በሽታም የማፈናቀልና የማሳደድ፤ የማስጋትና መበተን አቅሙን ያሳድጋል ጃል፤ ድሮ ድሮ ወረርሽኝ ሲከሰት ቸነፈር አገር ሲመታ አኮፋዳውን ጠቅሎ ቅሉን አንጠልጥሎ የመጀመሪያው ተበታኝ የቆሎ ተማሪ ነበር፤ ለዚህም ተስቦና ሌሎች ተዛምተው የነበሩ ተቀጣጣይና ተላላፊ ገዳይ በሽታዎች ምሥክሮቼ ናቸው።አሁን እኛ በዘመናችን እንሆ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎቻችን በወረርሽኝ ሥጋት ምክንያት ወደየመጡበት ሲበተኑ ዓየን።መቼስ ይሁን፤ በዚህ ይማርና!
አንድ መርከብ ውስጥ ነው አሉ፡- በመርከቧ ውስጥ አንድ ክፍል ለተከራዬ ፕሮፌሰር አንድ አስተናጋጅ ይቀጠርለታል።ታዲያ አስተናጋጁ ሻይና ቡና እንዲሁም ሌሎች ነገሮችን ለፕሮፌሰሩ ባደረሰ ቁጥር ፕሮፌሰሩ አስተናጋጁን አንድ ጥያቄ ይጠይቀዋል “ሥነ ሕዋ አጥንተሃል?” አይ አላጠናሁም ፕሮፌሰር፤ መልስ ካስተናጋጅ።የህይወትህን ሩብ አጥተኽዋላ ታዲያ- ፕሮፌሰሩ።
ሌላ ቀን አስተናጋጁ የተለመደ ተግባሩን ሊያከናውን ወደ ፕሮፌሰሩ ክፍል ገብቶ ሲወጣ አሁንም ፕሮፌሰር ጥያቄ ጠየቁት፡- “ሥነምድር አጥንተሃል?”
አስተናጋጅ፡- ኧረ በምን ዕድሌ ፕሮፌሰር፤
ፕሮፌሰር፡- ሥነሕዋም ካላጠናህ ሥነምድርም ካላጠናህማ ግማሹን የህይወት ክፍልህን እንደተነጠቅህ ቁጠረው፡፡
አሁንም ሌላ ቀን
ፕሮፌሰር፡- አስተናጋጅ፣ ሥነሕይወት አጥንተሃል?
አስተናጋጅ፡- አላጠናሁም ፕሮፌሰር
ፕሮፌሰር፡- የሕይወትህን እሩብ ጉዳይ አጥተሃል፡፡
በማግሥቱ አስተናጋጅ የተለመደ ሥራውን ለማከናወን ወደ ፕሮፌሰሩ ቢሮ ሲያመራ መርከቧ በማዕበል መናጥ ጀመረች፤ ያኔ ጠያቂው
አስተናጋጁ ነበረ።“ፕሮፌሰር፣ ሥነ ዋና (ስዊሞሎጂ) አጥንተዋል?”
ፕሮፌሰር፡- እንደሱ የሚባል ሳይንስ አለ? ኧረ አላጠናሁም አስተናጋጅ፡፡
አስተናጋጅ፡- ማእብለ መረከቧን እየናጣት ነው፤ ዋና ካልቻልክ ሙሉ ሕይወትህን አጥተሃል።አለው ይባላል፡፡
በኛ ወግ እንቀይረው እስኪ፤ እርስዎ አካላዊ ርቀት መፈፀም ይችላሉ? ካልቻሉ … ሕይወትዎን አጥተዋል ማለት ነው።እጅዎን በተደጋጋሚና በአግባቡ እየታጠቡ ነው? እያደረጉ ካልሆነ … ሕይወትዎ ለሞት ተጋልጧል ማለት ነው።ምክንያቱስ? ምክንያቱም ያው እንደሚያውቁት መርከቧ በኮቪድ 19 ማእበል እየተናጠች ነውና፡፡
ግን አንዳንድ ወረርሽኝ ብዙ ሕይወት የሚቀጥፈውንና አገርን በክርኑ አቅም እስክታጣ የሚደቁሰውን ያህል ብዙ አስተምሮ ያልፋል።በበኩሌ እኛ ሰዎች ምን ያህል ግብዞች እንደሆን የታዘብኩበት አጋጣሚ ነው። ተው እንጂ ጎበዝ፤ መከላከያው ሩቅ ቢሆን ምን ሊውጠን ነው? በእጃችን እያለ እንደዚህ ከሆን።ቆይ እስኪ ከበሽታ ጋር ለዚያውም ከብርሐን ፍጥነት በእጥፍ የመሰራጨት አቅሙን ካሳየ ወረርሽኝ ጋር ምን የሚሉት ትክሻ መለካካት ነው?
በእኔ እምነት ከኮቪድ 19 በፊት ለዚህኛው ትምክህታችን መድኃኒት ቢገኝለት መልካም ነው ባይ ነኝ።የመቀመጫ ቤት መኖር አለመኖሩ እንዳለ ሆኖ እቤትህ ተቀመጥ – እንቢ፤ ታጠብ – እንጃልህ፤ ሳኒታይዘር ተጠቀም – ኧረ ንክች እያልን አስቸገርን እኮ።የለት ጉርሳቸውን በዕለት ካልወጡ ማያገኙት ቢሆኑ አጥጋቢ ምክንያት አላቸው እንበል፤ ከራብ ጦር ይሻላል አይደል ብሂሉስ።
ተው እንጂ ሰዎች፤ በሀገሪቱ ፕሬዚደንት እና ጠቅላይ ሚኒስትር፤ በአገሪቱ ቁንጮ አርቲስት እና ከንቲባ በይፋ እየተለመኑ አልሰማሁም ማለት ጤነኝነት ነውን? እዚህ ጋ በማህበራዊ ድረ ገፅ ያየሁት አንድ መልዕክት ትዝ አለኝ፤ ወደ ጎን ሁለት ሜትር
አካላዊ ርቀት ይኑርህ ስትባል ካልሰማህ ወደታች ሦስት ሜትር ትርቃታለህ የሚል መልዕክት ሲዘዋወር ነበር።አዎ! ሲመክሩት ያልሰማ ቢቀልቡት አይድንም ነውና አካላዊ ርቀት መጠበቅ ካቃተህ ትሞታለህ ማለቱ ነው፡፡
ወዳጆቼ! እስኪ ዛሬ አንድ ዕውነት ላይ እንስማማ።“በሽታ አይናቅም” የሚል ሃቅ ላይ አንድ እንሁን። ኮቪድ 19 ደካማ ቫይረስ ነው ሲባል ሰምታችኋል አይደል? አዎ ደካማ ሊሆን ይችላል።ደካማ ቢሆንም ቅሉ ለመግደል ግን አላነሰም። ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎችን ሲይዝ ጭስም ሆነ ነበልባሉ በዓይን አልታየም።በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን ግብዓተ መሬት ሲፈፅምም ድምፁን የሰማው አልነበረም።እጅግ ማራኪና ልዕልና ያለው የጤና ተቋምና የጤና ሥርዓት ያላቸውና የዓለማችን ቀዳሚ የሚባሉ ሀገራትን አንገት ሲያስደፋ ከእጅ ጣት ያነሱ ሳምንታት ብቻ ናቸው የተቆጠሩት።
አዎ! በሽታ አይናቅም።የቫይረስ ደካማም የለውምና አትዘናጉ።ሥጋ ደዌን ታውቁታላችሁ? እጅግ ልፍስፍስ በሆነ ደካማ ባክቴሪያ የሚተላለፍ በሽታ ነው። ይህ በሽታ መድኃኒቱ ተገኝቶ እንኳን እስካሁን ድረስ በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ ብሎም በዓለም ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ የሚገኝ በሽታ ነው።ባክቴሪያው ደካማ ይባል እንጂ ከክርስቶስ ልደት በፊት ጀምሮ ይሄው አሁንም ድረስ አለ፤ እና እንዴት በሽታ ይናቃል?
እንዴት እዚህ ዘመን ላይ ያለ ሰው እጆችህን በአግባቡ ታጠብ ተብሎ ይመከራል፤ እሺ ይመከር እንዴት እጆችህን ታጠብ ተብሎ ይለመናል፤ እሺ ይለመን እንዴት ላለመታጠብ ምክንያት ይደረድራል።በሉ ወዳጆቼ እጆቻችሁን ታጠቡና ለእጥበት አገልግሎት ካልሆነ በስተቀር ከፊታችሁ ጋር አጣሏቸው።ብዙ ጊዜ እንደሰማነው እጆቹን ወደ ዓይን፣ አፍንጫ እና አፍ በላክ መጠን የመጀመሪያ ተጋላጭ ያደርገናል፤ ቀጥሎ አጠገባችን ያሉ እነዛ የምትወዳቸው፡፡
አረቄና ነጭ ሽንኩረት፤ ፌጦና ዝንጅብል፤ ጥቁር አዝሙድና ሰናፍጭ፤ እፆችና ሎሚ ያድነኛል እያልክ ራስክን አታታል።እነዚህን በአግባቡና በልክ የሠርክ ምግብህ አድርገህ ተጠቀምባቸው።የተጠቀሱት ነገሮች በሽታን የመከላከል አቅማቸው እና ፈዋሽነታቸው የተመሠከረ ነው፤ ግን ድሮ ከበሽታው በፊት ታዘወትራቸው ከነበረ ብቻ ሊረዱህ ይችላሉ።ህይወት ግን በግምትና በዘልማድ አትመራም፤ አስይዘሃት ቁማር ተጫውተህ ታውቃለህን? አታደርገውም።
በመገናኛ ብዙኃን ማህበራዊ ሚዲያን ጨምሮ እንደተመለከታችሁልኝ ያ ሁሉ ሕዝብ በሞት የተትረፈረፈባት ቻይና በማግስቱ ሳይቀር ስካሩና ሀንጎቨሩ የማይለቅና ቀምሳችሁት ቀርቶ አሽታችሁት ስንፋጤው በአካል ላይ ሁሉ ያሉ ፀጉሮችን የሚያቆም ‘ኦልድ ቻይኒዝ’ የሚባል አረቄ ነበራት።እንደሚታሰበው ቢሆን ቻይና ሕዝቧን ሰብስባ አረቄዋን እየጋተች ሕዝቧን ታተርፍ ነበረ።
እናም እላለሁ።እባካችሁ ተጠንቀቁ፤ አንተ ባትሞት የምትወዳቸውን ትገድላለህ፤ የምትወዳቸው ባይሞቱ የምትወዳቸው የሚወዷቸውን አጥተው ይሰበሩብሃል።በቸልታ፣ በእንዝህላልነትና በግዴለሽ አስተሳሰብ መደረግ የሚችለውን ጥንቃቄ በመተው ፈጣሪህን እንዳትፈታተነው አደራ እልሃለው።በሙሉ ልብህ ፈጣሪህን አምነህ ፀልይ፤ አንተ እያወቅህ የጣልከውን ራስህን ግን ማንም እንደማያቀናልህ ጠንቅቀህ ተገንዘብ።
ያው እንደሰማኸው ከሰዎች ጋር ያለህን አካላዊ ርቀትም ጠብቅ፤ መተቃቀፍ ካማረህ በመንፈስ ተቃቀፍ። ምንም እንኳን መንበረ ሥልጣንን በፈቃድህ ባታቆናጥጠኝም፣ እኔ ይህን ሕግ አንተ ላይ አወጅኩኝ፤ ይህን አዋጅ በሌላ አዋጅ እስክሽረውም አደራ ያለመዘናጋትና ያለመታከት ተግብር።እንኳን በሽታውን ተከላክሎልህ ይቅርና ብታደርገው ስለማይጎዳህ ነገር ቀንድህን አቁመህ ስትከራከር ባይህ እታዘብሃለው፤ ለነገሩ እንደኔ ባይነግሩህ እንጂ ሰዎችም በዚህ ጉዳይ ብዙ ጊዜ ታዝበውሃል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 26/2012
ውብሸት ሰንደቁ