀንዳ ውስጥ ኢትዮጵያ ከግብፅ በጣም ያነሰ ቦታ እንዳላት ለሚገነዘብ ሰው ዋሽንግተን በታላቁ የህዳሴ ግድብ ዙሪያ የምታደርገው ጣልቃ ገብነት ካይሮን በግብታዊነት ለመጥቀም እንደሆነ ገና ከመጀመሪያው ግልፅ ነበር።
አሁን ኢትዮጵያ እራሷን ያገኘችበት የድንጋይ አለት መነሻው አዲስ አበባ ይህን ጂኦፖለቲካዊ እውነታ ለመገንዘብ ካለመቻሏ ወይም ካለመፈለጓ የመነጨ ነው ማለት ይቻላል። ታዲያ የኢትዮጵያ መንግሥት ቀድሞውኑ ከርሱ በተቃራኒ የቆመና በግልፅ የሚያወግዘውን አስተዳደር ድርድሩን እንዲመራ ለምን ፈቀደ?
ግብፅ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ የቀጠናው እና የዓለም ኃያል መንግስታት ተሳትፎ እንዲረጋገጥ ማረጋገጥ ኢትዮጵያ የፈለገችውን ግድቡን የመሙላት እና የመቆጣጠር አቅሟን ይገድባል በሚል እምነት ይህንን ክርክር በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማቅረብ ጥረት ስታደርግ ቆይታለች። በዚህ ረገድ በከፊልም ቢሆን ተሳክቶላታል ማለት ይቻላል። በተለይ በርካታ አገራት በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድርድር ለመሳተፍ ያላቸውን ፍላጎት ከመግለፃቸው ጋር ተያይዞ ደግሞም ፣ ከግብፅ ጥረት ባሻገር ፣እንደ አውሮፓ ህብረት፣ ቱርክ ፣ እስራኤል እና የባህረ ሰላጤ ሀገራት ያሉ ብዙ አካባቢያዊ እና ዓለም አቀፋዊ መንግስታት ድርድሩን በቅርበት ለመከታተል ፍላጎት እንደነበራቸው ግልጽ ነው። ሁሉም ለረጅም ጊዜ በቀጠናው ካላቸው የጂኦስትራቴጂያዊ ፍላጎቶች አንፃር ይህን አይነት አቋም እንደሚኖራቸው ቀድሞውኑ የሚጠበቅ ነበር። የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን እንኳን በቅርቡ እኔ ልሸምግላችሁ አይነት የጋብዙኝ ጥሪ አቅርበዋል ።
ሃያሏ አሜሪካ ሰብራ ወደ መድረኩ እስከመጣችበት እለት ድረስ ኢትዮጵያ ማንኛውንም የውጭ ኃይል በድርድሩ ቀጥተኛ ሚና እንዳይኖረው ለማድረግ በተሳካ ሁኔታ ችላለች። ለምሳሌ፣ የፕሬዚዳንት ፑቲንን
የ“ላሸማግላችሁ” ጥያቄ ውድቅ አድርጋለች ።
ሆኖም የ “እናሸማግላችሁ” ጥያቄው ከወደ ትራምፕ አስተዳደር ሲመጣ ግን የኢትዮጵያን መንግስት እንደ ፑቲን ኬሬዳሽ ማለት አልተቻለውም፣ ምናልባትም በምዕራባውያን ወዳጆች ምፅዋት ላይ ከመጠን በላይ ጥገኛ በመሆኗ ምክንያት ኢትዮጵያ መንግስት አካሄዷን ለመቀየር ተገደደች።
በዚህ አሰቃቂ የፍርድ ሂደት ምክንያት በአንድ ወቅት በኢትዮጵያ እና በግብፅ-ሱዳን መካከል የነበረው ድርድር ድንገት ወደ ኢትዮጵያ እና ግብፅ-አሜሪካ መካከል ወደ ሚደረግ ድርድር የተለወጠ ሲሆን ሱዳን ደግሞ የታዛቢነት እና የአማካይነት ሚና የወሰደችበት ነበር።
ዋሽንግተን ካላት ዓለም አቀፋዊ ተደራሽነት እና ኃያልነት አኳያ ይህ ለአዲስ አበባ ምቾት የማይሰጥ እና የማትዘልቀው ሁኔታ ነው። የኢትዮጵያ መንግስት ከዚህ ድንገተኛ አደጋ ለመውጣት ብቸኛው መንገድ ትርክቱን እንደገና መለወጥ፣ ምዕራባዊያንን ለማስደሰት ብሎ አቋሙን አለማጠፍ እና ይልቁንም የህዝቦቹን ምኞትና ፍላጎት ማዳመጥ ነው አዋጩ መንገድ። ኢትዮጵያውያን ከዋይት ሃውሱ መድረክ ማግስት የገንዘብ ሚኒስትሩን ሚኑኪን መግለጫዎችን በፅኑ በመቃወም እና የናይል ውሀን ፍትሃዊ መጋራት በመደገፍ እራሳቸውን ወደ አንድ የጋራ ጥላ እያሰባሰቡ ይገኛሉ። የኢትዮጵያ መንግስት የሚንኪን እቅድን ውድቅ ለማድረግ እና በድርድሩ ውስጥ እንደ የበላይ ድርሻ እንዳለው ወገን ራሱን ለማቋቋም ይህንን ጠንካራ የህዝብ ምላሽ ለዚሁ መጠቀም ይኖርበታል። እንዲህ ዓይነቱ አቋም ለአሁኑ አመራር የህዝብ ድጋፉን ከፍ እንዲል የሚያስችለው እና የታቀዱት የድርድር አማራጮችም በሚከናወኑበት ጊዜ ወደኋላ እንዳይመለስ ሊያደርገው የሚያስችል እምቅ አቅም ነው።
ይህ ማለት ግን ኢትዮጵያ ከማናቸውም የሶስተኛ ወገን አደራዳሪዎች ጋር በታላቁ የህዳሴ ግድብ ድርድር ላይ እንዲያሸማግሏት መፍቀድ የለባትም ማለት አይደለም። ሐቀኛ እና ገለልተኛ አደራዳሪዎችን ማሳተፍ ሁሉም ተደራዳሪ አካላት መሰረታዊ ጥቅሞቻቸው ተጠብቆላቸው ለረጅም ጊዜ የቆየውን ይህን ክርክር በሰላማዊ መንገድ እና በፍጥነት ለመፍታት ያስችላል።
የናይል ክርክር በመርህ ደረጃ ኢትዮጵያን፣ ግብፅን እና ሱዳንን ብቻ ሳይሆን የተቀሩትን አህጉራትም ጭምር የሚነካ ፓና አፍሪካዊ ችግር ነው። አሥራ አንድ የተፋሰሱ አፍሪቃ አገራት በአባይ ወንዝ ላይ የተመሰረቱ ናቸው። እናም የድርድሩ ውጤት ለሌሎች የወንዝ ተፋሰሶችም አንድምታ ይኖረዋል። በዚህ ምክንያት የአፍሪካ ህብረት በዚህ ጉዳይ እልባት ላይ ቁልፍ ሚና ሊጫወት ይገባል።
የአፍሪካ ህብረት በጉዳዩ ላይ በንቃት በመሳተፍ በሁሉም የናይል ተፋሰስ አገራት መካከል ምክክሮችን መጀመር እና ሁሉንም ወገን የማቀራረብ ስራ ሊሰራ ይችላል። እንዲሁም የማንኛውንም ተደራዳሪ ወገን ጥቅም ሳይጎዱ ባላቸው የማደራደር ብቃት ይህንን ችግር ለመፍታት ድርሻ ያላቸው ሁሉም ዓለም አቀፍ ተጫዋቾችን ማማከር ይችላል። በዚህ ረገድ አንዳንድ እንቅስቃሴዎች ቀድሞውኑ የተጀመሩና መስመር ውስጥ የገቡ ሊሆኑ ይችላሉ። እ.ኤ.አ. በየካቲት ወር መጀመሪያ ላይ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ በበኩላቸው “እኛ በአፍሪካ ኅብረት በሱዳን ፣ በኢትዮጵያ እና በግብፅ የሚገኙ ወንድሞቻችን በዚህ ጉዳይ ላይ ሁሉንም የሚያቻችል እና እኩል ተጠቃሚነታቸውን የሚያረጋግጥ አሰራር እንዲኖር እንፈልጋለን” ብለዋል። እውነት ነው፤ የአፍሪካ ህብረት ተሞክሮ እንደሚያሳየን ከሆነ፣ ብዙዎቹ አባል ሀገራት በህብረቱ መዝገብ ባልተፈቱ ውዝግቦች የተሸነፉ መሆናቸው ታሳቢ ተደርጎ፣ በአሁኑ ወቅት ዋናዎቹ የዓለም እና የአፍሪካ ኃያላን ኃይሎች ጠንካራ ፍላጎት ያላቸውን ይህን ጉዳይ የአፍሪካ ህብረት ብቻውን ሆኖ ለመፍታት የሚያስችል ብቃት አለው ብሎ ለመናገር የማያስደፍር መሆኑ አይካድም። ሆኖም፣ በድርድሩ ውስጥ የበለጠ ንቁ ሚና የሚወስድ ከነበረው፣ የትራምፕ አስተዳደርን የእጃዙር የቅኝግዢ አካሄድ ለማቃለል እና ማንኛውንም ተደራዳሪ ወገን ህዝቡ የማይደግፈውን ስምምነት በእነዚህ አደራዳሪ ነን ባይ ተደራዳሪዎች ተገፍቶ እንዳይገባበት ሊረዳ ይችላል።
ቸር ያቆየን!
(በዚህ ፅሁፍ የዶክተር መሃሪ ታደሌ ማሩ የሰላምና ደህንነት ፣ የሕግ እና የአስተዳደር እንዲሁም የሰብአዊ መብቶች እና የስደት ጉዳዮች ምሁር ሃሳቦችን ተጠቅሜያለሁ።)
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 30/2012
በሐሚልተን አብዱልአዚዝ