አዲስ አበባ፡- ባለ አንድ ገጹና ከህዳር ወር ጀምሮ ስራ ላይ የዋለው የመቶ ቀን እቅድ ዋና ትኩረቱ የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ መሆኑን የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ አስታወቀ፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ የኮሙኒኬሽንና የህዝብ ግንኙነት ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ዝናቡ ቱኑ ትናንት ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፤ የእቅዱ ቁልፍ ጉዳይ የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ ሲሆን፣ የፍትህ ሥርዓት ግንባታ፣ የፍትህ አገልግሎት አሰጣጥ፣ የሰው ሀብትና ተቋም ግንባታም ከዚሁ እቅድ ውስጥ የሚካተቱ ናቸው፡፡
እንደ አቶ ዝናቡ ገለጻ፣ የእቅዱ መነሻ ሃሳብ የሆነው በህግና ፍትህ ሥርዓቱ ደካማነት ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በመከተሉና ህዝቡ በመንግስትና በፍትህ ሥርዓቱ አመኔታ ማጣቱ ተጠቃሽ ነው፡፡ በተጨማሪም የተንዛዛና ምልልስ የበዛበት እንዲሁም ፍትሃዊነት የጎደለው የፍትህ አገልግሎቱም ሌላው ጉዳይ ሆኗል፡፡ ሙያዊ ብቃትና ስነ ምግባር የጎደለው አመራርና የሰው ኃይል እንዲሁም ጠንካራ የዓቃቤ ህግ ተቋም በአገር ደረጃ አለመኖር ነው፡፡
በህግና ፍትህ ስራ ማሻሻያ ባለፉት ስድስት ወራት ተስፋ ሰጪ ጅምር መስተዋሉን የተናገሩት ዳይሬክተሩ፣ በቀጣይም የታራሚዎች ሰብዓዊ መብት እንዲጠበቅ የሚደረግ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ በአገሪቱም እየታየ ያለው የጸጥታ ችግር ላይ የሚሰራ ሲሆን፣ በተለያዩ አካባቢዎች ከሚሰጠውም የመንጋ ፍትህ ለመውጣት ስራ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ከወንጀል ድርጊት ጋር በተያያዘ በአሁኑ ወቅት የተጀመረውን ስራ አፋጣኝ ፍትህ በመስጠት ህዝቡ እንዲያምን የሚደረግ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
ከሙስና ጋር በተያያዘ በሜቴክ ላይ ብቻ ሳይሆን በቅርቡ ከሜጋ ፕሮጀክቶች ጋር ተያይዞ ሌሎችም ምርመራ እየተደረገባቸው በመሆኑ የህዝብና የመንግስትን ሀብት የመዘበሩ የሚጋለጡ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ህገ ወጥ የሰዎች፣ የገንዘብና የመሳሪያ ዝውውርንም በተመለከተ ህጉን የተላለፉትን ወደ ህግ የማቅረቡ ስራ ይሰራል፡፡ ለውጡንም ለማደናቀፍ ጥረት የሚያደርጉትን አካላትም ወደ ህግ ለማምጣት የሚሰራው ግብረ ኃይል የምርመራ ሂደቱን በማጠናቀቅ ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የተለያዩ አዋጆች እየተሻሻሉና እየተጠኑ ሲሆን፣ ይህ መቶ ቀን ሳያልቅ በአጭር ጊዜ ውስጥም ይጠናቀቃሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በተለይ የምርጫ ህጉ በተፋጠነ ሁኔታ የሚጠናቀቅ ሲሆን፣የጦር መሳሪያ አስተዳደር አዋጅ እንዲሁም የኃይል አጠቃቀም አዋጅም እየተጠናቀቀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የሰብዓዊ መብት አያያዝን የተመለከተም አዲስ አሰራር ለመተግበር ታቅዷል፡፡
እርሳቸው እንዳሉት፤ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የተቀናጀ የፍትህ ሥርዓት መረጃ ስለሚያስፈልግ ፕሮጀክት ተቀርጾ እየተሰራ ነው፡፡ ይህም ከፌዴራል እስከ ቀበሌ ድረስ የሚያስተዳድር ሥርዓትን የሚይዝ ነው፡፡
ምርመራ የሚደረግባቸው ሜጋ ፕሮጀክቶች የትኞቹ ናቸው? በቅርቡ የተላለፈው ዘጋቢ ፊልም በዳኞች ላይ ተጽዕኖ አይፈጥርም ወይ? ከፍትህ ጋር ተያይዞ በትግራይ ክልል የተሰጠው ሰሞነኛ መግለጫ ተገቢነት ያለው ነው ወይ? የሚሉና የተለያዩ ጥያቄዎች ከጋዜጠኞች ተነስተዋል፡፡
ዳይሬክተሩ በሰጡት ምላሽ፤ በአሁኑ ወቅት ሜጋ ፕሮጀክቶቹ እነዚህ ናቸው ተብሎ የሚሰጥ መረጃ አይኖርም፡፡ ዘጋቢ ፊልሙ ከምርመራ መዝገቡ የተለየ አይደለም፡፡ የምርመራ መዝገቡ ወደ ፍርድ ቤት የሄደው ደግሞ በደንብ ከተደራጀ በኋላ ነው፡፡ በመሆኑም ዳኛውንም ሆነ ህዝቡን አያወናብድም፡፡ ከክልሉ ጋር ተያይዞ ለተነሳው ጥያቄ ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ምላሽ የሚሰጠው አይደለም፡፡
አስቴር ኤልያስ